የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት የህወሓት ውሳኔ "የፕሪቶሪያ ስምምነትን ውድቅ የሚያደርግ ነው" አሉ

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ታደሰ ወረደ

የፎቶው ባለመብት, Tigray Communication Affairs Bureau

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ታደሰ ወረደ፤ ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ከስድስት ዓመት በፊት በክልሉ በተካሄደው ምርጫ የተቋቋመው ምክር ቤት እንዲመለስ ያስተላለፈው ውሳኔ "የፕሪቶሪያ ስምምነትን ውድቅ የሚያደርግ ነው" ሲሉ ተቹ።

ፕሬዝዳንቱ የሚመሩት ካቢኔ እና የመንግሥት መስሪያ ቤቶች "በመደበኛ ሥራቸውን እንደሚቀጥሉም" ገልጸዋል።

ሌተናንት ጄነራል ታደሰ ወረደ ይህንን ያሉት ዛሬ ማክሰኞ ሚያዝያ 13/2018 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሆነ የትግራይ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ በፌስ ቡክ ገጹ ላይ ያወጣው መረጃ ያመለክታል። ፕሬዝዳንቱ "ከጦርነት በፊት የነበረው መንግሥት ወደ ቦታው እንዲመለስ መወሰን ለፕሪቶሪያን ስምምነት" የሚያስገኘው ጥቅም እንደማይኖር ገልጸዋል።

ፕሬዝዳንቱ ይህ ያሉት ባለፈው ሳምንት የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባውን ያካሄደው ህወሓት፣ የትግራይ ጦርነት ከመጀመሩ አስቀድሞ በ2012 ዓ.ም. በክልሉ በተካሄደው ምርጫ የተመረጠው የትግራይ መንግሥት ምክር ቤት ወደ ሥራ እንዲመለስ መወሰኑን ካስታወቀ ከቀናት በኋላ ነው።

ማዕከላዊ ኮሚቴው ባወጣው መግለጫ፤ የፌደራል መንግሥት ላለፉት ሦስት ዓመታት ትግራይ ክልልን ያስተዳደረው ጊዜያዊ አስተዳደር ለተጨማሪ አንድ ዓመት እንዲራዘም ውሳኔ ማሳለፉን ተቃውሟል። ጊዜያዊ አስተዳደሩ የተቋቋመው "የሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤትነት እና የሕዝብ ውሳኔ ሰጪነት መገለጫ" የሆነው ምክር ቤት "ለሰላም ሲባል ወደጎን ተደርጎ" እንደሆነም ጠቅሷል።

አሁን ግን "2.8 ሚሊዮን ገደማ ሕዝብ የመረጠው የትግራይ መንግሥት ምክር ቤት ወደ ሥራ እንዲመለስ" መወሰኑን ገልጿል። ምክር ቤቱ ከተቋቋመ በኋላ በፕሬዝዳንት ታደሰ ወረደ የሚመራው የክልሉ አስፈጻሚ አካል " አቃፊ ሆኖ" እንዲቋቋም ያለውን ፍላጎትም አስታውቋል።

ይህ የህወሓት ውሳኔ የፕሪቶሪያ ስምምነትን የሚሽር እና ጊዜያዊ አስተዳደሩን የሚያፈርስ ተደርጎ ተቆጥሯል።

ዛሬ በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየት የሰጡት የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት ታደሰ፤ የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ "ከጦርነቱ በፊት የነበረው መንግሥት ወደ ነበረበት እንዲመለስ" ያስተላለፈው ውሳኔ የፕሪቶሪያው ስምምነትን "ውድቅ የሚያደርግ" እንደሆነ ተናግረዋል።

ውሳኔው የተላለፈው የፕሪቶሪያ ስምምነት ፈራሚ በሆነው ህወሓት መሆኑን ያስረዱት ሌተናንት ጄነራል ታደሰ፤ ይህንን እርምጃ "ተከትሎ ሊመጣ የሚችለው ጦርነት እንደሚሆን" መናገራቸውን ጽሕፈት ቤታቸው አስታውቋል።

"አማራጩ ጦርነትን መቀጠል ወይም ያለውን ሰላም በዘላቂነት ማስቀጠል" እንደሆነ የተናገሩት ፕሬዝዳንቱ፤ የጊዜያዊ አስተዳደሩን ሥልጣን ለመረከብ በሚደረግ ሂደት ውስጥ "መጓተት" ሊፈጠር እንደማይገባ ገልጸዋል።

ከስድስት ዓመት በፊት በተደረገው ምርጫ የተመሠረተው ምክር ቤት ማድረግ "ውሳኔ ምን ዓይነት አዎንታዊ እና አሉታዊ ተፅዕኖዎች" እንደሚኖሩን መመልከት እንደሚገባም አክለዋል። ከዚህ ጋር በተያያዘ ለተፈጠረው ችግር መፍትሔ ለማግኘት "መነጋገር እና ተደጋጋሚ ውይይቶችን ማድረግ እንደሚያስፈልግ" ገልጸዋል።

ሌተናንት ጄነራል ታደሰ ከአንድ ዓመት በፊት ወደ ሥልጣን የመጡት ከህወሓት የተለዩት የቀድሞው የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት ጌታቸው ረዳ የክልሉን መንግሥት መዋቅሮች ከተነጠቁ በኋላ ነበር። አሁንም ህወሓት የቀድሞው ምክር ቤት እንዲመለስ እና አስፈጻሚው አካል እንደገና እንዲዋቀር መወሰኑን ተከትሎ ተመሳሳይ ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል የሚል ስጋት ተነስቷል።

ፕሬዝዳንት ታደሰ ግን የሚመሩት የጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ ሥራውን እንደሚቀጥል በዛሬው መግለጫቸው ተናግረዋል። የክልሉ መንግሥት መሥሪያ ቤቶችም በመደበኛ ሥራቸው ላይ እንደሚገኙ እና በቀጣይም ተግባራቸውን መከናወን እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።

የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ያስተላለፈውን ውሳኔ በተመለከተ እስካሁን ድረስ ከፌደራል መንግሥት የተሰጠ ይፋዊ አስተያየት የለም።