ህወሓት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የሥልጣን ዘመን መራዘሙን ተቃወመ

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ሌተናንት ጄነራል ታደሰ ወረደ እና የህወሓት ሊቀመንበር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል

የፎቶው ባለመብት, Office of the President-Tigray/woyen

የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) የፌደራል መንግሥት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ሌተናንት ጄነራል ታደሰ ወረደ ሥልጣንን በአንድ ዓመት እንዲራዘም ማድረጉን "የተናጠል ውሳኔ" ሲል ተቃወመ።

ህወሓት፤ የፌደራል መንግሥት የጊዜያዊ አስተዳደሩ ሥልጣን ያራዘመው "ከፕሪቶሪያ ስምምነት በፊት የወጡ ሕጎችን" በመጠቀም ነው ሲልም ወቅሷል።

ህወሓት፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ረቡዕ ዕለት ያስተላለፉት ውሳኔ ላይ ያለውን ተቃውሞ ያሰማው ትናንት ሐሙስ ሚያዝያ 1/2018 ዓ.ም. ምሽት ባወጣው መግለጫ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጊዜያዊ አስተዳደሩ የሥልጣን ዘመን እንዲራዘም የወሰኑት ሌተናንት ጄነራል ታደሰ ወረደ የአንድ ዓመት አፈጻጸም ሪፖርት ባቀረቡላቸው ማግሥት ነው።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ረቡዕ ዕለት ባወጣው መግለጫ የፕሬዝዳንቱ የሥልጣን ዘመን በአንድ ዓመት እንዲራዘም የተወሰነው በቀረበው ሪፖርት፣ የፌደራል መንግሥት በክልሎች ውስጥ ጣልቃ የሚገባበትን ሥርዓት ለመደንገግ በወጣው አዋጅ እና "የትግራይ ክልል አካታች ጊዜያዊ አስተዳደር አስመልክቶ በጸደቀው ደንብ" እንደሆነ አስታውቋል።

ህወሓት ትናንት ባወጣው መግለጫ፤ የሁለት ዓመቱን የትግራይ ጦርነት ያስቆመውን የፕሪቶሪያ ስምምነት ጠቅሷል። በፕሪቶሪያ ስምምነት መሠረት የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የሚመሰረተው "በሁለቱ ተፈራራሚ አካላት ማለትም በህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ እና በኢትዮጵያ መንግሥት" መካከል በሚደረግ "ፖለቲካዊ ንግግር" እንደሆነ ገልጿል።

"ብዙ መደናቀፎች እያጋጠሙ ቢቆዩም"፤ ከፕሪቶሪያ መፈረም በኋላ በ2015 ዓ.ም. የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የተቋቋመው በሁለቱ አካላት መካከል "በተደረጉ ንግግሮች" እንደሆነ አስታውሷል። "ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ መንግሥት እየፈፀማቸው ለቆዩ የፕሪቶርያው ስምምነት የመጣስ ተግባራት [ቀጥሏል]" ሲል በዚህ ሳምንት ስለተራዘመው የፕሬዝዳንት ታደሰ የሥልጣን ቆይታ አንስቷል።

እንደ ህወሓት ገለጻ የፌደራል መንግሥት የጊዜያዊ አስተዳደሩን ቆይታ በአንድ ዓመት ያራዘመው "ከፕሪቶሪያ ስምምነት በፊት በነበሩ ሕጎችን መሰረት" በማድረግ እንዲሁም የዘላቂ ተኩስ አቁም ስምምነቱን "ሙሉ በሙሉ በመጣስ" ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ የሌተናንት ጄነራል ታደሰን ሥልጣን ማራዘማቸው ይፋ በተደረገበት የጽሕፈት ቤታቸው መግለጫ ላይ የተጠቀሰው፤ የትግራይ ጦርነት ከተጀመረ በኋላ በ2013 ዓ.ም. የወጣው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ነው። ከጦርነቱ መጀመር በኋላ የተመሰረተው እና በዶ/ር ሙሉ ነጋ ሲመራ የነበረውን የመጀመሪያ ጊዜያዊ አስተዳደር ለማቋቋም የወጣው ደንብ ከፕሪቶሪያ ስምምነት በኋላ ተሽሯል።

የህወሓት አመራሮች

የፎቶው ባለመብት, tplf

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ከጦርነቱ በኋላ በ2015 ዓ.ም. የወጣው "የትግራይ ክልል አካታች ጊዜያዊ አስተዳደር የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ" ካካተታቸው አንቀጾች አንዱ "በትግራይ ክልል የተቋቋመውን ጊዜያዊ አስተዳደር አስመልክቶ በ2013 የወጣው ደንብ በዚህ ደንብ ተሽሯል" የሚል ነው።

በስራ ላይ ያለው ደንብ የጊዜያዊ አስተዳደሩን ፕሬዝዳንት የመሾም ሥልጣንን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰጠ ቢሆንም ርዕሰ መስተዳደሩ የሚለየው "በሰላም ስምምነቱ መሠረት በሚደረግ የፖለቲካ ምክክር" እንደሆነ ደንግጓል።

የፕሬዝዳንት ታደሰ የሥልጣን ዘመን ሲራዘም ይህ ፖለቲካዊ ምክክር ስለመደረጉ እንዲሁም የቀድሞው ደንብ ስለተጠቀሰበት ምክንያት እስካሁን ይፋዊ ማብራሪያ አልተሰጠም። ቢቢሲ በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ ለማግኘት ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ጥያቄ አቅርቧል።

ህወሓት ትናንት ባወጣው መግለጫ የጊዜያዊ አስተዳደሩን የሥልጣን ቆይታ የማራዘም ውሳኔውን "የሁለቱ ተፈራራሚ አካላት ንግግር ያልተደረገበት" እና "የተናጠል ውሳኔ" ሲል ገልጾታል።

"ከህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ እውቅና እና ተሳትፎ ውጪ የተላለፈ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት የተናጠል ውሳኔ መሆኑ ለመላው ህዝባችን ፣ የፕሪቶሪያው ስምምነት አደራዳሪ አካላት እና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲገነዘቡት እንወዳለን" ብሏል።

ህወሓት የጊዜያዊ አስተዳደሩን የቆይታ ጊዜ መራዘም በተመለከተ የያዘው አቋም ከፕሬዝዳንት ታደሰ ጋር ያለውን ግንኙነት ሊቀይረው ይችል እንደሆነ ግልጽ አይደለም። በቀድሞ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት ጌታቸው ረዳ የሥልጣን ዘመን ወቅት የህወሓት አመራሮች ሌተናንት ጄነራል ታደሰ ወደ ሥልጣን እንዲመጡ ጥያቄ ሲያቀርቡ እንደነበር በወቅቱ ምንጮች ተናግረው ነበር።