የአዲግራት ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር በአዲሱ የትግራይ ክልል አዋጅ ተጠርጥረው ፍርድ ቤት ቀረቡ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

የአዲግራት ዩኒቨርሲቲ የሜዲስን እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን የሆኑት ዶ/ር የማነ ገብረማርያም በቅርቡ በትግራይ ክልል በወጣው አዋጅ ላይ የሚገኝን እና ከ15 ዓመት እስከ ሞት የሚያስቀጣ አንቀጽን በመጣስ ተጠርጥረው ፍርድ ቤት መቅረባቸውን ጠበቃቸው ለቢቢሲ ተናገሩ።

መርማሪ ፖሊስ፤ ዶ/ር የማነ "ከፌደራል መንግሥት እና ከሀራ መሬት ታጣቂዎች" ጋር ግንኙነት እንዳላቸው በመግለጽ የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜ እንዲፈቅደለት መጠየቁንም ጠበቃው አስረድተዋል።

የአዲግራት ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር እና የሕጻናት ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር የማነ በቁጥጥር ስር የዋሉት ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ሰኔ 27/2018 ዓ.ም. እንደሆነ የሥራ ባልደረቦቻቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ዶ/ር የነማ በዕለቱ ወደ አዲስ አበባ ለመድረስ ከአዲግራት ከተማ ተነስተው ወደ መቀለ እየተጓዙ እንደነበረም ገልጸዋል።

የሕክምና ባለሙያው ጠበቃ ብርሃነ ገብረማርያም እንደሚገልጹት ዶ/ር የማነ ወደ አዲስ አበባ ጉዞ የጀመሩት የአፍሪካ የሕክምና ትምህርት አህጉራዊ ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ነበር።

ሰኞ ዕለት በተጀመረው እና ዛሬ ረቡዕ ሐምሌ 1 በሚጠናቀቀው አህጉራዊ ጉባኤ መክፈቻ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ እና የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ ተገኝተዋል።

የትግራይ የሕክምና ማኅበርም እሁድ ሰኔ 28 ቀን የጤና ባለሙያውን እስር በተመለከተ ባወጣው መግለጫ ዶ/ር የማነ ጉባኤው ላይ ለመሳተፍ እየተጓዙ እንደነበር ጠቅሷል። ሐኪሙ "በትግራይ የሕክምና እና አካዳሚክ ማኅበረሰብ ዘንድ እጅግ የታወቁ" እንደሆኑ የጠቀሰው ማኅበሩ፤ ለእስራቸው "ምንም ሕጋዊ ማብራሪያ አልቀረበም " ሲል ተችቷል።

ጠበቃው ብርሃኔም በበኩላቸው፤ "ከአዲግራት ወጣ ብሎ ዕዳጋ ሐሙስ የሚባል ከተማ ነው የተያዙት። በመጀመሪያ ሲያዙ ምንም የተገለጸ ነገር የለም። ከላይ በተሰጠን ትዕዛዝ የሚል ምክንያት ብቻ ነው የተሰጣቸው" ሲሉ ዶ/ር ማነ የተያዙበት ሁኔታ ገልጸዋል።

ጠበቃው እንደሚናገሩት፤ በትራፊክ ፖሊስ እና "በአንድ የፀጥታ ሰው" የተያዙት የሕጻናት ስፔሻሊስቱ፤ "ወደ አዲግራት የፖሊስ ጣቢያ ጽህፈት ቤት ጊዜያዊ ማቆያ ተወስደው" ታስረዋል። አብረዋቸው ተሽከርካሪው ውስጥ የነበሩ ሁለት ሰዎች መለቀቃቸውን አስረድተዋል።

ከተያዙ በኋላ ፍርድ ቤት አለመቅረባቸውን የሚናገሩት ጠበቃው፤ ፖሊስ "ከላይ የመጣ ትዕዛዝ ስለሆነ የእኔ እስረኛ አይደሉም፤ እዚያ ይቆዩ በሚል ነው የያዝኳቸው" የሚል ምላሽ መስጠቱን ገልጸዋል። ይህንን ተከትሎም "አካልን ነፃ የማውጣት ማመልከቻ" ለፍርድ ቤት መቅረቡን ተናግረዋል።

የአዲግራት ከተማ አንደኛ ደረጃ ፍርድ ቤት ሰኞ በዋለው ችሎት ጉዳዩን መመልከቱን ጠበቃው ገልጸዋል። በችሎቱ መርማሪ ፖሊስ የጤና ባለሙያው ቁጥጥር ስር የዋሉት "ከጠላት ጋር በመተባበር ወንጀል ስለጠራቸው" እንደሆነ ማስረዳቱን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ጠበቃው ብርሃኔ እንደሚገልጹ፤ ዶ/ር የማነ የተጠረጠሩበት ወንጀል በህወሓት ውሳኔ ወደ ሥራ የተመለሰው የትግራይ ክልል ምክር ቤት ግንቦት ላይ ያጸቀደውን "የትግራይ ሕዝብ ኅልውና እና ደኅንነትን ለማረጋገጥ የወጣ አዋጅ" በመጣስ ነው።

መርማሪ ፖሊስ "ከፌደራል መንግሥት እና እዚያ ሀራ መሬት ተብለው ከሚታወቁ፤ ራሳቸውን የትግራይ የሰላም ሠራዊት ብለው ከሚገልጹ ታጣቂዎች ጋር ግንኙነት አላቸው" ሲል ለፍርድ ቤት መናገሩን ጠበቃው ገልጸዋል። ወደ ታጣቂዎቹ "የሚሄዱ ሰዎችን እየመለመሉ ፈንድ እያደረጉ ይልካሉ" ማለቱንም አክለዋል።

ጠበቃው እንደሚያስረዱት መርማሪ ፖሊስ ተጥሷል ያለው በአዋጁን አንቀጽ 44 ላይ የሰፈረውን ድንጋጌ ነው። ይህ አንቀጽ "የጠላት ዓላማ እንዲሳካ በማሰብ፣ በማማከር፣ በመምራት፣ በማሰማራት፣ በመመልመል ወይም በተግባር ጠላት በመደገፍ" የሚፈጸሙ ወንጀሎችን የሚደነግግ ነው።

በዚህ አንቀጽ ጥፋተኛ ሆነው የሚገኙ ተከሳሾች ከ15 እስከ 25 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት እንደሚቀጡ፤ "አፈጻጸሙ ከባድ" ከሆነ ደግሞ በዕድሜ ልክ እስራት ወይም በሞት እንደሚቀጡ ደንግጓል።

በተጨማሪ አዋጁ ከ15 ዓመት በላይ በሚያስቀጡ ወንጀሎች ለተከሰሱ ሰዎች የዋስትና መብት እንደሚከለክል ጠበቃው አስረድዋል።

በትናንቱ የችሎት ውሎ፤ መርማሪ ፖሊስ ተጨማሪ ምርመራ ለማድረግ የ14 ቀናት የጊዜ ቀጠሮ እንዲፈቀድለት ጠይቋል።

የዶ/ር የማነ ጠበቃ ይህ አዋጅ በራሱ "የግል ነፃነት፣ ሕገ መንግሥታዊ መብቶች እንደሚጋፋ" እንዲሁም የወጣበት አግባብ "ሕገ መንግሥታዊ እንዳልሆነ" በመጥቀስ በፍርድ ቤት መከራከራቸውን ገልጸዋል።

"እንዲሁም የድርጊቱ እና የተከሰሱበት አዋጅም ሁለቱም የማይገናኙ ስለሆነ በቂ የሆነ መጠርጠሪያ ምክንያት የላቸውም" የሚል መከራከሪያ አቅርበዋል።

በዚህም ተነሳ ፍርድ ቤት በዋስ ሊለቃቸው እና "አካልን ነፃ የማውጣት መብታቸው መከበር እንዳለበት" በማንሳት በችሎቱ መጠየቃቸውን ገልጸዋል።

የሁለቱን አካላት ክርክር የተመለከተው የአዲግራት ከተማ አንደኛ ደረጃ ፍርድ በጉዳዩ ላይ ብይን ለመስጠት ለዛሬ ረቡዕ ሐምሌ 1 ረፋድ ቀጠሮ ሰጥቶ የነበረ ቢሆንም ችሎቱ ወደ የሚቀጥለው ሳምንት ሰኞ መዛወሩን ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ ጠበቃው የተሰጠው የቀጠሮ ቀን "ረጅም በመሆኑ ተሰብሮ እንዲታይ" ባስገቡት ማመልከቻ መሠረት ለዛሬ ከሰዓት ሌላ ችሎት መቀጠሩን አስረድተዋል።