በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የኢቦላ ክትባት ሙከራ ሊጀመር ነው

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የኢቦላ ክትባት በሙከራ ደረጃ መሰጠት ሊጀምር እንደሆነ ተገለጸ።
በዲሞክራቲክ ኮንጎ እየተሰራጨ ያለው ቡንዲቡግዮ የኢቦላ ዝርያን በመከላከል ረገድ ክትባቱ ምን ያህል ውጤታማ እንደሆነ ለማወቅ ሙከራው በቅርቡ የሚካሄድ ይሆናል።
ኤርቬቦ የተሰኘው ክትባቱ ዛየር የሚባለውን የኢቦላ ዝርያ መከላከል ይችላል። አሁን የተከሰተውን 'ቡንዲቡግዮ' የተባለ የኢቦላ ዓይነትን የሚከላከል ክትባት የለም።
ኢቦላ በሰሜን እና ምሥራቅ ዲሞክራቲክ ኮንጎ "በከፍተኛ መጠን" እየተሰራጨ እንደሚገኝ የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል። ወረርሽኙ በአገሪቱ ታሪክ እጅግ የከፋው እንደሆነም ይፋ አድርጓል።
ወረርሽኙ መነሳቱ ይፋ የተደረገው ከሦስት ወራት በፊት ሲሆን እስከ አሁን 2,500 ገደማ ሰዎች ሞተዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት አስተባባሪ ጁሊያን ሀርኒስ እንደተናገሩት ግማሽ ያህሉ ሰዎች የሞቱት ባለፉት 20 ቀናት ነው።
"በሽታውን ለመከላከል ከሚደረገው ጥረት በላይ ወረርሽኙ በፍጥነት እና በስፋት እየተሰራጨ ነው" ማለታቸውን ኤኤፍፒ ዘግቧል።
ሴቭ ዘ ችልድረን እንዳለው ወረርሽኙ ከተነሳ ወዲህ ቢያንስ 180 ሕጻናት ሁለቱንም ወላጆቻቸውን ወይም አሳዳጊዎቻቸውን በሞት ተነጥቀዋል።
በአውሮፓውያኑ ከ2014 እስከ 2016 ባሉት ዓመታት በወረርሽኙ ከ11,000 በላይ ሰዎች ሞተዋል።
ቫይረሱ ጥር ላይ መሰራጨት እንደጀመረ እና በስህተት ወባ ወይም ታይፎይድ ነው ተብሎ እንደታሰበ ተገልጿል።
በዲሞክራቲን ኮንጎ ወረርሽኙ በተነሳበት አካባቢ ያለው ግጭት የወረርሽኙን ስርጭት ለመግታት የሚደረገውን ጥረት አስተጓጉሏል።
በባህላዊ ዕሳቤዎች ምክንያት የጤና ባለሙያዎችን አለማመን እና በተገቢው መንገድ የቀብር ሥነ ሥርዓት አለመፈጸሙም ሌሎች መሰናክሎች ናቸው።
ኤርቬቦ የተሰኘው ክትባት የወረርሽኙን ስርጭት ለመቀነስ እንደሚረዳ ይታመናል።
የዓለም ጤና ድርጅት እንዳለው የክትባቱን ውጤታማነት ለመፈተሽ 20,000 ያህል ክትባት ላይ ሙከራ የሚደረግ ሲሆን፤ 50,000 ክትባት ደግሞ ለጤና ባለሙያዎች ይሰራጫል።
የክትባቱ ስርጭት ወረርሽኙን ለመቆጣጠር ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት የአፍሪካ የበሽታ ቁጥጥር እና መከላከል ተቋም እንዲሁም የዓለም ጤና ድርጅት ገልጸዋል።
በምሥራቅ ዲሞክራቲክ ኮንጎ የተወሰኑ አካባቢዎችን የሚቆጣጠረው ታጣቂው ኤም23፤ በመንግሥት ይዞታ ሥር ባሉ ቦታዎች እና በአማጺያን ሥር ባለው ኪቩ ግዛት ያለው እንቅስቃሴ ላይ ገደብ ጥሏል።
በአካባቢው የተሽከርካሪ እና የጀልባ እንቅስቃሴ ተገድቧል።
እርምጃው የተወሰደው በኤም23 ቁጥጥር ሥር በሚገኝ መንደር ውስጥ ሁለት ተጓዦች በኢቦላ መያዛቸው ከታወቀ በኋላ ነው።
የታጣቂ ቡድኑ እርምጃ የጤና ባለሙያዎችን ሥራ የሚያስተጓጉል እንደሆነ ተገልጿል።
ኤም23 አምና ጎማ እና ቡካቩ ግዛቶችን የተቆጣጠረ ሲሆን፤ ያለውን አቅም ለማሳየት በሚል የራሱን ፀረ ኢቦላ ንቅናቄ እያደረገ ይገኛል።
ያለፈው ሰኔ ላይ በቡድኑ ቁጥጥር ሥር የሚገኙ አካባቢዎች ከኢቦላ ነጻ መሆናቸውን አስታውቆ ነበር።
በኢቦላ ቫይረስ የሚያዙ ሰዎች ከሁለት እስከ 12 ቀናት ባለው ጊዜ ምልክት ያሳያሉ።
ከጉንፋን እና ወባ ጋር የሚመሳሰል ምልክት ያለው ገዳይ ቫይረስ ነው። ድንገተኛ የሆነ ትኩሳት፣ ራስ ምታት እና ድካም ከምልክቶቹ መካከል ይጠቀሳሉ።
ቫይረሱ እየጠነከረ ሲሄድ ማስመለስ፣ ማስቀመጥ እና የሰውነት ክፍሎች ሥራ ማቆም ይከተላል።
እንደ ደም ባሉ ከሰውነት የሚወጡ ፈሳሾች አማካኝነት ቫይረሱ ከሰው ወደ ሰው ይተላለፋል።















