ኤርትራ "በሌሎች ኃይሎች ተማምና በጥፋት መንገድ የምትቀጥል ከሆነ ከባድ ውጤት እንደሚኖረው" ጠ/ሚ ዐቢይ አስጠነቀቁ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ሰላም እንደምትፈልግ እና የልማት አጋር መሆን እንደምትሻ ጠቅሰው፤ ኤርትራ "በሌሎች ኃይሎች ተማምና በጥፋት መንገድ የምትቀጥል ከሆነ ግን ከባድ ውጤት እንደሚኖረው" ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰኞ ጥቅምት 9/2013 ዓ. ም. በትግርኛ በሰጡት ቃለ መጠይቅ ላይ ነው ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር አጋርነት እንደምትፈልግ ተናግረው የማስጠንቀቂያ መልዕክትም ያስተላለፉት።

"የልማት አጋር መሆን ሲቻል የጠላቶች መጫወቻ መሆንን መምረጥ አያዋጣም" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ይህን ጥሪ አለመቀበል ግን "አደጋው እጅግ እጅግ እጅግ ከባድ ይሆናል" ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት፣ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ወደ ጦርነት ሊያመሩ ይችላሉ የሚል ስጋት ከመቼውም ጊዜ በላይ ባየለበት ወቅት ነው።

የትግራይ ጦርነት ዳግም መቀስቀሱን ተከትሎ የኤርትራ ወታደሮች የኢትዮጵያን ድንበር አልፈው ወደ ትግራይ ክልል ዘልቀው መግባታቸው መዘገቡ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም፣ ኢትዮጵያ በኤርትራ ወረራ እንደተፈጸመባት እና ራሷን ከመከላከል ውጪ ሌላ አማራጭ እንደሌላት በመግለጽ ለተባበሩት መንግሥታት በደብዳቤ አሳውቋል።

ውንጀላውን የማትቀበለው ኤርትራ በበኩሏ፣ ኢትዮጵያ "ራስን በመከላከል ስም" በሉዓላዊት የተመድ አባል ላይ የምትፈጽመውን ጦርነት ምክንያታዊ ለማድረግ እየሞከረች ነው ስትል ለመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በላከችው ደብዳቤ ምላሽ ሰጥታለች።

ይህን ተከትሎ አሜሪካ እና የተባበሩት መንግሥታትን ጨምሮ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሁለቱ አገራት ውጥረት መባባሱ እንዳሰሰበው ገልጿል።

ኢትዮጵያ የኤርትራን ዲፕሎማቶች ከአገር ስታስወጣ ኤርትራ በምላሹ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ሙሉ በሙሉ ማቋረጧን አስታውቃለች።

ኤርትራ ህወሓትን ጨምሮ በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ነፍጥ ያነሱ አማጺያንን እንደምትደግፍ፣ ለዚህም እንደ ሱዳን እና ግብፅ ካሉ ሌሎች የውጭ ኃይሎች ጋር እንደምትተባበር ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ መክሰሷ ይታወቃል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቆይታ ላይም፣ "ህግደፍ" ሲሉ የጠሩትን የኤርትራ መንግሥት "ልማትን እና ተቋማትን መገንባቱን ትቶ የኢትዮጵያ ጠላቶች መሣሪያ ሆኗል" ሲሉ ወንጅለዋል።

እንዲህ ያለው ድርጊት ተፈጥሯዊ ጉርብትናን እንደሚያበላሽም ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በተጨማሪ በሌሎችም የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን በተላለፈው በዚሁ ቃለ ምልልስ ላይ ተናግረዋል።

"ባለፉት 35 ዓመታት እንደታየው፣ ጥሩ ጉርብትና እና ወዳጅነት ብቻ ነው የሚያዋጣው" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ "አይዞህ ባዮችም ቢሆኑ ጥይት ከማቀበል አልፈው የኤርትራን ችግር ሊፈቱ አይችሉም" የሚል እምነት እንዳላቸው ገልፀዋል።

ከኤርትራ መንግሥት ጎን እንደተሰለፉ እና የኢትዮጵያ ጠላት እንደሆኑ የጠቀሷቸው እና በስም ያልጠሯቸው ኃይሎች የራሳቸውንም ችግር መፍታት ያልቻሉ መሆናቸውን አመልክተዋል።

"የራሱ ችግር ያለው፤ የራሱን ችግር ያልፈታ ደግሞ ለሌላው ሊሆን አይችልም" በማለት ኤርትራን ሊጠቅሙ እንደማይችሉ አስገንዝበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም፣ ከነጻነት በፊት "ያበቡ እና ያሸበረቁ" የነበሩ የኤርትራ ከተሞች ዛሬ ግን "የመንደር ያህል ሆነዋል" ብለዋል። ዛሬ አሥመራን ከአርባ ምንጭ ወይም ከጅግጅጋ "የምታንስ ከተማ" እንደሆነችም በማሳያነት አንስተዋል።

ኤርትራ የኢትዮጵያ አካል እያለች፣ ከ300 በላይ ፋብሪካዎች እንደነበሯት እና በወቅቱ ከአፍሪካ በኢንዱስትሪ ከበለጸጉት አንዷ እንደነበረችም ጠቅሰዋል።

"ምፅዋ ባዶዋን ቀርታለች፤ አሰብም ሰው አልባ ከተማ ሆናለች። የኤርትራ ሕዝብ ከነጻነት በኋላ የነበረውን ሁሉ አጥቷል" ሲሉም ኤርትራ ከነጻነት በኋላ የኋሊት መጓዟን አብራርተዋል።

የኤርትራ መንግሥት ከልማት ይልቅ የጥፋት መንገድን በመምረጡ የአገሪቱ ሕዝብ ዛሬ "ስደት እና እንግልት መገለጫው ሆኗል" ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ተችተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለ ኤርትራ የተናገሩት፣ በአብዛኛው ህወሓትን በመተቸት በሰጡት የ27 ደቂቃ ቃለ መጠይቅ ላይ ነው። በጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት አስተያየት ላይ ከኤርትራ በኩል ወዲያውኑ የተሰጠ ምላሽ የለም።