ትራምፕ በኢራን ጦርነት ለመሳተፍ ፈቃደኛ ካልሆነችው ደቡብ ኮሪያ ጋር የሚደረገው ወታደራዊ ልምምድ እንደሚቀንስ ተናገሩ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ጋር ባላቸው "መልካም ግንኙነት" ምክንያት ከደቡብ ኮሪያ ጋር የሚያደርጉትን የጋራ ወታደራዊ ልምምድ "በከፍተኛ መጠን እንደሚቀንሱ" አስታወቁ።

ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል ማኅበራዊ ሚዲያቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ እንደገለጹት፣ ደቡብ ኮሪያ ኢራንን "ከኒውክሌር ነጻ በማድረግ" እንቅስቃሴ ውስጥ ለመሳተፍ ፈቃደኛ አልሆነችም።

"እነዚህ ወታደራዊ ልምምዶች ዋጋቸው ውድ ነው። አብዛኛውን ወጪ የምትሸፍነው ደግሞ እንደተለመደው አሜሪካ ናት። ፈጽሞ የማያስፈልግ እና ነውጠኛ መሆኑን መልዕክት ያስተላልፋል" ብለዋል።

ደቡብ ኮሪያ ከአሜሪካ ጋር የሚደረገው ወታደራዊ ልምምድ "በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መሠረት" እንደሚቀጥል ገልጻለች። ሰሜን ኮሪያ ግን እስካሁን አስተያየት አልሰጠችም።

ሰሜን ኮሪያ በያዝነው ወር የባለስቲክ ሚሳዔል ሙከራ አድርጋለች። የመንግሥታቱ ድርጅት ይህ አይነቱ ድርጊት ላይ እገዳ ጥሏል።

ትራምፕ ትናንት እሑድ እንደተናገሩት ዛሬ ከደቡብ ኮሪያ ጋር የሚካሄደውን ዓመታዊ ወታደራዊ ልምምድ ለመሰረዝ ጊዜው ረፍዷል።

"በቅርቡ የደቡብ ኮሪያው ፕሬዝዳንት ኢራንን ከኒውክሌር ነጻ በማድረግ እንዲተባበረን ጠይቄዋለሁ። እምቢ ብሏል" ሲሉ ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል ገጻቸው ጽፈዋል።

ጽሑፉን ከማጋራታቸው ከ24 ሰዓታት አስቀድሞ ከኪም ጆንግ ኡን ጋር በአውሮፓውያኑ 2019 የተነሱትን ፎቶ ለጥፈዋል።

ሁለቱ መሪዎች በምሥሉ ላይ "ወዳጆች ባይመስሉም" መልካም ጓደኞች መሆናቸውን ጽፈዋል።

ባለፈው ሳምንት የአሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያ ወታደራዊ መሪዎች ለ11 ቀናት የሚቆይ ወታደራዊ ልምምድ እንደሚደረግ አስታውቀዋል።

'ዩልቺ ፍሪደም ሺልድ' የተባለው ልምምድ አምና ከነበረው ጋር ተመሳሳይ እንደሚሆን እና ወደ 18,000 የደቡብ ኮሪያ ወታደሮች እንደሚሳተፉበት ተገልጿል።

ሰሜን ኮሪያ ለሩሲያ ጦር ወታደሮች መስጠቷን የአሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያ ወታደራዊ መሪዎች ተናግረዋል።

የአሜሪካ ጦር ቃል አቀባይ ራየን ዶናልድ "ሥልጠና የምናደርገው ይሄ ስጋት ስላለ ነው" ብለዋል።

ወደ 28,500 የሚጠጉ የአሜሪካ ወታደሮች በደቡብ ኮሪያ ተሰማርተዋል።

የሰሜን ኮሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ የጋራ ወታደራዊ ልምምድ "የጦርነት ዝግጅት ነው" ሲል ኮንኗል።

ከቀናት በፊት ደቡብ ኮሪያ፣ አሜሪካ እና ጃፓን እንዳስታወቁት ሰሜን ኮሪያ ሁለተኛ የሚሳዔል ሙከራ ለማድረግ እየተዘጋጀች ነው።

ፒዮንግያንግ የኒውክሌር እና ሚሳዔል መሣሪያ ምርትን የማስፋፋት እንቅስቃሴዋን ቀጥላለች።

ትራምፕ ከሰባት ዓመት በፊት ሰሜን ኮሪያን በመጎብኘት የመጀመሪያው ሥልጣን ላይ ያሉ አሜሪካዊ ፕሬዝዳንት ሆነዋል።

የደቡብ ኮሪያ መንግሥት ትራምፕ ከኪም ጆንግ ኡን ጋር ተነጋግረው ወደ ድርድር ጠረጴዛው እንዲያመጧቸው ይፈልጋል።

ትራምፕ ይህንን ሊያደርጉ እንደሚችሉ የሚጠቁም ጽሑፍ ቢያጋሩም በደቡብ ኮሪያ መንግሥት ደስተኛ አለመሆናቸውንም ገልጸዋል።

ደቡብ ኮሪያ በኢራን ጦርነት ለመሳተፍ አለመፍቀዷ እንዳስቀየማቸው ትራምፕ ተናግረዋል።

ፕሬዝዳንቱ ከኢራን ጦርነት ጋር በተያያዘ ከጃፓን፣ ፈረንሳይ እና ዩናይትድ ኪንግደም ጋርም ሽኩቻ ውስጥ ገብተዋል።

በአውሮፓውያኑ 2018 ከኪም ጆንግ ኡን ጋር ለመነጋገር በሚል ከደቡብ ኮሪያ ጋር የሚደረግ ወታደራዊ ልምምድ ማድረግ አቋርጠው ነበር።

በወቅቱ ወታደራዊ ልምምድ ሰሜን ኮሪያን "የሚያስቆጣ" እንደሆነ የገለጹት ትራምፕ፤ ወደ ጦርነት አለመግባት ለአሜሪካ አዋጭ መንገድ መሆኑን ተናግረዋል።

የጋራ ወታደራዊ ልምምዱ በ2020 ዳግመኛ ተጀምሯል።

ባለፈው ሳምንት የደቡብ ኮሪያ ፕሬዝዳንት ሊ ጄ ሚዩንግ፤ ከሰሜን ኮሪያ ጋር ጦርነት በይፋ ለማቆም ለመወያየት ጥያቄ አቅርበዋል።