እስራኤል በጋዛ የአየር ጥቃት የሐማስ አዛዥን እንደገደለች አስታወቀች

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

እስራኤል በጋዛ በፈፀመችው የአየር ጥቃት የሐማስ አዛዥ ኢዝ አድ-ዲን አል-ሐዳድን እንደገደለች አስታወቀች።

አዛዡ "የመስከረም 26ቱን ጥቃት ከአቀነባበሩት አንደኛው" መሆናቸው ተገልጿል።

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እና የመከላከያ ሚኒስትሩ እዝራኤል ካትዝ በጋራ ባወጡት መግለጫ ሐዳድ "በሺዎች ለሚቆጠሩ እስራኤላውያን እና ወታደሮች [የእስራኤል መከላከያ ኃይሎች] መገደል፣ መታፈን እና መጎዳት ኃላፊነት አለባቸው" ብለዋል።

ሦስት የዓይን ምስክሮች ለቢቢሲ እንደተናገሩት "አል-ሙታዝ" ተብሎ የሚታወቀው የመኖሪያ ሕንፃ ከሁለት የተለያዩ አቅጣጫዎች በተነሱ ሦስት ሚሳኤሎች ተመትቷል፤ ከዚያም በመሸሽ ላይ የነበረ ተሽከርካሪ ተመትቷል።

ይህ ጥቃት ከሐማስ ጋር የተኩስ አቁም ስምምነት ቢኖርም እስራኤል በጋዛ ላይ እየፈፀመቻቸው ካሉ ጥቃቶች ውስጥ የቅርብ ጊዜው ነው።

ሐማስ ግን የቡድኑ የጦር ክንፍ ቃሳም ብርጌድ አዛዥ የሆነው ሐዳድ ስለመገደሉ እስካሁን ማረጋገጫም ሆነ ማስተባበያ አልሰጠም።

በጋዛ መሃል ከተማ ላይ በአየር ጥቃት የተመታው የመኖሪያ ሕንፃ ላይ ትልቅ እሳት ተነስቷል።

የሕይወት አድን ሠራተኞች በስፍራው በፍጥነት ቢደርሱም የተጎዱ ሰዎችን ለማውጣት ከባድ ችግር እንደገጠማቸው እማኞች ተናግረዋል።

አንድ የዓይን እማኝ ለቢቢሲ አንድ አስከሬን እና ብዙ የተጎዱ ሰዎች ከሕንፃው ሲወጡ መመልከቱን ተናግሯል።

በአካባቢው ለማምለጥ ሲሞክር የነበረ ተሽከርካሪ ላይ በተሰነዘረው ሁለተኛው የአየር ጥቃት ሦስት ሰዎች መገደላቸውን የዓይን እማኞች እና አንድ የአካባቢው ምንጭ ገልፀዋል።

ምንጮች እንዳሉት ተሽከርካሪው የሐማስ አዛዥ የሆኑት ሐዳድ በመጀመሪያው ጥቃት ከተጎዱ በኋላ ይዞ ለመውጣት ሲሞክር የነበረ ሳይሆን አይቀርም ብለዋል።

የዓይን እማኞች እና የአካባቢው ምንጭ የታጠቁ የሐማስ አባላት የሲቪል ልብስ የተለበሱ አንድ የቆሰሉ ሰውን በኋላ በር አውጥተው መኪና ውስጥ እንዳስገቧቸው ተናግረዋል።

የዓይን እማኞች እንዳሉት ከሆነ መኪናው ከሕንፃው 1.5 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ነው የተመታው።

አንድ ከፍተኛ የእስራኤል የደኅንነት ባለሥልጣን የመጀመሪያ ደረጃ መረጃዎች ሐዳድ በተሳካ ሁኔታ መመታቱን እንደሚጠቁሙ አስታውቋል።

በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት ከመስከረም 30 ጀምሮ ተፈጻሚ ቢሆንም፤ ከዚህን ጊዜ ጀምሮ እስራኤል በየጊዜው በመላው የፍልስጤም ግዛቶች ጥቃቶችን መፈፀሟን ቀጥላለች።

ሐማስ እስራኤል የተኩስ አቁሙን በመጣስ እና ሕዝቡን በማጥቃት በተደጋጋሚ ይከሳል። የእስራኤል መንግሥት ግን የሐማስ አባላትን ለመመታት ፍቃድ አለኝ ብሎ ይከራከራል።

ለሁለት ዓመታት የቀጠለው የጋዛ ጦርነት ሐማስ በደቡባዊ እስራኤል መስከረም 26 2016 ዓ.ም. ጥቃት ፈጽሞ 1,200 ሰዎችን ከገደለ እና 251 ሰዎችን አግቶ ከወሰደ በኋላ የተቀሰቀሰ ነው።

እስራኤል ለሐማስ ጥቃት በጋዛ ወታደራዊ ዘመቻ በመክፈት ምላሽ የሰጠች ሲሆን እንደ ሐማስ መሩ የጤና ሚኒስቴር መረጃ ከሆነ 72,744 ሰዎች ተገድለዋል። ከእነዚህም ውስጥ 857ቱ ከተኩስ አቁም ስምምነቱ በኋላ የተገደሉ መሆናቸውን አስታውቋል።