የኔዘርላንድስ ፍርድ ቤት በሩዋንዳ የዘር ጭፍጨፋ ተሳትፈዋል ባላቸው ግለሰብ ላይ የእድሜ ልክ እስር በየነ

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
የኔዘርላንድስ ፍርድ ቤት እአአ በ1994 በሩዋንዳ በተፈፀመው የዘር ጭፍጨፋ ተሳትፈዋል ባላቸው ሆላንዳዊ - ሩዋንዳዊ ዜጋ ላይ የእድሜ ልክ እስር በየነ።
ኢዩጊን ኤን በሚል የሚጠሩት የ66 ዓመቱ ግለሰብ ከተከሰሱባቸው ወንጀሎች መካከል በስታዲየም ተጠልለው በነበሩ ቱትሲዎች ላይ የእጅ ቦምብ መወርወር ይገኝበታል።
ግሰለቡ የዘር ማጥፋትን ዓላማ በማድረግ "የጦር እና የዘር ጭፍጨፋ ወንጀል በመፈፀማቸው" ፍርዱ እንደተላለፈባቸው ዳኛው አስረድተዋል።
ሩዋንዳ ግለሰቡ ተላልፎ እንዲሰጣት እአአ በ2014 ጠይቃ የነበረ ሲሆን የኔዘርላንድስ ባለሥልጣናት የሆላንድ ዜግነት ባላቸው ግለሰቡ ላይ የራሳቸውን ምርመራ ከፍተዋል።
እአአ በ1994 በ100 ቀናት ውስጥ በተፈፀመው ጭፍጨፋ ወደ 800 ሺህ የሚገመቱ የቱትሲ ብሔር አባላት እና በፖለቲካ ለዘብተኛ አመለካከት ያላቸው ሁቲዎች በአክራሪ ሁቲዎች ተገድለዋል።
የሄግ ፍርድ ቤት እንዳለው ጭፍጨፋው በተፈፀመበት ወቅት ኤን በማኅበረሰቡ ውስጥ ሥልጣን የነበራቸው ሲሆን በደቡባዊ ሩዋንዳ በምትገኘው ምባዚ ውስጥ ከ1 ሺህ በላይ ሰዎችን ያስተዳድሩ ነበር።
" ተጠርጣሪው ከፍተኛ ክብር የነበረው ሰው ነበር፤ በመሆኑም እንደ አካባቢው አስተዳዳሪነቱ ኃላፊነቱን እና የነበረውን ተፅዕኖ ማወቅ ነበረበት" በማለት "በርካታ ከባድ ወንጀሎችን በመፈፀሙን" ፍርድ ቤቱ አስረድቷል።
በእግር ኳስ ስታዲየም ሁቱዎች እዲያመልጡ እንዳይፈቅዱ ለቱትሲዎች መመሪያም ሲሰጡ ነበር። ቱትሲዎች ከስታዲየሙ እንዳይወጡ በማድረግ በድንጋይ ተወግረዋል፣ በጥይት ተመትተዋል እንዲሁም የእጅ ቦንብ ተወርውሮባቸዋል።
"ከዚህ የተረፉትም በዱላ እና በስለት ተገድለዋል" ብሏል ፍርድ ቤቱ።
ከስታዲየሙ ጥቃት ቀደም ብሎም ኤን ሰዎች ቤቶችን ሲዘርፉ እና ሲያቃጥሉ እጃቸውን አጣጥፈው ሲመለከቱ እንደነበርም አክሏል።
"ለተጎጂዎች እና በሐዘን ላይ ባሉ ቤተሰቦች ላይ ለደረሰው ከፍተኛ ስቃይ ፍትሕ የሚሆነው የዕድሜ ልክ እስራት ብቻ ነው" ብሏል ፍርድ ቤቱ።
እአአ በ2020 ኔዘርላንድስ በከፈተችው ምርመራ ከ30 በላይ የዓይን ምስክሮች ተጠይቀዋል። ይህንን ተከትሎም ከአራት ዓመት በኋላ ኤን በቁጥጥር ሥር ውለዋል።
ኤን " በዚያ አሰቃቂ ክስተት ቤተሰባቸውን ያጡ ተጎጂ መሆናቸውን" በመጥቀስ የቀረበባቸውን ሁሉንም ክሶች ውድቅ ማድረጋቸውን ኤኤፍ ፒ የዜና ወኪል ዘግቧል።
ጠበቆቻቸውም " ክሱ ቁስላቸውን እንደገና ነካክቶታል፤ ጉዳት የደረሰበት ሰው ነው" ሲሉ መከላከላቸውን ኤኤፍፒ በዘገባው ጠቅሷል። ከቀረቡባቸው ሁሉም ክሶች ነፃ ለማውጣትም ሲንቀሳቀሱ ነበር። ጠበቆቻቸው "በፍርዱ ላይ ይግባኝ እንደሚጠይቁ" መናገራቸውን የአካባቢው የዜና ወኪል ኤኤንፒ ዘግቧል።















