ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኢሰመኮ በትግራይ ክልል "ለግዳጅ ወታደራዊ ምልመላ" ከተዳረጉት ውስጥ "አብዛኛዎቹ ከ18 ዓመት በታች ናቸው" አለ
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በትግራይ ክልል እየተካሄደ ባለው "የግዳጅ ለወታደራዊ ምልመላ"፤ "ከሚታፈሱ ሰዎች መካከል አብዛኞቹ ከ18 ዓመት በታች" መሆናቸውን ማረጋገጡን ገለጸ።
በክልሉ የሚካሄደው ሰዎችን "በግዳጅ ለወታደራዊ ምልመላ ወይም ለጦርነት የማሰማራት" ተግባር እንደ "ጉልበት ብዝበዛ" እና "የጦር ወንጀል" ሊቆጠር እንደሚችልም አሳስቧል።
መንግሥታዊው የሰብአዊ መብቶች ተቋም ትናንት ቅዳሜ ሰኔ 27/2018 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ይህንን ያለው በመቀለ ከተማ ወጣቶች ሲታፈሱ እና ነዋሪዎች ተቃውሟቸውን ሲገልጹ ያሳያሉ የተባለ ቪዲዮዎች በማኅበራዊ ሚዲያ በተሰራጩ ማግሥት ነው።
በህወሓት ሊቀ መንበር ዶ/ር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል የሚመራው የክልሉ ካቢኔ፤ በመቀለ '05 ቀበሌ' ተፈጽሟን የተባለውን ክስተት "እንደሚያጣራ" መናገሩን ትግራይ ቲቪ ዘግቧል።
ኢሰመኮ በቅዳሜ ዕለት መግለጫው፤ ትግራይ ክልል ውስጥ የሚፈጸሙ ድርጊቶች እንዲሁም ክልሉን በሚያጎራበቱ አካባቢዎች "ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች እና ግጭቶች" የፈጠሯቸውን "አሳሳቢ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታዎች በቅርበት" እየተከታተለ መሆኑን አስታውቋል።
ኮሚሽኑ በቀዳሚነት የጠቀሰው በትግራይ ክልል ነዋሪዎች "በግዳጅ ወደ ውትድርና ለማሰማራት" ውሏል ያለውን "የውሳኔ ሰነድ" ነው።
ኢሰመኮ "የውሳኔ ሰነድ" በሚል የጠቀሰው "የትግራይ ሕዝብ ኅልውና እና ደኅንነትን ለማረጋገጥ የወጣ አዋጅ" የጸደቀው ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ወደ ሥራ በመለሰው የትግራይ ክልል ምክር ቤት ነው።
ካለፈው ሳምንት አንስቶ ተፈጻሚ እንዲሆን በምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ትዕዛዝ የተሰጠበት ይህ አዋጅ፤ ከዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብቶች ተቋም ሂውማን ራይትስ ዎች ጭምር ተቃውሞ ቀርቦበታል።
ኢሰመኮ በትናንት መግለጫው፤ "የውሳኔ ሰነዱ" የወጣው "በፕሪቶሪያ ስምምነት መሠረት በፈረሰ" ምክር ቤት መሆኑን ጠቅሷል። ይህ እርምጃም የዘላቂ ግጭት ማቆም ስምምነቱን "የሚጥስ" እና የአገሪቱን ሕገ መንግሥት "የሚጻረር" መሆኑን ገልጿል።
በዚህ አዋጅ መሠረት "የግዳጅ ውትድርና ጥሪን" ያልተቀበሉ ነዋሪዎች ላይ የገንዘብ ቅጣት እንደሚጥል፣ ተቃውሞ የሚያሰሙ ሰዎችን እስከ 25 ዓመት በሚደርስ እስራት እንደሚቀጣ እንዲሁም ሕጉ ወደኋላ ተመልሶ ጭምር ተግባራዊ እንደሚሆን ዘርዝሯል።
ይህ አዋጅ ከመውጣቱ አስቀድሞም ግን በትግራይ ክልል "ወጣቶችን፤ በተለይም ሕጻናትን፣ ተፈናቃዮችን፣ የአእምሮ ጤና ሕሙማንን" የመያዝ ተግባር ሲፈጸም እንደነበር "ታፍሰው ከተመለሱ ወጣቶች፣ ከቤተሰቦቻቸው እና ከተለያዩ ሰነዶች" ማረጋገጡን ገልጿል።
የኢሰመኮ መግለጫ እንደሚያሳየው "ከስደተኛ ካምፖች እና ከጸበል ሥፍራዎች" ጭምር የተያዙት ሰዎች "ወደ ወታደራዊ [የ]ሥልጠና ካምፖች" እንዲገቡ ተደርገዋል። አዋጁ ከወጣ በኋላ ደግሞ "ይህ ተግባር ይበልጥ ተጠናክሮ" መቀጠሉን ገልጿል።
"የአብነት ትምህርት ቤት ተማሪዎችን ከአብያተ ክርስትያናት፣ እንዲሁም በርካታ ሌሎች ሰዎችን ከገበያ ስፍራ፣ ከወጣቶች ማዘውተሪያ ማዕከላት እና ቤት ለቤት በሚደረግ አሰሳ በማፈስ ወደ ወታደራዊ ተግባር እንዲሰማሩ [ተደርገዋል]" ሲል ከስሷል።
በተጨማሪም ኮሚሽኑ፤ "በግዳጅ ከሚታፈሱ ሰዎች መካከልም በአብዛኛው እድሜያችዉ ከ18 ዓመት በታች መሆናቸዉን ኢሰመኮ ለማረጋገጥ ችሏል" ሲል ግኝቱን ገልጿል።
ኢሰመኮ በመግለጫው የጠቀሰው የአብነት ተማሪዎች "አፈሳ" የተካሄደው ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ሰኔ 18/2018 ዓ.ም. ሌሊት ላይ እንደሆነ ወጣቶቹ የነበሩበት የ"ጽርሐ አርያም ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያ" አንድ ምንጭ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ምንጩ እንደገለፁት፤ "የቤተክርስቲያን ተማሪዎች አይደላችሁም" ተብለው የተወሰዱት ወጣቶች ብዛት "በግምት እስከ 20" ይደርሳል።
"ማንነታቸው ያልታወቁ የታጠቁ ሰዎች፤ [አብነት ተማሪዎች] የሚያድሩበት ጎጆን፣ በራቸውን እየመቱ፣ 'ኑ ውጡ' እያሉ፤ ወደ ውጭ አውጥተው ሰብስበው ታላላቆቹን መርጠው [ወስደዋቸዋል]" ሲሉ የተፈጠረውን አስረድተዋል።
"ፊታቸውም በማስክ" በሸኑ የታጠቁ ሰዎች የተወሰዱ ሰዎች የት እንዳሉ በትክክል እንዳልታወቀም ገልጸዋል። ይሁን እንጂ ተወስደዋል የተባሉት ተማሪዎች ስልክ ደውለው "ማሰልጠኛ ካምፕ" ውስጥ እንደሚገኙ መናገራቸውን ምንጩ አንስተዋል።
ስለዚህ ጉዳይ የተጠየቁት የህወሃት ቃል አቀባይ ሚካኤለ አስገዶም መረጃው "ትክክል አይደለም" ሲሉ አስተባብለዋል።
ከቢቢሲ አማርኛ የሬዲዮ ፕሮግራም ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ "አልተካሄደም ነው እያልኩህ ያለው። ቢኖር አወግዘዋለሁ። እንደ መንግሥትም እንደ ድርጅትም እንደዚህ አይነት እንቅስቃሴ እንዲደረግ በፍጹም አንፈቅድም" ሲሉ ተናግረዋል።
አርብ ዕለት ደግሞ አንድ ሕዝብ ትራንስፖርት ተሽከርካሪ መቐለ ከተማ "ዒላላ" የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ደጃፍ ላይ ቆሞ፤ ከግቢው የሚወጡ ወጣቶችን ሲጭን የሚያሳይ ቪዲዮ ተለቅቋል። ከመኪናው ጀርባ በርቀት በርካታ ሰዎች ቆመው ይታያል።
'05 ቀበሌ' በተባለው የከተማው ስፍራ ተሽከርካሪው እየተንቀሳቀሰ ባለበት ሰዓትም ድርጊቱን የተቃወሙ ነዋሪዎች መኪናው ላይ ድንጋይ ሲወረውሩ ታይቷል። ሌላ ቪዲዮ ላይ ደግሞ ተቃውሟቸውን እያሰሙ እንደሆነ የተገለጹ በርካታ እናቶች እያለቀሱ ሲጓዙ ይታያል።
ቢቢሲ የእነዚህን ቪዲዮዎች ትክክለኛነት በገለልተኝነት ማረጋገጥ አልቻለም። በዚያው ዕለት የክልሉ መገናኛ ብዙኃን በሆነው ትግራይ ቲቪ የቀረቡት ኮሚዩኒኬሽንጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር አብርሃም ሀጎስ ስለ እነዚህ ቪዲዮዎች ተጠይቀዋል።
ቪዲዮዎቹን ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ "መመልከታቸውን" የገለጹት የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊው፤ "ጉዳዩ እንዲጣራ በመንግሥት አቅጣጫ" መሰጠቱን ተናግረዋል። "በዝርዝር ይጣራል። ተጣርቶ ለምን እንደዚህ አይነት ሁኔታ ተፈጠረ የሚለው ይታያል" ብለዋል።
በዚህ ክስተት ውስጥ ተሳትፎ ያደረጉ "የመንግሥት ወይም የጸጥታ አካላት ካሉ በግልጽ አስተዳደራዊና ሕጋዊ እርምጃ" እንደሚወሰድም ገልጸዋል።
በክልሉ የሰብአዊ መብት ጉዳዮችን የሚከታተለው ቅድሚያ ለሰብአዊ መብቶች የተባለው ተቋም በበኩሉ የአብነት ተማሪዎች እና በቪዲዮዎቹ የታዩት ክስተቶች አስገዳጅ ወታደራዊ ምልመላው "በትልልቅ ከተሞችም የመስፋፋት አዝማሚያ" እያሳየ መሆኑን በማንሳት ስጋቱን ገልጿል።
የድርጅቱ ምክትል ዳይሬክተር መብርሂ ብርሃን እንደሚናገሩት ተቋማቸው ከአንድ ወር በፊት ስለ አስገዳጅ ወታደራዊ ምልመላ ምርመራ ባደረገበት ወቅት ድርጊቱ የሚታየው የወረዳ ከተሞች እና ገጠራማ አካባቢዎች አስታውሰዋል።
"አሁን ግን ወደ ከተሞች እየመጣ እየተስፋፋ ነው" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል። በተጨማሪም ቅድሚያ ለሰብአዊ መብቶች ምርመራ ባደረገበት ወቅት "እድሜያቸው ከ18 በታች የሆኑ" ልጆች ተይዘው ማግኘታቸውን አስረድተዋል።
ይህንን ተግባር ያወገዘው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በበኩሉ፤ "ሕፃናትን እና ሌሎች ለመብቶች ጥሰት ተጋላጭ የሆኑ ሰዎችን በግዳጅ ለወታደራዊ ምልመላ ወይም ለጦርነት ማሰማራት" ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን የሚጥስ እንደሆነ ገልጿል።
"ይህ ተግባር ከመንግሥት ውጪ ባለ ታጣቂ ቡድን የሚፈጸም በመሆኑ፤ እንደ ጉልበት ብዝበዛ ብሎም እንደ የጦር ወንጀል ሊቆጠር የሚችል ነው" ሲልም አሳስቧል። የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ "በቅርቡ በክልሉ ወጣ የተባለው የግዳጅ ውትድርና ሰነድ ዓለም አቀፍ ሕግን የጣሰ" እንደሆነ ገልጸዋል።
አዋጁ "ሕገ መንግሥታዊ መሠረት የሌለው እና ለተደራራቢ እና ከፍተኛ ለሆነ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ምክንያት" እንደሆነ የተናገሩት ዋና ኮሚሽነሩ፤ "በአስቸኳይ ተፈጻሚነቱ እንዲቆም" ጠይቀዋል።
በትግራይ ክልል የሚታየውን "የፖለቲካ ውጥረትና ወታደራዊ እንቅስቃሴ" ለማርገብ እንዲቻልም "በክልሉ የሚንቀሳቀሰውን ታጣቂ ኃይል ጨምሮ ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት ውጥረትን እና ግጭትን ከሚያባብሱ ድርጊቶች እንዲቆጠቡ" ጥሪ አቅርበዋል።