1 ሚሊዮን ዶላር የማሸነፍ ከ50 በመቶ ዕድል እና 50 ሺህ ዶላር አሁኑኑ ከመውሰድ የቱን ይመርጣሉ?

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

አሁኑኑ 50 ሺህ ዶላር ከማግኘት እና 1 ሚሊዮን ዶላር የማሸነፍ 50 በመቶ ዕድል የትኛውን ይመርጣሉ?

4 ሺህ 600 ብሪታኒያውያን ተመሳሳይ ምርጫ ተሰጥቷቸው እንደነበር የዓለም አቀፉ የምርምር እና መረጃ ተቋም- ዩጎቭ አስታውቋል።

በዚህም ወደ ሦስት አራተኛ የሚጠጉት (73 በመቶ) አሁን 50 ሺህ ዶላሩን መውሰድን እንደሚመርጡ ተናግረዋል።

ከአንድ አምስተኛ በላይ (21 በመቶዎቹ) የሆኑት ደግሞ 1 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ያላቸውን ዕድል እንደሚጠብቁ ሲናገሩ፣ 6 በመቶ የሚሆኑት ግን ምን ማድረግ እንዳለባቸው መወሰን አልቻሉም።

82 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች እንዲሁም 63 በመቶ ወንዶች 50 ሺህ ዶላሩን ለማግኘት ከወሰኑት መካከል ይገኙበታል፤ ይህም በፆታ ረገድም ግልጽ ልዩነት መኖሩን አመልክቷል።

መጀመሪያ ላይ ጥናቱ የተካሄደው በዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ብቻ ሲሆን ውጤቱም በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ክርክር አስነስቷል።

"ብሪታንያ በምድር ላይ ካሉት ሁሉ ኪሳራን በጣም የምትጠላ መሆን አለባት!" ሲል አንድ ግለሰብ አስተያየቱን ሰጥቷል፤ ሌላኛው ደግሞ "ይህ የዩኬ ችግር ነው!" ሲል አስተያየቱን አስፍሯል።

ግን ያ እርግጥ እውነት ነው? ብሪታኒያውያን እና ምናልባትም እርስዎ የመጀመሪያውን አማራጭ ከመረጡ ምክንያታዊ ባልሆነ መንገድ አደጋን የሚፈሩ ናቸው?

ብልጥ ልጅ የሰጡትን ይዞ ያለቅሳል . . .

የቢቢሲ የኢኮኖሚክስ አርታኢ ፋይሰል ኢስላም ጥያቄውን የዕድል ጉዳይ ብቻ አድርጎ መመልከት በጣም ገዳቢ ነው ሲል ይከራከራል።

"ዕጣ ማውጣት እንዳለብህ የሚያስቡ ሰዎች በጣም ረቀቅ ያሉ መሆናቸውን እና የ50 ሺህ ዶላሩን ለመውሰድ የወሰኑ ደግሞ ሞኝ እንደሆኑ ያስባሉ። ግን አስቂኝ የሆነው ይህ ኢኮኖሚክስ ሀ ሁ ነው። በባህሪ ኢኮኖሚክስ ውስጥ የውሳኔ ኅልዮት ብለን የምንጠራው አለ።"

የአንድን ነገር የመከሰት ዕድል ከሚጠበቀው ውጤት ጋር በማባዛት የሚሰላው ስሌት፣ ሰዎች ውሳኔዎችን እንዴት እንደሚያሳልፉ ሙሉ በሙሉ እንደማያንጸባርቅ ይናገራል።

ኢስላም ወደ ስዊትዘርላንዱ የሂሳብ ሊቅ ዳንኤል ቤርኑሊን ሥራ በመጠቆም፣ እርሱ ከ300 ዓመታት ገደማ በፊት ሰዎች ለገንዘብ ያላቸውን ግምት የሚወስኑት በገንዘቡ ዋጋ ላይ ብቻ ተመሥርተው እንዳልሆነ አሳይቶ እንደነበር ያስረዳል።

በቀላል አነጋገር፣ የአንድ ነገር የገንዘብ ዋጋ ሁልጊዜ ለአንድ ሰው ካለው ጠቀሜታ ጋር አቻ አይደለም።

የቤርኑሊ ሥራ፣ አንድን የምንፈልገውን ነገር እየገዛን በመጣን ቁጥር እየቀነሰ የሚሄድ የደስተኝነት ስሜት ሃሳብን ለማዳበር አስተዋጽኦ አድርጓል። ይህም ማለት አንድን ነገር በብዛት ባላችሁ ቁጥር፣ ከእያንዳንዱ ተጨማሪ ቁስ የምታገኙት ተጨማሪ ጥቅም ወይም እርካታ ይቀንሳል ማለት ነው።

ለምሳሌ፦

  • ከ0 ዶላር ተነስቶ 50 ሺህ ዶላር ማግኘት ሕይወትን በእጅጉ ሊለውጠው ይችላል።
  • ከ50 ሺህ ዶላር ወደ 100 ሺህ ዶላር ከፍ ማለትም ብዙ ይረዳል፣ ግን ምናልባት የመጀመርያውን ያህል ስሜት ላይሰጥ ይችላል።
  • ከ950 ሺህ ዶላር ወደ 1 ሚሊዮን ዶላር መሄድ ግን ምናልባት ላለንበት ሁኔታ ብዙም ለውጥ አያመጣም።

በዚህ አመክንዮ ውስጥ ሆነን ካየነው በአሁኑ ጊዜ በበርካታ ብሪታኒያውያን ዘንድ የሚታየውን የፋይናንስ ጫናን ከግምት ውስጥ በማስገባት 50 ሺህ ዶላር በእርግጠኛነት ማግኘት እጅግ ማራኪ ነው።

ይህ ገንዘብ በዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ አንድ ግለሰብ በአማካይ ከሚያገኘው 10 ሺህ ፓውንድ ወርሃዊ ደሞዝ ጋር ሲነጻጸር በእጅጉ ከፍ ያለ ነው።

ይህ ግን ብቸኛው ጉዳይ ብቻ አይደለም፣ ሌላው አስፈላጊ ሀሳብ የመጻዒ ዕድል ቲዎሪ (Prospect Theory) የሚባለው ነው።

ኪሳራን መፍራት

የፕሮስፔክት ቲዎሪ የሚነሳው በአውሮፓውያኑ 1979 በዳንኤል ካህነማን እና በአሞስ ትቨርስኪ ከተጻፉት የጥናት ወረቀቶች ሲሆን፣ የቢሄቬሪያል ኢኮኖሚክስ መሠረቶች አንዱ እንደሆነ ይታሰባል።

ሰዎች በተለያዩ የፋይናንስ አማራጮች መካከል ምርጫ የሚያደርጉባቸውን በርካታ በጥንቃቄ የተመሩ ጥናቶችን ካካሄዱ በኋላ፣ ሁለቱ ተመራማሪዎች ሰዎች ኪሳራን እና ጥቅሞችን እንዴት እንደሚያመዛዝኑ በተመለከተ ጠቃሚ ድምዳሜዎች ላይ ደርሰዋል።

አንዱ ግኝት ሰዎች ለአነስተኛ ዕድሎች ከመጠን በላይ ክብደት የሚሰጡ መሆኑ ነው። ለመካከለኛ እና ለትልቅ ዕድሎች ደግሞ በጣም ትንሽ ክብደት እንደሚሰጡ ደርሰውበታል። ሰዎች ስለገንዘብ እና ኪሳራ የሚወስኑት ከሚያወዳድሩት ነገር ጋር በማነጻጸር ነው።

ለምሳሌ፣ በውርርድ 10 ዶላር ካጡ፣ ያንን ገንዘብ መልሰው ለማግኘት ሌላ 10 ዶላር ለማውጣት፣ ከመጀመሪያውኑ በ20 ዶላር ለመወራረድ ከነበረዎት ፍላጎት ይልቅ የበለጠ ፍላጎት ሊኖርዎት ይችላል።

በሌላ አነጋገር ሃሳብዎ ተጠቅልሎ የተመሠረተው ከሚያነጻጽርበት ነጥብ ጋር ነው ማለት ነው።

ከዚያም ጥናቱ የደረሰበት እና በጣም ታዋቂ የሆነው መደምደሚያ "ኪሳራዎች ከትርፍ የበለጠ ያንዣብቡብናል" የሚል ነው።

ገንዘብ ማጣት፣ ብዙውን ጊዜ ተመሳሳይ መጠን ያለው ገንዘብ አግኝተን ከሚሰማን ደስታ ይልቅ የከፋ ስሜት ይፈጥራል። ሰዎች ቀደም ሲል የያዙትን ነገር ከማጣት ለመቆጠብ ከፍተኛ ግምት ይሰጣሉ።

አንድ ሚሊዮን ዶላር የማግኘት ዕድልን ከመረጡ እና ካላሸነፉ፣ 50 ሺህ ፓውንድ እንዳጡ ያህል ይሰማዎታል።

ለብዙ ሰዎች ይህ ብዙ ገንዘብ ነው። በዩኬ፣ የመኖሪያ ቤትና የጡረታ ክፍያን ሳይጨምር፣ 25 በመቶ የሚሆኑ ብሪታኒያውያን ብቻ 50 ሺህ ፓውንድ ወይም ከዚያ በላይ የገንዘብ ሀብት አላቸው። በሌላኛው ወገን ደግሞ 25 በመቶ የሚሆኑት ከ300 ፓውንድ በታች አላቸው።

ይሁን እንጂ በአጠቃላይ ዝቅተኛ ገቢ ቢያገኙም፣ ከ18 እስከ 24 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ሰዎች፣ በጥናቱ መሠረት፣ ከማንኛውም የዕድሜ ክልል ይልቅ በ1 ሚሊዮን ፓውንድ ላይ ለመወራረድ የበለጠ ፈቃደኛ ነበሩ። ከ65 ዓመት በላይ ከሆኑት መካከል 11 በመቶ የሚሆኑት ብቻ ዕጣ አውጥቶ ለመወሰን ፈቃደኛ ነበሩ።

ከፆታ እና ከዕድሜ በተጨማሪ፣ አንዳንድ ሰዎች የባህል ልዩነቶች በውሳኔያቸው ላይ ሚና ሊኖራቸው እንደሚችል ጠቁመዋል። በኦንላይን ክርክሩ ላይ የተሳተፉ አንዳንድ አሜሪካውያን ሌሎች ማኅበረሰቦች የበለጠ ኪሳራ ለመጋፈጥ ፈቃደኛ እንደሚሆኑ ጠቁመዋል። ከጥቂት ቀናት በኋላም ዩጎቭ በዩናይትድ ስቴትስ ተመሳሳይ ጥያቄ አቅርቧል።

ውጤቱ በጣም ተመሳሳይ ነበር።