ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኡጋንዳ የተከሰተው ድርቅ ባስከተለው ረሃብ ቢያንስ 16 ሰዎች ሞቱ
በኡጋንዳ ሰሜን ምሥራቃዊ ግዛት ካራሞጃ በተከሰተ ድርቅ ምክንያት ባለፉት ሳምንታት ውስጥ ቢያንስ 16 ሰዎች በረሃብ መሞታቸውን የአገሪቱ መንግሥት አስታወቀ።
በአካባቢው ሰብል ከሚዘራበት ከሚያዝያ ወር መጀመሪያ አንስቶ ዝናብ ባለመዝነቡ ወይም በቂ ዝናብ ባለማግኘታቸው ሰብላቸው እንደወደመባቸው አርሶ አደሮች ተናግረዋል።
ባለሙያዎች በአካባቢው ለሚከሰተው ተደጋጋሚ ድርቅ የአየር ንብረት ለውጥ፣ በቂ ዝናብ አለመኖር፣ የደን መጨፍጨፍ፣ ከመጠን በላይ ደጋግሞ ማረስ እና የሰብል ተባዮችን በምክንያትነት ጠቅሰዋል።
እነዚህ ተደማምረው የአካባቢውን ማኅበረሰብ ለከፋ ረሃብ አጋልጠውታል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሮቢናህ ናባንጃ እንዳሉት የተከሰተው ድርቅ በሺዎች የሚቆጠሩ ቤተሰቦችን ያለ ምግብ አስቀርቷል።
በመሆኑም ቢሯቸው በድርቅ ለተጎዱ አካባቢዎች የሚውል ተጨማሪ የምግብ ግዥን ለማጽደቅ ሰኞ ለካቢኔው እንደሚያቀርብ ጠቅላይ ሚኒስትሯ ተናግረዋል።
እስከዚያ ድረስ መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ እያከፋፈለ እንደሆነ ገልጿል።
በቆሎ፣ ማሽላ እና አኩሪአተር በብዛት የሚመረቱቸባው አካባቢዎች በድርቁ ክፉኛ የተጎዱ ሲሆን ከፍተኛ ምርት የማግኘት ተስፋን አጨልሟል።
ባለሙያዎች በተሻለ የአየር ትንበያ፣ የመስኖ ግንባታ እና ድርቅን በሚቋቋሙ ሰብሎች ላይ እንዲሰራ ጥሪ አቅርበዋል።
የኡጋንዳ ከፊል በረሃማ የሆነው የሰሜን ምሥራቅ አካባቢ ከዚህ ቀደምም በከፍተኛ ድርቅ ተመትቷል።
እንደ አውሮፓውያኑ 2022 በሰሜን ምሥራቅ ኡጋንዳ ከ2 ሺህ 200 በላይ ሰዎች በረሃብ እና ከረሃብ ጋር ተያያዥ በሆኑ በሽታዎች መሞታቸውን የሰብዓዊ መብት ተቋም ሪፖርት አመልክቷል።
ይህንን ተከትሎ በወቅቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት ሄንሪ ኦኬሎ ኦርይም፣ ኡጋንዳ ተስማሚ የሆነ አየር ንብረት እና ለም መሬት አላት ስለዚህ ሰዎች የራሳቸውን ምግብ ማምረት ይገባቸዋል እንዲሁም በረሃብ የሞቱት ሰዎችን " ሞኞች' ካሉ በኋላ ቁጣ ተቀስቅሶ ነበር።
የቀድሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፣ " በኡጋንዳ በረሃብ የሚሞቱ ሰዎች ሞኞች ብቻ ናቸው፤ ትክክለኛ ሞኞች" ሲሉ ነበር በወቅቱ ለአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን የተናገሩት።
" ጠንክራችሁ ከሠራችሁ በኡጋንዳ መሬት አለ። የአየር ንብረት ለውጥ ቢኖርም አየሩ ተስማሚ ነው። ጠዋት ተነስታችሁ ለማረስ፣ ለመዝራት እና ለመንከባከብ ጥረት ካደረጋችሁ እንዴት ምግብ ለማግኘት ይሳናችኋል?" ብለዋል።
በወቅቱ በሰሜን ምሥራቃዊ የአገሪቷ ክፍል በተከሰተው ድርቅ ሳቢያ ከሞቱት በተጨማሪ "ለከፋ ረሃብ የተዳረጉ" ግማሽ ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች መፈናቀላቸውን የኡጋንዳ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን መግለጹ ይታወሳል።