አሜሪካ ከዴንማርክ ጋር በደረሰችው ስምምነት መሠረት በግሪንላንድ ሁለት የጦር ሠፈሮችን ልትገነባ ነው

ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ እና የዴንማርክ ጠቅላይ ሚኒስትር ሲጨባበጡ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

አሜሪካ፣ ዴንማርክ እና ግሪንላንድ ዋሽንግተን በአርክቲኳ ግዛት ሁለት የጦር ሠፈሮችን ለመገንባት የሚያስችላትን የመከላከያ ስምምነት ተፈራረሙ።

ትናንት በኒው ዮርክ በተጀመረው የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባዔ ከተካደሄው የፊርማ ሥነ ሥርዓት አስቀድሞ የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ "በትክክለኛው ቦታዎች ትልቅ የጦር ሠፈር የመገንባት ሒደቱን ቶሎ እንጀምራለን" ብለዋል።

የዴንማርክ ጠቅላይ ሚኒስትር ሚት ፍሬደሪክሰን ስምምነቱ " ለአሜሪካ፣ ለዴንማርክ እና ግሪንላንድ እንዲሁም ለአውሮፓ እና ኔቶ መልካም ነው" ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሯ ጨምረውም ስምምነቱ "የዴንማርክን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነትን እንዲሁም የግሪንላንድን የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት ያከበረ ነው" እንደሆነ ገልጸዋል።

የግሪንላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ጂንስ ፍሬድሪክ ኔልሰን በበኩላቸው "ሁሉም ወገን አሸናፊ የሆነበት ስምምነት" እንደሆነ ተናግረዋል።

ግሪንላንድ ለሰሜን አሜሪካ እና አትላንቲክ ተሻጋሪ አገራት ደኅንነት ወሳኝ ናት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) በሰሜን አትላንቲክ ያለውን የጸጥታ ሁኔታ በመለወጥ ወሳኝ ሚና እንደነበረው አስታውሰዋል።

ሦስቱ መሪዎች በስምምነቱ ላይ ፊርማቸውን ያኖሩ ሲሆን በአርክቲክ ግዛቷ ጉዳይ ከአንድ ዓመት በላይ ተፈጥሮ የነበረውን ውጥረት እንዲቋጭ ያደረገው ይመስላል።

ትራምፕ ባላት ስትራቴጂያዊ አቀማመጧ እና ብርቅዬ ማዕድናት ምክንያት የብሔራዊ ደኅንነት ስጋት መሆኗን በመግለጽ ከፊል ራስ ገዝ አስተዳደር የሆነችውን ግሪንላንድን ለመጠቅለል ሲዝቱ ቆይተዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
BBC News Amharic የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናላችንን ይቀላቀሉ!
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ይህ ንግግራቸው በግሪንላንዳውያን፣ ዴንማርካውያን እና የአውሮፓ መሪዎች ቁጣ ቀስቅሶ የነበረ ሲሆን በወቅቱ ባወጡት የጋራ መግለጫ " የአትላንቲክ ተሻጋሪ አገራትን ግንኙነት የሚያዳክም እና አደጋ የሚያስከትል" ብለውት ነበር።

አሁን ላይ የደረሱት ስምምነት እአአ በ1951 በዴንማርክ እና በአሜሪካ መካከል የተደረሰውን ስምምነት ያሻሻለ ነው።

አዲሱ ስምምነት አሜሪካ በግሪንላንድ ደቡብ እና ምሥራቃዊ ክፍል ናርሳርሱዋቅ እና ማስተርስቪንግ ተጨማሪ የጦር ሠፈሮችን እንድታቋቁም የሚፈቅድ ነው።

ናርሳርሱዋቅ የቀድሞው የሲቪል አውሮፕላን ማረፊያ እና በሁለተኛው ዓለም ጦርነት የጦር ሠፈር ነበር። አካባቢው ውሃ ገብ ሲሆን ትልቅ የማኮብኮቢያ መንገድ እንዳለው የአሜሪካ የሰሜን እዝ ለቢቢሲ አረጋግጧል።

ማስተርስቪንግ ደግሞ ራቅ ያለ አካባቢ እና ብዙም ያልለማ እና ዴንማርኮች አነፍናፊ ውሾች ለማርባት የሚጠቀሙበት ቦታ ነው።

አሜሪካ የምትገነባቸው የጦር ሠፈሮች ዓይነት እና ቴክኒካዊ ዝርዝሮች እስካሁን አልተገለጹም። ሆኖም እንደ ስምምነቱ ከሆነ ሁሉም ወገኖች የተስማሙበት መሆን ይኖርበታል።

ዋሽንግተን አሁን ላይ በግሪንላንድ ሰሜን ምዕራብ የፑቲፊክ የአየር ኃይል ጣቢያ ያላት ሲሆን አዲሱ ስምምነትም ይህንን ሰፈር እንድታዘምን እና እንድታስፋፋ ይፈቅድላታል።

በተጨማሪም "የኔቶ አባል ያልሆነ ማንኛውም ግዛት በግሪንላንድ ወታደራዊ ተቋማት እንዲያቋቁም እንዲሁም ቋሚ ወታደራዊ ኃይሎች እንዲኖሩ አይፈቀድለትም" ይላል።

የኔቶ አባል ያልሆኑ አገሮች ወታደሮች አሁን በደሴቲቱ ላይ በግልጽ የተከለከሉ ቢሆኑም፣ አጋር ያልሆኑ ወታደሮች መጀመሪያውኑም ወደ ግዛቷ እንዲገቡ ይፈቀድላቸው ነበር የሚለው ጉዳይ አጠራጣሪ ነው።

ስምምነቱ ግሪንላንድ ከዴንማርክ ነፃነቷን ካገኘች የኔቶ አባል ሆና እንደምትቆይም የሚያረጋግጥ ነው።

የ1951ቱ ስምምነት አሜሪካ የፈለገችውን ያህል ወታደሮችን ወደ ግሪንላንድ እንድትልክ አስችሏታል። ዋሽንግተን በፒቱፊክ የጦር ሰፈሯ ከ100 በላይ ወታደሮች በቋሚነት አስፍራለች።

56,000 ሕዝብ ላላት ግሪንላንድ ስምምነቱ ትልቅ እፎይታ የሰጠ ሆኗል። መሪዋ ከዓለም ኃያል ሰው ጋር ጎን ለጎን ተቀምጠው ለወራት የዘለቀውን ቀውስ የሚያስቆም ስምምነትን መፈራረም ችላለች።