አሜሪካ 250ኛ ዓመት የልደት በዓሏን በርችት እና በከፍተኛ ሙቀት ታጅባ አከበረች

ሰዎች ተሰባስበው ርችቶች ሲፈነዱ እየተመለከቱ

የፎቶው ባለመብት, REUTERS/Evan Vucci

የምስሉ መግለጫ, በዋሽንግተን 'ናሽናል ሞል' የተዘጋጀው እና ፕሬዝዳንት ትራምፕ የታደሙበት 'የፎርዝ ኦፍ ጁላይ' በዓል
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ የ250ኛ የልደት በዓሏን በርችት፣ የአውሮፕላን ትርኢት እንዲሁም በአንዳንድ አካባቢዎች በከባድ ሙቀት ታጅባ አከበረች።

የምሽቱን ጨለማ የርችት ብርሃን ከመለኮሱ አስቀድሞ በዋሽንግተን በነበረው የበዓል ሰልፍ ላይ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ "የአሜሪካ ህልም ተመልሷል" ብለዋል።

'ፎርዝ ኦፍ ጁላይ' እየተባለ የሚጠራው የአሜሪካ የነፃነት ቀን እ.አ.አ በ1776፤ 13 የአሜሪካ ግዛቶች ከብርታኒያ ቅኝ ግዛት ነፃ ለመሆን የፈረሙትን የነፃነት አዋጅን በመዘከር ይከበራል።

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወሳኝ ምዕራፍ በሆነው በዓል ላይ ራሳቸውን ዋና ተዋናይ አድርገው አቅርበዋል እንዲሁም ለበዓሉ ፖለቲካዊ ዓይን ሰጥተውታል የሚል ትችት ቀርቦባቸዋል። ፕሬዝዳንቱ ለበዓሉ አከባበር የሕግ መወሰኛው ምክር ቤት ካፀደቃቸው 'አሜሪካ 250' ሁነቶች ውጭ የራሳቸውን በዓል ይፋ አድርገዋል።

የትራምፕ ንግግር ኮሚኒዝምን ውድቅ ማድረግ ላይ ያጠነጠነ ነበር።

"የነፃነት ትግል ለዘለዓለም ይኑር" ያሉት ትራምፕ፤ "እስከመቼውም እና ለዘለዓለም ይንገስ፤ ሁሌም ቢሆን የበላይ እንሆናለን፤ መቼም ቢሆን አገራችን እንድትወድቅ አናደርግም፤ ሁልግዜም ምርጥ እንሆናለን" ብለዋል።

ትራምፕ ንገግራቸውን ሲያጠናቅቁ ለተሰበሰበው ታዳሚ የአገራቸው እጣ ፈንታ "በእግዚአብሔር የተፃፈ" እንደሆነ ተናግረዋል። "ይህ የአሜሪካ ወርቃማ ዘመን መባቻ ነው" ሲሉም ተደምጠዋል።

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና ቀዳማዊት እመቤት ሜላኒያ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, REUTERS/Jonathan Ernst

የምስሉ መግለጫ, ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና ቀዳማዊት እመቤት ሜላኒያ ትራምፕ በበዓሉ ላይ

በዓሉ አዲሱን የፕሬዝዳንቱን አውሮፕላን 'ኤር ፎርስ ዋን' ጨምሮ ሰማዩን ባደመቁ አውሮፕላኖች፣ የሙዚቃ ድግስ እንዲሁም ንግግሮች እና ርችቶች ያሸበረቀ ነበር።

ከዚህ በተጨማሪ በዋሽንግተን 400 የሚሆኑ የነጭ ብሔርተኛ አቀንቃኝ ቡድን አባላት የአሜሪካን ሰንደቅ ዓላማ በመያዝ በጎዳናዎች ሲተሙ ታይተዋል።

በመላው አገሪቱ በዓሉን ለማክበር በጎዳናዎች እና አደባባዮች ዝግጅቶችም ተሰናድተዋል።

በዓሉን ለማክበር የተሰባሰቡ ሰዎች

የፎቶው ባለመብት, REUTERS/Jonathan Ernst

የነፃነት አዋጁ በተፈረመባት እና "የአሜሪካ የትውልድ ስፍራ" ተብላ በምትታወቀው ፊላደልፊያ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤቱ አባላት ተሰባስበው የአሜሪካ የነፃነት የምርጫ ቀንን ዘክረዋል።

'የአሜሪካ 250' አዘጋጆች ከ200 ዓመት በኋላ የሚከፈት ማስታወሻ የሚሆኑ ቁሳቁሶችን የያዘ ሳጥን መሬት ውስጥ ቀብረዋል። ከእነዚህም መካከል የኮካ ኮላ ጠርሙስ፣ ፊርማ ያረፈበት ሕገ መንግሥት እና ከ50 የአሜሪካ ግዛቶች እና አካባቢዎች የተሰባሰቡ ቅርሶች ይገኙበታል።

የመጀመሪያው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት በሆኑት በጆርጅ ዋሽንግተን መኖሪያ ማውንት ቨርነን ቨርጅኒያ ከ50 አገራት የመጡ 150 ሰዎች የአሜሪካ ዜግነትን ተቀብለዋል።

በሕይወት ያሉት የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዝዳንቶች ጆ ባይደን፣ ባራክ ኦባማ፣ ጆርጅ ቡሽ እና ቢል ክሊንተን ትልቅ ምዕራፍ የሆነውን የ250ኛ ዓመት የነጻነትን ቀን በማስመልከት መልዕክት አስተላልፈዋል።