በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ክፍፍል ሊፈጥር ይችላል የተባለው የጳጳሳት ሹመት በስዊትዘርላንድ

ከስዊትዘርላንድ፣ ከፈረንሳይ እና ከአሜሪካ የተሾሙት አወዛጋቢዎቹ አራቱ ጳጳሳት

የፎቶው ባለመብት, EPA/Shutterstock

የምስሉ መግለጫ, ከስዊትዘርላንድ፣ ከፈረንሳይ እና ከአሜሪካ የተሾሙት አወዛጋቢዎቹ አራቱ ጳጳሳት
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ያቀረቡትን ባለመቀበል በስዊትዘርላንድ በምትገኝ ትንሽ መንደር ውስጥ የተፈጸመው የአራት አዳዲስ የካቶሊክ ጳጳሳት ሹመት በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ክፍፍልን ይፈጥራል የሚል ተሰግቷል።

በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በታደሙበት የሲመት ሥነ ሥርዓት ላይ አንድ ከአሜሪካ፣ አንድ ከስዊትዘርላንድ እና ሁለት ከፈረንሳይ የሴንት ፒየስ ኤክስ ማኅበር አባላት የሆኑ ጳጳሳት ተሹመዋል።

ይህ የካቶሊክ ቤተ ክርሰቲያን አካል የሆነው ማኅበር በአውሮፓውያኑ 1960ዎቹ እና 1970ዎቹ ቫቲካን በላቲን ቋንቋ ብቻ ሳይሆን ምዕመናን በሚናገሩት ቋንቋዎች ቅዳሴ ማካሄድን ጨምሮ ያሳለፈቻቸውን ቁልፍ የማሻሻያ እርምጃዎችን የሚቃወም ነው።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ድርጊቱ "የክርስቶስን የተዋሃደ አካል ልብስ የሚለያይ ሊሆን ይችላል" በማለት የገለጹትን "የመከፋፈል ድርጊት" ያሉትን የማኅበሩ መሪዎች የጳጳሳቱን ሹመት እንዳያካሂዱ በመጨረሻው ደቂቃ ላይ ጥሪ አቅርበዋል።

ነገር ግን ረቡዕ ዕለት ጠዋት፣ ማኅበሩ በዓለም ዙሪያ ባሉ በሚሊዮኖች በሚቆጠሩ ካቶሊኮች ዘንድ በምድር ላይ የእግዚአብሔር ወኪል አድርገው የሚቆጥሯቸውን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳትን ሐሳብ በመቃወም በሺዎች የሚቆጠሩ ምዕመናን እና ካህናት በተገኙበት ሹመቱን አከናውኗል።

እነዚህ አራት የተሾሙት ጳጳሳት በተሰጣቸው የክህነት ሥልጣን ላይ ለረዥም ጊዜ ሊቆዩ አይችሉም እየተባለ ነው።

ማኅበሩ ከዚህ በፊት አዳዲስ ጳጳሳትን ለመጨረሻ ጊዜ የሾመው በአውሮፓውያኑ 1988 የነበረ። ነገር ግን ሹመቱ ከተሰጠ በኋላ ተወግዘው ተለይተዋል።

በአውሮፓውያኑ 2009 በማኅበሩ እና በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መካከል የተፈጠረውን ክፍተት ለመዝጋት በሚል ሊቀ ጳጳስ ቤኔዲክት 6ኛ ውግዘቱን አንስተውት ነበር።

በአራቱ የሲመት ሥነ ሥርዓት ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ታድመዋል

የፎቶው ባለመብት, EPA/Shutterstock

የምስሉ መግለጫ, በአራቱ ጳጳሳት የሲመት ሥነ ሥርዓት ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ታድመዋል
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

አሁን ደግሞ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የቤተ ክርስቲያኗን የበላይነት እና አንድነትን ለማስጠበቅ ሲሉ ስዊትዘርላንድ ውስጥ የተሾሙትን አዳዲስ ጳጳሳትን አውግዘው ይለያሉ ተብሎ ይጠበቃል።

አንዳንዶች በሌሎች አብያተ ክርስቲያንት ውስጥ ያለውን የሹመት ልምድ በመጥቅስ የቫቲካን ተቃውሞን የተጋነነ አድርገው ይመለከቱታል።

ነገር ግን በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት መሠረት የርዕሰ ሊቀ ጳጳሱ ይሁንታ ሳይገኝ ጳጳሳትን መሾም የቤተ ክርስቲያኗን አንድነት የሚጥስ ከባድ ጥፋት ተደርጎ ይቆጠራል።

በአውሮፓውያኑ 1970 በአወዛጋቢው የፈረንሳዊው ሊቀ ጳጳስ ማርሴል ሌፌብቭሬ የተመሠረተው ይህ በስዊትዘርላንድ ያለው ማኅበር፤ ካህናት፣ ጳጳሳት፣ ካርዲናሎች እና ቅዳሴውን በራሱ መንገድ የሚመራ ሲሆን ከዋናዋ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የሚለየው በርካታ አቋሞች አሉት።

የማኅበሩ የበላይ ተቆጣጣሪ ዴቪድ ፓግሊያራኒ የጳጳሳቱ ሹመት መካሄዱን አገጋግጠው "ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሱ የክርስቶስ ቄስ፣ የቤተ ክርስቲያን ተጠሪ እንደመሆናቸው" እንደሚወዷቸው በመገለጽ የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሱን ሥልጣን እንደሚያክብሩ ተናግረዋል።

ይህ የጳጳሳት ሹመት ትልቋን ቤተ ክርስቲያን ለመምራት በቅርቡ ለተሾሙት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የመጀመሪያ ፈተና ደቅኖባቸዋል።

የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በዓለም ዙሪያ ካሏት ከ1.4 ቢሊዮን በላይ ተከታዮች ጋር ሲነጻጸር 600 ሺህ ያህል ተከታዮች ያሉት ማኅበሩ ትንሽ ቢሆንም፣ አሁን ግን ካንሳስ ግዛት ውስጥ ካሉት አጥባቂ ተከታዮች ያሉትን አሜሪካን ጨምሮ በበርካታ አገራት ውስጥ ተወካዮች አሉት።

ማኅበሩ ገንዘብ እንዳለው ግልጽ ሲሆን፤ የጳጳሳቱ ሹመት በቀጥታ በዩቲዩብ በሰባት ቋንቋዎች ተሠራጭቷል።

በበዓለ ሲመቱ ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ ታዳሚዎች የተገኙ ሲሆን በነጻ ኮፍያ ታድሏቸዋል። በተጨማሪም እያንዳንዱ ጠርሙስ ላይ የጳጳሱ ዘውድ ምሥል ያለበት 92 ዶላር የሚያወጣ አዲስ የስዊዝ ወይን ጠጅ የስጦታ ጥቅል ተበርክቶላቸዋል።

የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ የአዲሶቹ ጳጳሳት ሹመት ሕገ-ወጥ እንደሆነ እና በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ላይ እንደተፈጸመ ግልጽ ጥቃት አድርገው እንደሚመለከቱት ግልጽ ቢያደርጉም፤ የተፈራውን የቤተ ክርስቲያኒቱን መከፋፈል ላለማባባስ ምንም ማድረግ ላይፈልጉ ይችላሉ እየተባለ ነው።