16 ኬንያውያን የሩሲያን ጦር ከተቀላቀሉ በኋላ መጥፋታቸው ተገለጸ

ልጆቻቸው የጠፉባቸው ወላጆች

የፎቶው ባለመብት, Anadolu via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ባለፈው ወር ልጆቻቸው በዩክሬን ጦርነት መሰለፋቸውን የገለጹ ኬንያውያን ወላጆች በአገሪቱ ምክር ቤት የተቃውሞ ሰልፍ አድርገዋል።
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

16 ኬንያውያን የሩሲያን ጦር ከተቀላቀሉ በኋላ እንደጠፉ የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አስታወቁ። ሌሎች 47 ኬንያውያን ከዩክሬን ጦርነት ወደ አገራቸው መመለሳቸውም ተገልጿል።

ሚኒስትሩ ሙሳሊያ ሙዳቫሊ በሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር ላይ 38 ኬንያውያን ጉዳት ደርሶባቻው በተለያዩ የሩሲያ ሆስፒታሎች እንደሚገኙ ጠቁመዋል።

ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ የጠፉ ኬንያውያን ቁጥር ከ10 ወደ 16 ከፍ ማለቱን ጠቅሰዋል። ኬንያውያኑ በሕይወት ይኑሩ ወይም ይሙቱ አይታወቅም።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ እንዳሉት አሁን ላይ በዩክሬን ጦርነት የተሰለፉ ኬንያውያን ቁጥር 165 ይሆናል ተብሎ የሚገመት ሲሆን፤ አጠቃላይ የኬንያውያን ቁጥር 250 ይደርሳል።

በዩክሬን ጦርነት የሚዋጉ ኬንያውያን ቁጥር ከተጠቀሰውም በላይ ሊሆን እንደሚችል ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

ሁለት ኬንያውያን በዩክሬን ተማርከው መያዛቸውን አክለዋል።

ኬንያውያኑ ሲመለመሉ የፈረሙት ኮንትራት ላይ የሎጅስቲክስ ወይም የውጊያ መሪ እንደሚሆኑ ተጠቅሷል።

"ሪፖርቶች የሚጠቁሙት ግን አብዛኞቹ ኬንያውያን ተዋጊ እንደሚሆኑ አውቀው እንደሄዱ እና ፈቃደኛ እንደሆኑ ነው" ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የሩሲያን ጦር በመቀላቀል ከወርሃዊ ደመወዝ (2,700 ዶላር) በተጨማሪ ከ11,500 እስከ 23,000 ዶላር እንደሚከፈላቸው እንዲሁም ዜግነት እንደሚያገኙ በመግለጽ ምልመላው እንደሚካሄድ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

ቃል የሚገባላቸው ገንዘብ "ከፍተኛ ማነቃቂያ" እንደሆነ አክለዋል።

በኬንያ፣ ሩሲያ፣ ኳታር፣ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የሚገኙ ተቋማት ኬንያውያኑን እንደሚመለምሉ ገልጸዋል።

በዩክሬን ጦርነት የሚሳተፉ ኬንያውያን በሕገ ወጥ መንገድ ነው የተመለመሉት በሚል አገሪቱ ምርመራ ከፍታለች።

ያለፈው ወር ከቢቢሲ ጋር ቆይታ ያደረጉት የኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር 600 የምልመላ ተቋማት መዘጋታቸውን ተናግረዋል። ተቋማቱ ኬንያውያንን ለውጭ አገር ሥራ ሲመለምሉ ቆይተዋል።

ባለፈው ወር ልጆቻቸው በዩክሬን ጦርነት መሰለፋቸውን የገለጹ ኬንያውያን ወላጆች በአገሪቱ ምክር ቤት የተቃውሞ ሰልፍ አድርገዋል። መንግሥት ልጆቻቸውን እንዲያስመልስም ጠይቀዋል።

የኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሩሲያ አቻቸው ሰርጌ ላቭሮቭን በሞስኮ አግኝተው ኬንያውያን በሩሲያ ጦር መመልመላቸውን በተመለከተ ተወያይተዋል።

ሁለቱ አገራት ምልመላውን ለማስቆም መስማማታቸውም ተገልጿል።

የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በውይይቱ ወቅት "ኬንያውያን እንደ ሩሲያውያን ሁሉ በጦሩ ለመግባት ፈቃዳቸውን ሰጥተዋል" ብለዋል።

የኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አሁንም ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተለ መሆኑ ተገልጿል።

የዩክሬን የደኅንነት መረጃ እንደሚጠቁመው ከ36 የአፍሪካ አገራት ከ1,700 በላይ ሰዎች በሩሲያ ጦር ተመልምለዋል።

ዩክሬንም ከተለያዩ አገራት ተዋጊዎች እየመለመለች ትገኛለች። የዩክሬን መንግሥት ያለፈው ረቡዕ በኤክስ ገጹ ባወጣው መግለጫ "ኮብራ" በሚል መጠሪያ የሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) ባለሙያዎችን ከናይጄርያ ወስዷል።