ኤምሬትስ በጦርነቱ መያዟ በአፍሪካ ቀንድ ያላትን ተጽእኖ ይቀንሰዋል? ሁቲዎችስ ለቀጣናው ምን ያህል ስጋት ናቸው?

የፎቶው ባለመብት, Reuters
አሜሪካ እና እስራኤል በቴህራን ላይ የከፈቱት ጦርነት 35ኛ ቀኑን ይዟል። የዓለም አገራት በነዳጅ ዘይት እጥረት እየተፈተኑ ነው። እስካሁን ድረስ ድምጻቸውን አጥፍተው የነበሩት የሁቲ አማፂያንም ወደ እስራኤል ሚሳዔሎችን በማስወንጨፍ ውጊያውን ተቀላቅለዋል።
ምንም እንኳ እስካሁን ያስወነጨፉት ሁለት ሚሳዔል ብቻ ቢሆንም የአፍሪካ ቀንድ አገራትን ግን እንደ ሆርሙዝ ወሽመጥ ሁሉ ባብ ኤል መንደብ ይዘጋ ይሆን የሚል ስጋት ውስጥ ከትቷቸዋል።
በመካከለኛው ምሥራቅ ግጭት፣ አንሳር አላህ በመባል የሚታወቀው ሁቲዎች መሳተፋቸው ከየመን ድንበሮች ባሻገር በአፍሪካ ቀንድ ላይ ትልቅ አንድምታ አለው።
የዓለም 15 በመቶ የንግድ መርከቦች እንቅስቃሴ የሚተላለፍበት ቀይ ባሕር መግቢያ ላይ የተቀመጠው ታጣቂ ቡድኑ ከዚህ ቀደም በመርከቦች ላይ ያደረሰው ጥቃት እና ከቀጣናዊ ኃይሎች ጋር ያለው ትስስር በዓለም ላይ በጣም ወሳኝ በሆነው የንግድ መስመር ላይ ውጥረትን ጨምሯል።
ኢትዮጵያን፣ ሶማሊያን እና ኤርትራን ጨምሮ በአፍሪካ ቀንድ አገራት ላይ የሚኖረው ተጽእኖ ደግሞ ከፍተኛ ይሆናል።
ሁቲዎች በቀይ ባሕር ላይ የሚደረጉ የመርከብ እንቅስቃሴን የሚያውኩ ከሆነ የንግድ መስመሮችን ከማስተጓጎል ባሻገር፣ በቀጣናው የፀጥታ ስጋቶችን የሚያሳድግ ሲሆን፣ የኢኮኖሚ ቀውስን ያባብሳል ሲሉ የቀጣናው ተንታኞች ያስረዳሉ።
ሁቲዎች በዚህ ጦርነት ውስጥ በርትተው ቢቀጥሉ ለኢትዮጵያ እና ለሌሎች አፍሪካ ቀንድ አገራት የሚኖረው ስጋት ምንድን ነው? የኢትዮጵያ ወዳጅ የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ በዚህ ጦርነት መያዟ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል የተከሰተውን ውጥረት ወደ ጦርነት እንዳይቀየር አዘግይቶት ይሆን?
በኢትዮጵያ ፐብሊክ ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ የፖሊሲ ጥናት ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር ሙከረም ሚፍታህ የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት ከባሕረ ሰላጤው አገራት አልፎ የአፍሪካ ቀንድ አገራት ጉዳይ ከሆነ ከራርሟል ይላሉ።
የአፍሪካ ቀንድ ጉዳይ የሚሆንባቸው በርካታ መንገዶች አሉ የሚሉት ዶ/ር ሙከረም በአንድ በኩል በቀይ ባሕር ዳርቻ የሚገኘውን በየመን አብዛኛውን ክፍልን እያስተዳደሩ ያሉት የሁቲ አማጺያን መሆናቸውን ያነሳሉ።
በኢራን የሚደገፉት የሁቲ አማፂያን ቴህራን ከእስራኤል እና ከአሜሪካ ጋር በገባችው ጦርነት ውስጥ የግጭቱ ሁለተኛ ምዕራፍ አድርጋ እንዲሳተፉ እንዳስገባቻቸው መውሰድ ይቻላል ሲሉ ያብራራሉ።
የመካከለኛው ምሥራቅ ጉዳዮች ተንታኝ የሆኑት ኤርትራዊው ማህሙድ አቡበከር በበኩላቸው ሁቲዎች ባብ ኤል መንደብን የሚዘጉ ከሆነ የኤርትራ ምጣኔ ሀብት "ክፉኛ" እንደሚጎዳ ይናገራሉ።
15 ከመቶ የዓለም የንግድ መርከብ የሚንቀሳቀስበት ባብ ኤል መንደብ የሚዘጋ ከሆነ ምጣኔ ሀብቷን ከወደቦቿ በማግኘት የምትደጉመው ኤርትራ ፈተና እንደሚገጥማት ጨምረው ገልጸዋል።
የኤርትራ ምጣኔ ሀብት ጠንካራ ባይሆንም በዋናነት የተመሠረተው በወደቦች ላይ ነው ያሉት ተንተኙ፣ በተለይ ከሩሲያ እና ከቻይና ጋር የምታደርገው የንግድ ልውውጥ በአሰብ እና በምጽዋ ወደቦች ላይ የተመሠረተ መሆኑን ይናገራሉ።
ሁቲዎች ባብ ኤል መንደብን የሚዘጉ ከሆነ አሜሪካ ፊቷን ወደ ቀይ ባሕር ልታዞር ትችላለች የሚል እምነት በኤርትራ መንግሥት ዘንድ ስለሚኖር ስጋት መፈጠሩ እንደማይቀር ጨምረው አስረድተዋል።
የኤርትራ መንግሥት "በጣም በስጋት የሚኖር መንግሥት ከመሆኑ አንጻር" ማንኛውም ኃይል በዚህ በኩል መጥቶ ውጊያ መክፈት የለበትም የሚል አቋም እንደሚያራምድ ተናግረዋል።
ኢራን በባሕረ ሰላጤው አገራት የሚገኙ የአሜሪካ ጦር ኃይል ሠፈሮችን እንዲሁም የአገራቱን መሠረተ ልማቶች አጥቅታለች።
ከዚህም ባሻገር የዓለም 20 በመቶ ነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ የሚተላለፍበትን የሆርሙዝ ወሽመጥን በመዝጋት የነዳጅ ዋጋ መናር እንዲከሰት አድርጋለች።
ቴህራን በቀይ ባሕር ዙሪያ ያሏትን አጋሮች በመጠቀም በባብ ኤል መንደብ ላይ ጥቃት መሰንዘር የግጭቱ ሁለተኛ ምዕራፍ ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚችል የፖሊሲ ጥናት ተመራማሪ ዶ/ር ሙከረም ያስረዳሉ።
በርካታ የፖለቲካ ልሂቃኗ የተገደሉባት ኢራን የሚፈጸምባት ጥቃት እየበረታ ሲመጣ ጥቃቱን ወደ ተለያዩ የባሕረ ሰላጤው አገራት ለማስፋት አማራጭ ተጽእኖ ማሳደሪያ መንገዶችን ከመጠቀም አኳያ እስካሁን በዝምታ የቆዩትን የሁቲ አማጺያን ወደ ግጭቱ እንዲገቡ ማድረጓን ጨምረው ገልጸዋል።

የዓለም የነዳጅ ዘይት ቀውስ ኢኮኖሚያዊ ስጋት ውስጥ የጣላቸው የአፍሪካ ቀንድ አገራት በተለየ ጉዳዩን አሳሳቢ የሚያደርገው የሁቲ አማፂያን በዚህ ጦርነት ውስጥ በቀጥታ መሳተፋቸው ነው።
ዶ/ር ሙከረም የሁቲዎች በቀጥታ በዚህ ጦርነት ውስጥ መሳተፍ የአፍሪካ ቀንድ አገራትን የዓለም የኢነርጂ ቀውስ በቀጥታ እንዲሰማቸው ያደርጋል ብለዋል።
የቀንዱ አገራት በርካታ የኢኮኖሚ ዘርፎቻቸው የሚደገፉት በቀይ ባሕር በኩል በሚመጣ የነዳጅ ዘይት እና የምርቶች አቅርቦት መሆኑን በማስታወስ የዚህ መስመር መስተጓጎል ጫናው ከፍተኛ መሆኑን ነው ይለሉ።
በተለያዩ አጋጣሚዎች ኤርትራ ሁቲዎችን ትደግፋለች የሚል ክስ ይቀርብባት እንደነበር ያስታወሱት አቶ ማህሙድ በበኩላቸው የመካከለኛው ምሥራቅ ቀውስ ወደ ቀይ ባህር የሚሰፋ ከሆነ አሜሪካ እና አጋሮቿ በአካባቢው የሚገኙ ደሴቶችን በመጠቀም ጥቃቶችን ለመፈጸም ፍላጎት ማሳየታቸው እንደማይቀር ጠቅሰዋል።
ይህ ደግሞ የኤርትራን መንግሥት ስጋት ነው ያሉት ተንታኙ አሥመራ እነዚህን ደሴቶች ዋሽንግተን እና አጋሮቿ እንዲጠቀሙ የማትፈቅድ ከሆነ በፀጥታ ብቻ ሳይሆን በጂኦፖለቲክሲም በጣም ትጎዳለች ሲሉ አብራርተዋል።
ሁቲዎች በመካከለኛው ምሥራቅ ግጭት ላይ ቀጥተኛ ተሳታፊ መሆናቸው ሌላው ስጋት በሶማሊያ ከሚንቀሳቀሰው አል ሸባብ ጋር የአሜሪካን ተጽዕኖ ለመቋቋም ትብብር ለማድረግ ስምምነት ያላቸው መሆኑ አንዱ ጉዳይ እንደሆነ የፖሊሲ ጥናት ተመራማሪው ያስረዳሉ።
እነዚህ ሁለት አካላት በአፍሪካ ቀንድ ትብብር የሚያደርጉ ከሆነ የአሜሪካ እና የእስራኤል የቅርብ አጋር የሆኑትን የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ ፍላጎቶች ላይ ጥቃት ሊፈጽሙ ይችላሉ የሚል ስጋት እንዳለም ጠቅሰዋል።
በአፍሪካ ቀንድ ባሉ አገራት ዘንድ እንደ የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ ያሉ አገራት ጠንካራ የሆነ ተጽእኖ ስላላቸው በመካከለኛው ምሥራቅ ያለው ጦርነት የማይረግብ ከሆነ በኤምሬትስ ኢንቨስትመንቶች ላይ ሁቲዎች ወይንም አል ሸባብ ጥቃት ሊፈጽሙ ይችላሉ ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።
ዶ/ር ሙከረም የኢራን መንግሥት የአሜሪካ እና የእስራኤልን ጥቅም በባሕረ ሰላጤው ያራምዳሉ ያላቸውን አገራት እና መሠረተ ልማቶቻቸውን ሲደበድብ ሁሉም ላይ በእኩል አለማጥቃቱን ይናገራሉ።
ከኩዌት፣ ከኳታር፣ ከኦማን እና ከሳዑዲ አረቢያ ሁሉ በተለየ ኢራን ወደ የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ የሚሳዔል እና የድሮን ጥቃት በተደጋጋሚ መፈጸሟን አስታውሰዋል።
የኢራን አጋር የሆኑት ሁቲዎችም ወይንም አል ሸባቦች በአፍሪካ ቀንድ ያለን ማንኛውም የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ ዒላማ ማጥቃታቸው እንደማይቀር ጨምረው ይናገራሉ።

የፎቶው ባለመብት, Gallo Images via Getty
በኢትዮጵያ እና ኤርትራ ውጥረት ላይ የሚኖረው ውጤት
በመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ተፈጥሮ የነበረው ውጥረት ወደ ለየለት ጦርነት አለመሸጋገሩ በአፍሪካ ቀንድ ያሉ የፖለቲካ ኃይሎች መካከል የሚፈጠር ልዩነት መነሻ ላይ ጥያቄ እንዲያነሱ እንዳደረጋቸው አቶ ሙከረም ይናገራሉ።
"በመሠረታዊነት በአፍሪካ ቀንድ ያሉ ግጭቶች አፍሪካ ቀንድ ውስጥ ባሉ የፖለቲካ ኃይሎች መካከል ያለ የፖለቲካ ልዩነት የፈጠረው መሆን አለመሆኑን እንድንጠይቅ ዕድል የከፈተ ይመስለኛል።"
በአፍሪካ ቀንድ የሚገኙ አገራት በፖለቲካ ልሂቃኖቻቸው፣ በአመራሮቻቸው ወይም በአስተዳደሩ እና በአገረ መንግሥቱ መካከል የፍላጎት መጣረስ ኖሮ ወደ ግጭት እንደማይገቡ "በከፊልም ቢሆን ፍንጭ የሚሰጥ ነው" ይላሉ።
የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ በአፍሪካ ቀንድ ላይ ጠንካራ ፍላጎት ያላት በመሆኑ የምትደግፋቸው ኃይሎች በአሁኑ ወቅት በሱዳን እንዲሁም ከዚህ በፊት በሊቢያ የመንግሥት እና የሥርዓት ለውጥ ለማምጣት ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸውን ጠቅሰዋል።
ስለዚህ በኢትዮጵያም ሆነ በአፍሪካ ቀንድ በሚኖሩ ግጭቶች የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ ተሳትፎ "የእነርሱን ብሔራዊ ደኅንነት ፍላጎት ከማሳካት ባሻገር" የእነዚያ አፍሪካ አገራት ውስጣዊ አለመግባባት፣ የልሂቃን ተግባቦት መጥፋት፣ ለአገር ከማሰብ የመነጨ ልዩነት አለመሆኑን በከፊል የሚያሳይ ይመስለኛል ሲሉ ተናግረዋል።
አቶ ሞሐሙድ በበኩላቸው በመካከለኛው ምሥራቅ የተቀሰቀሰው ጦርነት በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል የነበረውን የጦርነት ስጋት አስቀርቶታል ብለው አንደሚያምኑ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ለዚህም ምክንያታቸውን ሲያስረዱ በኤርትራ እና በኢትዮጵያ መካከል መካረር የተፈጠረው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ "የባሕር በር የኅልውና ጉዳይ ነው" ካሉ በኋላ መሆኑን አስታውሰዋል።
ኢትዮጵያ የባሕር በር ጉዳይን ከጂቡቲ፣ ከሶማሌላንድ ጋር እንዳላት ስምምነት ከኤርትራም ጋር ሊኖራት የሚችል ቢሆንም ኤምሬትስ እጇን በማስገባቷ ይህ ሁኔታ ተቀይሯል ብለው ሞሐመድ ያምናሉ።
አክለውም ዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ ከጂቡቲ እና በርበራ ወደቦች እንድትወጣ ከተደረገ በኋላ ይህንን "የኢትዮጵያን የባሕር በር ባለቤት የማድረግ ፕሮጀክት የያዘችው ይመስለኛል" የሚሉት አቶ ሞሐመድ፤ ነገር ግን በባሕረ ሰላጤው ጦርነት ምክንያት በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ ቀንድ ሊደረግ የሚችል ጦርነትን ለመደገፍ የምትችለበት ሁኔታ ላይ አለመሆኗን ይናገራሉ።
በዚህም ምክንያት በመካከለኛው ምሥራቅ የተቀሰቀሰው ቀውስ የፈጠረው አጠቃላይ የዓለም ሁኔታ እንዲሁም የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የኢራን ዋነኛ ዒላማ ከመሆኗ አንጻር በሙሉ አቅም እና ፍላጎት በአፍሪካ ቀንድ ጉዳይ ውስጥ ለመሳተፍ የምትችልበት አቋም ላይ አይደለችም።
ስለዚህም ለወራት እየተጋጋለ ቆይቶ ከዛሬ ነገ ጦርነት ይቀሰቀሳል ሲባልለት የነበረው የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ውጥረት ፈንድቶ በአሁኑ ወቅት ጦርነት እንዳይፈጠር ምክንያት እንደሆነ ያምናሉ።















