ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአርቲመስ ጠፈርተኞች ከምድር ጋር ግንኙነታቸው ተቋርጦ የሚቆይባቸው 40 ደቂቃዎች
ከአርቲመስ ጠፈርተኞች በላይ ከምድር የሚርቅ ያለ አይመስልም።
መሬት መንኮራኩራቸው ውስጥ ባለው የኋለኛ መስታወት ስትታይ እያነሰች እየሄደችም ቢሆን ሂውስተን ቴክሳስ ከሚገኘው የቁጥጥር ማዕከል ጋር የማያቋርጥ ግንኙነት ነበራቸው።
ከናሳ ባለሙያዎች የሚሰማው የተረጋጋ ድምፅ ለጠፈር ቡድኑ ከቤታቸው ከምድር ጋር የሚያፅናና ግንኙነትን ፈጥሯል።
ይህ ግንኙነት አሁን ሊቋረጥ ነው።
ጠፈርተኞቹ ሰኞ ሌሊት ላይ በጨረቃ ጀርባ በኩል ለማለፍ ሲቃረቡ በመንኮራኩሩ እና በመሬት መካከል ግንኙነት እንዲኖር የሚያስችለው የራዲዮ እና የጨረር ግንኙነት በራሷ በጨረቃ ይጋረዳል።
ለ40 ደቂቃ ያህል አራቱ ጠፈርተኞች ብቻቸውን ይሆናሉ፤ በጨለማው ሕዋ ጉዟቸውን ሲቀጥሉ በራሳቸው ሀሳብ እና ስሜት ውስጥ ብቻ ይሆናሉ። ይህም ጥልቅ የዝምታ እና የብቸኝነት ጊዜ ሆኖ ይመዘገባል።
የአርቲመስ አብራሪ ቪክተር ግሎቨር ይህን ጊዜ ዓለም ለመቀራረብ ይጠቀምበታል የሚል ተስፋ እንዳለው ተናግሯል።
"ከጨረቃ ጀርባ ስንሆን፤ ከሁሉም ሰው ጋር ግንኙነት ስናቋርጥ ይህን እንደ ዕድል እንውሰደው" በማለት የጠፈር ጉዟቸውን ከማድረጋቸው አስቀድሞ ለቢቢሲ ተናግሯል።
"እንፀልይ፤ ተስፋ እንሰንቅ፤ ከባልደረቦቻችን ጋር ዳግም ግንኙነት እንድንቀጥል መልካም ሀሳባችሁን እና ስሜታችሁን ላኩልን" በማለትም አክሏል።
ከ50 ዓመታት በፊትም የአፖሎ ጠፈርተኞችም ወደ ጨረቃ በነበራቸው ተልዕኮ በተፈጠረ የግንኙነት መቋረጥ ተመሳሳይ ብቸኝነት ገጥሟቸው ነበር።
ምን አልባትም ከአፖሎ 11ዱ ጠፈርተኛ ማይክል ኮለንስ በላይ ብቸንነቱ የተሰማው አይኖርም።
እ.አ.አ በ1969 ኒል አርምስትሮንግ እና በዝ አልድሪን በጨረቃ ወለል ላይ በመራመድ ታሪክ ሲሰሩ ኮለንስ ብቻውን ጨረቃን እየዞረ ነበር።
መንኮራኩሩ ራቅ ባለው ጎን ሲያልፍ ጨረቃ ላይ ከነበሩት ባልደረቦቹ እና ከተልዕኮው ተቆጣጣሪዎች ጋር ግንኙነቱ ተቋርጦ የነበረ ሲሆን፤ ጠፈርተኛው ለ48 ደቂቃ ጠፍቶ ነበር።
እ.አ.አ በ1947 ባሳተመው ግለ ታሪኩ በዚያ ወቅት "እውነተኛ ብቸኝነት"እና "ከሚታወቅ ሕይወት መነጠል" እንደተሰማው ገልጿል። ሆኖም ፍርሃትም እንዳልተሰማው ጽፏል።
ከተልዕኮው በኋላ በሰጣቸው ቃለ ምልልሶች ራዲዮው ዝም ሲል ምን ያህል ሰላም እና ፀጥታ እንደተሰማው እንዲሁም ከማዕከላዊ ቁጥጥሩ አፍታ እና እረፍት ማግኘቱን ገልጿል።
ከመሬት ጋር የሚደረግ ግንኙነት ፀጥ ረጭ የሚልበት ጊዜ ከመንኮራኩሩ ጋር የሚደረገውን ግንኙነትን መመለስ ሥራቸው ለሆነ ባለሙያዎች የጭንቀት ጊዜ ነው።
በደቡብ ምዕራብ እንግሊዝ በሚገኘው የጉንሂሊ የመሬት ጣቢያ በመንኮራኩሯ ጉዞ ሁሉ በግዙፉ አንቴና ምልክቶችን በመሰብሰብ ወደ ናሳ ዋና መስሪያ ቤት መረጃውን ይልካል።
የጣቢያው የቴክኖሎጂ ኃላፊ የሆነው ማት ካስቢ "ሰው ያለበትን መንኮራኩር ስንከታተል ይህ የመጀመሪያው ነው" ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።
"በጨረቃ ጀርባ መንኮራኩሩ ሲጓዝ የተወሰነ ፍርሃት ይሰማናል እናም ዳግም ስናየው ደግሞ በጣም ደስ እንሰኛለን። ምክንያቱም ደህና እንደሆኑ እናውቃለን።"
እንደዚህ አይነቱ የግንኙነት መስተጓጉል በቅርቡ ታሪክ እንደሚሆን ተስፋ አለ። ናሳ እና ሌሎችም የሕዋ ተቋማት በጨረቃ ቤዝ ሲከፍቱ እና ፍለጋው ከዚህ በበለጠ ሲጠናከር አስፈላጊ ነው ይላል።
"በጨረቃ ዘላቂነት ላለው ቆይታ ሙሉ ለሙሉ ግንኙነት ያስፈልጋል። በሩቁ ጫፍም ቢሆን በቀን ለ24 ሰዓታት ያስፈልጋል። ምክንያቱም ሩቁ ጫፍንም ማየት ስለምንፈልግ" ሲል አክሏል።
በአውሮፓ የሕዋ ኤጀንሲ ስር ያሉ መርሃ ግብሮች ወደፊት ቀጣይነት ያለው እና አስተማማን ግንኙነት ለመፍጠር ተከታታይ መንኮራኩሮችን በጨረቃ ዙሪያ ለመላክ እቅድ ይዘዋል።
ለአርቲመስ ጠፈርተኞች ከመሬት ጋር ካለ ግንኙነት የሚያሳልፉት ጊዜ ሙሉ ትኩረታቸውን ጨረቃ ላይ እንዲያሳርፉ ይፈቅድላቸዋል።
40ውን ደቂቃ ምስሎችን በመውሰድ፣ የጨረቃን ስነምድር በማጥናት እና የጨረቃን ግርማ ሞገስ በማየት ያሳልፋሉ።
ታሪክ ሰሪ የሆኑት ጠፈርተኞች ልዩ የሆነውን ምልከታቸውን ለሁሉም ወደ ምድር በመላክ ያጋራሉ።