ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሩሲያ እና ዩክሬን ለትንሳኤ በዓል ተኩስ ለማቆም ተስማሙ
ሩሲያ እና ዩክሬን በኦርቶዶክስ የትንሳኤ በዓል ቀናት የተኩስ አቁም ለማድረግ ተስማሙ። ቭላድሚር ፑቲን የሩሲያ ወታደሮችን በሳምንቱ መገባደጃ ቀናት "በሁሉም አቅጣጫ" ተኩስ እንዲያቆሙ ትዕዛዝ መስጠታቸውን ተናግረዋል።
ሩሲያ የተኩስ አቁም ያወጀችው፤ የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ በተደጋጋሚ ያቀረቡትን ተመሳሳይ ጥሪ ችላ ብላ ከቆየች በኋላ ነው።
ፕሬዝዳንት ፑቲን ከቅዳሜ ጀምሮ እስከ እሁድ የትንሳኤ ምሽት የሚዘልቀውን የተኩስ አቁም ውሳኔ ዩክሬንም "የሩሲያን ተምሳሌት" በመከተል ትተገብራለች ብለው እንደሚጠብቁ ገልፀዋል።
ፕሬዝዳንቱ ወታደሮች "ጠላት ሊያስነሳቸው ለሚችሉ ጥቃቶች" እና "የጥቃት እርምጃ" ለመቀልበስ እንዲዘጋጁም ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።
የሩሲያ ውሳኔ እና እርምጃውን በቀዳሚነት መውሰዱ ዩክሬንን ሊያበሳጭ የሚችል ቢሆንም ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ በኤክስ ገፃቸው "ተመሳሳይ እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ ነን" ብለዋል።
"ሰዎች ትንሳኤን ከስጋት ነፃ ሆነው እና በእውነተኛ የሰላም እንቅስቃሴ ማሳለፍ አለባቸው" ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ "ሩሲያ ከፋሲካ በኋላም ያለማጥቃት ዕድል አላት" ብለዋል።
በሳምንቱ መጀመሪያ ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ እንደ መጀመሪያ እርምጃ የበዓል የተኩስ አቁም ስምምነት በአሜሪካ በኩል ለሞስኮ እንዲቀርብ መልዕክት መላካቸውን ተናግረው ነበር።
ያለእረፍት የድሮን ጥቃቶች በሚፈፀምበት በረጅሙ የምስራቅ ዩክሬን ግንባር ለተሰማሩ ወታደሮች፤ ከውጊያ የሚያሳርፋቸውን ማንኛውም እፎይታን ማግኘት በአዎንታ የሚቀበሉት ጉዳይ ነው።
በሩሲያ ድሮኖች እና ሚሳዔሎች ንፁኃን ሰዎች በሚገደሉበት እና የአየር ጥቃት ማስጠንቀቂያ ደውሎች የዕለት ከዕለት ሕይወት አካል በሆኑበት በመላው የአገሪቱ ክፍልም እንዲሁ ሰዎች ዘና እንዲሉ የሚያደርግ ነው።
በቅርቡ በደቡብ ምሥራቅ ዩክሬን አውቶብስ ላይ በተፈፀመ ጥቃት በርካታ ሰዎች ተገድለዋል። በምዕራብ ኪዬቭ ደግሞ አንዲት ሴት ቤቷ ላይ በወደቀ ሚሳኤል ተገድላለች።
የፋሲካ በዓል የተኩስ አቁም ስምምነት ከታወጀ ከአጭር ጊዜ በኋላ የማስጠንቀቂያ ደወሉ በኪዬቭ ተሰምቷል።
ዩክሬንም ሩሲያ ላይ የምትፈፅመውን የድሮን ጥቃት ያጠናከረች ሲሆን የኃይል አቅርቦቶችን ዒላማ በማድረግ ተከታታይ ጥቃቶችን ፈፅማለች። የሩሲያ የመኖሪያ መደሮችም ተመትተዋል።
ባለፈው ግንቦት ሩሲያ የሶቪየት ሕብረት ናዚ ጀርመኒን ያሸነፈበትን 80ኛ ዓመት በዓል ለማክበር የተናጠል ተኩስ አቁም አድርጋለች። በዚህ ጊዜ ዩክሬን በተኩስ አቁሙ በመቶዎች የሚቆጠሩ ጥሰቶች መፈፀማቸውን ገልጻለች።
ኪዬቭ የሩሲያን ወረረራ ለመቀልበስ እና ድርድር ለማድረግ የሚያችል የተረጋጋ የተኩስ አቁም ስምምነት ትፈልጋለች።
ሆኖም ሞስኮ በመጀመሪያ የሰላም ስምምነት መፈፀም እንደሚያስፈልግ ትወተውታለች። ይህም ኪዬቭ ሩሲያ ጦርነቱን ማቆም አትፈልግም የሚል ክስ እንድታቀርብ አድርጓታል።
በአገራቱ መካከል በአሜሪካ አደራዳሪነት በርካታ ዙር ድርድሮች የተደረጉ ሲሆን፤ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ ግን ትኩረቱ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ዞሯል።