አውሮፓ ያላት የአውሮፕላን ነዳጅ ክምችት ከአንድ ወር ያነሰ መሆኑ ተዘገበ
የአውሮፓ አገራት የአውሮፕላን ነዳጅ ክምችት ከአንድ ወር ላነሰ ጊዜ ብቻ የሚበቃ መሆኑን ሮይተርስ ዘገበ።
አውሮፓ ለአውሮፕላን የምትጠቀምበትን ነዳጅ እያስገባች ያለችው ከአሜሪካ እና እስያ ሲሆን ይህም ያላት ክምችት እንዲሳሳ ማድረጉን ዘገባው ጠቅሷል።
በመካከለኛ ምሥራቅ ዳግም ያገረሸው ግጭት አውሮፓ የአውሮፕላን ነዳጅ የአቅርቦት ሰንሰለት ላይ ዳግመኛ ስጋት መፍጠሩ ተገልጿል።
በተለይ ብሪታኒያ፣ ፈረንሳይ እና ጀርመን የሆርሙዝ ወሽመጥ በመዘጋቱ እና የነዳጅ አቅርቦት ሰንሰለቱ በመስተጓጎሉ የበለጠ ተጎጂ የሆኑ አገራት ናቸው።
የዓለም አንድ አምስተኛ ነዳጅ የሚተላለፍበት የሆርሙዝ ወሽመት፤ በየካቲት ወር መጨረሻ ላይ በመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት በመቀስቀሱ ተዘግቶ ቆይቷል።
ወሽመጡ በሰኔ ወር ላይ በከፊል ተከፍቶ የነበረ ቢሆንም አሁን ዳግም ያገረሸው ግጭት የመርከቦች እንቅስቃሴን ገድቧል።
በሐምሌ ወር ላይ የተደረሰው የተኩስ አቁም አሜሪከ እና ኢራን ዳግም መታኮስ በመጀመራቸው የመርከቦች እንቅስቃሴን ገድቧል።
የአውሮፓ ኮሚሽን በአውሮፓ ያለው ነዳጅ መመናመኑን ገልጾ ሁኔታው በነሐሴ ወር የበለጠ ሊባባስ ይችላል ሲል አስጠንቅቋል።
በየካቲት መጨረሻ በኢራን እና በአሜሪካ መካከል ጦርነት እስኪጀመር ድረስ የአውሮፓ አገራት ግማሽ የሚሆነውን የአውሮፕላን ነዳጅ ያገኙ የነበረው ከመካከለኛ ምሥራቅ አገራት ነበር።
ተንታኞች የአፍሪካ አገራት መጋቢት ላይ የአውሮፕላን ነዳጅ እጥረት እንደሚያጋጥማቸው ተንብየው ነበር።
ቢሆንም ከናይጄሪያ የዳንጎቴ ነዳጅ ማጣሪያ እዲሁም ሕንድ እና ኦማን ማስገባት በመጀመራቸው እጥረቱ ተቃልሏል።
በአሁኑ ወቅት የአውሮፓ አገራት ከካናዳ ነዳጅ መግዛት መጀመራቸው ተሰምቷል።
አሜሪካ እና ናይጄሪያ ወደ አውሮፓ ነዳጅ የሚልኩ ዋነኞቹ አገራት ናቸው። ነገር ግን ኩዌት፣ ካናዳ፣ ሕንድ እና ደቡብ ኮሪያ የአውሮፕላን ነዳጅ ያቀርባሉ።