ቀጥታ, ትራምፕ የሆርሙዝ ወሽመጥን “እንቆጣጠረዋለን” በማለት ዛቱ

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን ስምምነቱን “መጣሷን” ጠቅሰው አገራቸው የሆርሙዝ ወሽመጥን “እንደምትቆጣጠር” ገለጹ። ከፎክስ ኒውስ ጋር ባደረጉት ቆይታ “የሆርሙዝ ወሽመጥን እንቆጣጠረዋለን። ምንም ነገር የላቸውም” ብለዋል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. ትራምፕ በኢራን ወደቦች ላይ በድጋሚ እገዳ ጣሉ

    አሜሪካ በድጋሚ በኢራን ወደቦች ላይ እገዳ እንደምትጥል ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስታወቁ።

    በትሩዝ ሶሻል ማኅበራዊ ገጻቸው “የሆርሙዝ ወሽመጥ ክፍት ነው፤ ኢራን አለችም አላለችም ተከፍቶ ይቆያል። ኢራን ላይ በድጋሚ እገዳ ይጣላል” ብለዋል።

    እገዳው የኢራን መርከቦች “እንዳይገቡ እና እንዳይወጡ” እንደሚያደርግ እና ለሌሎች አገራት ግን የሆርሙዝ ወሽመጥ “ፍትሐዊ እና ክፍት” ሆኖ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

    “ከዚህ በኋላ አሜሪካ የሆርሙዝ ወሽመጥ ጠባቂ ናት” ያሉት ትራምፕ፤ ሁሉም የንግድ መርከቦች 20% ክፍያ እንዲፈጽሙ እንደሚጠየቁ አስታውቀዋል።

    ደኅንነቱ በተጠበቀ መንገድ በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል መተላለፍ እንዲቻል የሚያስፈልገውን ወጪ ለመሸፈን እንደሚውል አክለዋል።

    ትራምፕ ከዚህ ቀደምም በኢራን ወደቦች ላይ እገዳ ጥለው እንደነበር ይታወሳል።

    ኢራን ከነዳጅ ንግድ የምታገኘውን ገቢ ለመገደብ በሚል የወደብ እንቅስቃሴዎች ላይ እገዳ ተጥሎ ቆይቷል።

    የተባበሩት መንግሥታት የማሪታይም ተቋም እንደሚለው የትኛውም አገር ዓለም አቀፍ መተላለፊያን የመቆጣጠር ሕጋዊ መብት የለውም።

    ኢራን እና አሜሪካ የመግባቢያ ሰነድ ሲፈራረሙ እገዳው ተነስቶ ነበር።

    አሁን ትራምፕ በድጋሚ እገዳውን ጥለው 20% ክፍያ እንደሚኖርም ተናግረዋል።

  2. “አሜሪካ በሆርሙዝ ወሽመጥ አስተዳደር ጣልቃ እንድትገባ አንፈቅድም”- ኢራን

    የኢራን ከፍተኛ ወታደራዊ ዕዝ፤ አሜሪካ በሆርሙዝ ወሽመጥ አስተዳደር “ጣልቃ እንድትገባ እንደማይፈቅድ” አስታወቀ።

    የኢራን ጦር “የአሜሪካ ተደጋጋሚ የጀብደኝነት እንቅስቃሴ የቀጣናውን ደኅንነት ክፉኛ አውኳል” ማለቱን ታስኒም የዜና ወኪል ዘግቧል።

    አሜሪካ የሆርሙዝ ወሽመጥን እንድትቆጣጠር “አልፈቀድንም፤ አንፈቅድምም” ሲልም የኢራን ጦር አክሏል።

    ከአሜሪካ “ሽፍታ ጦር” የተቃጡ ረብሻዎችን እንደሚቆጣጠር አስታውቋል።

    ከአሜሪካ ጋር የሚደረግ ትብብር የኢራንን ሉዓላዊነት የሚጥስ “የጦርነት ድርጊት” ተደርጎ እንደሚወሰድም አስጠንቅቋል።

    “ጦርነቱ ከተባባሰ ቀጣናውን ያዳርሳል” ማለቱም ተዘግቧል።

  3. ትራምፕ የሆርሙዝ ወሽመጥን “እንቆጣጠረዋለን” በማለት ዛቱ

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን ስምምነቱን “መጣሷን” ጠቅሰው አገራቸው የሆርሙዝ ወሽመጥን “እንደምትቆጣጠር” ገለጹ።

    ከፎክስ ኒውስ ጋር ባደረጉት ቆይታ “የሆርሙዝ ወሽመጥን እንቆጣጠረዋለን። ምንም ነገር የላቸውም” ብለዋል።

    ትናንት ምሽት አሜሪካ ኢራንን “ክፉኛ መደብደቧን” ተናግረዋል።

    “ይዘናቸዋል፤ እያሳደድናቸው ነው። አብዛኞቹ መሣሪያዎቻቸው ወድመዋል” ሲሉም አክለዋል።

    በዩናይትድ ኪንግደም የኢራን ኤምባሲ ባወጣው መግለጫ፤ በሆርሙዝ ወሽመጥ ደኅንነቱ የተጠበቀ ጊዜያዊ መተላለፊያ እንዳዘጋጀ አስታውቋል።

    መተላለፊያው “ከቴክኒክ እና ወታደራዊ ክልከላ” ነጻ እንደሆነ ገልጿል።

    አሜሪካ ግን የሆርሙዝ ወሽመጥ “ለከፍተኛ አደጋ የተጋለጠ መተላለፊያ ነው” ብላለች።

    ከአሜሪካ ጋር የተደረሰውን ስምምነት በተመለከተ ኢራናውያን ትናንት “11 ሰዓት የወሰደ ውይይት” ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

    “የተወሰኑ ለውጦች ማድረግ አለብን” ብለው ከውይይቱ ክፍል እንደወጡ ጠቅሰውም “ሁሌም ለውጥ ያደርጋሉ፤ የሠለጠኑ ተደራዳሪዎች ናቸው፤ ጎበዝ ግን አይደሉም። ለእኔ ምንም ይዘው አልመጡም” ሲሉም አክለዋል።

  4. ዩኬ ለኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ድጋፍ መስጠትን አገደች

    የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ለዩናይትድ ኪንግደም ብሔራዊ ደኅንነት አስጊ ተብሎ እንደሚፈረጅ የአገር ውስጥ ጉዳይ ጸሐፊዋ ሻባና ማሕሙድ ተናገሩ።

    ለዩኬ ምክር ቤት በጽሑፍ ባቀረቡት መግለጫ መሠረት ስለ እስላማዊ አብዮታዊ ዘቡ አወንታዊ አስተያየት ከመስጠት አንስቶ ድጋፍ እስከማድረግ ድረስ ያሉ ድርጊቶች እስከ 14 ዓመት እስራት የሚያስቀጡ ይሆናሉ።

    የኢራን ደጋፊ የሆነው ወታደራዊ ቡድን ‘ኢስላሚክ ሙቭመንት ኦፍ ኮምፓኒየንስ ኦፍ ዘ ራይት’ እንዲሁም የሩሲያ ወታደራዊ ስለላ ተቋም ክንፍ የሆነው ‘ዘ ቮሉንተር ኮርፕስ ኦፍ ራሽያስ ጂአርዩ’ ላይም እገዳ ተጥሏል።

    ለፖሊስ እና የደኅንነት ተቋማት በሚሰጣቸው አዲስ ሥልጣን አማካኝነት የውጭ ጣልቃ ገብነት፣ በእነዚህ ቡድኖች የሚፈጸም ጥቃት እንዲሁም ስለላን መከላከል እንደሚቻል ተገልጿል።

    የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ በዩናይትድ ኪንግደም የአይሁድ እና እስራኤላዊ ማኅበረሰቦች ላይ ያነጣጠሩ ሰባት ጥቃቶች እንዲፈጸሙ ትዕዛዝ ማስተላለፉ ይታመናል።

  5. በሆርሙዝ ወሽመጥ የሚያልፉ መርከቦች ቁጥር መቀነሱ ተገለጸ

    በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል የሚያልፉ መርከቦች ቁጥር በከፍተኛ መጠን ማሽቆልቆሉ ተገለጸ።

    የመርከቦችን እንቅስቃሴ የሚከታተለው ድረ ገጽ 'ማሪን ትራፊክ' እንደሚጠቁመው ከትናንት እሑድ ምሽት ጀምሮ አንዳችም የንግድ መርከብ በወሽመጡ አላለፈም።

    ቅዳሜ ለእሑድ አጥቢያ ስምንት መርከቦች አልፈዋል።

    ኢራን የንግድ መርከቦች ላይ ጥቃት መፈጸሟን ተከትሎ አሜሪካ “በርካታ” የቴህራን ወታደራዊ ዒላማዎችን እንደመታች አስታውቃለች።

    በተለያዩ የኢራን አካባቢዎች ፍንዳታዎች መሰማታቸውን የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

    የአሜሪካ ጦር የቴህራንን የአየር መቃወሚያ፣ የባሕር መቆጣጠሪያ፣ ሚሳዔሎች እንዲሁም አነስተኛ ጀልባዎችን መምታቱን ገልጿል።

    ኢራን በወሰደችው የአጸፋ እርምጃ በዮርዳኖች፣ ባህሬን፣ ኩዌት እና ኦማን ላይ ጥቃት አድርሳለች።

    በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል መርከቦች መተላለፍ ማቆማቸው በአውሮፓ የአውሮፕላን ነዳጅ እጥረት እንደሚያስከትል ተዘግቧል።

    የአውሮፓ ኅብረት የኢነርጂ ግብረ ኃይል ዛሬ ያደረገውን ውይይት ተከትሎ ባወጣው መግለጫ አሁን ላይ ያለው ክምችት “የተረጋጋ” መሆኑን ጠቅሷል።

    ሆኖም ግን የሆርሙዝ ወሽመጥ በመዘጋቱ እና የነዳጅ አቅርቦት ሰንሰለት በመስተጓጎሉ የአውሮፓ አገራት ለነዳጅ እጥረት እንደሚጋለጡ ተመልክቷል።

  6. አውሮፓ ያላት የአውሮፕላን ነዳጅ ክምችት ከአንድ ወር ያነሰ መሆኑ ተዘገበ

    የአውሮፓ አገራት የአውሮፕላን ነዳጅ ክምችት ከአንድ ወር ላነሰ ጊዜ ብቻ የሚበቃ መሆኑን ሮይተርስ ዘገበ።

    አውሮፓ ለአውሮፕላን የምትጠቀምበትን ነዳጅ እያስገባች ያለችው ከአሜሪካ እና እስያ ሲሆን ይህም ያላት ክምችት እንዲሳሳ ማድረጉን ዘገባው ጠቅሷል።

    በመካከለኛ ምሥራቅ ዳግም ያገረሸው ግጭት አውሮፓ የአውሮፕላን ነዳጅ የአቅርቦት ሰንሰለት ላይ ዳግመኛ ስጋት መፍጠሩ ተገልጿል።

    በተለይ ብሪታኒያ፣ ፈረንሳይ እና ጀርመን የሆርሙዝ ወሽመጥ በመዘጋቱ እና የነዳጅ አቅርቦት ሰንሰለቱ በመስተጓጎሉ የበለጠ ተጎጂ የሆኑ አገራት ናቸው።

    የዓለም አንድ አምስተኛ ነዳጅ የሚተላለፍበት የሆርሙዝ ወሽመት፤ በየካቲት ወር መጨረሻ ላይ በመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት በመቀስቀሱ ተዘግቶ ቆይቷል።

    ወሽመጡ በሰኔ ወር ላይ በከፊል ተከፍቶ የነበረ ቢሆንም አሁን ዳግም ያገረሸው ግጭት የመርከቦች እንቅስቃሴን ገድቧል።

    በሐምሌ ወር ላይ የተደረሰው የተኩስ አቁም አሜሪከ እና ኢራን ዳግም መታኮስ በመጀመራቸው የመርከቦች እንቅስቃሴን ገድቧል።

    የአውሮፓ ኮሚሽን በአውሮፓ ያለው ነዳጅ መመናመኑን ገልጾ ሁኔታው በነሐሴ ወር የበለጠ ሊባባስ ይችላል ሲል አስጠንቅቋል።

    በየካቲት መጨረሻ በኢራን እና በአሜሪካ መካከል ጦርነት እስኪጀመር ድረስ የአውሮፓ አገራት ግማሽ የሚሆነውን የአውሮፕላን ነዳጅ ያገኙ የነበረው ከመካከለኛ ምሥራቅ አገራት ነበር።

    ተንታኞች የአፍሪካ አገራት መጋቢት ላይ የአውሮፕላን ነዳጅ እጥረት እንደሚያጋጥማቸው ተንብየው ነበር።

    ቢሆንም ከናይጄሪያ የዳንጎቴ ነዳጅ ማጣሪያ እዲሁም ሕንድ እና ኦማን ማስገባት በመጀመራቸው እጥረቱ ተቃልሏል።

    በአሁኑ ወቅት የአውሮፓ አገራት ከካናዳ ነዳጅ መግዛት መጀመራቸው ተሰምቷል።

    አሜሪካ እና ናይጄሪያ ወደ አውሮፓ ነዳጅ የሚልኩ ዋነኞቹ አገራት ናቸው። ነገር ግን ኩዌት፣ ካናዳ፣ ሕንድ እና ደቡብ ኮሪያ የአውሮፕላን ነዳጅ ያቀርባሉ።

  7. ኢራን “በአሜሪካ ጫና” ምክንያት ሆርሙዝን በተመለከተ ከኦማን ጋር ስምምነት ላይ አለመድረሷን ገለጸች

    ኢራን እና ኦማን በሆርሙዝ ወሽመጥ የሚደረግ የመርከቦች ጉዞን በተመለከተ ያደረጉት ንግግር ያደረጉት “በአሜሪካ ጫና” ምክንያት ስምምነት ላይ መድረስ እንዳልቻሉ ቴህራን አስታወቀች።

    በኢራን እና አሜሪካ ጦርነት እንዲሁም ድርድር የክርክር ማዕከል የሆነው የሆርሙዝ ወሽመጥ ከዓለም ነዳጅ እና ጋዝ ምርት ውስጥ 20 በመቶ ገደማው ይተላለፍበት የነበረ የወሳኝ የባሕር መስመር ነው። ከጦርነቱ ወዲህ በወሽመጡ ላይ ያላትን ቁጥጥር ያጠናከረችው ኢራን፤ በሆርሙዝ ሌላኛው ጫፍ ከአሁን በኋላ ከምትገኘው ኦማን ጋር በመነጋገር እንደምታስተዳድረው ስትናገር ቆይታለች።

    የኢራን እና ኦማን ባለሥልጣናት ትናንት ቅዳሜ ዕለት የባሕር መስመሩን ትራፊክ አስተዳደር በተመለከተ መወያየታቸው ተገልጾ ነበር።

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ኢስማኢል ባቃኢ ዛሬ ሰኞ ውይይቱን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ፤ በኦማን ዋና ከተማ በተካሄደው ውይይት ስምምነት ላይ አለመደረሱን አስታውቀዋል። ቃል አቀባዩ፤ “ቅዳሜ ዕለት ሙስካት ውስጥ የተደረገው ንግግር [ከአሜሪካ ጋር በተፈረመው] የመግባቢያ ስምምነት አንቀጽ 5 ላይ በሚገኘው የሆርሙዝ ወሽመጥ ጉዳይ ላይ ብቻ ያተኮረ ነበር” ብለዋል።

    አክለውም፤ “አሜሪካ ግልጽ እና ድብቅ በኦማን ላይ ባሳደረችው ጫና ምክንያት መከናወን የነበረበት ነገር ባለመሳካቱ እና ባለመፈጸሙ እናዝናለን" ሲሉ ዋሽንግተንን ተጠያቂ አድርገዋል።

    ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ ኢራን ሆርሙዝ በድጋሚ መዘጋቱን ካስታወቀች በኋላ ከትናንት ምሽት አንስቶ እስካሁን ምንም መርከብ በወሽመጡ እንዳላለፈ ‘ማሪን ትራፊክ’ ከተሰኘው የመርከቦች ጉዞ መከታተያ ድረ ገጽ የተገኘው መረጃ አሳይቷል።

    ኢራን የአሜሪካ ጦር በሚያደርገው “ሕገ ወጥ እንቅስቃሴ” ምክንያት በአሁኑ ሰዓት በሆርሙዝ በኩል ጉዞ ማድረግ “የማይቻል” መሆኑን በትናንትናው ዕለት ገልጻ ነበር።

    አሜሪካ በበኩሏ ወሳኙ የባሕር መተላለፊያ ክፍት ነው በሚል አቋሟ ጸንታለች። የአሜሪካ ማዕከላዊ እዛ በወጣው መግለጫ ሆርሙዝ ክፍት እንደሆነ እንዲሁም ጦሩ የመርከብ ጉዞ ነጻነትን ለማስጠበቅ ዝግጁ መሆኑን ገልጿል።

  8. የአሜሪካ ጦር ኢራንን መደብደቡን ሲቀጥል፤ ቴህራን የባሕረ ሰላጤው አገራትን ላይ የምታደርሰውን ጥቃት አስፋፋች

    አሜሪካ እሁድ ሌሊት ኢራን ውስጥ በፈጸመችው ድብደባ በሆርሙዝ ወሽመጥ የሚያልፉ መርከቦችን ለማጥቃት ጥቅም ላይ ይውላል ያለችውን የሚሳዔል ክምችት መምታቷን አስታወቀች።

    ለዚህ እርምጃ ምላሽ የሰጠው የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ በበኩሉ ባህሬን፣ ኩዌት እና ዮርዳኖስ ውስጥ የሚገኙ የአሜሪካ የጦር ሰፈሮች ላይ በፈጸማቸው የአጸፋ ጥቃቶችን በርካታ ዒላማዎችን ማውደሙን ገልጿል።

    ካለፈው ሳምንት ወዲህ በድጋሚ ያገረሸው የአሜሪካ እና ኢራን ግጭት፤ ወደ ሌላ ሳምንት ተሸጋግሯል። ቅዳሜ ዕለት አሜሪካ በመላው ኢራን የሚገኙ ከ140 በላይ ዒላማዎችን መምታቷን አስታውቃ ነበር። እንደ አሜሪካ ገለጻ ይህ ጥቃት የተፈጸመው የኢራን ኃይሎች በሆርሙዝ ወሽመጥ ይጓዙ የነበሩ መርከቦችን በማጥቃታቸው ነው።

    መርከቦቹ በትክክለኛው የጉዞ መስመር ላይ እንዳልነበሩ የገለጸችው ኢራን በአንጻሩ፤ ከእሁድ ዕለት አንስቶ በድጋሚ እስኪገለጽ ድረስ የሆርሙዝ ወሽመጥ መዘጋቱን አስታውቃለች። በተጨማሪም የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ በትናንትናው ዕለት በቀጣናው በሚገኙ የአሜሪካ የጦር ሰፈሮች እና አጋሮቿ ጋር ጥቃት አድርሷል።

    በዚህ መልኩ ከፍ ወዳለ ደረጃ የደረሰው የሁለቱ አገራት ግጭት፤ ትናንት ሌሊትም ቀጥሏል። የአሜሪካ ጦር ማዕከላዊ ዕዝ (ሴንትኮም) እሁድ ሌሊት ኢራን ላይ በከፈተው አዲስ ዙር ጥቃት የቴህራንን በሆርሙዝ ወሽመጥ ጥቃት የማድረስ አቅም ይቀንሳል ያለውን ድብደባ መፈጸሙን አስታውቋል።

    የአሜሪካ ኃይሎች ኢራንን አየር መከላከያ ሥርዓቶችን፣ የባህር ዳርቻ የራዳር ማዕከላትን፣ የሚሳዔል እና የድሮን አቅሞችን እንዲሁም አነስተኛ የጦር መርከቦችን ዒላማ ማድረጋቸውን ገልጿል። በዚህ ወደታራዊ ዘመቻ ላይ የአሜሪካ ተዋጊ ጄቶች፣ የባህር ኃይል መርከቦች እንዲሁም ለዚህ ዘመቻ ለመጀመሪያ ጊዜ የባሕር ኃይል አጥፍቶ ጠፊ ድሮኖች ጥቅም ላይ መዋላቸውን ዘርዝሯል።

    ማዕከላዊ ዕዙ ባወጣው መግለጫ፤ “ሆርሙዝ ወሽመጥ ለዓለም አቀፍ ንግድ ወሳኝ የባሕር መተላለፊያ ነው። ኢራን አትቆጣጠረውም” ብሏል። የአሜሪካ ኃይሎች “የንግድ መርከቦችን የጉዞ ነጻነት ለማረጋገጥ ዝግጁ” መሆናቸውንም አክሏል።

    በተመሳሳይ መግለጫ ያወጣው ኢራን አብዮታዊ ዘብ በኩሉ የአሜሪካ ጦር ይዞታዎችን ይዘዋል በተባሉ በቀጣናው አገራት ላይ ጥቃት ማድረሱን አስታውቋል። ባህሬን፣ ኩዌት እና ዮርዳኖስ ጥቃት የተፈጸመባቸው አገራት እንደሆኑ ተጠቅሷል።

    አብዮታዊ ዘቡ፤ "ዮርዳኖስ ውስጥ በሚገኘው ፕሪንስ ሀሰን የአየር ኃይል ጦር ሰፈር በርካታ ትላልቅ የሚሳዔል ማከማቻዎች እና የነዳጅ ታንከሮች በሚሳዔል እንዲሁም ድሮን ጥቃቶች በእሳት ጋይተዋል" ብሏል።

    እነዚህ ጥቃቶች የተፈጸሙት ለአሜሪካ ድብደባዎች ምላሽ ለመስጠት መሆኑን የገለጸው አብዮታዊ ዘቡ፤ ባሕሬን ውስጥ ደግሞ “ወሳኝ የአሜሪካ ጦር የሄሊኮፕተር ጥገና ማዕከላትን፣ የፒ8 የኤሌክትሮኒክስ የጦር አውሮፕላን ማቆሚያዎችን እንዲሁም የድሮን ዕዝ እና ቁጥጥር ማዕከልን” መምታቱን ገልጿል።

    ለአብዮታዊ ዘቡ ቅርበት ያላቸው የዜና ወኪሎች ኩዌት ውስጥ ፍንዳታ መሰማቱን የዘገቡ ሲሆን፤ አብዮታዊ ዘቡ ባወጣው መግለጫ ፍንዳታው የአሜሪካ ጦር ሠፈር ላይ ከተፈጸመ ጥቃት ጋር የተያያዘ መሆኑን ተናግሯል።

    እንደ የተጀመረው ጥቃት አሜሪካ እና ኢራን ተፈራርመውት የነበረውን የጊዜያዊ የተኩስ አቁም ስምምነት አደጋ ውስጥ ጥሎታል። ይህ ስምምነት ሆርሙዝ ወሽመጥ እንዲከፈት እንዲሁም ግጭቱ በቋሚነት እንዲቆም የማድረግ ዓላማ ነበረው።

    ይሁን እንጂ አደራዳሪዎች ስምምነቱን በድጋሚ ለመመለስ ጥረት እያደረጉ መሆኑን የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ተናግረዋል።