በፋርስ ባሕረ ሰላጤ የተሰማሩ የአሜሪካ ወታደሮች እና የአእምሮ ጤና ጉዳይ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኘው የአሜሪካ ሠራዊት ከፍተኛ አዛዥ የሆኑት አድሚራል ብራድ ኩፐር በባሕረ ሰላጤው በተሰማራው የአሜሪካ ግዙፍ የጦር መርከብ ላይ ለሚገኙ ወታደሮች የአእምሮ ጤና “ቀዳሚ” ትኩረት እንደሚሰጥ ተናገሩ።
ወታደራዊ መኮንኑ ይህንን ያሉት ከኢራን ጋር በሚደረገው ጦርነት ተሳታፊ በሆነው ዩኤስኤስ ሊንከን የጦር መርከብ ላይ ያሉ የአሜሪካ ወታደሮች በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ እንዲሁም አንዳንዶችም ራስን የማጥፋት ሙከራ ማድረጋቸው ከተዘገበ በኋላ ነው።
አውሮፕላን ተሸካሚው መርከብ ወደ ባሕረ ሰላጤው የደረሰው ባለፈው ጥር ሲሆን ከኢራን ጋር በሚደረገው ጦርነት ተሳታፊ ነው። ከዚህም ባሻገር አሜሪካ በኢራን ወደቦች ላይ የጣለችውን እገዳ በማስፈጸም ላይ ነው።
በመርከቡ ላይ የሚገኙ የአሜሪካ የሠራዊት አባላት ከ240 ቀናት በላይ በባሕር ላይ መቆየታቸው የተነገረ ሲሆን ይህም የተለያዩ ችግሮችን እያስከተለባቸው መሆኑ ተዘግቧል።
በዚህም ሳቢያ በመርከቧ ላይ የሚገኙ ባሕረተኞች ቤተሰቦችም የወታደሮቹ የአእምሮ ጤና ሁኔታ እያሽቆለቆለ በመሆኑ አንዳንዶች ከመርከቧ ላይ ለመዝለል ሙከራ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
ይህንን ተከትሎ በመርከቧ ላይ ጉብኝት ያደረጉት አድሚራል ኩፐር እሁድ ዕለት እንዳሉት “ለአካላዊ ጤና የምናደርገውን ዓይነት ትኩረት ለአእምሮ ጤና ማድረግ እንዳለብን አምናለሁ” ሲሉ ለሁኔታው ትኩረት እንደሚሰጡ ተናግረዋል።
ባለፈው ሳምንት የአሜሪካ ባሕር ኃይል አምስት ሺህ ሰዎችን በያዘው መርከብ ላይ የአቅርቦት ችግር እንዳለ ቢያምንም፣ የአእምሮ ጤና ችግርን በተመለከተ ግን ማስተባበያ ሰጥቷል።
አውሮፕላን ተሸካሚው የሊንከን መርከብ ተልዕኮ ባለፈው ግንቦት ወር እንዲያበቃ እቅድ ተይዞ የነበረ ቢሆንም በተደጋጋሚ እንዲራዘም ተደርጓል።
ወታደሮቹ በባሕር ላይ ለረጅም ጊዜ መቆየታቸውን በተመለከተ በአሜሪካ ምክር ቤት የጦር ኃይሎች አገልግሎት ጉዳዮች ኮሚቴ አባል የሆኑ 13 ዲሞክራቶች ለመከላከያ ሚኒስትሩ ፔት ሄግሴት የወቀሳ ደብዳቤ ጽፈዋል።
ሚኒስትሩ ፔት ሄግዜትም ሆኑ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የቀረበውን ወቀሳ አጣጥለውታል። ነገር ግን፣ ዩኤስሰስ ጆርጅ ዋሺንተግን የተባለ ሌላ መርከብ የሊንከንን ቦታ እንዲተካ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ እንደተላከ እና በአንድ ሳምንት ውስጥ ወደ አካባቢው እንደሚደርስ ተዘግቧል።



