ቀጥታ, በፋርስ ባሕረ ሰላጤ የተሰማሩ የአሜሪካ ወታደሮች እና የአእምሮ ጤና ጉዳይ

በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኘው የአሜሪካ ሠራዊት ከፍተኛ አዛዥ የሆኑት አድሚራል ብራድ ኩፐር በባሕረ ሰላጤው በተሰማራው የአሜሪካ ግዙፍ የጦር መርከብ ላይ ለሚገኙ ወታደሮች የአእምሮ ጤና “ቀዳሚ” ትኩረት እንደሚሰጥ ተናገሩ። ወታደራዊ መኮንኑ ይህንን ያሉት ከኢራን ጋር በሚደረገው ጦርነት ተሳታፊ በሆነው ዩኤስኤስ ሊንከን የጦር መርከብ ላይ ያሉ የአሜሪካ ወታደሮች በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ እንዲሁም አንዳንዶችም ራስን የማጥፋት ሙከራ ማድረጋቸው ከተዘገበ በኋላ ነው።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. በፋርስ ባሕረ ሰላጤ የተሰማሩ የአሜሪካ ወታደሮች እና የአእምሮ ጤና ጉዳይ

    በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኘው የአሜሪካ ሠራዊት ከፍተኛ አዛዥ የሆኑት አድሚራል ብራድ ኩፐር በባሕረ ሰላጤው በተሰማራው የአሜሪካ ግዙፍ የጦር መርከብ ላይ ለሚገኙ ወታደሮች የአእምሮ ጤና “ቀዳሚ” ትኩረት እንደሚሰጥ ተናገሩ።

    ወታደራዊ መኮንኑ ይህንን ያሉት ከኢራን ጋር በሚደረገው ጦርነት ተሳታፊ በሆነው ዩኤስኤስ ሊንከን የጦር መርከብ ላይ ያሉ የአሜሪካ ወታደሮች በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ እንዲሁም አንዳንዶችም ራስን የማጥፋት ሙከራ ማድረጋቸው ከተዘገበ በኋላ ነው።

    አውሮፕላን ተሸካሚው መርከብ ወደ ባሕረ ሰላጤው የደረሰው ባለፈው ጥር ሲሆን ከኢራን ጋር በሚደረገው ጦርነት ተሳታፊ ነው። ከዚህም ባሻገር አሜሪካ በኢራን ወደቦች ላይ የጣለችውን እገዳ በማስፈጸም ላይ ነው።

    በመርከቡ ላይ የሚገኙ የአሜሪካ የሠራዊት አባላት ከ240 ቀናት በላይ በባሕር ላይ መቆየታቸው የተነገረ ሲሆን ይህም የተለያዩ ችግሮችን እያስከተለባቸው መሆኑ ተዘግቧል።

    በዚህም ሳቢያ በመርከቧ ላይ የሚገኙ ባሕረተኞች ቤተሰቦችም የወታደሮቹ የአእምሮ ጤና ሁኔታ እያሽቆለቆለ በመሆኑ አንዳንዶች ከመርከቧ ላይ ለመዝለል ሙከራ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

    ይህንን ተከትሎ በመርከቧ ላይ ጉብኝት ያደረጉት አድሚራል ኩፐር እሁድ ዕለት እንዳሉት “ለአካላዊ ጤና የምናደርገውን ዓይነት ትኩረት ለአእምሮ ጤና ማድረግ እንዳለብን አምናለሁ” ሲሉ ለሁኔታው ትኩረት እንደሚሰጡ ተናግረዋል።

    ባለፈው ሳምንት የአሜሪካ ባሕር ኃይል አምስት ሺህ ሰዎችን በያዘው መርከብ ላይ የአቅርቦት ችግር እንዳለ ቢያምንም፣ የአእምሮ ጤና ችግርን በተመለከተ ግን ማስተባበያ ሰጥቷል።

    አውሮፕላን ተሸካሚው የሊንከን መርከብ ተልዕኮ ባለፈው ግንቦት ወር እንዲያበቃ እቅድ ተይዞ የነበረ ቢሆንም በተደጋጋሚ እንዲራዘም ተደርጓል።

    ወታደሮቹ በባሕር ላይ ለረጅም ጊዜ መቆየታቸውን በተመለከተ በአሜሪካ ምክር ቤት የጦር ኃይሎች አገልግሎት ጉዳዮች ኮሚቴ አባል የሆኑ 13 ዲሞክራቶች ለመከላከያ ሚኒስትሩ ፔት ሄግሴት የወቀሳ ደብዳቤ ጽፈዋል።

    ሚኒስትሩ ፔት ሄግዜትም ሆኑ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የቀረበውን ወቀሳ አጣጥለውታል። ነገር ግን፣ ዩኤስሰስ ጆርጅ ዋሺንተግን የተባለ ሌላ መርከብ የሊንከንን ቦታ እንዲተካ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ እንደተላከ እና በአንድ ሳምንት ውስጥ ወደ አካባቢው እንደሚደርስ ተዘግቧል።

  2. የዴሞክራቲክ ኮንጎ ኢቦላ ወረርሽኝ እስካሁን በአገሪቱ ከተከሰቱት የከፋው ሆኖ ተመዘገበ

    በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የተነሳው የኢቦላ ወረርሽኝ እስካሁን በአገሪቱ ታሪክ ከተከሰቱት እጅግ የከፋው ሆኖ መመዝገቡን የማኅበረሰብ ጤና ባለሥልጣናት ተናገሩ።

    ቫይረሱ መከሰቱ ግንቦት ላይ ከታወጀ ወዲህ በአጠቃላይ 2,325 ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል። ይህ የሞት ቁጥር አገሪቱ ከአውሮፓውያኑ 2018 እስከ 2020 ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ ካጋጠማት የበለጠ ነው።

    የወረርሽኙ የስርጭት መጠን በታሪክ ከታዩት ፈጣኑ እንደሆነ የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ኃላፊ ቶም ፍሌቸር ባለፈው ሳምንት ተናግረዋል። “ወረርሽኑ በየ30 ደቂቃው ሰው እየገደለ ነው” ሲሉም አስጠንቅቀው ነበር።

    የኮንጎ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እሁድ ዕለት ባወጣው መረጃ 4,945 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው እንደተረጋገጠ አስታውቋል። ከእነዚህ ውስጥ 101 ያህሉ የተመዘገቡት በ24 ሰዓታት ውስጥ ነው።

    ቫይረሱ ከዴሞክራቲክ ኮንጎ ውጪ ያለው ስርጭት በአንጻራዊነት አነስተኛ ነው። በአጎራባቿ ዩጋንዳ 20 ሰዎች መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን ጀርመን ውስጥ ሁለት ሰዎች ሕክምና እያገኙ ነው። ፈረንሳይ በቫይረሱ የተያዘ አንድ ሰው ማግኘቷን አስታውቃለች።

    ኢቦላ ኮንጎ ውስጥ ያለው የስርጭት ፍጥነት ግን ከዚህ ተቃራኒ ነው። የዓለም ጤና ድርጅት “ልዩ” ሲል የገለጸው ይህ ወረርሽኝ፣ በኮንጎ 26 ግዛቶች ውስጥ ተሰራጭቷል።

    በዓለም አቀፍ ደረጃ በርካታ ሰዎች የሞቱበት እና ከአውሮፓውያኑ 2014 እስከ 2016 በምዕራብ አፍሪካ የተከሰተው ወረርሽኝ 1,000 ሰዎችን ለመግደል አምስት ወራት እንደፈጀበት ሮይተርስ ዘግቧል። የአሁኑ ወረርሽን ግን ከሦስት ወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ 2,000 ሞቶች ተመዝግበውበታል።

    ከ50 ዓመት በፊት ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘው ኢቦላ፣ ዴሞክራቲክ ኮንጎ ውስጥ ሲከሰት ይህ ለ17ተኛ ጊዜ ነው። በአገሪቱ ለዓመታት የዘለቀ ግጭት እና ከፍተኛ የሰዎች እንቅስቃሴ መኖሩ የበሽታውን ስርጭት ለመቆጣጠር የሚደረገውን ጥረት አስቸጋሪ አድርጎታል።

    የዓለም የጤና ድርጅት የበሽታው ስርጭት በሦስት ወር ውስጥ ይቀለበሳል የሚል ተስፋ ቢኖረውም፣ ስርጭቱ በቁጥጥር ስር ይውላል ወይም ወርሽኙ ሙሉ በሙሉ ያበቃል ማለት እንዳልሆነ ገልጿል።

    ኢቦላ ብዙም ያልተለመደ ነገር ግን ገዳይ በሽታ ነው። አሁን የተከሰተው የቡንዲቡግዮ የተባለው የኢቦላ ቫይረስ ዝርያ ደግሞ ከዚህ ቀደም ከሚታወቁት ሁለት ዝርያዎች አንጻር እጅግ ያልተለመደ ነው።

    እስካሁን ድረስ ለዚህ ዝርያ የሚሆን የተረጋገጠ ክትባት የለም። የተለያዩ ተቋማት ክትባት ለመስራት ሂደት ላይ ናቸው።

  3. ጥቃቶች ከተፈጸሙ በኋላ በሆርሙዝ በኩል የሚያልፉ መርከቦች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ቀነሰ

    ባለፈው ሳምንት በነዳጅ ጫኝ መርከቦች ላይ ጥቃቶች ከተፈጸሙ በኋላ፣ ቅዳሜ እና እሁድ በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል ያለፉ መርከቦች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሱን መረጃዎች አመለከቱ።

    ይህ ዜና የተሰማው በኢራን እና በአሜሪካ መካከል እየተካሄደ ያለውን ግጭት ለማስቆም የሚደረገው ድርድር ተቋርጦ ባለበት ሁኔታ ነው።

    ኢራን ወሳኙ የባሕር መተላለፊያ መስመር፣ የሆርሙዝ ወሽመጥ የሉዓላዊ ግዛቷ አካል በመሆኑ በቁጥጥሯ ስር እንደሚሆን እየገለጸች ነው። አሜሪካ ደግሞ ስፍራው ነጻ ዓለም አቀፍ የባሕር አካል እንዲሆን እየጣረች ነው።

    በዚህም ሳቢያ ኢራን ሳያሳውቁ እና ከተፈቀደው መስመር ውጪ በሆርሙዝ በኩል ለማለፍ በሚሞክሩ መርከቦች ላይ ጥቃት እየፈጸመች ሲሆን፣ አሜሪካ በበኩሏ የኢራን መርከቦች በወሽመጡ እንዳይንቀሳቀሱ ዕገዳ ጥላለች።

    ባለፈው ሳምንት በተፈጸሙ ጥቃቶች ምክንያት በአካባቢው በሚደረገው እንቅስቃሴ ላይ ስጋት ተፈጥሯል። ኬፕለር የተባለው የባሕር ጉዞ እንቅስቃሴን የሚከታተል ተቋም ያወጣው መረጃ እንደሚያሳየው፣ ቅዳሜ ዕለት አምስት የጭነት መርከቦች ሲያልፉ፣ እሁድ ዕለት ግን አንድም መርከብ በሆርሙዝ አላለፈም።

    በወዲያኛው ሳምንት ቅዳሜ እና እሁድ 31 መርከቦች በወሳኙ የባሕር መተላለፊያ ወሽመጥ በኩል ማለፋቸው ተመዝግቦ ነበር። ይህም ካለፉት ቀናት ጋር ሲነጻጸር በከፍተኛ ሁኔታ የመርከቦች እንቅስቃሴ መገታቱን ያመለክታል።

  4. የትራምፕ ልዩ መልዕክተኛ የጋዛ የሰላም ዕቅድን ለማስፈጸም ከሐማስ መሪዎች ጋር ተገናኙ

    የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የመካከለኛው ምሥራቅ መልዕክተኛ የሆኑት ጃሬድ ኩሽነር፣ ባልተለመደ ሁኔታ በአሜሪካ ስለሚደገፈው የጋዛ የሰላም ዕቅድ አተገባበር ከሐማስ መሪዎች ጋር ተወያዩ።

    የትራምፕ አማች የሆኑት ኩሽነር በአዲሱ የሐማስ መሪ ኻሊል አል ሃያ የሚመራውን ልዑክ ያገኙት ትናንት እሁድ ግብፅ ውስጥ እንደሆነ አንድ የፍልስጤም ባለሥልጣን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

    የሰላም እቅዱን ትግበራ የሚቆጣጠረው የትራምፕ የሰላም ቦርድ ሐማስ እና በጋዛ የሚገኙ ሌሎች ታጣቂ ቡድኖች “ሙሉ በሙሉ ትጥቅ እንዲፈቱ” የሚያደርግ ስምምነት ላይ መድረሱን ሐምሌ ላይ አስታውቆ ነበር።

    ባለፈው ሳምንት ግን እስራኤል ወታደሮቿን እንድታስወጣ እንዲሁም ጋዛ ውስጥ አዲስ የፍልስጤም ሲቪል አስተዳደር እንዲመሠረት የሚያደርገውን ባለ 15 ነጥብ እቅድ እንደማትቀበለው ገልጻለች።

    ስምንት ሙስሊም አገራት ትናንት እሁድ ባወጡት መግለጫ እስራኤል እቅዱን ውድቅ ማድረጓን ኮንነዋል።

    መጀመሪያ ላይ ጋዛ ውስጥ ሰላም ለማምጣት ታስቦ የተቋቋመውን እና ኋላ ላይ በዓለም ዙሪያ የሚካሄዱ ግጭቶችም እንዲያካትት የተቋቋመውን የሰላም ቦርድ የሚመሩት ፕሬዝዳተት ትራምፕ ናቸው።

    የትራምፕ መልዕክኛ ኩሽነር ከሐማሱ መሪ አል ሃያ ጋር ያደረጉት ስብሰባ፣ የጋዛ ተኩስ ማቆም ስምምነት ከተፈረመ ወዲህ የተካሄደ የመጀመሪያው ንግግር እንደሆነ ተገልጿል።

    የሰላም ቦርድ መልዕክተኞች የሆኑት ኒኮላይ ምላደኖቭ እንዲሁም የቀድሞው የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ ብሌር ስብሰባው ላይ መገኘታቸውን ዘገባዎች አመልክተዋል። የሰላም ጥረቱን ሲያሸማግሉ የቆዩት የግብፅ፣ ኳታር እና ቱርክ ተወካዮችም መሳተፋቸው ተሰምቷል።

    የሐማስን ትጥቅ መፍታት በተመለከተ ስለሚወሰዱ ተግባራዊ እርምጃዎች እንዲሁም የእስራኤል ወታደሮችን መውጣት እና ሰብዓዊ ጥረቶችን በተመለከተ በውይይቱ ምን እንደተባለ እስካሁን ይፋ አልሆነም።

    የትራምፕ መልዕክተኛ ኩሽነር በግብፅ ቆይታቸው፣ ከአገሪቱ ፕሬዝዳንት አብደል ፋታህ አል ሲሲ ጋርም ተገናኝተዋል። ዛሬ ሰኞ ደግሞ ኩሽነር፣ ምላደኖቭ እና ብሌር የትራምፕን እቅድ ለማስፈጸም ከእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ ጋር ይገናኛሉ።

    የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ስምምነቱ እንዲተገበር መጀመሪያ ሐማስ ሙሉ በሙሉ ትጥቅ መፍታት እንዳለበት ገልጸዋል።

    ኔታንያሁ ባለፈው ሳምንት ባደረጉት ንግግር፣ “እስራኤል የሰላም ቦርዱን ባለ 15 ነጥብ የጋዛ ሰነድ አትቀበልም። ሐማስ የእውነት ትጥቁን እስካልፈታ የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት በምንም አይነት አይወጣም” ሲሉ የቅርብ አጋራቸው አሜሪካን ተቃውመዋል።

    ግብፅ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ ኳታር፣ ሳውዲ አረቢያ፣ ዮርዳኖስ፣ ቱርክ፣ ፓኪስታን እና ኢንዶኔዥያ እሁድ ዕለት ባወጡት የጋራ መግለጫ፣ እስራኤል የአሜሪካን ዕቅድ ውድቅ ማድረጓ የትራምፕን የሰላም ጥረት አደጋ ላይ ይጥለዋል የሚል ስጋታቸውን አንጸባርቀዋል።

    ከጥቅምት አንስቶ ወደ ሥራ የገባው የተኩስ አቁም ስምምነት አሁንም ተግባራዊ መሆን አላቆመም።

    ነገር ግን እስራኤል ስምምነቱ ከተፈረመ ጊዜ ጀምሮ በጋዛ ውስጥ በርካታ ጥቃቶችን ፈጽማለች። ሐማስ ተኩስ አቁሙን ጥሷል በሚል የመጨረሻውን ጥቃት ያደረሰችው ኻን ዩኒስ እና ኑሴራት በተባሉት የጋዛ አካባቢዎች ነው።