የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ወደ ሞስኮ ተጓዙ

የፎቶው ባለመብት, @hawelti
የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በሩሲያ-አፍሪካ ጉባዔ ላይ ለመሳተፍ ዛሬ ማክሰኞ ማለዳ ወደ ሞስኮ ማቅናታቸውን የማስታወቂያ ሚኒስትራቸው ገለጹ።
ሩሲያ ከአፍሪካ አገራት ጋር በተለያዩ ዘርፎች ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር በየዓመቱ የምታካሂደው ጉባዔ ሦስተኛው ዙር ረቡዕ እና ሐሙስ ጥቅምት 18 እና 19/2019 ዓ. ም. በዋና ከተማዋ ውስጥ ይደረጋል።
የማስታወቂያ ሚኒስትሩ የማነ ገብረ መስቀል በማኅበራዊ ገጻቸው ላይ እንዳመለከቱት ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸው ጋር የተጓዙት ፕሬዝዳንት ኢሳያስ በጉባዔው ላይ ከመሳተፋቸው በተጨማሪ ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር በሁለትዮሽ እና በሌሎች የጋራ ጉዳዮች ላይ ይወያያሉ።
በዚህ ጉባዔ ላይ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ በርካታ የአፍሪካ አገራት መሪዎች እንደሚሳተፉ ይጠበቃል።
በቅርቡ ሕንድ ውስጥ በተካሄደው የብሪክስ አባል አገራት ስብሰባ ወቅት ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በጉባዔው እንዲሳተፉ ያቀረቡላቸውን ጥሪ መቀበላቸው ተገልጿል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከሳምንታት በፊት የሩሲያ ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሌክሳንደር አሊሞቭ አገራቸው በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል የተፈጠረውን ውጥረት ለማርገብ የአሸማጋይነት ሚና ለመጫወት ፍላጎት እንዳላት መግለጻቸው ይታወሳል።
ሚኒስትሩ ለአንድ ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ ሁለቱ አገራት ፈቃደኞች ከሆኑ የሩሲያ-አፍሪካ ጉባኤ በሚካሄድበት ወቅት ንግግር እንዲያካሂዱ መድረክ ለማመቻቸት ዝግጁ መሆናቸውን እና ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ዕድሉን እንደሚጠቀሙበት ተስፋ እንዳላቸው ገልጸው ነበር።
አሊሞቭ የአገራቸው “የረዥም ጊዜ ታማኝ አጋሮች” ባሏቸው በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል የተፈጠረው ውጥረት ለሩሲያ አሳሳቢ መሆኑን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ያለው ውዝግብ በተካረረበት ጊዜ የአገራቱ ወዳጅ የሆነችው ሩሲያ ሁለቱም ከግጭት በመቆጠብ የመተማመን እርምጃዎችን እንዲያጠናክሩ እና በንግግር ልዩነቶቻቸውን እንዲፈቱ ቀደም ሲል ጥሪ አቅርባለች።












