የቀድሞው የሱዳን ፕሬዚዳንት አል ባሽር "አስቸኳይ" የውጭ ሕክምና እንደሚያስፈልጋቸው ተዘገበ

የፎቶው ባለመብት, AFP
ከሥልጣን የተወገዱት የቀድሞው የሱዳን ፕሬዚዳንት ኦማር አል ባሽር ለሕክምና ኻርቱም ወደ’ሚገኘው ወታደራዊ ሆስፒታል መላካቸውን እና ከአገር ውጭ ሕክምና እንደሚያስፈልጋቸው ጠበቃቸው መናገራቸውን ሮይተርስ ዘገበ።
የ82 ዓመቱ ባሽር ለወራት ከቆየ ተቃውሞ በኋላ በአገሪቱ ጦር እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ (አርኤስኤፍ) ትብብር ከሥልጣን የተወገዱት እአአአ ሚያዝያ 2019 ነበር።
በኋላ ላይ ግን ወደ ሲቪል አስተዳደር ለመመለስ የሽግግር ሥርዓት በሚደረግበት ወቅት ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ እና የአገሪቱ ጦር ኃይላቸውን ለማዋሃድ በነበራቸው ዕቅድ ላይ መስማማት ባለመቻላቸውን ከሦስት ዓመታት በላይ በእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ይገኛሉ።
ባሽር ጦርነቱ ከመቀስቀሱ አስቀድሞ ከእስር ቤት ወጥተው ወደ ሆስፒታል ተወስደው የነበረ ሲሆን በኋላ ላይ በሰሜን ሱዳን ወደምትገኘው ሚሮው ከተማ ተወስደው በወታደራዊ ጥበቃ ሥር ቆይተዋል።
የቀድሞ ፕሬዚዳንቱ አሁን ላይ ለሕክምና ምርመራ ወደ ኻርቱም የተወሰዱ ሲሆን የተሻለ የውጭ አገር ሕክምና እንደሚያስፈልጋቸው የሚያሳዩ ምልክቶች እንደነበሯቸው ጠበቃቸው መሐመድ አልሃሳን አላሚን ለሮይተርስ የዜና ወኪል ተናግረዋል።
ሮይተርስ እንደዘገበው የባሽር ቤተሰቦችም ዛሬ በሰጡት መግለጫ ባሽር ከሱዳን ውጭ ሕክምና እንደሚያስፈልጋቸው እና “ወሳኝ እና አስቸኳይ እንደሆነ እንዲሁም ብዙ መቆየት እንደማይችሉ” ተናግረዋል። ሆኖም ወደ ውጪ እንዲሄዱ ፈቃድ አላገኙም።
ባሽር ያጋጠማቸው የጤና ችግር ምን እንደሆነ ግልጽ አይደለም።
ሮይተርስ የሱዳን ጦርን በጉዳዩ ላይ አስተያየት ቢጠይቅም ምላሽ እንዳላገኘ ገልጿል። በርካታ የሱዳን እስላማዊ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች የቀድሞ ፕሬዚዳንቱ ወደ ውጪ ተልከው ሕክምና እንዲያገኙ በማኅበራዊ ሚዲያ እየጠየቁ ነው።
ሆኖም አል ባሽር በዘር ማጥፋት ወንጀል ተከሰው በዓለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት ስለሚፈለጉ እና በሱዳን ውስጥም ክሶች ስላሉባቸው ከአገር እንዲወጡ ማድረጉ በሱዳን አለመግባባት ሊፈጥር ይችላል።
በባሽር የሦስት አስርት ዓመታት የሥልጣን ዘመን ሱዳን በአሜሪካ የሽብርተኛ ደጋፊ ዝርዝር ውስጥ ተካትታ ማዕቀብ ተጥሎባታል።
በሕዝባዊ አመጽ ወቅት ተቃዋሚዎች እርሳቸውን እና ‘እስላሚክ ናሽናል ኮንግረንስ’ ፓርቲያቸውን በሙስና እና በጭቆና ከስሰዋል።
አልበሽር ከሥልጣን ከተወገዱ በኋላም የተለያዩ ክሶች ቀርቦባቸው በሙስና እና በሕገ ወጥ ገንዘብ ድጋፍ ጥፋተኛ ሆነው ተፈርዶባቸዋል። በጦርነቱ መጀመሪያ ወቅትም እስር ላይ ነበሩ።





















