ቀጥታ, ሩቢዮ የኢራን ልዑካን ቡድን ኒው ዮርክን ለቅቆ እንዲወጣ አዘዙ

የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ፣ የኢራን ልዑካን ቡድን ከታቀደለት ጊዜ ቀድሞ ከአሜሪካ እንዲወጣ ማዘዛቸውን አንድ የአሜሪካ ባለሥልጣን እና የዲፕሎማሲያዊ ጉዳዮች ምንጭ ለሲቢኤስ ኒውስ ገለጹ። በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር የሆነው ሲቢኤስ ሩቢዮ የልዑካን ቡድኑ እንዲወጣ ያዘዙት በሁለቱ አገራት ባለሥልጣናት መካከል ከተደረጉ ቴክኒካዊ ውይይቶች በኋላ ሰኞ ዕለት መሆኑን ምንጮቹን ጠቅሶ ዘግቧል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. የቀድሞው የሱዳን ፕሬዚዳንት አል ባሽር "አስቸኳይ" የውጭ ሕክምና እንደሚያስፈልጋቸው ተዘገበ

    የቀድሞ የሱዳን ፕሬዚደንት ኦማር አል ባሽር
    የምስሉ መግለጫ, አል-ባሽር ሱዳንን ለ30 ዓመታት ያህል መርተዋል

    ከሥልጣን የተወገዱት የቀድሞው የሱዳን ፕሬዚዳንት ኦማር አል ባሽር ለሕክምና ኻርቱም ወደ’ሚገኘው ወታደራዊ ሆስፒታል መላካቸውን እና ከአገር ውጭ ሕክምና እንደሚያስፈልጋቸው ጠበቃቸው መናገራቸውን ሮይተርስ ዘገበ።

    የ82 ዓመቱ ባሽር ለወራት ከቆየ ተቃውሞ በኋላ በአገሪቱ ጦር እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ (አርኤስኤፍ) ትብብር ከሥልጣን የተወገዱት እአአአ ሚያዝያ 2019 ነበር።

    በኋላ ላይ ግን ወደ ሲቪል አስተዳደር ለመመለስ የሽግግር ሥርዓት በሚደረግበት ወቅት ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ እና የአገሪቱ ጦር ኃይላቸውን ለማዋሃድ በነበራቸው ዕቅድ ላይ መስማማት ባለመቻላቸውን ከሦስት ዓመታት በላይ በእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ይገኛሉ።

    ባሽር ጦርነቱ ከመቀስቀሱ አስቀድሞ ከእስር ቤት ወጥተው ወደ ሆስፒታል ተወስደው የነበረ ሲሆን በኋላ ላይ በሰሜን ሱዳን ወደምትገኘው ሚሮው ከተማ ተወስደው በወታደራዊ ጥበቃ ሥር ቆይተዋል።

    የቀድሞ ፕሬዚዳንቱ አሁን ላይ ለሕክምና ምርመራ ወደ ኻርቱም የተወሰዱ ሲሆን የተሻለ የውጭ አገር ሕክምና እንደሚያስፈልጋቸው የሚያሳዩ ምልክቶች እንደነበሯቸው ጠበቃቸው መሐመድ አልሃሳን አላሚን ለሮይተርስ የዜና ወኪል ተናግረዋል።

    ሮይተርስ እንደዘገበው የባሽር ቤተሰቦችም ዛሬ በሰጡት መግለጫ ባሽር ከሱዳን ውጭ ሕክምና እንደሚያስፈልጋቸው እና “ወሳኝ እና አስቸኳይ እንደሆነ እንዲሁም ብዙ መቆየት እንደማይችሉ” ተናግረዋል። ሆኖም ወደ ውጪ እንዲሄዱ ፈቃድ አላገኙም።

    ባሽር ያጋጠማቸው የጤና ችግር ምን እንደሆነ ግልጽ አይደለም።

    ሮይተርስ የሱዳን ጦርን በጉዳዩ ላይ አስተያየት ቢጠይቅም ምላሽ እንዳላገኘ ገልጿል። በርካታ የሱዳን እስላማዊ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች የቀድሞ ፕሬዚዳንቱ ወደ ውጪ ተልከው ሕክምና እንዲያገኙ በማኅበራዊ ሚዲያ እየጠየቁ ነው።

    ሆኖም አል ባሽር በዘር ማጥፋት ወንጀል ተከሰው በዓለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት ስለሚፈለጉ እና በሱዳን ውስጥም ክሶች ስላሉባቸው ከአገር እንዲወጡ ማድረጉ በሱዳን አለመግባባት ሊፈጥር ይችላል።

    በባሽር የሦስት አስርት ዓመታት የሥልጣን ዘመን ሱዳን በአሜሪካ የሽብርተኛ ደጋፊ ዝርዝር ውስጥ ተካትታ ማዕቀብ ተጥሎባታል።

    በሕዝባዊ አመጽ ወቅት ተቃዋሚዎች እርሳቸውን እና ‘እስላሚክ ናሽናል ኮንግረንስ’ ፓርቲያቸውን በሙስና እና በጭቆና ከስሰዋል።

    አልበሽር ከሥልጣን ከተወገዱ በኋላም የተለያዩ ክሶች ቀርቦባቸው በሙስና እና በሕገ ወጥ ገንዘብ ድጋፍ ጥፋተኛ ሆነው ተፈርዶባቸዋል። በጦርነቱ መጀመሪያ ወቅትም እስር ላይ ነበሩ።

  2. ፓኪስታን በአፍጋኒስታን ላይ በርካታ ሰዎች የተገደሉበት የአየር ጥቃቶችን ፈፀመች

    ጥቃት የተፈፀመበት ሥፍራ

    ፓኪስታን በአፍጋኒስታን ላይ በፈፀመችው የአየር ጥቃት ዘጠኝ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን እና ሌሎች 11 ሰዎች መቁሰላቸውን የታሊባን መንግሥት አስታወቀ።

    የኢዝላማባድ የኢንፎርሜሽን ሚኒስቴር በበኩሉ ጥቃቱ መፈፀሙን አረጋግጦ፣ 22 ታጣቂዎችን መግደሉን ገልጿል።

    አፍጋኒስታንን የሚመራው ታሊባን ቃል አቀባይ ዛቢሁላህ ሙጃሂድ ግን በጥቃቱ ከፓኪስታን ጋር አዋሳኝ በሆኑት በኩናር እና ሄልማንድ ግዛቶች የሚገኙ መኖሪያ ቤቶች ተመትተዋል ብለዋል። ቃል አቀባዩ በኤክስ ገጻቸው ባጋሩት ጽሑፍ ከሟቾቹ መካከል ሴቶች እና ሕፃናት እንደሚገኙበትም ጠቅሰው፣ ጥቃቱን አውግዘዋል።

    ፓኪስታን በበኩሏ "በደንብ የታቀደው እና ትክክለኛ የሆነ" ባለችው ጥቃት ዒላማ የተደረገው በአፍጋኒስታን ውስጥ ከፍተኛ መጠን ያላቸው የጦር መሳሪያዎች እና ጥይቶች የተከማቹበት “የሽብር ካምፖች” እንደሆኑ ገልጻለች።

    የአገሪቷ የኢንፎርሜሽን ሚኒስቴር ጥቃቱ ዒላማውን እንዳይስት ከፍተኛ ጥንቃቄ ተደርጓል ብሏል።

    የዓይን እማኞች የአየር ጥቃቱ ትናንት ሌሊት 8:00 ሰዓት ጀምሮ ለ30 ደቂቃ መዝለቁን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

    "ተኝተን ነበር፤ የመጀመሪያው ቦምብ ሲፈነዳ ከእንቅልፋችን ተነሳን፣ ከሁለተኛው ጥቃት በኋላ ልጆቻችንን ይዘን ከአካባቢው ሸሸን። ሦስተኛው ቦምብ የጎረቤቶቻችን ቤት ላይ አረፈ። አራት እና አምስት የቤተሰብ አባላቶቻቸው ተገደሉ። ሌሎቹ ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል።" ብለዋል።

    ፓኪስታን፤ አፍጋኒስታን ድንበር ተሻጋሪ ጥቃቶችን የሚፈፅሙ ቡድኖችን ታስጠልላለች የሚል ክስ ለረጅም ጊዜ ስታሰማ ቆይታለች። የታሊባን መንግሥት ግን ክሱን በተደጋጋሚ ውድቅ አድርጓል።

  3. ካሊፎርኒያ በ32 የአሜሪካ ግዛቶች አሁንም ሕጋዊ የሆነውን ያለ እድሜ ጋብቻ አገደች

    ቢርትኒ ቢ ታዳጊ ሳለች ነበር የተዳረችው
    የምስሉ መግለጫ, ቢርትኒ ቢ ታዳጊ ሳለች ነበር የተዳረችው

    የካሊፎርኒያ አስተዳዳሪ ጋቪን ኒውሶም በግዛታቸው ተግባራዊ እየሆነ ያለውን ያለ እድሜ ጋብቻ የሚከለክል ሕግ ፈረሙ።

    ሕጉ እአአ ከጥር 1 2027 ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናል የተባለ ሲሆን ማንኛውም ሰው ትዳር ለመመስረት እድሜው 18 መሙላት አለበት ተብሏል።

    ኒውሶም ሕጉን ሕጻናት እና ታዳጊዎችን ለመከላከል “ለረዥም ጊዜ የዘገየ እርምጃ” ሲኡ ገልጸውታል።

    አስተዳዳሪው ሕጉን ፈርመው ሲያጸድቁ ከአጠገባቸው በ16 ዓመቷ ለ50 ዓመት የሆሊውድ ተዋናይ የተዳረችው ኮርትኒ ስቶደን ነበረች።

    ስቶደን ያለ እድሜ ጋብቻ በካሊፎርኒያ እንዲቀር ስትወተውት ነበር ተብሏል። አዲሱን ሕግ “ድል ነው” ያለችው ስቶደን፣ ያለ እድሜያቸው የሚዳሩ ሴቶች የሚደርስባቸውን ስቃይ ብቻቸውን መሸከም የለባቸውም ስትል ተናግራለች።

    ስቶደን “በሁሉም 50 ግዛቶች ሕጻናት ከካለ እድሜ ጋብቻ መጠበቅ እስኪቻል ድረስ ትግሌን እቀጥላለሁ” ብላለች።

    ከአስር ዓመታት በፊት ይህ አሰራር በሁሉም የአሜሪካ ግዛቶች ይፈቀድ የነበረ ቢሆንም፣ ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ ግዛቶች ሕጎቻቸውን እየቀየሩ ይነው።

    ካሊፎርኒያ እአአ ከ2018 ወዲህ ያለ እድሜ ጋብቻን የከለከለች 18ኛዋ ግዛት ሆናለች።

    በካሊፎርኒያ ግዛት ውስጥ ለጋብቻ የተቀመጠ የዕድሜ ገደብ አልነበረም፤ ይህም ወላጆች ፈቃዳቸውን ከሰጡ እና በጋብቻው መስማማታቸውን ህጻናት እንዲያገቡ ያስችል ነበር።

  4. የመንግሥታቱ ድርጅት የሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት በጦርነት የተፈናቀሉትን ጨምሮ ሲቪሎችን ለአደጋ ያጋለጠ ነው አለ

    በኢትዮጵያ የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (ኦቻ)

    በኢትዮጵያ የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (ኦቻ) የሰሜን ኢትዮጵያው ግጭት የቀደመው ጦርነት ተፈናቃዮችን ጨምሮ ሲቪሎችን ለአደጋ እያጋለጠና ተጨማሪ ነዋሪዎችን እያፈናቀለ ነው አለ።

    ኦቻ ትናንት ረቡዕ ዕለት ባወጣው መግለጫ ሁሉም ተፋላሚ ወገኖች የእርዳታ ሠራተኞችን እና ንብረቶችን ደኅንነት እንዲጠብቁና ለተጋላጭ ወገኖች ያለ ምንም ጣልቃ ገብነት የሕይወት አድን እርዳታ እንዲደርስ እንዲያደርጉ ጠይቋል።

    የታጠቁ ኃይሎች በተለያዩ ጊዜያት በኃይል የያዟቸውን ሁሉንም የረድኤት ድርጅቶች ተሽከርካሪዎች በአስቸኳይ እንዲመልሱም ኦቻ በመግለጫው ጥሪ አቅርቧል።

    የድርጅቱ አስተባባሪ ኦዞኒያ ኦጂሎ (ዶ/ር) በመግለጫቸው በተለይም በቀደመው ግጭት ተፈናቅለው የነበሩ ዜጎች ለተደራራቢ የደህንነት ስጋት መጋለጣቸው እና አዳዲስ መፈናቀሎች መከሰታቸው በሰላማዊ ሰዎች ጥበቃ ላይ ከፍተኛ ስጋት ፈጥሯል ብለዋል።

    ​ኃላፊው አክለውም የሰብዓዊ እርዳታ ማኅበረሰብ በተጎዱ አካባቢዎች ድጋፍ መስጠቱን ቢቀጥልም፣ በተለይ በቅርቡ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ከተከሰተው ውጥረት መባባስ ጋር ተያይዞ በእርዳታ ሠራተኞች፣ በንብረቶች፣ በቢሮዎች እንዲሁም በሲቪል መሠረተ ልማቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች በእጅጉ እንዳሳሰቧቸው ገልጸዋል። ​

    ኦቻ በመግለጫው በታጣቂ ቡድኖች ቢያንስ 10 የሰብዓዊ እርዳታ ተሽከርካሪዎች መዘረፋቸውን አስታውቆ እስካሁን የተመለሱት ሁለት ብቻ ናቸው ብለዋል። ​

    ​አስተባባሪው የእርዳታ ሠራተኞችና ንብረቶች በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ሕግ መሰረት ከጥቃት የተጠበቁ መሆናቸውንና መቼም ቢሆን ዒላማ መደረግ እንደሌለባቸው አሳስበዋል።

    ኃላፊው አክለውም ሁሉም ወገኖች ዓለም አቀፍ ሕጎችንና መርሆዎችን እንዲያከብሩ፣ የእርዳታ ስራዎችን ከማደናቀፍ እንዲቆጠቡ እንዲሁም ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች ያለምንም እንቅፋት እርዳታ እንዲደርስ ሁኔታዎችን እንዲያመቻቹ ጥሪ አቅርበዋል።

  5. ሩቢዮ ከኢራን ጋር የሚደረገው ድርድር ለውጥ አለማምጣቱን ተከትሎ የልዑካን ቡድኑ ኒው ዮርክን ለቅቆ እንዲወጣ አዘዙ

    የኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ

    የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ፣ የኢራን ልዑካን ቡድን ከታቀደለት ጊዜ ቀድሞ ከአሜሪካ እንዲወጣ ማዘዛቸውን አንድ የአሜሪካ ባለሥልጣን እና የዲፕሎማቲክ ምንጭ ለሲቢኤስ ኒውስ ገለጹ።

    በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር የሆነው ሲቢኤስ ሩቢዮ የልዑካን ቡድኑ እንዲወጣ ያዘዙት በሁለቱ አገራት ባለሥልጣናት መካከል ከተደረጉ ቴክኒካዊ ውይይቶች በኋላ ሰኞ ዕለት መሆኑን ምንጮቹን ጠቅሶ ዘግቧል።

    የኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ የሚመሩት ልዑክ፣ የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ለመካፈል ባለፈው ሳምንት ወደ ኒውዮርክ የሄደ ሲሆን፣ የሆርሙዝ ባህር ወሽመጥን ዳግም ለመክፈት ከአሜሪካ ጋር ቀጥተኛ ያልሆነ ውይይት ሲያደርግ ቆይቷል።

    አራግቺ ከዚህ ቀደም ለሲቢኤስ ኒውስ እንደገለጹት ከአሜሪካ ማክሰኞ ዕለት ለመውጣት አቅደው ነበር።

    ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን ባለፈው ሳምንት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ንግግር ካደረጉ በኋላ በሚቀጥለው ቀን ከኒው ዮርክ ቢወጡም፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አባስ አራግቺ ግን የሆርሙዝ ወሽመጥን ዳግም ስለመክፈት እና ግጭቱን በዘላቂነት በማስቆም ዙሪያ በሚደረጉ ቀጥተኛ ያልሆኑ ውይይቶች ላይ ለመሳተፍ በዚያው ቆይተው ነበር።

    አሜሪካ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ የተመደቡትንና በግዛቷ ውስጥ የሚገኙትን የኢራን ዲፕሎማቶች በሙሉ ከአገር እንዲወጡ አላደረገችም።

    በመንግሥታቱ ድርጅት የአሜሪካ ተወካይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሩቢዮን ትዕዛዝ ተከትሎ ሰኞ ዕለት ምሽት አራግቺ እና ልዑካን ቡድናቸው ኒው ዮርክን “ወዲያውኑ” ለቅቀው እንዲወጡ ማዘዛቸውን አክሲዮስ ዘግቧል።

    ኢፒ በበኩሉ የአሜሪካ ባለሥልጣናትን ጠቅሶ፣ የልዑካን ቡድኑ “ከተፈቀደለት ጊዜ በላይ ቆይቷል” እንዲሁም “የመንግሥታቱ ድርጀት ጉባዔ አብቅቷል፤ ስለዚህ ወደ አገራቸው መመለስ አለባቸው” መባሉን ዘግቧል።

    የኢራን የልዑካን ቡድን ማክሰኞ ዕለት ከኒው ዮርክ ወደ ዶሃ ጉዞውን ጀምሯል።

    እንደዘገባው ከሆነ፣ ዋይት ሐውስ ሰኞ ጠዋት ከኢራን ጋር በሚደረገው ድርድር ላይ የተወሰነ መሻሻል ይኖራል ብሎ ጠብቃ የነበረ ቢሆንም ነገር ግን ከሰዓት በኋላ ድርድሩ ለውጥ አለመሳየቱን ግልጽ ሆኗል።

    የኳታር አደራዳሪዎች ከሁለቱም አገራት ተወካዮች ጋር የሰላም ስምምነት ላይ ሊደረስበት በሚችሉ ጉዳዮች ላይ በተናጠል እየተወያዩ ናቸው።

    እስራኤል እና አሜሪካ በጋራ በመሆን የካቲት 28 2018 ዓ.ም. በኢራን ላይ ጦርነት የከፈቱ ሲሆን በምላሹም ኢራን ወደ ባህረ ሰላጤው አገራት ድሮኖችን እና ሚሳዔሎችን አስወንጭፋለች።

    በመካከለኛው ምሥራቅ ኢራን ጦርነት ከተቀሰቀሰ ጊዜ ጀምሮ የዓለም አንድ አምስተኛ የነዳጅ የሚጓጓዝበት የሆርሙዝ ወሽመጥ በመዘጋቱ የዓለም ነዳጅ ዋጋ ላይ ከፍተኛ ጭማሪ ተስተውሏል።

  6. ብሔራዊ መረጃና ደኅንነት በአዲስ አበባና አካባቢው ላልተወሰነ ጊዜ ድሮን ለማብረር ፈቃድ እንደማይሰጥ አስታወቀ

    ብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት

    ብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት በአዲስ አበባ እና አካባቢው ከዛሬ ጀምሮ ላልተወሰነ ጊዜ ማንኛውንም ድሮን ለማብረር ፈቃድ እንደማይሰጥ አስታወቀ።

    ዛሬ መስከረም 20/2019 ዓ. ም. በማኅበራዊ ድረ ገጹ ባወጣው መግለጫ የተሰጠውን ማሳሰቢያ በመጣስ “የሚነሱ እንዲሁም በየትኛውም አካባቢ እና ከፍታ የሚበሩ ድሮኖችን በመለየት፣ በመጥለፍ እና ወደ አስፈላጊው ቦታ በማሳረፍ እንዲሁም የአብራሪዎቹን ትክክለኛ መገኛ ቦታ በመለየት እና በቁጥጥር ሥር በማዋል ሕጋዊ እርምጃ ይወሰዳል” ብሏል።

    “እንደ ወትሮው ሁሉ በአዲስ አበባ እና አካባቢው የሚንቀሳቀሱ ድሮኖችን እና ሌሎች ተመሳሳይ በራሪ አካላትን የሚቆጣጠር የተቀናጀ የፀረ ድሮን ቴክኖሎጂ በመጠቀም ክትትል እና ቁጥጥር እየተደረገ ይገኛል” ሲልም አክሏል።

    ብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት ማሳሰቢያውን የሰጠው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ዳግም ባገረሸበት ወቅት ነው።

    የፌደራል ሠራዊት እና የትግራይ ኃይሎች ከባለፈው ሳምንት አንስቶ ውጊያ እያካሄዱ ይገኛሉ።

    ብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት ባወጣው መግለጫ፤ ከዚህ ቀደም በሥራ ምክንያት ድሮኖች መጠቀም የሚፈልጉ አካላት “የበረራውን ዓላማ፣ የሚበርበትን ቦታ፣ የድሮኑን ዓይነት እና የሞዴል ቁጥር በመጥቀስ” ፈቃድ ጠይቀው ይሰጣቸው እንደነበር ጠቅሷል።

    አያይዞም “የመሪዎችን፣ የቁልፍ መሠረተ ልማቶችን እና ብሔራዊ ኩነቶችን ደኅንነት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን የማስጠበቅ ኃላፊነቱን ለመወጣት ላልተወሰነ ጊዜ ፍቃድ መስጠቱን እና የበረራ ክልከላውን ተግባራዊ ማድረጉን” አብራርቷል።

    ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በስፋት ጥቅም ላይ እየዋሉ የመጡ ድሮኖች እና “መሰል ቴክኖሎጂ ወለድ መሣሪያዎች” የሚፈጥሯቸውን የብሔራዊ ደኅንነት ስጋቶችን ለመከላከል የሚያስችሉ “የረቀቁ ቴክኖሎጂዎች መታጠቁን” በመግለጫው አመልክቷል።

    አክሎም ማሳሰቢውያውን “ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ለማስፈጸም በቂ ዝግጅት እንዳለው” አትቷል።

  7. ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት ለላሙ የነዳጅ ማጣሪያ ፋብሪካ መሠረተ ድንጋይ ተቀመጠ

    ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ
    የምስሉ መግለጫ, ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መሠረተ ድንጋይ በማኖር ሥነ ሥርዓቱ ላይ ተገኝተዋል

    በሰሜን ኬንያ የወደብ ከተማ ላሙ ለሚገነባው የነዳጅ ማጣሪያ ዛሬ ረቡዕ መሠረተ ድንጋይ የማኖር ሥነ ሥርዓት ተከናውኗል።

    የአፍሪካ ቁጥር አንድ ባለ ሃብት የሆኑት ናይጄርያዊው ቢልየነር አሊኮ ዳንጎቴ የሚያስገነቡት የነዳጅ ማጣሪያ 16 ቢሊዮን ዶላር ያወጣል።

    ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እንዲሁም የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊልያም ሩቶ መሠረተ ድንጋይ በማኖር ሥነ ሥርዓቱ ላይ ተገኝተዋል።

    የፋብሪካው ግንባታ ሲጠናቀቅ በቀን 700,000 በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ ማጣራት ይችላል። በዚህም የፋብሪካው የኢንዱስትሪ አቅም በምሥራቅ አፍሪካ ቀዳሚው ይሆናል።

    ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በማኅበራዊ ሚዲያቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ ለላሙ ነዳጅ ማጣሪያ መሠረተ ድንጋይ መጣሉ “የአፍሪካን የኢንዱስትሪ አቅም በማሳደግ አንድ እርምጃ ነው” ብለዋል።

    “በምሥራቅ አፍሪካ ዕድል የሚፈጥር፣ ለትልቅ የምጣኔ ሃብት እና ኢንዱስትሪ ሉዓላዊነት መሠረት የሚጥል” እንደሆነም ገልጸዋል።

    ባለ ሃብቶች አፍሪካ ላይ እምነት ጥለው ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጥሪ ያቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “የአፍሪካ የወደፊት ዓለም በጋራ የምንገነባው ነው” ብለዋል።

    የፋብሪካው የመሠረት ድንጋይ ከመጣሉ በፊት የተወሰኑ የአካባቢው ነዋሪዎች አደባባይ ወጥተው ፋብሪካው ለሚገነባበት መሬት ተጨማሪ ካሳ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።

    ዳንጎቴ ግን ተቃውሞውን አጣጥለው የፋብሪካው ግንባታ በተያዘው ዕቅድ መሠረት እንደሚከናወን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

    የፋብሪካው ግንባታ በአውሮፓውያኑ 2030 እንደሚጠናቀቅ ተገልጿል።

    ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በተጨማሪ የኡጋንዳ፣ ቶጎ እና ቤኒን መሪዎች ተገኝተዋል።

    ዳንጎቴ ለቀጣናው መንግሥታት በአጠቃላይ በፋብሪካው የ30% ድርሻን ይፋ ማድረጋቸውን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

    የፋብሪካው ግንባታ ሲጀመር ዳንጎቴ ባደረጉት ንግግር “አፍሪካውያን አፍሪካን ለመገንባት ተሰባስበዋል። ዛሬ እየጀመርን ያለነው ነዳጅ ማጣሪያ ብቻ አይደለም፤ አፍሪካ ብሩህ ተስፋ እንዲኖራት የኢንዱስትሪ ግንባታ አዲስ ምዕራፍ እየከፈትን ነው” ብለዋል።

    በናይጄርያ ያላቸውን የነዳጅ ማጣሪያ ‘ሌኪ’ እንደ ምሳሌ በመጥቀስ “በላሙም እንደሚደገም” ገልጸዋል።

    ፕሬዝዳንት ዊልያም ሩቶ
    የምስሉ መግለጫ, የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊልያም ሩቶ መሠረተ ድንጋይ በማኖር ሥነ ሥርዓቱ ላይ ተገኝተዋል
    አሊኮ ዳንጎቴ
    የምስሉ መግለጫ, የአፍሪካ ቁጥር አንድ ባለ ሃብት የሆኑት ናይጄርያዊው ቢልየነር አሊኮ ዳንጎቴ
  8. ወደ እስራኤል እየተጓዘ በነበረው አውሮፕላን ላይ ፓይለቱን በስለት የወጋው አብራሪ መታሰሩ ተገለጸ

    ከዱባይ ወደ ቴል አቪቭ እየተጓዘ የነበረው አውሮፕላን

    ከዱባይ ወደ ቴል አቪቭ እየተጓዘ በነበረ አውሮፕላን ላይ ፓይለቶች በመጣላታቸው በረራው ወደ ሳዑዲ አረቢያ እንዲለወጥ ተደርጓል።

    ዋና አብራሪው እና ምክትል አብራሪው ተጣልተው ጉዳት እንደደረሰባቸው እና ወደ ሆስፒታል እንደተወሰዱ ተገልጿል።

    የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ “የስለት ጥቃት የፈጸመው ፓይለት በቁጥጥር ሥር ውሎ በሳዑዲ ባለሥልጣናት ጥያቄ እየቀረበለት ነው” ብለዋል።

    አውሮፕላኑ ወደ እስራኤል ሲቃረብ አንደኛው ፓይለት ሌላኛውን ፓይለት በስለት እንደወጋው እና አውሮፕላኑን ለመከስከስ እንደሞከረ ተገልጿል።

    ከዱባይ የተነሳው የፍላይዱባይ አውሮፕላን በረራውን በጀመረ በሁለት ሰዓታት ውስጥ የድንገተኛ ጊዜ ምልክት ማሳየቱን በረራዎችን የሚከታተለው ፍላይትራዳር24 ድረ ገጽ ጠቁሟል።

    ከሁለት ደቂቃ በኋላ ደግሞ አውሮፕላን ሲጠለፍ የሚሰጠውን ምልክት አውሮፕላኑ ማሳየት ጀምሯል።

    ዋና አብራሪው እና ምክትሉ “መጋጨታቸውን” የእስራኤል መከላከያን ጠቅሰው መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

    በኤፍዜድ1073 በረራ ላይ 150 ተሳፋሪዎች የነበሩ ሲሆን አብዛኞቹ እስራኤላውያን ናቸው።

    ሁሉም ተሳፋሪዎች ደኅና እንደሆኑ እና አውሮፕላኑም በታቡክ አየር ማረፊያ እንደደረሰ ተገልጿል።

    ልጇ ሚርያም በረራው ላይ እንደነበረች የተናገረችው ያስሚን አቡካሲስ፣ ስለት የያዘ ግለሰብ ከፓይለቶቹ አንዱ መሬት ላይ እንዲወርድ እንዳስገደደው ገልጻለች። አውሮፕላኑ ውስጥ ደም ይታይ እንደነበርም ተናግራለች።

    ጀሩሳሌም ፖስት ያነጋገረው ተጓዥ እንዳለው አንደኛው ፓይለት ሌላኛውን በስለት ወግቶታል። አውሮፕላኑ ፊት ወንበር ላይ ተቀምጠው የነበሩ ተሳፋሪዎች ጥቃት አድራሹን ከጀርባው እንዳነቁትም ተናግረዋል።

    አውሮፕላኑ ውስጥ የነበሩ ሌሎች ሁለት ፓይለቶች አውሮፕላኑን በማሳረፍ እንደተባበሩ ተገልጿል።

    ሁለቱም ፓይለቶች ጉዳት እንደደረሰባቸው ተገልጿል።

  9. “ለቀናት የጥይት እና ከባድ መሣሪያ ድምጽ ይሰማናል”- ከላሊበላ መውጣት ያልቻሉት ቱሪስቶች

    የላሊበላ አውሮፕላን ማረፊ

    የአውሮፕላን በረራ በመቋረጡ ምክንያት ከላሊበላ ለመውጣት ያልቻሉ ቱሪስቶች 33 እንደሚደርሱ ቢቢሲ ያነጋገራቸው ቱሪስቶች ተናገሩ።

    በታሪካዊቷ ከተማ ዙሪያ ግጭት እየተባባሰ በመሄዱ ለቀናት የጥይት እና ከባድ መሣሪያ ድምጽ እየሰሙ እንደሆነ ገልጸዋል።

    ጎብኚዎቹ በረራ እስከሚጀመር ድረስ በጭንቀት እየተጠባበቁ እንደሚገኙ ለቢቢሲ ኒውስደይ አስረድተዋል።

    እንግሊዛዊ ቱሪስት ትናንት ማክሰኞ እንደተናገረው 33 ቱሪስቶች ከላሊበላ መውጣት አልቻሉም።

    14 እስራኤላውያን ቱሪስቶች በወታደራዊ ሄሊኮፕተር፣ ሌሎች አምስት ቱሪስቶች እና አንድ የእርዳታ ሠራተኛ ደግሞ በተራድኦ ድርጅት ተሽከርካሪ ከከተማዋ ወጥተዋል።

    ሁለት እንግሊዛውያንን ጨምሮ አሜሪካውያን፣ እስራኤላውያን፣ ደቡብ ኮሪያውያን፣ ደቡብ አፍሪካውያን፣ ሜክሲኳውያን እና የሌሎችም አገራት ቱሪስቶች አሁንም በከተማዋ ይገኛሉ።

    በላሊበላ ዙርያ ውጊያ ቢኖርም ከተማዋ ሰላም መሆኗን እንግሊዛውያኑ ቱሪስቶች ለቢቢሲ ገልጸዋል።

    ከአስጎብኚዎች፣ ከኢትዮጵያ መንግሥት፣ ከአየር መንገድ፣ ከኤምባሲዎች እና ከቀይ መስቀል መረጃ እንደሚጠባበቁም ተናግረዋል።

    ቢቢሲ ያነጋገረው እንግሊዛዊ ቱሪስት “ውጊያ ይሰማናል፤ ሙሉ ሳምንቱን ጥይት እና ከባድ መሣሪያ ሲተኮስ እንሰማለን” ሲል ገልጿል።

    ከትናንት በስትያ በነበሩት 48 ሰዓታት ውስጥ ውጊያው ጋብ በማለቱ በረራ ሊጀመር ይችላል ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉም አክሏል።

    መስከረም 21/2019 ዓ. ም. በረራ ሊጀመር ይችላል የሚል መረጃ ቢደርሳቸውም “እርግጠኛ እንዳልሆነ” ጎብኚዎቹ ገልጸዋል።

    ባለፈው ሳምንት በፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት እና በትግራይ ኃይሎች መካከል እንደ አዲስ ጦርነት መነሳቱን ተከትሎ የላሊበላ አውሮፕላን ማረፊያ በረራ አቋርጧል።

  10. ዓለሚቱ ኡሞድ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሆነው ተሾሙ

    ዓለሚቱ ኡሞድ

    የጋምቤላ ክልል ምክር ቤት ዛሬ መስከረም 20/ 2019 ዓ. ም. 7ኛ የሥራ ዘመን፣ 1ኛ ዓመት፣ 1ኛ መደበኛ ጉባዔውን ያካሄደ ሲሆን፤ ዓለሚቱ ኡሞድ ​በድጋሚ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሆነው ተሹመዋል።

    የክልሉ የማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ ሆነው ያገለግሉ የነበሩት ዓለሚቱ፤ ነሐሴ 2016 ዓ. ም. ላይ ኡመድ ኡጁሉን ተክተው ርዕሰ መስተዳደር መሆናቸው ይታወሳል።

    ከዚያ ቀደም የክልሉን ሴቶች እና ሕጻናት ቢሮም በኃላፊነት መርተዋል።

  11. አዳነች አቤቤ የአዲስ አበባ ከንቲባ ሆነው ተሾሙ

    ወ/ሮ አዳነች አቤቤ

    የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የከተማ አስተዳደር መንግሥት ምሥረታ እና 4ኛ ዙር የመክፈቻ ጉባዔውን ዛሬ መስከረም 20፣ 2019 ዓ. ም. ያደረገ ሲሆን፤ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ የከተማዋ ከንቲባ ሆነው በድጋሚ ተሹመዋል።

    የደሴ ከተማ ከንቲባ የነበሩት አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ እና የፕላን ልማት ቢሮ ኃላፊ ሆነው በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ተሹመዋል።

    የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት ከንቲባዋ “በቀጣዩ ምዕራፍ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችን ኑሮ ለማሻሻል በትኩረት ይሠራል” ብለዋል።

    ከንቲባዋ ባደረጉት ንግግር “የኑሮ ውድነት እና የዋጋ ግሽበትን በመቀነስ የከተማውን ነዋሪ የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል በትኩረት ይሠራል” ማለታቸውን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

  12. ኢራን በአደራዳሪዋ ኳታር በኩል የአሜሪካን ምላሽ መቀበሏን ገለጸች

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ የሆርሙዝ ወሽመጥን ለመክፈት ያስችላል በሚል በኳታር በኩል ላቀረቡት ዕቅድ የአሜሪካን ምላሽ መቀበላቸውን የመንግሥት ቃል አቀባይ ፋጢመህ ሞሃጄራኒ ረቡዕ ዕለት መግለጻቸውን የመንግሥት የዜና አገልግሎት ኢሪብ ዘገበ።

    ሞሃጄራኒ የዋሽንግተንን ምላሽ ይዘት ወዲያውኑ ይፋ ያላደረጉ ሲሆን የቴህራን ቀጣይ እርምጃ ምን እንደሚሆንም አልገለጹም።

    አራግቺ ረቡዕ ዕለት በቴህራን በአሜሪካ ምላሽ ዙሪያ እንደሚወያዩ ይጠበቃል ሲሉ ባለሥልጣኑ ተናግረዋል።

    ኢራን ባለፈው ሳምንት በሰባት ቀናት ውስጥ የሆርሙዝ ወሽመጥን መክፈት ያስችላል ያለችውን ዕቅድ አቅርባ ነበር። በዚህም መሰረት አስፈላጊዎቹ ሁኔታዎች ከተሟሉ የሆርሙዝ ባሕር ወሽመጥ እንደገና ሊከፈት እና መርከቦች በነጻነት መንቀሳቀስ እንደሚችሉ አራግቺ ገልጸው ነበር።

    ሆኖም የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዕቅዱን ውድቅ በማድረጋቸው፣ ጉዳዩን በድርድር ለመፍታት ኳታር ተጨማሪ ጥረት እያደረገች መሆኑ ተገልጿል።

    በሌላ በኩል፣ የኢራን ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን ቴህራን የኢዝላማባዱን የመግባቢያ ስምምነት ስኬታማ ለማድረግ የሚቻላትን ሁሉ ጥረት እያደረገች መሆኑን ኢስና የዜና ወኪል ዘግቧል።

    ፕሬዚዳንቱ ከድርድሩ ስለተገኙት ጥቅሞች እና ውጤቶች ማብራራት እንደ እጅ መስጠት ወይም ለኢራን ተቃዋሚዎች መገዛት ተደርጎ መወሰድ የለበትም፤ ይልቁንም እንደ ግልጽነት መገለጫ ሊታይ ይገባል ብለዋል።

    ፔዜሽኪያን በተጨማሪም ኢራን በኢዝላማባድ የመግባቢያ ሰነድ ውስጥ በተካተተ በማንኛውም ድንጋጌ ላይ ከመሠረታዊ መርሆቿ አለማፈግፈጓን ገልጸዋል።

    ይህንን ስምምነት በኢራን ታሪክ ውስጥ “የኩራት ምንጭ” እንዲሁም “ወሳኝ እና ከፍተኛ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰነድ” ሲሉ ገልጸውታል።

    ይህ የተከሰተው የሆርሙዝ ባሕር ወሽመጥን እንደገና ለመክፈት ኢራን ያስቀመጠቻቸውን ቅድመ ሁኔታዎች የኳታር አደራዳሪዎች ለዋሽንግተን እንደሚያቀርቡ አራግቺ ሰኞ ዕለት ከተናገሩ በኋላ ነው።

    ከአደራዳሪዎቹ ጋር ከተደረጉት ውይይቶች በኋላ የአሜሪካ ምላሽ ለኢራን እንደሚደርስ እንደሚጠብቁም ገልጸው ነበር።

    ኢራን፤ የአሜሪካን ወታደራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና ለማስቆም፣ የታገዱ የኢራን ንብረቶችን መልቀቅ እና ደኅንነቱ የተጠበቀ የመርከብ መተላለፊያ መስመር ላይ ስምምነት መድረስ የሚሉ ነጥቦችን በቅድመ ሁኔታነት አስቀምጣለች።

    ቴህራን እነዚህን አቋሞቿን ለዋሽንግተን ያቀረበችው ባለፈው ሳምንት ከተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ጎን ለጎን በተደረገ የሁለት ሰዓት ውይይት ወቅት በኳታር በኩል ነው።

  13. በሶማሊያ የባሕር ላይ ወንበዴዎች አምስት የነዳጅ ጫኝ መርከብ ሰራተኞች ተገደሉ

    ባሕር ላይ ያለች ጀልባ

    በሶማሊያ የባሕር ዳርቻ አምስት የመርከብ ሰራተኞች መገደላቸውን አንድ ከፍተኛ የክልሉ ባለሥልጣን ለቢቢሲ ተናገሩ።

    የፑንትላንድ ምክትል የማስታወቂያ ሚኒስትር ቢል ቃቦውሳድ እንዳሉት አምስቱ ባሕረተኞች የተገደሉት በባሕር ላይ ወንበዴዎች ነው።

    ተጠልፋ የቆየችው እና 'ኤምቲ ሆርነር 25 የተሰኘችው' ነዳጅ ጫኝ መርከብ በአካባቢው የጸጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ሥር መዋሏን የገለጹት ሚኒስትሩ፣ ባሕረተኞቹ የተገደሉት መርከቧ በጸጥታ ኃይሎች እጅ ከመግባቷ አስቀድሞ እንደሆነ ገልጸዋል ።

    ሟቾቹ ሦስት ፓኪስታናዊ፣ ሕንዳዊ እና ምያንማራዊ መሆናቸውንም ሚኒስትሩ ገልጸዋል። ሦስት ፓኪስታናዊ እና አንድ ሕንዳዊ እንዲሁም ሌሎች አራት ባሕረተኞች ላይም ጉዳት ደርሷል።

    ነዳጅ ጫኝ መርከቧ ወደ 18 ሺህ 500 በርሜል ነዳጅ ጭና ወደ ሶማሊያ መዲና ሞቃዲሹ እየተጓዘች ሳለ ነበር ሚያዚያ ላይ በስድስት ታጣቂዎች የተጠለፈችው። አስራ ስድስት ተጠርጣሪ ወንበዴዎች በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሲሆን ሌሎች ማምለጣቸውን እና ክትትል እየተደረገባቸው መሆኑን ባለሥልጣናት ገልጸዋል።

    የተወሰኑ ወንበዴዎች እንዲያመልጡ ከፊል ራስ ገዝ የሆነችው ፑንትላንድ ረድታላች በሚል የቀረቡ ክሶችን የማስታወቂያ ሚኒስትሩ አጣጥለዋል።

    ባለሥልጣናት ወንበዴዎቹ መርከቧን እንዴት እንደተቆጣጠሩ እና አምስቱ ባሕረተኞች እንዴት እንደተገደሉ ዝርዝር መረጃ አልሰጡም።

    ሆኖም ሚያዝያ ወር ላይ መርከቧ ስትጠለፍ 17 ባሕረተኞችን ይዛ እንደነበር ባለሥልጣናት ገልጸዋል። እነዚህም 10 ፓኪስታናዊ፣ አራት ኢንዶኔዥያውያን ፣ አንድ ሕንዳዊ፣ አንድ ስሪላንካዊ እና የምያንማር ዜጋ ናቸው።

    ከአውሮፓውኑ 2011 ዓለም አቀፍ የባሕር ላይ ዘመቻዎች በኋላ የወንበዴዎች እንቅስቃሴ ቢቀንስም ጥቃቶች እና ጠለፋዎች ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እንደገና ጨምረዋል።

  14. በፈረንሳይ ከተባባሰው የተማሪዎች ተቃውሞ ጋር በተያያዘ ከ400 በላይ ሰዎች በቁጥጥር ሥር ዋሉ

    በእሳት የተያያዘ የቆሻሻ ቅርጫት

    በመላው ፈረንሳይ በተቀሰቀሰው የተማሪዎች ተቃውሞ ጋር በተያያዘ ታዳጊዎችን ጨምሮ ከ400 በላይ ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሯ ተናገሩ።

    በፓሪስ የተጀመረው እና ታዳጊዎች ለቀናት ትምህርት የዘጉበት የተቃውሞ ሰልፍ የተነሳው የክፍለ ጊዜዎች መጨናነቅ እና የመምህራን እጥረትን ጨምሮ ከተነሱ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ነው።

    ማክሰኞ ዕለት በተካሄደው የተቃውሞ ሰልፍም ቢያንስ 10 መምህራን፣ በርካታ ተማሪዎች እንዲሁም 48 ሕግ አስፈፃሚ አካላት ላይ ጉዳት መድረሱ ተገልጿል። እንደ ትምህርት ሚኒስቴር ከሆነ በተቃውሞ ሰልፉ ቢያንስ 400 የሚሆኑ ትምህርት ቤቶች ተስተጓጉለዋል።

    ቪዲዮ እና ምስሎችም በተቃዋሚዎች የወደሙ የአውቶብስ መቆሚያዎች እና በእሳት የተያያዙ የቆሻሻ ቅርጫቶችን አሳይተዋል።

    ተማሪዎች በዱላ እና አስለቃሽ ጭስ በመተኮስ ምላሽ በሰጡት የጸጥታ ኃይሎች ላይ የተለያዩ ቁሳቁሶችን መወርወራቸውንም የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

    የትምህርት ሚኒስትሩ ኤዶርድ ጂፍሬይ፣ ተማሪዎች ተቃውሞ የማካሄድ መብት እንዳላቸው ገልጸው፤ ነገር ግን የሚፈፅሙትን ጥቃት " ስህተት" ሲሉ አውግዘዋል።

    የውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ ላውረንት ኑንዝ በበኩላቸው ከተቃውሞው ጋር በተያያዘ 440 ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ጠቅሰው፤ ከእነዚህ መካከል ሁለት ሦስተኛ የሚሆኑት እስር ላይ መሆናቸው እንደተነገራቸው ገልጸዋል።

    የተማሪዎቹ ተወካይ እና የማኅበሩ ፕሬዚደንት የሆነው ሪያድ ራኒ ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል “በአፈና” እና "ፖሊስ ያልተመጣጠነ ኃይል ተጠቅሟል” ሲል መንግሥትን ከስሷል።

    ፖሊስ የሰጠው ምላሽ በበርካታ የአገሪቱ ፖለቲከኞችም የተተቸ ሲሆን የውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ ግን ክሱን አስተባብለዋል።

  15. አሜሪካ ከቴህራን የጦር መሣሪያ ግዢ ጋር ንክኪ አላቸው ያለቻቸው የሩሲያ ኩባንያዎች ላይ ማዕቀብ ጣለች

    የኢራኑ እና የሩሲያው ፕሬዚዳንቶች ስምምነት ሲፈራረሙ

    አሜሪካ ከኢራን ጦር መሣሪያ ግዢ ጋር ግንኙነት አላቸው ያለቻቸው በርካታ ግለሰቦች፣ ድርጅቶች እና ሁለት የሩሲያ ኩባንያዎች ላይ ማዕቀብ ጣለች።

    የአሜሪካ ግምጃ ቤት በትናንትናው ዕለት የጣለው አዲስ ማዕቀብ የሩሲያ ኩባንያዎችን ጨምሮ በሆንግ ኮንግ፣ ቻይና እና ፓኪስታን የሚገኙ 13 ግለሰቦችን ዒላማ ያደረገ ነው።

    አሜሪካ በቴህራን ላይ የምጣኔ ሃብት ጫና ለመፍጠር በማሰብ የምታካሄደውን ዘመቻ መቀጠሏን ተናግራለች።

    ማዕቀቡ ከተጣለባቸው የሩሲያ ኩባንያዎች መካከል ለአገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴር የጦር መሣሪያዎችን የሚያጓጉዘው እና የሩሲያ አውሮፕላን አምራች ኩባንያዎች እንደሚገኙበት ሮይተርስ ዘግቧል።

    ከዚህ ቀደም ሩሲያ ለቴህራን የድሮን መለዋወጫዎችን እና የጦር መሣሪያዎችን መስጠቷን የሚያሳዩ ሪፖርቶች ወጥተዋል።

    ከዚህ በተጨማሪም ሞስኮ፣ ቴህራን በባሕረ ሰላጤው የሚገኙ የአሜሪካ ጦር ሠፈሮችን ማጥቃት እንድትችል ድጋፍ ማድረጓ ተገልጿል።

    ሩሲያ በዩክሬን ላይ ሙሉ ወታደራዊ ጥቃት መክፈቷን ተከትሎ የቴህራን እና የሞስኮ ግንኙነት በከፍተኛ ሁኔታ እየተጠናከረ መጥቷል።

    በጦርነቱ የመጀመሪያ ዓመት ኢራን በወታደራዊ እና በሲቪል ዒላማዎች ላይ በስፋት ጥቅም ላይ የሚውሉትን 'ሻሄድ' ድሮኖች ለሩሲያ አቅርባ ነበር።

    በምላሹም የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን፤ ኢራን በሆርሙዝ ባሕረ ሰላጤ አካባቢ ከአሜሪካ ጋር በምታደርገው ግጭት ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉ እና "አስፈላጊ ቁሳቁሶችን" እንደሚያቀርቡላት ተናግረዋል።

    የካቲት 28/2018 ዓ.ም. አሜሪካ ኢራን ላይ ጦርነት የከፈተች ሲሆን ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ውጊያው እንደቀጠለ ነው።

    ኢራን ለሩሲያ በምታደርገው ድጋፍ ምክንያት በኪየቭ እና በቴህራን መካከል ውጥረት በነገሰበት በዚህ ወቅት ኪየቭ ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ላይ በካስፒያን ባሕር ወታደራዊ ቁሳቁሶችን እያጓጓዘ በነበረ የኢራን መርከብ ላይ ጥቃት ፈጽማለች።

  16. የኳታር አደራዳሪዎች በአሜሪካ እና በኢራን መካከል የሰላም ስምምነት እንዲደረስ ግፊት እያደረጉ ነው

    የኳታር ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሼክ መሐመድ ቢን አብዱልራህማን አል ታኒ
    የምስሉ መግለጫ, የኳታር ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሼክ መሐመድ ቢን አብዱልራህማን አል ታኒ

    ኳታር ማክሰኞ ዕለት በኢራን እና በአሜሪካ መካከል የሰላም ስምምነት ለማምጣት የዲፕሎማሲ ሥራዎችን እየሰራች መሆኑን አስታወቀች።

    የኳታር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማጂድ አል አንሳሪ "ከሁለቱም ወገኖች ጋር መልዕክቶችን እየተለዋወጥን ሲሆን ሁላችንንም ከግጭቱ ጦስ የሚታደግ ስምምነት ላይ ለመድረስ የሚያስችል የጋራ መግባባት ለመፍጠር እየሠራን ነው" ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

    አሜሪካ እና ኢራን ስምንተኛ ወሩን ከያዘው ጦርነቱ ለመውጣት በሚያስችላቸው ጉዳዮች ላይ እስካሁን ድረስ መግባባት አልቻሉም።

    ባለፈው ሳምንት በኒው ዮርክ በተካሄደው የመንግሥታቱ ድርጅት ጉባዔ ወቅት የዲፕሎማሲ ጥረቶች ተጠናክረው የቀጠሉ ቢሆንም የዓለም አንድ አምስተኛ ነዳጅ የሚንቀሳቀስበትን የሆርሙዝ ወሽመጥን ሊያስከፈት የሚያስችል ስምምነት ላይ ግን መድረስ ሳይቻል ቀርቷል።

    ኳታር ለአጭር ጊዜም ቢሆን የተኩስ አቁም እንዲኖር ያስቻለውን የሰኔውን የመግባቢያ ሰነድ እንዲፈረም በማድረግ ረገድ ቁልፍ ሚና የተጫወተች ሲሆን አሁንም የሰላም ስምምነት ላይ እንዲደረስ ብርቱ ጥረት እያደረገች ነው።

    ሰኞ ዕለት የአሜሪካ እና ኢራን ባለሥልጣናት በተናጠል የኳታር አደራዳሪዎችን ማነጋገራቸውን አስታውቀዋል።

    ነገር ግን ማክሰኞ ዕለት ቀጣይ ንግግር ስለመካሄዱ እስካሁን የታወቀ ነገር የለም።

    ትራምፕ በተደጋጋሚ ኢራን የኒውክሌር ጦር መሣሪያ መታጠቅ እንደማትችል እና ጦርነቱ በቅርቡ እንደሚያበቃ ሲናገሩ ተደምጠዋል።

    ጦርነቱ የኢራንን መከላከያ ኃይል በከፍተኛ ሁኔታ የጎዳ ሲሆን ቀድሞውንም የተዳከመ የነበረው የአገሪቱ ምጣኔ ሃብት የበለጠ እንዲንኮታኮት አድርጎታል።

    ነገር ግን ቴህራን ጦርነት ከተከፈተባት በኋላ በባሕረ ሰላጤው በሚገኙ የአሜሪካ አጋሮች እና ጦር ሠፈሮች ላይ ሚሳዔሎችን እና ድሮኖችን እያስወነጨፈች ነው።

    የሆርሙዝ ወሽመጥንም በመዝጋት ዓለም የነዳጅ ዋጋ እንዲያሻቅብ አድርጋለች።

    ትራምፕ ማክሰኞ ዕል “እስካሁን ተስፋ ስላለመቁረጣቸው የማውቀው ነገር የለም፤ ነገር ግን ተስፋ መቁረጣቸው አይቀርም” ሲሉ ማክሰኞ ዕለት ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

    አክለውም “በጣም ደካማ ጥረት ነው እያደረጉ ያሉት” ብለዋል።

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ከኢራን ጋር የገቡትን ጦርነት ለማቆም የማዕቀብ እፎይታ ለመስጠት ቃል ገብተዋል ሲሉ የዘገቡትን አስተባብለዋል።

    የአሜሪካ ባለሥልጣናትን ጠቅሰው ዘገባቸውን ያቀረቡ የመገናኛ ብዙኃን ትራምፕ ኢራን በኒውክሌር ፕሮግራሟ ላይ “ተጨባጭ” እርምጃ የምትወስድ ከሆነ የተጣለባትን ማዕቀብ ለማርገብ እና እንዳይንቀሳቀሱ የታገዱ ሃብቶችን ለመልቀቅ ተስማምተዋል ብለዋል።

    ትራምፕ ሰኞ ዕለት በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ “ይህ ውሸት ነው። ምንም ነገር ለመስጠት ቃል አልገባሁም” ብለዋል።

    ባለፈው ሳምንት በመንግሥታቱ ድርጅት ጉባዔ ላይ ለመሳተፍ ወደ ኒው ዮርክ ያቀናው የኢራን ልዑካን ቡድን የሆርሙዝ ወሽመጥን በሰባት ቀን ውስጥ መክፈት ያስችላል ያለውን የሰላም ዕቅድ ቢያቀርብም ትራምፕ ውድቅ አድርገውታል።

  17. ኔታንያሁ አገሪቱ በጥቅምት ወር ከምታደርገው ምርጫ አስቀድሞ ጥቃት ሊፈጸም እንደሚችል መረጃ እንዳላቸው ተናገሩ

    የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ

    የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በጥቅምት ወር አጋማሽ ላይ ከሚደረገው ምርጫ በፊት አገሪቱ ላይ ጥቃት ለመፈጸም የሚፈልጉ ኃይሎች ስለመኖራቸው ተናገሩ።

    "ከምርጫው በፊት ጠላቶቻችን ጥቃት ሊሰነዝሩብን እንደሚሞክሩ የሚያሳዩ ምልክቶች አሉ" ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ከቴል አቪቭ በስተደቡብ በሚገኘው የቴል ኖፍ የአየር ኃይል ሆነው ባስተላለፉት የቪዲዮ መልእክት ተናግረዋል።

    እንዲህ ዓይነቱን ጥቃት ሊፈጽሙ ስለሚችሉ አካላት ወይም ስለተገኘው የደህንነት መረጃ ዝርዝር መግለጫ አልሰጡም።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው "እኛን አትነካኩን፤ ረዥም ክንዳችን በማንኛውም ቦታና ጊዜ ይደርስባችኋል" ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

    ኔታንያሁ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ጥቅምት 27 ለሚካሄደው ምርጫ ቅስቀሳ እያደረጉ ነው።

    እስራኤል ጋዛ እና ሊባኖስን ጨምሮ በተለያዩ ግንባሮች ወታደራዊ ዘመቻዎቿን እንደቀጠለች፣ እንዲሁም በቅርብ ሳምንታት ውስጥ በጋዛ ከ100 በላይ "አሸባሪዎችን" መግደሏን ገልጸዋል።

    በተጨማሪም ማክሰኞ ዕለት፣ በምዕራብ ጋዛ ከተማ በሚገኘው አል-ናስር ሰፈር ውስጥ በሚገኝ የመኖሪያ ሕንፃ ላይ በፈጸመችው ጥቃት ሁለት ፍልስጤማውያን ተገድለዋል።

  18. ትራምፕ ለኢራን የማዕቀብ እፎይታ ለመስጠት ቃል አለመግባታቸውን ተናገሩ

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ከኢራን ጋር የገቡትን ጦርነት ለማቆም የማዕቀብ እፎይታ ለመስጠት ቃል ገብተዋል ሲሉ የዘገቡትን አስተባበሉ።

    የአሜሪካ ባለሥልጣናትን ጠቅሰው ዘገባቸውን ያቀረቡ የመገናኛ ብዙኃን ትራምፕ ኢራን በኒውክሌር ፕሮግራሟ ላይ “ተጨባጭ” እርምጃ የምትወስድ ከሆነ የተጣለባትን ማዕቀብ ለማርገብ እና እንዳይንቀሳቀሱ የታገዱ ሃብቶችን ለመልቀቅ ተስማምተዋል ብለዋል።

    ትራምፕ ሰኞ ዕለት በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ “ይህ ውሸት ነው። ምንም ነገር ለመስጠት ቃል አልገባሁም” ብለዋል።

    አክሲዮስ እና ሲኤንኤን ማንነታቸው ያልጠቀሷቸውን የአሜሪካ ባለሥልጣናት በመጠቀም ትራምፕ ኢራን በኒውክሌር ጉዳይ ላይ “ተጨባጭ እርምጃ” ለመውሰድ የምትስማማ ከሆነ የማዕቀብ እፎይታ ለመስጠት እና የታገዱ ሃብቶቿን ለመልቀቅ ፈቃደኛ ናቸው ብለዋል።

    ትራምፕ ከኢራን ጋር የሚያደርጉት ጦርነት የኒውክሌር ጦር መሣሪያ እንዳይኖራት ለመከላከል፣ ጎረቤቶቿን የማጥቃት አቅሟን ለማስቀረት እንዲሁም ኢራናውያን አመራሮቻቸውን ከሥልጣን እንዲያወረዱ ሁኔታዎችን ለማመቻቸት መሆኑን ተናግረዋል።

    ኢራን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ እንደሌላት ነገር ግን የኒውክሌር ኃይል ለሰላማዊ ግልጋሎት የማበልጸግ መብት እንዳላት ትከራከራለች።

    የኢራን ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን ከሲቢኤስ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ ቴህራን በኒውክሌር ፕሮግራሟ እና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ለመወያየት ዝግጁ መሆኗን ቢናገሩም “ማስገደድን” ግን እንደማይቀበሉ ተናግረዋል።

    “ኢራን ጦርነት አትፈልግም፣ ነገር ግን ራሷን ከጫና፣ ዛቻ እና ጥቃቶች ትከላከላለች” ሲሉ ፔዜሽኪያን ተናግረዋል። ቀደም ሲል “የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ማምረት እንደሌለብን” ስምምነት ላይ መድረሳቸውንም አስታውሰዋል።

    የአሜሪካ እና የኢራን ባለሥልጣናት ሰኞ ዕለት ከአደራዳሪዎች ጋር ለየብቻቸው መነጋገራቸውን ይህም ለሰባት ወር የተካሄደውን ጦርነት ለማስቆም በሚደረገው ጥረት አካል መሆኑን የሁለቱም አገራት ባለሥልጣናት ተናግረዋል።

    ኢራን እሁድ ዕለት ከዩናይትድ ስቴትስ እና ከእስራኤል ጋር ያላትን ግጭት መፍታት የምትችለው በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ብቻ እንደሆነ ገልጻለች።

  19. የአሜሪካ ወታደሮች ከሁለት አስር ዓመታት በኋላ ኢራቅን ለቅቀው ሊወጡ ነው

    የአሜሪካ ጦር ኢራቅን በይፋ የወረረው እና ሳዳም ሁሴንን ከሥልጣን ያወረደው እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር መጋቢት 2003 ነበር።

    የአሜሪካ ወታደሮች እስከ ነገ ረቡዕ ድረስ በኢራቅ ከሚገኙት የመጨረሻዎቹ የጦር ሠፈሮቻቸው ለመውጣት መዘጋጀታቸው ተሰማ። የወታደሮቹ የጦር ሠፈሮቹን ለቅቆ መውጣት በኢራን እና አጋሮቿ ዘንድ እንደ ድል ተቆጥሯል።

    ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ በኢራቅ ውስጥ የቆየው የአሜሪካ ጦር ከ4,500 ወታደሮቹ ሕይወታቸውን አጥተዋል።

    የኢራቅ የደህንነት ባለሙያዎች እንደሚናገሩት፣ በፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ዘመን ከስምምነት የተደረሰው እና ከኢራን ጋር ጦርነት እየተካሄደ ባለበት ወቅት በዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር የተፈጸመው ይህ ወታደሮቹን የማስወጣት እርምጃ፤ ለቴህራን እና ለአጋሮቿ ሰፊ የመንቀሳቀስ ነፃነትን ሊሰጥ፣ እንዲሁም እንደ እስላማዊ መንግሥት ያሉ ሌሎች የአሜሪካ ጠላቶች እንደገና እንዲጠናከሩ ሊያደርግ ይችላል።

    ከኢራን ጋር ግንኙነት ያላቸውን የታጠቁ ቡድኖችን በማጥናት ላይ ያተኮሩት የኢራቅ የደህንነት ጉዳዮች ተንታኝ ጃሲም አል-ባሃድሊ፣ “ለዓመታት በኢራቅ ውስጥ የቴህራን ተጽዕኖ መገዳደሪያ ሆኖ ያገለግል የነበረውን ጦርን ስለሚያስወግድ፣ የጥምረት ኃይሉ መውጣት ለኢራን ስትራቴጂካዊ ጥቅም ያስገኛል” ብለዋል።

    ከኢራን ጋር ወገንተኛ የሆኑት የታጣቂ ቡድኖች፣ የአሜሪካ ጦር መውጣትን ለእንቅስቃሴያቸው እንደ ድል ከመቁጠር ባለፈ፣ ያንን ሁኔታ በመጠቀም “በደህንነት እና በፖለቲካዊ ውሳኔ አሰጣጥ ሂደት ላይ የበለጠ ተጽዕኖ ለመፍጠር” እንደሚሞክሩ ተንብየዋል።

    በኢራን የሚደገፉ የታጠቁ ቡድኖች ጥምረት የሆነው ‘ኢስላሚክ ሪዚስስታንስ ኢን ኢራቅ’ አዛዥ አቡ ሞጅታባ አል-ያሲሪ፣ የአሜሪካ ኃይሎች መውጣት “ለኢስላሚክ ሪዚስስታንስ ኢን ኢራቅ እና ለታላቁ የኢራቅ ሕዝብ ታሪካዊ ድል፣ እንዲሁም ለአሜሪካ ፕሮጀክት ደግሞ ከባድ ሽንፈት” ሲሉ ገልጸውታል።

    “እአአ መስከረም 30፣ በኢራቅ ታሪክ ውስጥ ያለውን አንድ ጥቁር ምዕራፍ የሚዘጋበት እና ወረራው በአገራችን ላይ የራሱን ፍላጎት ለመጫን ያደረገው ሙከራ የከሸፈበት በመሆኑ እንዘክረዋለን” ሲሉ ለሮይተርስ ተናግረዋል።

    “ኢራቅ፣ ሉዓላዊነቷ ሊረጋገጥ የሚችለው በውጭ ኃይሎች ሳይሆን በሕዝቧ ትግል እና ቁርጠኝነት እንደሆነ አስመስክራለች” ሲሉም አክለዋል።

    የአሜሪካ ጦር ኢራቅን በይፋ የወረረው እና ሳዳም ሁሴንን ከሥልጣን ያወረደው እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር መጋቢት 2003 ነበር።

  20. “ኢራን ነዳጅ መሸጥ የማትችል ከሆነ ማንም ነዳጅ አይሸጥም”- የቴህራን ባለሥልጣን

    የኢራን አፈ ጉባዔ መሐመድ ባጋር ጋባሊፍ ቢቢሲ አማርኛ

    የኢራን ፓርላማ አፈ ጉባዔ መሐመድ ባጋር ጋባሊፍ፣ ቴህራን ነዳጅ መሸጥ የማትችል ከሆነ “ማንም ነዳጅ አይሸጥም” ሲሉ አስጠነቀቁ።

    “ደኅንነታችን የማይረጋገጥ ከሆነ የትኛውም መሠረተ ልማት ደኅንነቱ አይጠበቅም” ብለዋል።

    አፈ ጉባዔው ዛሬ በበይነ መረብ አማካኝነት በምክር ቤት ባደረጉት ንግግር፣ የኢራን ሕዝብ “በከበባ እና ዛቻ” ፍርሃት ውስጥ መግባት የለበትም ብለዋል።

    “የአሜሪካው ጠላት ኃይል ይሄንን መሠረታዊ እውነታ አልተረዳም፤ በኢራን ከፍተኛ ጥቃት እየደረሰበት በአዙሪት ውስጥ ይቀጥላል” ሲሉም አክለዋል።

    በሌላ በኩል የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ፣ አገራቸው ሰባት ነጥብ ያለው ዕቅድ፣ በኳታር አደራዳሪዎች አማካኝነት ለአሜሪካ ልካ ምላሽ እየጠበቀች እንደሆነ አስታውቀዋል።

    ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን በሰባት ቀናት ውስጥ ለመክፈት ያቀረበችውን ሐሳብ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ውድቅ ማድረጋቸው ይታወሳል።