የተባበሩት አረብ ኤሚሬትስ (ዩኤኢ) ህወሓት እና አጋሮቹ በኢትዮጵያ የፌዴራል ኃይሎች ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን ገልጻ ድርጊቱን አወገዘች።
ኤሜሬትስ ይህንን ያለችው በአዲስ አበባ የሚገኘው ኤምባሲዋ ትናንት አርብ ምሽት በይፋዊ
የማኅበራዊ ድረ ገጹ ላይ ባጋራው መግለጫ ነው።
ህወሓት በትግራይ ክልል የሚገኙ ሦስት የአውሮፕላን ማረፊያዎችን መቆጣጠሩን እና በአጎራባች አፋር እና አማራ ክልሎች ወታደራዊ ግጭት መባባሱን አጥብቃ እንደምታወግዝ በዚሁ መግለጫ ላይ አስታውቃለች።
በኢትዮጵያ መንግሥት እና በህወሓት መካከል ረቡዕ ጦርነት የተቀሰቀሰ ሲሆን በአማራ እና በአፋር ክልሎች ውጊያዎች እየተካሄዱ መሆኑ ተዘግቧል።
ህወሓትም ይሁን የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ለተፈፀመባቸው ጥቃት ምላሽ እየሰጡ እንደሆነ በመግለፅ ተወነጃጅለዋል።
የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሼክ ሻክቡት ቢን ናህያን አል ናህያን፣ እነዚህ ክስተቶች የኢትዮጵያን አንድነት፣ ሉዓላዊነት እንዲሁም ጸጥታና መረጋጋት አደጋ ላይ የሚጥሉ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ሚኒስትሩ ዩኤኢ ከኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ ጎን ሙሉ በሙሉ እንደምትቆም ገልጸው፣ በኃይል ወይም በትጥቅ ትግል የኢትዮጵያን ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ለመቀየር የሚደረግ ማንኛውንም ጥረት እንደማትደግፍ ገልጻለች።
ዩኤኢ ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት፣ የግዛት አንድነት፣ ጸጥታ፣ ደኅንነትና መረጋጋት የማያቋርጥ ድጋፏን እንደምትሰጥ ሼክ ሻክቡት ገልጸዋል።
ዩናይትድ ኪንግደም፣ ፈረንሳይ እና አሜሪካ እንዲሁ ህወሓትበአጎራባች ክልሎች እና በደቡብ ትግራይ ፈፀመ ያሉትን ጥቃት እና በትግራይ ክልል ያሉ አየር ማረፊያዎችን መቆጣጠሩን አውግዘዋል።
በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኧርቪን ማሲንጋ ረቡዕ መስከረም 13/2019 ዓ.ም. በሰሜን ኢትዮጵያ ዳግም የተቀሰቀሰውን ጦርነት በተመለከተ የህወሓት አመራሮችን "መጠነ ሰፊ ጥቃት በመክፈት" ወቅሰዋል።
ፈረንሳይ እና ዩናይትድ ኪንግደም ዳግም የተቀሰቀሰውን የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት አስመልክተው ሐሙስ መስከረም 14/2019 ዓ.ም በተናጠል ባወጧቸው መግለጫዎች የህወሓትን ድርጊት ኮንነዋል።
የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ችግሮች በውይይትና በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ቅድሚያ መሰጠት እንዳለበት ገልጸዋል።
ሚኒስትሩ በተጨማሪም ግጭቱ በአስቸኳይ እንዲቆም እና የተባባሰው ውጥረት እንዲረግብ አሳስበዋል።
በተጨማሪም ሰላማዊ ሰዎችን መጠበቅ፣ ተጨማሪ ጥቃትና ግጭት እንዳይፈጠር መከላከል እንዲሁም የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነትን ማክበር አስፈላጊ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
ዩኤኢ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋትን ለማረጋገጥ የሚደረጉ ጥረቶችን ሁሉ እንደምትደግፍ ሼክሻክቡት አረጋግጠዋል።
በተለይም የኢትዮጵያ ደኅንነትና መረጋጋት እንዲጠበቅ እና በአፍሪካ ቀንድ ደኅንነትን የሚያሰጋ ተጨማሪ ግጭት እንዳይፈጠር ጥረቶች እንደሚጠናከሩ አሳውቀዋል።
የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ማሕሙድ አሊ ዩሱፍ በሰሜን ኢትዮጵያ የተቀሰቀሰው ውጥረት እና ወታደራዊ መካረር "እጅግ እንዳሳሰባቸው" ገልጸው፤ ግጭቱ "በአፋጣኝ እንዲቆምም" አሳስበው ነበር።
የህወሓት ከፍተኛ አመራር እና የክልሉ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አማኑኤል አሰፋ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ በሰጡት ምላሽ በመግለጫዎቹ "ማዘናቸውን" ገልጸዋል።
አቶ አማኑኤል፤ የአሜሪካ አምባሳደር እንዲሁም የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽነር በትግራይ ውስጥ ሰላማዊ ሰዎች ላይ ጉዳት ያደረሱ የአየር ጥቃቶች ሲፈጸሙ በዝምታ ቆይተው አሁን የሰነዘሩት ወቀሳ "ፍትሐዊ አይደለም" ብለዋል።
የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው ውጥረት መባባሱ "እጅግ እንዳሳሰበው" የገለጸ ሲሆን፣ የአውሮፓ ኅብረትም በሰሜን ኢትዮጵያ በፍጥነት እየተባባሰ ያለው ሁኔታ እና ይህ ሁኔታ በሕዝቡ ላይ እያሳደረ ያለው ተጽዕኖ በጥልቅ እንደሚያሳስበው አስታውቋል።
"ውጥረቱን በአስቸኳይ ማርገብ ያስፈልጋል" ያለው የአውሮፓ ኅብረት፣ ሁለቱም አካላት ግጭትን በዘላቂነት ለማቆም ለተደረሰው ስምምነት ዳግም ቁርጠኝነታቸውን እንዲያሳዩ ጠይቋል። ለዚህም "ጊዜው አልረፈደም" ብሏል።