ቀጥታ, ቱርክ፣ ኢራቅ እና ጆርጂያ የኢራን አየር መንገዶች በግዛታቸው በረራ እንዳያካሂዱ አገዱ

በቀጣይ ቀናት ውስጥ ሁሉም የኢራን አየር መንገዶች ዓለም አቀፍ በረራ ማከናወን እንደማይችሉ የአሜሪካ ግምጃ ቤት ኃላፊ ስኮት ቤሳንት መግለጻቸውን ተከትሎ ቱርክ፣ ኢራቅ እና ጆርጂያ የኢራን አየር መንገዶች ወደ ግዛታቸው እንዳይገቡ አግደዋል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. ትራምፕ የተመድ በጀት በ15 በመቶ መቀነሱን እና በሺዎች የሚቆጠሩ ሰራተኞቹ መሰናበታቸውን ተናገሩ

    የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ መንግሥታቸው ከሌሎች በርካታ አገራት ጋር በመተባበር በመንግሥታቱ ድርጅት ታሪክ እጅግ ሰፊ የሆነ ማሻሻያ ማድረጉን አስታወቁ።

    ትራምፕ ዛሬ በተጀመረው የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር የድርጅቱ በጀት በዘንድሮው የአውሮፓውያኑ ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ 15 በመቶ መቀነሱን እና ከ4000 በላይ ሰራተኞቹም እንደተሰናበቱ ተናግረዋል።

    ድርጅቱ "አስደናቂ አቅም" እንዳለው የጠቀሱት ፕሬዚደንቱ፣ ነገር ግን የግራ ዘመሞችን "አጀንዳ መሸከም" ማቆም አለበት ብለዋል።

    ትራምፕ በሁለተኛው የሥልጣን ዘመናቸው ትላልቅ እርምጃዎችን የወሰዱ ሲሆን ከእነዚህ መካከል አሜሪካን ከበርካታ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች አባልነት ማስወጣት ይገኝበታል።

    የፕሬዚደንቱ እርምጃ ካረፈባቸው 66 ተቋማት መካከል ግማሽ ያህሉ ከመንግሥታቱ ድርጅት ጋር የተገናኙ ናቸው።

    በወቅቱ ዋይት ሃውስ በሰጠው መግለጫ እርምጃው የተወሰደው ተቋማቱ "ለአሜሪካ ጥቅም የሚሰሩ" ባለመሆናቸው እና "ውጤታማ ያልሆኑ ወይም ድብቅ አጀንዳዎችን ስለሚያራምዱ" እንደሆነ ገልጿል።

  2. አፍሪካ በተመድ የጸጥታ ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራት ዋና ጸሐፊው ጠየቁ

    የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ አፍሪካ በመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታ ምክር ቤት ውስጥ ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራት ጠየቁ።

    ዋና ፀሐፊው ይህን ያሉት ዛሬ በተጀመረው የተመድ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ የመክፈቻ ንግግር ባደረጉበት ወቅት ነው።

    ጉቴሬዝ በንግግራቸው አፍሪካ ቢያንስ አንድ ቋሚ መቀመጫ ሊሰጣት እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥተዋል።

    “ በ21ኛው ክፍለ ዘመን የፀጥታው ምክር ቤት የአፍሪካ ቋሚ ውክልና አለመኖር ኢ ፍትሃዊ እና ምክንያታዊ ያልሆነ ነው” ሲሉ መቀየር እንዳለበት አሳስበዋል።

    ዋና ፀሐፊው ባለፈው ዓመትም “ከ1945 በኋላ ብዙ የዓለም እውነታ ተቀይሯል፤ ይሁን እንጂ የፀጥታው ምክር ቤት ስብጥር ጉልህ ለውጥ ሳያሳይ እንደቀጠለ ነው” ሲሉ ተመሳሳይ ጥሪ አቅርበው ነበር።

    የፀጥታው ምክር ቤት አራት ቋሚ አባላት ያሉት ሲሆን እነዚህም ቻይና፣ ፈረንሳይ፣ ሩሲያ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና አሜሪካ ናቸው።

    በዚህም የአፍሪካ ክፍል በቅኝ ግዛት ሥር በነበረበት በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የነበረውን እውነታ አሁንም ያንፀባርቃል በሚል ምክር ቤቱ ለረዥም ጊዜ ሲተች ቆይቷል።

    ምክር ቤቱ የተለያዩ የዓለም ቀጣናዎችን የሚወክሉ አስር ቋሚ ያልሆኑ አባላት ቢኖሩትም እንደ አምስቱ ቋሚ መቀመጫ እንዳላቸው አገራት ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት የላቸውም።

    የአፍሪካ ሕብረት በምክር ቤቱ ውስጥ ሁለት ቋሚ ተወካዮች እና ተጨማሪ ሁለት ቋሚ ያልሆኑ ተወካዮች እንዲኖሩት ለረዥም ጊዜ ግፊት ሲያደርግ ቆይቷል።

    የፀጥታው ምክር ቤት አገራት፣ ተቋማት እና ግለሰቦች ላይ ዓለም አቀፍ ማዕቀቦችን መጣል፣ የሰላም ማስከበር ስምሪቶችን መፍቀድ፣ እንዲሁም ለግጭቶች ተመድ ምን ዓይነት ምላሽ መስጠት አለበት የሚለውን የመወሰን ሥልጣን አለው።

  3. ሳዑዲ በየመን በፈፀመችው ጥቃት ከ20 በላይ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸው እና መቁሰላቸው ተገለጸ

    ሳዑዲ አረቢያ ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ በየመን በፈፀመችው ጥቃት ከ20 በላይ ሰላማዊ ሰዎች እንደተገደሉ እና ጉዳት እንደደረሰባቸው የየመን ሁቲዎች እና ከቡድኑ ጋር ግንኙነት ያለው ሚዲያ አስታወቁ።

    የሁቲ ጦር ቃል አቀባይ ሳዑዲ አረቢያ ግጭቱ ከተባባሰ ወዲህ ከ900 በላይ የአየር እና የሚሳዔል ጥቃቶችን በይዞታቸው ላይ መፈፀሟን ተናግረዋል።

    በዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ዘንድ እውቅና ያለው የየመን መንግሥት በበኩሉ ቡድኑ ለተፈፀመበት ጥቃት አፀፋ ለመስጠት በላህጂ ግዛት በገበያ ሥፍራ ላይ በፈፀመው ጥቃት ሰላማዊ ሰዎች ተጎድተዋል ሲል ከስሷል።

    ሁቲዎች ግን የሳዑዲ ጥቃት የየመን ሰላማዊ ሰዎችን ዒላማ ያደረገ እንደሆነ ጠቅሰው፣ ግጭቱ ከተቀሰቀሰ ወዲህ የሚፈፀመው ጥቃት መባባሱን ገልጸዋል።

    ታጣቂ ቡድኑን የምትደግፈው ኢራንም ሳዑዲ አረቢያ በሁቲ ግዛቶች ላይ የምትፈፅማቸውን ጥቃቶች እንድትታቆም አሳስባለች።

  4. አሜሪካ ከኢራን ጋር ለመነጋገር ዝግጁ መሆኗን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ተናገሩ

    የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ በኒው ዮርክ በሚካሄደው የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባዔ ጎን ለጎን ከኢራን ባለሥልጣናት ጋር ለመነጋገር ዝግጁ መሆናቸውን ገለጹ።

    ሩቢዮ "አሁን ላይ ምንም ነገር የታቀደ አይመስለኝም ፤ ነገር ግን ለእንዲህ ዓይነት ውይይት በእርግጠኝነት ዝግጁ ነን። በተለይ ተገናኝቶ መነጋገሩ አዎንታዊ ውጤት ካመጣ እና በመጨረሻም ዋናውን ዓላማ የማሳካት ተስፋ ካለ” ብለዋል።

    ሚኒስትሩ ዋና ዓላማ ሲሉ የገለጹት ኢራን የኒውክሌር የጦር መሣሪያ መታጠቅ እንዳትችል ማረድግን ነው።

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራቅቺ ሰኞ ዕለት ጀመርው በኒው ዮርክ የሚገኙ ሲሆን ማስዑድ ፔዝሽኪያንም ለጠቅላላ ጉባኤው ወደ ኒውዮርክ ተጉዘዋል።

    ከሁለት ቀናት በፊት ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ከኢራኑ ፕሬዚደንት ማስዑድ ፔዝሽኪያን ጋር ለመገናኘት ዝግጁ መሆናቸውን ለፎክስ ኒውስ ተናግረው ነበር።

    ጠቅላላ ጉባኤው ዛሬ የተጀመረ ሲሆን የኢራን ተወካዮች ንግግር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።

  5. በቱርክ በትምህርት ቤት አቅራቢያ በተፈፀመ ጥቃት 11 ሰዎች ተጎዱ

    በቱርክ በትምህርት ቤት አቅራቢያ በተከፈተ ተኩስ 11 ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን ፖሊስ አስታወቀ።

    ማክሰኞ ጠዋት ላይ አንድ መሣሪያ የታጠቀ ግለሰብ በከፈተው ተኩስ ከተጎዱት መካከል ሁለቱ በአስጊ ሁኔታ ውስጥ መሆናቸው ተገልጿል።

    ጥቃቱ የተፈፀመው በምዕራባዊ ማኒሳ ግዛት በሚገኝ ኢንሲ ኡዝሜዝ በተባለ የሙያ እና የቴክኒክ ትምህርት ቤት አቅራቢያ ሲሆን ጉዳት የደረሰባቸው ሁሉም ተማሪዎች ናቸው ተብሏል።

    ጥቃቱን በመፈፀም የተጠረጠረው የ15 ዓመት ታዳጊ በቁጥጥር ሥር መዋሉን ፖሊስ ገልጿል።

    ተጠርጣሪው የጦር መሣሪያ ይዞ ጭር ባለ መንገድ ወደ ትምህርት ቤቱ ሲራመድ እና ተመልሶ በሩጫ ሲያመልጥ ከደኅንነት ካሜራ የተገኙ ተንቃሰቃሽ ምሥሎች አሳተይዋል።

    የተጠርጣሪው እናት፣ አባት እና የመሣሪያው ባለቤት እንደሆኑ የተገለፁት አያትም ከክስተቱ ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የአገሪቷ የፍትሕ ሚኒስትር አኪን ጉርሌክ ተናግረዋል።

    የጥቃቱ ዓላማ ምን እንደሆነ እስካሁን ግልጽ አይደለም።

    የአገሪቷ የትምህርት ሚኒስቴር “ክስተቱ አገራችንን በተለይም የትምህርት ማኅበረሰቡን እጅግ ያሳዘነ ነው” ብሏል።

    ሚኒስቴሩ ጨምሮም ሦስት ብሔራዊ መርማሪዎች ወደ ማኒሳ ግዛት መላካቸውን ገልጿል።

    በቱርክ በዚህ ዓመት ብቻ በትምህርት ቤት ላይ ጥቃት ሲፈፀም ይህ ሦስተኛው ነው።

    የአሁኑ ጥቃት የተፈፀመው መንግሥት እየጨመረ የመጣውን መሰል ጥቃት ለማስቆም እየታገለ ባለበት ወቅት ነው።

  6. የአሜሪካ ዋነኛ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ለትራምፕ እንቅስቃሴ ሽፋን መስጠታቸውን አቋረጡ

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሲኤንኤን፣ ፖለቲኮ እና ኤምኤስ ናው መገናኛ ብዙኃን ዋይት ሐውስ ገብተው እንዳይዘግቡ የጣሉትን ዕገዳ በመቃወም ዋነኛ የአሜሪካ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ለፕሬዝዳንቱ የሚሰጡትን ሽፋን አቋረጡ።

    ትራምፕ አርብ ዕለት እገዳውን ሲያሳውቁ፣ መገናኛ ብዙኃኑ ስለ አስተዳደራቸው “የፈጠራ ወይም የውሸት” ዘገባዎችን እያቀረቡ ነው ሲሉ ከስሰዋል። የዜና ተቋማቱ በበኩላቸው፣ ዘጋቢዎቻቸው ቅዳሜ ዕለት ወደ ዋይት ሐውስ እንዳይገቡ መከልከላቸውን ገልጸዋል።

    ሦስቱ የአሜሪካ የዜና ተቋማት በመቀጠል፣ “መንግሥት ፕሬሱ ምን እንደሚዘግብ አይወስንም የሚለውን መርኅ ለማስከበር” በትራምፕ አስተዳደር ላይ ክስ እንደሚመሠርቱ አስታውቀዋል።

    ዋነኞቹ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ለትራምፕ ሽፋን ላለመስጠት መወሰናቸውን ተከትሎ የፕሬዝዳንቱ ጽህፈት ቤት “ትራምፕ ቲቪ” የተባለ የራሱን በኢንተርኔት የሚተላለፍ ቻናል ጀምሯል፤ ይህም ስለ ፕሬዝዳንቱ ያለማቋረጥ ለ24 ሰዓታት ቪዲዮዎችን የሚያስተላልፍ ነው።

    ሌሎችም በርካታ የአሜሪካ የዜና ተቋማት በጋራ በሚደረጉ የፕሬዝዳንቱ ዘገባዎች ላይ እንደማይሳተፉ አስታውቀዋል። ከእነዚህ መካከል ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ እና ዘ ዋሽንግተን ፖስት ከትራምፕ ዝግጅቶች የሚገኙ ፎቶዎችን እንደማያጋሩ አሳውቀዋል።

    በዚህ ምክንያት ትራምፕ በፕሬዝዳንታዊ አውሮፕላናቸው ሲሳፈሩ ወይም በተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ለመሳተፍ ኒው ዮርክ ሲደርሱ የሚያሳይ ምንም ቪዲዮ በቴሌቪዥን ጣቢያዎች አልቀረበም።

    ትራምፕ በዋይት ሐውስ ደቡባዊ መስክ ላይ በተገነባው አዲስ ሄሊኮፕተር ማረፊያ ምረቃ ላይ የተገኙ ሲሆን፣ ዝግጅቱ በአዲሱ የዋይት ሐውስ ድረ-ገጽ ላይ በቀጥታ ተላልፏል፣ ሆኖም የፕሬዝዳንቱ ንግግር በግልጽ አልተሰማም።

  7. የግንባታ ሠራተኞች በቆረጡት ኬብል ምክንያት በአሜሪካ ውስጥ በረራዎች ተስተጓጎሉ

    በአሜሪካ ውስጥ የግንባታ ሠራተኞች ለአየር ትራፊክ ቁጥጥር አስፈላጊ የሆነ ኬብል በስህተት በመቁረጣቸው በአገሪቱ በሚገኙ ዋና ዋና አየር ማረፊያዎች በመቶዎች የሚቆጠሩ በረራዎች እንዲዘገዩ ምክንያት ሆነ።

    በዚህም የተነሳ ሰኞ ከሰዓት በኋላ በኒው ዮርክ፣ ፔንስልቬኒያ፣ ኒው ጀርሲ እና ማሳቹሴትስ በሚገኙ አየር ማረፊያዎች ውስጥ የሚካሄዱ በረራዎች ዘግይተዋል።

    የአሜሪካ ትራንስፖርት ሚኒስትር ሴን ዳፊ ኬብሉ መጠገኑን እና አየር ማረፊያዎቹ ወደ መደበኛ ሥራቸውን እንደሚመለሱ የገለጹ ቢሆንም፣ አሁንም መዘግየቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ አስጠንቅቀዋል።

    ይህ በአሜሪካ ምሥራቃዊ ክፍል የተፈጠረው ከፍተኛ የበረራ መስተጓጎል ዛሬ ማክሰኞ በኒው ዮርክ ከሚካሄደው የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ አስቀድሞ የተፈጠረ ሲሆን፣ ለጉባኤው በርካታ የዓለም መሪዎች በከተማዋ አካባቢ ወዳሉ አየር ማረፊያዎች ይደርሳሉ ተብሎ ይጠበቃል።

    የአሜሪካ የትራንስፖርት ባለሥልጣናት እንዳሉት፣ የተቆረጠረው ኬብል የበረራ መቆጣጠሪያ ሥርዓትን ጎድቶታል። ይህ ሥርዓት አውሮፕላኖችን በሚነሱበት እና በሚያርፉበት ጊዜ ደኅንነታቸው በተጠበቀ ሁኔታ ለመምራት ይጠቅማል።

    የኒው ጀርሲ የሕዝብ ማመላለሻ ተቋም የቢቢሲ የአሜሪካ አጋር ለሆነው ሲቢኤስ ኒውስ እንደገለጸው፣ በቁፋሮ ቦታው የነበሩ ምልክቶች በተሳሳተ ሁኔታ ተቀምጠው ስለነበረ የግንባታ ሠራተኞቹ መስመሩን በስህተት ቆርጠውታል።

  8. ዩኬ ለሳዑዲ አረቢያ “ወታደራዊ ድጋፍ” እንደምትሰጥ አስታወቀች

    የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር አንዲ ቡርንሀም አገራቸው ለሳዑዲ አረቢያ ወታደራዊ ድጋፍ እንደምትሰጥ አስታወቁ።

    በኢራን በሚደገፉት የሁቲ አማጽያን ጥቃት የተሰነዘረባትን ሳዑዲ ለመርዳት በበረራ ላይ ላሉ አውሮፕላኖች ነዳጅ የመሙላት አገልግሎት እንደሚሰጥ ተናግረዋል።

    ወታደራዊ ድጋፉ በቀጣይ ቀናት እንደሚጀመር ተገልጿል። በቆጵሮስ በሚገኘው ራፍ የዩኬ የጦር ሰፈር የሚገኝ አንድ የእንግሊዝ አውሮፕላን በወታደራዊ ድጋፉ እንደሚካተትም ተመልክቷል።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደተናገሩት ሳዑዲ አረቢያ ወታደራዊ ድጋፍ እንዲደረግላት ጠይቃለች። ከመከላከያ ሚኒስትሩ ዌስ ስተርሊንግ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ኤድ ሚሊባንድ በተሰጣቸው ምክር መሠረት ጥያቄውን ለመቀበል መወሰናቸውን ተናግረዋል።

    ወታደራዊ ድጋፉ “ለሳምንታት” ሊዘልቅ እንደሚችል ተገልጿል።

  9. ኢራን ሁቲዎችን “ማስታጠቅ እና መደገፍ” እንድታቆም የቡድን ሰባት አገራት አሳሰቡ

    ኢራን ሁቲዎችን “ማስታጠቅ እና መደገፍ” ማቆም አለባት ሲሉ የቡድን ሰባት አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በጋራ ባወጡት መግለጫ አሳሰቡ።

    በየመን ሁቲ ታጣቂዎች በሳዑዲ አረቢያ ላይ የተፈጸሙ ጥቃቶችን “እጅግ እናወግዛለን” ሲሉም በመግለጫው አቋማቸውን አስታውቀዋል።

    በየመን በሳዑዲ ከሚደገፉ የመንግሥት ኃይሎች ጋር በቅርቡ እየተባባሰ የመጣው ውጊያ ለቀጣናው እንዲሁም ለዓለም አቀፍ የኃይል አቅርቦት ዘርፍም አስጊ እንደሆነ ገልጸዋል።

    በኢራን የሚደገፉት ሁቲዎች በቀይ ባሕር አቅራቢያ ግዛቶችን መያዛቸውን ተከትሎ ባለፉት ጥቂት ቀናት ውስጥ በሺህዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ከየመን ሸሽተው ወጥተዋል።

    የቡድን ሰባት አገራት መግለጫውን ያወጡት በኒው ዮርክ ከሚካሄደው የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባዔ አስቀድሞ ነው። በጉባዔው የኢራን ተወካዮች ንግግር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።

    የዩናይትድ ኪንግደም፣ ካናዳ፣ ፈረንሳይ፣ ጣልያን፣ ጃፓን እና አሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በጋራ ባወጡት መግለጫ “ሁቲዎች በአፋጣኝ ሁሉንም ወታደራዊ እንቅስቃሴ እንዲያቆሙ እንጠይቃለን” ብለዋል።

    “የመርከብ ጉዞዎች ላይ የሚደርስ ጥቃት እና ዛቻ እንዲገታ እና ወደ ፖለቲካዊ የንግግር ሒደት መመለስ እንዲቻል” ሲሉም አሳስበዋል።

  10. ቱርክ፣ ኢራቅ እና ጆርጂያ የኢራን አየር መንገዶች በግዛታቸው በረራ እንዳያካሂዱ አገዱ

    በቀጣይ ቀናት ውስጥ ሁሉም የኢራን አየር መንገዶች ዓለም አቀፍ በረራ ማከናወን እንደማይችሉ የአሜሪካ ግምጃ ቤት ኃላፊ ስኮት ቤሳንት መግለጻቸውን ተከትሎ ቱርክ፣ ኢራቅ እና ጆርጂያ የኢራን አየር መንገዶች ወደ ግዛታቸው እንዳይገቡ አግደዋል።

    የኢራኑ ማህን ኤር አየር መንገድ እንዳለው ወደ ቱርክ በረራ እንዳያካሂድ ታግዷል።

    ኤኤፍፒ ያነጋገራቸው ሁለት ምንጮች ኢራቅ የኢራን አየር መንገዶችን በረራ መሰረዟን አስታውቀዋል። ጆርጂያም ተመሳሳይ እርምጃ ወስዳለች።

    ከሁለት ሳምንት በፊት የአሜሪካ ግምጃ ቤት 27 የኢራን አየር መንገዶች ላይ ማዕቀብ ጥሏል።

    የአሜሪካ መንግሥት ኢራን ላይ የምጣኔ ሃብት ጫና ለማሳደር ባንኮች፣ የንግድ ተቋማት፣ የቴክኖሎጂ እና በረራ ዘርፎች ላይ ማዕቀብ እንደሚጥል ከሳምንታትበፊት ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

    የአሜሪካ ግምጃ ቤት ኃላፊ ስኮት ቤሳንት በኢራን አየር መንገዶች ላይ የተጣለው ዓለም አቀፍ እገዳ በቀጣይ ሁለት ቀናት እንደሚተገበር ለሲኤንቢኢ ተናግረዋል።

    የኢራን አየር መንገዶች በመላው ዓለም ማንኛውንም ዓይነት እንቅስቃሴ ለማድረግ እንደማይችሉ አስታውቀዋል።

    የኢራን ንብረት የሆኑ አውሮፕላኖች “በአየር መንገዳችሁ ቢያርፉ ነዳጅ መስጠት አትችሉም፤ የአየር መንገድ አገልግሎት ልትሰጧቸውም አትችሉም፤ ትኬት መሸጥም ክልክል ነው” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

    ይህንን የሚጥሱ አገራት “ከዶላር ግብይት ሥርዓት ውጪ እንደሚደረጉም” አስታውቀዋል።

    የኢራን አየር መንገዶች በአሜሪካ በተጣለባቸው እገዳ ምክንያት ለዓመታት ሲፈተኑ ቆይተዋል። አውሮፕላኖች እንዲሁም መለዋወጫዎች የመግዛት እና ጥገና የማድረግ አቅማቸው ተገድቧል።

    ባለፉት ጥቂት ወራት ወደ ኢራን የሚደረጉ የውጭ አገራት በረራዎች ተሰርዘዋል።

    ከኢራን ጋር የሚደረገው ውጊያ እስከመቼ እንደሚቀጥል እንደማያውቁ የተናገሩት የአሜሪካ ግምጃ ቤት ኃላፊ፤ ማዕቀቡን በተመለከተ ከቻይና ጋር መወያየታቸውን ገልጸዋል።

    የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂንግፒንግ ከአንድ ቀን በኋላ ወደ አሜሪካ ተጉዘው በተለያዩ ጉዳዮች ዙርያ ከፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር ይመክራሉ።

    የሁለቱ አገራት መሪዎች ኢራን ላይ ስለተጣለው ማዕቀብ እንዲወያዩ ለማመቻቸት የቻይና ምክትል ፕሬዝዳንት ዋንግ ይ እና የአሜሪካ ግምጃ ቤት ኃላፊ ስኮት ቤሳንት እንደሚነጋገሩ ተገልጿል።

  11. በጃፓን በተከሰተ አውሎ ንፋስ ምክንያት 2 ሚሊዮን ሰዎች ከአካባቢያቸው እንዲወጡ ትዕዛዝ ተሰጠ

    በጃፓን በተከሰተ ከባድ አውሎ ንፋስ ምክንያት ወደ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ከሚኖሩበት አካባቢ ለቅቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ ተላለፈ።

    ዱጁዋን የተባለው ዝናብ የቀላቀለው ከባድ አውሎ ንፋስ በተለያዩ የጃፓን ግዛቶች ጉዳት እንደሚያስከትል ተገልጿል።

    የጃፓን የሜትሮሎጂ ኤጀንሲ ከባዱ አውሎ ንፋስ “ሕይወትን አደጋ ላይ እንደሚጥል” አስታውቋል። በተለያዩ አካባቢዎች የተሰጠው ማስጠንቀቂያ እየለዘበ ቢመጣም በኦሺማ ከተማ አውሎ ንፋሱ ለሰዎች ሕይወት አስጊ ነው ተብሏል።

    ከፍተኛ መጠን ያለው ንፋስ በመነሳቱ ከ50,000 በላይ ሰዎች መብራት ተቋርጦባቸዋል። በመቶዎች የሚቆጠሩ በረራዎች እና የባቡር ጉዞዎችም ተሰርዘዋል።

    አውሎ ንፋሱ በከፍተኛ ኤል ኒኖ ምክንያት እንደተነሳ እና የንፋሱ ፍጥነት በሰዓት እስከ 130 ኪሎሜትር እንደሚደርስ ተገልጿል።

    ከፍተኛ ዝናብ እንዲሁም የመሬት መንሸራተት እንደሚከሰት ማስጠንቀቂያዎች ተሰጥተዋል።

    ዱጁዋን በጃፓን ዘንድሮ የተከሰተ 25ኛው አውሎ ንፋስ ነው። በርካታ መሰናዶዎች እንዲሰረዙም ምክንያት ሆኗል።

  12. አሜሪካ አደንዛዥ ዕፅ ጭነዋል ባለቻቸው ጀልባዎች ላይ ያደረሰችው ጥቃት ሰብአዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል መሆኑን ተመድ ገለጸ

    አሜሪካ አደንዛዥ ዕፅ ጭነዋል ባለቻቸው ጀልባዎች ላይ ያደረሰችው የአየር ጥቃት ዓለም አቀፍ ሕግን እንደሚጥስ እና ሰብአዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል ተደርጎ እንደሚቆጠር የተባበሩት መንግሥታት ባወጣው ሪፖርት አስታወቀ።

    የተመድ ልዩ ልዑክ ቤን ሳውል ያዘጋጁት ሪፖርት እንደሚያሳየው፤ ካለፈው ዓመት መስከረም ጀምሮ በካሪቢያን እና በፓስፊክ ውቅያኖስ አሜሪካ ቢያንስ 68 ጥቃቶች ፈጽማለች።

    አሜሪካ ከግዛቷ ውጭ በሆኑት አካባቢዎች ባደረሰችው ጥቃት ከ220 በላይ ሰዎች ተገድለዋል።

    የተመድ ባለሙያ እንደተናገሩት፤ ዒላማ የተደረጉት ሰዎች የአሸባሪ ቡድን አባላት ናቸው በሚል የተለዩ ቢሆንም እንኳን በአሜሪካ ላይ ጥቃት አልፈጸሙም። ስለዚህም አሜሪካ በዓለም አቀፍ ሕግ ሥር ራሷን የመከላከል መብቷን መተግበር አትችልም።

    ከሁለት ቀናት በፊት የአሜሪካ ጦር በካሪቢያን በሚጓዝ ጀልባ ላይ ባደረሰው ጥቃት ሁለት ሰዎች መገደላቸውን አስታውቋል።

    በቀጣናው የአሜሪካን ኃይሎች የሚመራው ሳውዝኮም “ጀልባዎቹ አደንዛዥ ዕፅ እያዘዋወሩ እንደነበር የተረጋገጠ የደኅንነት መረጃ ይጠቁማል” ብሏል።

    የተመድ የሰብአዊ መብቶች ካውንስል በበኩሉ “እንዲህ ያሉ ጥቃቶች ከሕግ ውጭ ከሚፈጸሙ ግድያዎች ጋር ይስተካከላሉ” ብሏል።

    “በዓለም አቀፍ ሰብአዊ መብት፣ በዓለም አቀፍ ራስን የመከላከል መብት፣ በዓለም አቀፍ የባሕር ሕግ፣ በፀረ አደንዛዥ ዕፅ ድንጋጌ እና በዓለም አቀፍ ፀረ ሽብር ሕግ ተቀባይነት ስለሌላቸው በሕይወት የመኖር መብትን ይጋፋሉ” ሲልም አክሏል።

    አሜሪካ ባደረሰቻቸው 68 ጥቃቶች 223 ሰዎች መገደላቸው “በዓለም አቀፍ ሕግ ሰብአዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል” እንደሆነ የተመድ ሪፖርት ይጠቁማል።

    ቢቢሲ ከዋይት ሀውስ እና ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ምላሽ ጠይቋል።

  13. በሁሉም የኢራን አየር መንገዶች ላይ የተጣለው ማዕቀብ ከነገ ጀምሮ እንደሚተገበር ተገለጸ

    የአሜሪካ ግምጃ ቤት ኃላፊ ስኮት ቤሳንት ከነገ ጀምሮ “ሁሉም የኢራን አየር መንገዶች በረራ ማከናወን አይችሉም” ሲሉ አስታወቁ።

    ከሁለት ሳምንት በፊት የአሜሪካ ግምጃ ቤት 27 የኢራን አየር መንገዶች ላይ ማዕቀብ መጣሉ ይታወሳል።

    ከኢራን ጋር የሚደረገው ውጊያ እስከመቼ እንደሚቀጥል እንደማያውቁ የተናገሩት ኃላፊው፤ ማዕቀቡን በተመለከተ ከቻይና ጋር መወያየታቸውን ገልጸዋል።

    የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂንግፒንግ ከሁለት ቀናት በኋላ ወደ አሜሪካ ተጉዘው በተለያዩ ጉዳዮች ዙርያ ከፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር ይመክራሉ።

    የሁለቱ አገራት መሪዎች ኢራን ላይ ስለተጣለው ማዕቀብ እንዲወያዩ ለማመቻቸት የቻይና ምክትል ፕሬዝዳንት ዋንግ ይ እና የአሜሪካ ግምጃ ቤት ኃላፊ ስኮት ቤሳንት እንደሚነጋገሩ ተገልጿል።

    የአሜሪካ መንግሥት ኢራን ላይ የምጣኔ ሃብት ጫና ለማሳደር ባንኮች፣ የንግድ ተቋማት፣ የቴክኖሎጂ እና በረራ ዘርፎች ላይ ማዕቀብ እንደሚጥል ከሳምንታት በፊት ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

  14. ትራምፕ ወደ ዋይት ሀውስ እንዳይገቡ ያገዷቸው መገናኛ ብዙኃን ክስ ሊመሠርቱ ነው

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ዋይት ሀውስ እንዳይገቡ ያገዷቸው መገናኛ ብዙኃን ክስ እንደሚመሠርቱ አስታወቁ።

    ሲኤንኤን፣ ፖለቲኮ እና ኤምኤስ ናው ወደ ዋይት ሀውስ እንዳይገቡ በፕሬዝዳንቱ የታገዱት ባለፈው ሳምንት አርብ ነበር።

    ትራምፕ መገናኛ ብዙኃኑ ስለ አስተዳደራቸው “የፈጠራ እና ሐሰተኛ” መረጃ አውጥተዋል ሲሉ ወንጅለዋል።

    ቅዳሜ ዕለት ጋዜጠኞች ወደ ዋይት ሀውስ ለመግባት ሲሞክሩ እንዳልተፈቀደላቸው እና የይለፍ ካርዳቸውን እንደተነጠቁ መገናኛ ብዙኃኑ ገልጸዋል።

    ሦስቱ መገናኛ ብዙኃን ዛሬ በጋራ ባወጡት መግለጫ “የመጀመሪያው አንቀጽ የሚሰጠንን መብት ለማግኘት እና ይህ መንግሥት ጋዜጠኞች ምን እንደሚዘግቡ እንደማይወስን ለማሳየት ክስ እንከፍታለን” ብለዋል።

    የአገሪቱ ሕገ መንግሥት የመጀመሪያ አንቀጽ መንግሥት የመገናኛ ብዙኃንን ነጻነት እንዳያፍን ያግዳል።

    መገናኛ ብዙኃን በዘገባቸው ምክንያት መድልዎ እንዳይደርስባቸውም ከለላ ይሰጣል።

    መገናኛ ብዙኃኑ ባወጡት መግለጫ “ያለ ማስጠንቀቂያ ወይም ሒደቱን ሳይከተል ዋይት ሀውስ የጋዜጠኞቻችን ፈቃድ ሰርዟል” ብለዋል።

    አክለውም “ዝም ከተባለ የመገናኛ ብዙኃን ነጻነት እና ሕዝብ ነጻ መረጃ የማግኘት መብቱ በመንግሥት ይጣሳል” ብለዋል።

    ቢቢሲ ከዋይት ሀውስ ምላሽ ጠይቋል።

  15. በምዕራብ ወለጋ በታጣቂዎች ታግተው የነበሩ አሽከርካሪዎች መለቀቃቸውን ማኅበሩ ገለፀ

    በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን፣ ጊምቢ ከተማ አቅራቢያ በታጣቂዎች ታግተው የነበሩ የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች መለቀቃቸውን ማኅበሩ ለቢቢሲ ገለፀ።

    የኢትዮጵያ ከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ማኅበር ፕሬዝዳንት አቶ ሰለሞን ዘውዱ፣ እሑድ ጳጉሜ 1/2018 ዓ.ም. በተፈፀመው ጥቃት የታገቱ አሽከርካሪዎች መለቀቃቸውን ስለማረጋገጠቻው ተናግረዋል። የተለቀቁት የማኅበሩ አባላት የነበሩት የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ዘጠኝ መሆናቸውን አቶ ሰለሞን ገልፀዋል።

    የማኅበሩን አባላት ጨምሮ በወቅቱ የታገቱት አጠቃላይ ታጋቾች ቁጥር ከ13 እስከ 14 እንደሚደርስ አስታውሰው ሁሉም ስለመለቀቃቸው መረጃ የደረሳቸው መሆኑን ጠቅሰዋል።

    ታጋቾቹ እንዴት ሊለቀቁ እንደቻሉ ወይም ለታጣቂዎች ገንዘብ ተከፍሎ እንደሆነ የጠየቅናቸው አቶ ሰለሞን፣ ስለዚህ ጉዳይ መረጃ እንደሌላቸው ተናግረዋል።

    ታጣቂዎች ከሁለት ሳምንት በፊት ፈፀሙት በተባለው የምዕራብ ወለጋው ጥቃት ከዘጠኝ ያላነሱ ነዳጅ ጫኝ ከባድ ተሽከርካሪዎች ሙሉ በሙሉ እና በከፊል መቃጠላቸውን ቢቢሲ ከምንጮች እና ከሳተላይት ምሥል አረጋግጧል።

    ታጣቂዎቹ መኪኖቹን በተኩስ አስቁመው አሽከርካሪዎቹን አፍነው እንደወሰዷቸው እና ተሽከርካሪዎቹን በእሳት እንዳቀጣጠሉ ምንጮቻችን ገልፀዋል።

    የታገቱት አሽከርካሪዎች ከሁለት ሳምንታት ያህል እገታ በኋላ ከሦስት ቀናት በፊት ዓርብ መስከረም 8/2019 ዓ.ም መለቀቃቸውን ነው የኢትዮጵያ ከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ማኅበርፕሬዝዳንት አቶ ሰለሞን ዘውዱ የተናገሩት።

    አካባቢው “የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት እንዲሁም በይፋ የሚታወቅ ስም የሌላቸው በቡድን የተደራጁ ታጣቂዎች” የሚንቀሳቀሱበት እንደሆነ አንድ የአካባቢው የመንግሥት ባለሥልጣን የገለፁ ሲሆን፣ ለጥቃቱ ኃላፊነቱን የወሰደ አካል ግን የለም።

  16. የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የትግራይ ቴሌቪዥንን ማገዱን አስታወቀ

    የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የትግራይ ቴሌቪዥን “የአገርን እና የሕዝብን ደኅንነት”፣ “ብሔራዊ ጥቅምን አደጋ ላይ የሚጥሉ”፣ “ወደ ግጭት የሚገፋፉ” እንዲሁም “ጽንፈኝነትን የሚያበረታቱ መልዕክቶች” እያስተላለፈ መሆኑን በመግለጽ ማገዱን አስታወቀ።

    ባለሥልጣኑ ሰኞ መስከረም 11/2019 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ከዚህ በፊት የቴሌቪዥን ጣቢያው ታግዶ እንደነበር አስታውሶ፣ ህወሓት ከፌደራል መንግሥቱ ጋር የተፈራረመውን የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነትን ተከትሎ እገዳው ተነስቶለት እንደነበር ገልጿል።

    የትግራይ ቴሌቪዥን ላይ የተጣለው እገዳ ላልተወሰነ ጊዜ መሆኑን ጨምሮ አስታውቋል።

    ባለሥልጣኑ አክሎም የትግራይ ቴሌቪዥንን እንደ መረጃ ምንጭ መጠቀምም ሆነ የሚያሰራጫቸውን ዘገባዎች ማሰራጨት "በጥብቅ የተከለከለ" መሆኑን ጨምሮ ገልጿል።

    ህወሓት እና ሌሎች በአገሪቱ ስድስት ክልሎች የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች በዕሁድ ዕለት “ትብብር ለኅልውና” የሚል ጥምረት መመሥረታቸው ይታወሳል።

    የትብብሩ ምሥረታን በሚመለከት ሰብሳቢው ዘመነ ካሴ መግለጫውን በትግራይ መገናኛ ብዙኃን ላይ አንብቧል።

    ትብብሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መንግሥትን በመጣል "በሽግግር ቻርተር የሚመራ አካታች የሽግግር መንግሥት" ለመመሥረት ዓላማ እንዳለውም አስረድተዋል።

    የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ከዚህ ቀደም የአዲስ ስታንዳርድ እና የዋዜማ ሬዲዮን የምዝገባ ፈቃዶች የሰረዘ ሲሆን፣ የሮይተርስ ጋዜጠኞች የዘገባ ፈቃድም ከሰረዘ በኋላ በቅርቡ መልሶ ሰጥቷል።

  17. ኤምኤስኤፍ በጋምቤላ ውስጥ በርካታ የቆሰሉ ሰዎች ወደ ጤና ጣቢያው መምጣታቸውን አስታወቀ

    መንግሥታዊ ያልሆነው ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን (ኤምኤስኤፍ) በጋምቤላ ክልል ውስጥ በሚገኘው ኩሌ ጤና ጣቢያ በርካታ የቆሰሉ ሰዎችን እያከመ መሆኑን ገለጸ።

    ባለፈው አርብ መስከረም 8/2019 ዓ.ም. በክልሉ ኢታንግ ልዩ ወረዳ ውስጥ የተፈጸመ ጥቃትን ተከትሎ የተጎዱ ሰዎች ናቸው ወደ ጤና ጣቢያው የመጡት።

    ጤና ጣቢያው በጥቃቱ የተጎዱ 88 ሰዎችን የተቀበለ ሲሆን፣ ከመካከላቸውም ስምንቱ የሞቱ ሲሆን ሌሎች አራት ሰዎች ወደ ጤና ጣቢያው ከሄዱ በኋላ በሕክምናው ቡድን ሕይወታቸውን ለማትረፍ ጥረት ቢደረግም መትረፍ አለመቻላቸውን ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን አስታውቋል።

    ከከባድ እስከ ቀላል ጉዳት የደረሰባቸው የቀሩት ተጎጂዎች ሕክምና ማግኘታቸውን እና 13 ሰዎች ለተጨማሪ የሕክምና ድጋፍ ወደ ጋምቤላ ሆስፒታል መላካቸውን ቡድኑ ገልጿል።

    ናይሮቢ ኬንያ የሚገኙት የድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን የኢትዮጵያ ኃላፊ ጉል ባድሻህ “እኛ በዋናነት ቅድሚያ የምንሰጠው የተጎጂዎችን ማንነት ከግምት ውስጥ ሳናስገባ ለማንኛውም ሰው የሚያስፈልገውን የሕክምና ድጋፍ ነው" በማለት "የግጭቱ ተሳታፊዎች ለሰላማዊ ሰዎች ጥበቃ እንዲያደርጉ" ጥሪ አቅርበዋል።

  18. ኢራን በቴህራን የሚገኝ የፈረንሳይኛ ቋንቋ ማዕከልን መዝጋቷን ተከትሎ ፈረንሳይ የአጸፋ እርምጃ ለመውሰድ ዛተች

    ፈረንሳይ በቴህራን የሚገኘው የቋንቋ ትምህርት ቤቷ መዘጋቱን ተከትሎ የኢራንን አምባሳደር ጠርታ እንደምታነጋግር አስታወቀች።

    የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፓስካል ኮንፋቭሩክስ “ይህ ፈረንሳይ በኢራን ባላት የባሕል ማዕከል ላይ የተቃጣ ጥቃት በሐምሌ ወር በሁለት የኤምባሲ ሠራተኞቻችን ላይ ከተፈጸመው የቀጠለ ሲሆን ምክንያት እና ተቀባይነት የሌለው ነው” ብለዋል።

    እሁድ ዕለት የኢራን ባለሥልጣናት በቴህራን የሚገኝ የፈረንሳይ የቋንቋ ማዕከል በአቃቤ ሕግ ትዕዛዝ መሠረት መዘጋቱን አስታውቀዋል።

    ከኢራን የፍትህ ተቋማት ጋር በቅርበት የሚሰራው ሚዛን የዜና ወኪል “በቴህራን ከሚገኘው የፈረንሳይ ኤምባሲ ጋር ግንኙነት ያለው እና በማስተማር ሽፋን ለዓመታት ሲንቀሳቀስ የነበረው ሕገወጥ ማዕከል ተዘግቷል” ሲል ዘግቧል።

    የኢራን የፍትህ አካላት “ከዲፕሎማሲ ስምምነት ውጪ ያፈነገጠ ሕገወጥ ተግባር ላይ ተሰማርቷል” ሲል ወንጅሎታል።

    አክሎም ማዕከሉ "የቋንቋ ማሰልጠኛ ተቋምነቱን አላግባብ ተጠቅሟል" እንዲሁም "የአገሪቱን ታዋቂና ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች በመለየትና በመካከላቸው ትስስር በመፍጠር፣ ከአገር እንዲወጡም አመቻችቷል" ሲል ከስሷል።

    ፈረንሳይ የቀረቡባትን ውንጀላዎች ውድቅ አድርጋ ከቅርብ ወራት ወዲህ ተደጋጋሚ ትንኮሳዎች እንዳጋጠሟት አስታውቃለች።

    ከቅርብ ወራት ወዲህ በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ውጥረት እየተባባሰ መጥቷል።

    ባለፈው ወር ፈረንሳይ ወደ ኢራን ያቀኑ ሁለት ዲፕሎማቶቿ ለአጭር ጊዜ መታሰራቸውንና እንቅስቃሴያቸው መገደቡን ተከትሎ ሁለት የኢራን ዲፕሎማቶችን ከአገሯ አስወጥታለች።

    ቴህራን ዲፕሎማቶቹን በአገሪቱ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት ወንጅላቸዋለች።

  19. አሜሪካ እና ኢራንን ወደ ድርድር ለመመለስ ጥረቶች እየተደረጉ መሆናቸውን ኳታር ገለጸች

    በአሜሪካ እና በኢራን መካከል ንግግር ለመጀመር አደራዳሪ ቡድኑ ለሁለት ሳምንታት ለሚጠጋ ጊዜ በእቅዶች ላይ እየተወያየ መሆኑን ኳታር ገለጸች።

    የአገሪቷ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማጂድ አል አንሳሪ “ዋሽንግተንን እና ቴህራንን ወደ ድርድር ለመመለስ ለሁለት ሳምንት ለሚጠጋ ጊዜ የተለያዩ ሃሳቦችን እየተለዋወጥን ነው” ማለታቸውን የአገሪቷ መገናኛ ብዙኃን ዘግቧል።

    ኳታር ከፓኪስታን ጋር በመሆን ሁለቱን ወገኖች ስታደራድር ቆይታለች።

    “ድርድሩን መጀመር ይቻል እንደሆነ በአደራዳሪ ቡድናችን በኩል ከቴህራን እና ከዋሽንግተን ጋር እየሰራን ነው። አደራዳሪዎችም በዚህ ሒደት ላይ ለውጥ ለማምጣት እየተንቀሳቀሱ ነው።” ብለዋል አል አንሳሪ።

    ቃል አቀባዩ ጨምረውም አካባቢውን ለማረጋጋት እና እንደ የሆርሙዝ ወሽመጥ ያሉ የባሕር መስመሮችን ለመጠበቅ ዓለም አቀፍ መረዳትን ለማምጣት ቀጣናዊ መፍትሔ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

    "የባሕር መስመሮችን ከአንድ አገር ሉዓላዊነት ጋር ማያያዝ እና እንደ መሣሪያ መጠቀም ለሁላችንም አደገኛ ነው” ብለዋል።

    አሜሪካ በቅርቡ በኢራን ላይ ወታደራዊ ጥቃት ከፈፀመች በኋላ ወሽመጡን ሊያስከፍት ይችላል የሚል ተስፋ ተጥሎበት የነበረው ድርድር ተቋርጧል።

    ኢራንም ሳዑዲ አረቢያን ጨምሮ በአረብ አገራት በሚገኙ የአሜሪካ መሠረተ ልማቶ ችላይ ጥቃት በመፈፀም ምላሽ ሰጥታለች።

    የተወሰኑ ጥቃቶች በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጉዳት ያደረሱ ሲሆን በሲቪል መሠረተ ልማቶች ላይም ውድመትን አስከትለዋል።

    በጥቃቱ ዒላማ የሆኑ አገራትም ጥቃቱን አውግዘው ኢራን ይህንን ድርጊቷን እንድታቆም ጥሪ አቅርበዋል።

    የካቲት ወር ላይ አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ በከፈቱት ጦርነት ከ3000 በላይ ሰዎች መሞታቸውን ቴህራን አስታውቃለች። ኢራንም በወሰደችው የአፀፋ ጥቃት አሜሪካውያን እና እስራኤላውያን መገደላቸውን ገልጻለች።

    ኳታር አሁን ላይ ሁለቱን ወገኖች ወደ ድርድር ለመመለስ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የገለፀችው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በመካከለኛው ምሥራቅ ባለው ውጥረት ምክንያት በአካባቢው ለሚኖሩ ዜጎቹ እሁድ ዕለት የደኅንነት ማስጠንቀቂያ ካወጣ በኋላ ነው።

    ሚኒስቴሩ በቀጣናው የሚኖሩ ዜጎቹ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ እና ከቀጣናው ውጭ ያሉ ወይም በዚያ የሚያልፉም የሚያደርጉትን ጉዞ እንዲያጤኑ አሳስቧል።

    የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ፣ ኢራቅ እና ጆርዳንን ጨምሮ በቀጣናው ያሉ በርካታ የአሜሪካ ኤምባሲዎችም እሁድ ዕለት ተመሳሳይ ማስጠንቀቂያ አውጥተዋል።