ትራምፕ ከኢራን ጋር በሰፊው ውይይት መደረጉን ከገለጹ በኋላ ሩቢዮ “ተጨባጭ ለውጥ” ታይቷል አሉ

በሕንድ በይፋዊ የሥራ ጉብኝት ላይ የሚገኙት የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ የተወሰኑ መግባባቶች ላይ መድረሳቸውን ገልጸው “የመጨረሻው ባይሆንም ተጨባጭ ለውጦች ላይ ተደርሷል” ብለዋል። በሚቀጥሉት ጥቂት ሰዓታት ዓለም “ቢያንስ የሆርሙዝ ወሽመጥን በሚመለከት” መልካም ዜና ይሰማል ሲሉም ተናግረዋል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. በኢራን ድርድር የመጨረሻው ውሳኔ የማን ነው?

    የኢራን ፕሬዝዳንት መሱድ ፔዘሽኪያን

    የፎቶው ባለመብት, WANA/Reuters

    የምስሉ መግለጫ, የኢራን ፕሬዝዳንት የጠቅላይ መሪውን ፈቃድ ሳይጠይቁ የተኩስ አቅም ስምምነት ተቀብለዋል በሚል ትችት ቀርቦባቸዋል

    የኢራን ፕሬዝዳንት መሱድ ፔዘሽኪያን “የትኛውም ውሳኔ” ያለ የኢራን ሦስተኛ ጠቅላይ መሪ ሞጅታባ ኻሚኔ “ፍቃድ” አይወሰንም ብለዋል።

    ፕሬዝዳንቱ ይህን ያሉት ወግ አጥባቂ አመለካከት ያላቸው ኢራናዊ የፓርላማ አባል ካምራን ጋዛንፋሪ በሳምንቱ መጀመሪያ የተኩስ አቁም ስምምነቱን “ያለ ኻሚኔ ፍቃድ” ተቀብለዋል በማለት ከተቹ በኋላ ነው።

    የ56 ዓመቱ የኢራን አዲሱ ጠቅላይ መሪ ከተሾሙ ወዲህ በሕዝብ ፊት ታይተው አያውቁም። በአንፃሩ እንደ ኢራን መገናኛ ብዙኃን ገለፃ ጠቅላይ መሪው በርካታ የጽሑፍ መግለጫዎችን አስተላልፈዋል።

    ነገር ግን ፔዘሽኪያንን ጨምሮ በርካታ ከፍተኛ የኢራን ባለሥልጣናት በቅርብ ሳምንታት ከኻሚኔ ጋር ተገናኝተዋል ተብሏል።

    ኻሚኔ በጽሑፍ መልዕክቶቻቸው አሜሪካን እና እስራኤልን በመቃወም የኢራንን አቋም ያረጋገጡ ሲሆን፤ ስለ አሁኑ ድርድር ግን አስተያየት አልሰጡም።

    የጠቅላይ መሪው የጤና ሁኔታ ጥርጣሬ ላይ የወደቀም ሲሆን፤ አባታቸው አሊ ኻሚኔ ሲገደሉ እርሳቸውም ቆስለዋል ተብሎ ይገመታል።

    የአሜሪካ መከላከያ ኃላፊ ፒት ሄግሴት ቀደም ሲል ኻሚኔ “በከፍተኛ ደረጃ ተጎድተው ሊሆን ይችላል” ብለው ነበር። ይህን ግን የኢራን ጤና ሚኒስቴር አስተባብሏል።

  2. አሜሪካ እና ኢራን ስምምነት ላይ ለመድረስ “አንድ ወይም ሁለት” ጉዳዮች ብቻ እንዳላስማሟቸው የኢራን መገናኛ ብዙኃን ዘገቡ

    የሆርሙዝ ወሸመጥ ላይ የኢራን ፈጣን ጀልባዎች

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የኢራን ከፊል-መንግሥታዊ የዜና ወኪል የሆነው ታስኒም አሜሪካ እና ኢራን ስምምነት ላይ ለመድረስ “አንድ ወይም ሁለት” የሚሆኑ አንቀጾች እንዳላግባቧቸው አስታወቀ።

    እነዚህ ነጥቦች ላይ “በአሜሪካ በሚደረግ እንቅፋት” ምክንያት ጉዳዩ እስካሁን አልተጠናቀቀም ብሏል።

    የዜና ወኪሉ እንደዘገበው አደራዳሪዋ ፓኪስታን ስለ ኢራን አቋም ተነግሯታል። እናም “የአሜሪካ እንቅፋት ከቀጠለ” ስምምነቱ ሊጠናቀቅ እንደማይችል ታስኒም ጠቅሷል።

    ከኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ጋር ቅርበት ያለው ፋርስ የዜና ወኪል ደግሞ፤ እነዚህ ያላግባቡ ጉዳዮች እንዳይንቀሳቀሱ እግድ የተጣለባቸው የኢራን ፈንዶች፣ በነዳጅ እና ተዛማጅ ምርቶች ላይ የተጣሉ ማዕቀቦች ናቸው ብሏል።

    አክሲዮስ እና ኒውዮርክ ታይምስ በበኩላቸው ሁለቱ አገራት ለ60 ቀናት የሚቆይ የተኩስ አቁም እና የሆርሙዝ ወሽመጥን ዳግም መክፈት ላይ ከስምምነት ሊደርሱ መቃረባቸወን ዘግበዋል።

    በ60 ቀናቱ የተኩስ አቁም ወቅት የመርከቦች ነጻ እንቅስቃሴን ለማመቻቸት የተቀበሩ ፈንጂዎችን ኢራን ስታስወግድ አሜሪካ በበኩሏ የኢራን ወደቦች ላይ የጣለችውን እገዳ ታነሳለች ተብሏል።

    ይሁን እንጂ አሁንም የኢራን የኒውክሌር ፕሮግራም እና በከፍተኛ ደረጃ የተብላላ ዩራኒየም ጉዳዮች በስምምነቱ ውስጥ ስለመካተታቸው በግልጽ የተባለ ነገር የለም።

  3. አክሲዮስ የአሜሪካ እና የኢራን ስምምነት ሆርሙዝን መክፈት እና የተኩስ አቁሙን ለ60 ቀን ማራዘም ያካትታል አለ

    በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ የሚሄድ መርከብ

    የፎቶው ባለመብት, REUTERS

    አሜሪካ እና ኢራን ከስምምነት ለመድረስ መቃረባቸው እየተነገረ ነው።

    ስምምነቱ የተኩስ አቁሙን ለ60 ቀናት በማራዘም የሆርሙዝ ወሽመጥን ዳግም እንዲከፈት የሚያደርግ እንደሚሆን አክሲዮስ የአሜሪካ ባለሥልጣናትን ጠቅሶ ዘግቧል።

    እንደ አክሲዮስ ዘገባ ከሆነ በ60 ቀኑ የተኩስ አቁም ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥ እንደምትከፍት እና የመርከቦች እንቅስቃሴ ያለ ምንም ቀረጥ እንድትፈቅድ ይደረጋል ተብሏል።

    ኢራን በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ ያስቀመጠቻቸውን ፈንጂዎች መርከቦች በነጻነት መቅዘፍ እንዲችሉ ታነሳለች ሲል ዘገባው አክሏል።

    በምትኩ በስምምነቱ ዕቅድ መሠረት አሜሪካ በኢራን ወደቦች ላይ የጣለችውን እገዳ የምታነሳ ሲሆን ኢራን ነዳጇን በነጻነት መሸጥ እንዳትችል የተጣለው ማዕቀብ ይነሳል ተብሏል።

    ረቂቅ ስምምነቱ ኢራን የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ለመታጠቅ የምታደርገውን ጥረት እንድታቆም እንዲሁም የበለጸገ ዩራኒየም ፕሮግራሟን እንድታቋርጥ እንዲሁም በከፍተኛ ደረጃ የተብላላ ዩራኒየሟን ከአገር ለማስወጣት ድርድር እንድታደርግ እንደሚጠይቅ አክሲዮስ ዘግቧል።

    ኢራን ለአደራዳሪዎች በኒውክሌር ፕሮግራሟ እና በተብላላው ዩራኒየሟ ዙሪያ ከአሜሪካ ጋር ለመነጋገር ፈቃደኛ መሆኗን በቃል መናገሯ ቢገለጽም የተረጋገጠ ነገር አለመኖሩን አክሲዮስ ሁለት ምንጮችን ጠቅሶ ዘግቧል።

    አሜሪካ በበኩሏ በ60 ቀናት ውስጥ ማዕቀቦቹን ለማንሳት፣ እንዳይንቀሳቀሱ የተደረጉ የኢራን ፈንዶች ላይ ለመነጋገር መስማማቷን አክሲዮስ ዘግቧል።

    ዋይት ሐውስ በአክሲዮስ ዘገባ ዙሪያ እስከሁን ድረስ ያለው ነገር የለም።

  4. ኢራን በከፍተኛ ደረጃ የተብላላ ዩራኒየሟን ለማስረከብ አለመስማማቷን አንድ የኢራን ከፍተኛ ተደራዳሪ ለሮይተርስ ተናገሩ

    ጦርነቱ ሲጀመር ኢራን 440 ኪሎ ግራም ዩራኒየም እንዳላት እና ይህም 60 በመቶ በከፍተኛ ደረጃ የተብላላ መሆኑን አንድ የአሜሪካ ባለሥልጣን ተናግረው ነበር።

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images/BBC

    የምስሉ መግለጫ, ጦርነቱ ሲጀመር ኢራን 440 ኪሎ ግራም ዩራኒየም እንዳላት እና ይህም 60 በመቶ በከፍተኛ ደረጃ የተብላላ መሆኑን አንድ የአሜሪካ ባለሥልጣን ተናግረው ነበር

    አንድ ከፍተኛ የኢራን ባለሥልጣን ለሮይተርስ የዜና ወኪል ቴህራን በከፍተኛ ደረጃ የተብላላውን የዩራኒየም ክምችቷን ለማስረከብ እንዳልተስማማች ተናገሩ።

    ምንጩ አክለውም ከአሜሪካ ጋር ባለው የመጀመርያ ዙር ስምምነት የኢራን የኒውክለር ጉዳይ አለመነሳቱን አስታውቀዋል።

    “የኒውክሌር ጉዳይ ለመጨረሻው ስምምነት በይደር ቆይቷል። ስለዚህ በዚህኛው ስምምነት ውስጥ አልተካተተም። በከፍተኛ ደረጃ የተብላላ የኢራን ዩራኒየምን ከአገር ስለማስወጣት በሚመለከት ምንም ዓይነት ስምምነት አልተደረሰም” ብለዋል።

    ጦርነቱ ሲጀመር ኢራን 440 ኪሎ ግራም ዩራኒየም እንዳላት እና ይህም 60 በመቶ በከፍተኛ ደረጃ የተብላላ መሆኑን አንድ የአሜሪካ ባለሥልጣን ተናግረው ነበር።

    ይህም ጦር መሣሪያ ለማምረት ወደሚያስችለው 90 በመቶ የበለጸገ ዩራኒየም በአንፃራዊነት በፍጥነት ሊያድግ ይችላል።

    ኢራን በተጨማሪም 20 በመቶ ድረስ የበለጸገ 1,000 ኪሎ ግራም፣ እንዲሁም 3.6 በመቶ ገደማ የበለጸገ 8,500 ኪሎ ግራም ዩራኒየም አላት።

    ይህም በተለምዶ ለሰላማዊ አገልግሎት ማለትም ለኃይል ማመንጨት ወይም ለሕክምና ምርምር ይውላል።

    ወደ ኒውክሌር ጦር መሣሪያነት ሊቀየር የሚችለው በከፍተኛ ደረጃ የበለፀገ ዩራኒየም በአብዛኛው በኢስፋሃን እንደተከማቸ ይታመናል። ተቋሙ ባለፈው ዓመት በአሜሪካ እና በእስራኤል የአየር ድብደባ ዒላማ ከተደረጉት የኢራን ሦስት የመሬት ውስጥ የኒውክሌር ጣቢያዎች አንዱ ነው።

    ይሁን እንጂ በከፍተኛ ደረጃ ከበለፀገው ዩራኒየም ምን ያህል በሌሎች ቦታዎች እንደተከማቸ ግልጽ አይደለም።

    ምንጮች እንደሚሉት ቴህራን ለ20 ዓመት ኒውክሌር እንዳታበለጽግ የተቀመጠውን እገዳ ውድቅ አድርጋለች። በምትኩ ጦርነቱ ከመፈንዳቱ በፊት ያቀረበችውን የአምስት ዓመት ገደብ ለድርድር አቅርባለች።

    በተጨማሪም 440 ኪሎ ግራም የበለፀገውን የዩራኒየም ክምችት እንድታስረክብ የቀረበውን ጥያቄ ውድቅ አድርጋለች።

    ይህም ቀደም ሲል 60 በመቶ የበለፀገውን ዩራኒየሟን ለማዳከም በሚለው አቋሟ ጸንታለች።

    የዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ኃላፊ ራፋኤል ግሮስ ባለፈው ዓመት በጥቅምት ወር ለኤፒ እንደተናገሩት ይህ መጠን የበለጠ ቢበለጽግ 10 የኒውክሌር ቦምቦች ለማምረት በቂ ይሆናል።

  5. አሜሪካ እና ኢራን ከስምምነት ላይ ለመድረስ መቃረባቸውን እየተናገሩ ነው፤ ማን ምን አለ?

    የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኢስማኤል ባጌይ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኢስማኤል ባጌይ

    በሕንድ የሚገኙት የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ የተወሰኑ መግባባቶች ላይ መድረሳቸውን ገልጸው “የመጨረሻው ባይሆንም ተጨባጭ ለውጦች ላይ ተደርሷል” ብለዋል።

    ሩቢዮ “ምናልባት ዛሬ ወደ በኋላ ላይ ተጨማሪ ዜና ይኖር ይሆናል” በማለት “ያንን ግን ይፋ ማድረግ ለፕሬዚዳንቱ [ዶናልድ ትራምፕ] እተወዋለሁ” ብለዋል።

    በሚቀጥሉት ጥቂት ሰዓታት ዓለም “ቢያንስ የሆርሙዝ ወሽመጥን በሚመለከት” መልካም ዜና ይሰማል ሲሉም ተናግረዋል።

    “መስራት ያለብን ስራ ገና አለ” ያሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማርኮ ሩቢዮ “መልካም ዜና አለ” ነገር ግን “የመጨረሻው ዜና አይደለም” ብለዋል።

    ቅዳሜ ዕለት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በአሜሪካ እና ኢራን መካከል የሆርሙዝ ወሽመጥን መክፈት ጨምሮ አብዛኞቹ ጉዳዮች “በስፋት ድርድር እንደተደረገባቸው” ገልጸዋል።

    ፕሬዚዳንቱ ዝርዝር መረጃ ባይሰጡም “የስምምነቱ የመጨረሻው ነጥቦች እና ዝርዝር ጉዳዮች ንግግር እየተደረገባቸው በመሆኑ በቅርቡ ይፋ ይደረጋል” ብለዋል።

    አክለውም ማንኛውም ስምምነት ኢራን “በፍጹም” የኒውክሌር ጦር መሣሪያ እንዳታገኝ የሚያደርግ ይሆናል ብለዋል።

    የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኢስማኤል ባጌይ ባለፈው ሳምነት ቴህራን እና ዋሺንግተን በሚያደርጉት ንግግር መቀራረብ እያሳዩ መሆናቸውን ተናግረዋል። ነገር ግን ይህ ማለት በቁልፍ ጉዳዮች ላይ ከስምምነት ይደረሳል ማለት አይደለም ብለዋል።

    አክለውም አሜሪካኖች “እርስ በእርሱ የሚጣረስ” መግለጫ ይሰጣሉ ሲሉ ወንጅለዋል።

    የኢራን የዜና ወኪል ታስኒም ዛሬ ማለዳ የሆርሙዝ ወሽመጥ በስምምነት ‘ከጦርነቱ በፊት ወደ ነበረበት ይዞታው አይመለስም” ሲል ዘግቧል።

    የፓኪስታን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢሻቅ ዳር እየተደረገ ያለውን ድርድር በመጥቀስ “አዎንታዊ እና ዘላቂ ውጤት ላይ ለመድረስ እየተቃረብን ነው” ብለዋል።

  6. የአሜሪካ እና ኢራን አደራዳሪ አዎንታዊ ውጤት ላይ ለመድረስ “ተቃርበናል” አሉ

    የፓኪስታን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የፓኪስታን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የኢራን ጦርነትን ለማስቆም በሚደረገው ድርድር “አዎንታዊ እና ዘላቂ ውጤት ላይ ለመድረስ ተቃርበናል” አሉ።

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ቅዳሜ ዕለት ከኢራን ጋር በሚደረሰው ስምምነት ዙሪያ “በአብዛኛው ንግግር እንደተደረገበት” አስታውቀው ነበር።

    የፓኪስታን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ኢሻቅ ዳር በበኩላቸው ከትራምፕ እንዲሁም ሳዑዲ አረቢያ፣ ቱርክ፣ ኳታር፣ ግብጽ፣ ዩኤኢ፣ ዮርዳኖስ እንዲሁም የፓኪስታን ተወካይ “በቀጣናው ሰላም” ዙሪያ ያደረጉት ውይይት “ትልቅ እመርታ ያሳየ ነው” ብለዋል።

    "ፓኪስታን ዘላቂ ሰላምን፣ መከባበርን እና ቀጣናዊ መረጋጋትን ለማስፈን የታለሙ ሁሉንም ቅን ጥረቶችን ለመደገፍ ቁርጠኛ ነች" ካሉ በኋላ “የእነዚህ ድርድሮች ስኬት አዎንታዊ እና ዘላቂ ውጤት ላይ ለመድረስ ያለን ተስፋ መሠረት ነው” ብለዋል።

  7. ኢራን ዓለም ዋንጫ ላይ የሚሳተፈው ቡድኗ የሚቆይበት ስፍራ ከአሜሪካ ወደ ሜክሲኮ እንዲዛወር አደረገች

    ኢራን የእግር ኳስ ቡድኗ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ኢራን የእግር ኳስ ቡድኗ በሜክሲኮ የድንበር ከተማ ቲዋና እንዲቀመጥ የዓለምን እግር ኳስ ከሚያስተዳድረው ፊፋ ይሁንታ ማግኘቷን አስታወቀች።

    የኢራን እግር ኳስ ፌደሬሽን አርብ ዕለት ቡድኑ በዓለም ዋንጫ ውድድር ወቅት በአሪዞና እንዲቀመጥ ተደልድሎ የነበረ ቢሆንም ለፊፋ የቀረበ ጥያቄን ተከትሎ ወደ ሜክሲኮ ተዛውሯል ብሏል።

    የኢራን እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዚዳንት መህዲ ታጅ በቴሌግራም ገጻቸው ላይ ባስተላለፉት የቪዲዮ መልዕክት “መቀመጫቸው ቲዋና በሚገኘው ካምፕ ይሆናል። ለሜክሲኮ እና ዩናይትድ ሰቴትስ ድንበር እንዲሁም ለፓሲፊክ ውቅያኖስ ቅርብ ነው” ብለዋል።

    ታጅ አክለውም ውሳኔው ከቪዛ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ውጣ ውረዶችን ያስቀራል፤ እንዲሁም ቡድኑ ከኢራን በቀጥታ ወደ ሜክሲኮ መብረር ያስችለዋል ብለዋል።

    ፊፋ በጉዳዩ ላይ አስተያየቱን ቢጠየቅም ምላሽ አልሰጠም።

    ኢራን የመጀመርያውን ሁለት ጨዋታዎች በሎስ አንጀለስ ከኒውዚላንድ እና ቤልጂየም ጋር የምትጫወት ሲሆን ሦስተኛዋን ጨዋታ በሲያትል ከግብጽ ጋር ታደርጋለች።

    “በሎስ አንጀለስ የምንጫወትበት ከምናርፍበት ያለው ርቀት በአጠቃላይ 55 ደቂቃ ነው” ያሉት ታጅ ከዚህ በፊት በአሪዞና ተይዞላቸው ከነበረው መቀመጫ ቲዋና በጣም ቅርብ መሆኑን ተናግረዋል።

    ኢራን ለበርካታ ወራት በዓለም ዋንጫ ላይ የሚኖራት ተሳትፎ ከደህንነት እና ከጉዞ ጋር በተያያዘ እርግጠኛ መሆን ሳይቻል ቀርቶ ነበር።

    የዚህ ዓመት የዓለም ዋንጫን ዩናይትድ ስቴትስ፣ ሜክሲኮ እና ካናዳ በጥምረት ያዘጋጃሉ።

  8. ትራምፕ ከኢራን ጋር የሆርሙዝ ወሽመጥን ዳግም ማስከፈት ጨምሮ “በበርካታ ጉዳዮች ላይ መደራደራቸውን” አስታወቁ

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, EPA/Shutterstock

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከኢራን ጋር በስምምነቱ ዙሪያ “በሰፊው ተነጋግረናል” በማለት ዝርዝሩ በቅርቡ ይፋ ይሆናል አሉ።

    ፕሬዚዳንቱ ቅዳሜ ዕለት ስምምነቱ የሆርሙዝ ወሽመጥን ዳግም ማስከፈት እንደሚያካትት ተናግረው ዝርዝር ከመግለጽ ተቆጥበዋል።

    የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኢስማኤል ባጋይ ለአገሪቱ ቴሌቪዥን ጣቢያ ከአሜሪካ ጋር እየተደረገ ያለው ንግግር መቀራረብ እንደሚታይበት ባለፈው ሳምንት ተናግረው ነበር።

    ቃል አቀባዩ ይህ ግን በወሳኝ ነጥቦች ዙሪያ ከስምምነት ላይ ሊደረስ ይችላል ማለት አይደለም ሲሉ አስጠንቅቀዋል። አሜሪካ “እርስ በእርሱ የሚጣረስ” መልዕክትን ታሰራጫለች ሲሉ ወንጅለዋታል።

    ትራምፕ በማኅበራዊ ሚደያ ገጻቸው ላይ ከሳዑዲ አረቢያ፣ ዩናይትድ አረብ ኤሜሬትስ፣ ኳታር እና ሌሎች ጋር “በሰላም ጥረቱ የመግባባያ ሰነድ” ዙሪያ “ጥሩ ውይይት” ማድረጋቸውን ጽፈዋል።

    ዶናልድ ትራምፕ “አሜሪካ፣ ኢራን እና ሌሎች አገራት በአብዛኛዎቹ የድርድሩ ነጥቦች ላይ ተስማምተናል፤ ነገር ግን ይፋ ከመሆኑ በፊት መጠናቀቅ ያለባቸው ጥቂት ዝርዝር ጉዳዮች አሉ” ብለዋል።

    “የስምምነቱ የመጨረሻ ነጥቦች እና ዝርዝሮች ላይ ውይይት እየተደረገ ነው፤ በቅርቡ ይፋ ይሆናል።”

    ቅዳሜ ዕለት ከእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጋር በስልክ “ጥሩ” ውይይት ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል።

    ፕሬዚዳንቱ በስምምነቱ ላይ ተጨማሪ መረጃ ያልሰጡ ቢሆንም የትኛውም ስምምነት ኢራን የኒውክሌር ጦር መሣሪያ እንዳይኖራት የሚያደርግ እንደሚሆን አረጋግጠዋል።

    የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ሻቤዝ ሻሪፍ ደግሞ ከዶናልድ ትራምፕ ጋር የነበራቸው የስልክ ውይይት “በጣም ጠቃሚ እና ውጤታማ” እንደነበር ተናግረው "ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሰላምን ለማስፈን ላደረጉት የተለየ ጥረት ላደንቃቸው እፈልጋለሁ" ብለዋል።

    ፓኪስታን በአሜሪካ እና በኢራን መካከል በሚደረገው ንግግር አደራዳሪ በመሆን እያገለገለች ትገኛለች።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኤክስ ገጻቸው ላይ “በቅርቡ ቀጣዩን ዙር ንግግር እንደምናስተናግድ ተስፋ እናደርጋለን” ብለዋል።

    አሜሪካ እና እስራኤል በጋራ በመሆን ቴህራን ላይ ጦርነት የከፈቱት የካቲት 21 2018 ዓ.ም. ነበር።

    ኢራን በበኩሏ ወደ እስራኤል ሚሳዔሎችን ያስወነጨፈች ሲሆን በባሕረ ሰላጤው በሚገኙ የአሜሪካ ጦር ሠፈሮች እና የኤነርጂ መሠረተ ልማቶች ላይም ጥቃቶችን ፈጽማለች።

    በሚያዚያ ወር መጀመርያ ላይ በአሜሪካ እና ኢራን መካከል የተኩስ አቁም የተደረሰ ሲሆን ከዚያ ጊዜ ጀምሮም ቴህራን እና ዋሺንግተን ንግግር እያደረጉ ይገኛሉ።

  9. ኢራን የዓለም የኃይል አቅርቦትን “እንድታግት” እንደማይፈቅዱ የአሜሪካው ባለሥልጣን ተናገሩ

    የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩብዮ ከሕንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ንሬንድራ ሞዲ ጋር

    የፎቶው ባለመብት, Indian Government

    የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩብዮ “ኢራን የዓለም የኃይል አቅርቦትን እንድታግት አንፈቅድም” አሉ።

    ከሕንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ንሬንድራ ሞዲ ጋር የተገናኙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፤ የኃይል አቅርቦት ጉዳይን ጨምሮ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት ማድረጋቸው ተገልጿል።

    የሕንድ እና አሜሪካ ስትራቴጂያዊ ግንኙነት ስላለው ጠቀሜታ ሩቢዮ መናገራቸው ተዘግቧል።

    በሕንድ ለአራት ቀናት የሚቆዩት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ሞዲ አሜሪካን እንዲጎበኙም ጥሪ አቅርበዋል።

  10. “ከሕዝባችን መብት አናፈነግጥም”- የኢራን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ

    የፓኪስታን ጦር አዛዥ ፊልድ ማርሻል አሲም ሙኒር እና የኢራን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ መሐመድ ባጋር ጋሊባፍ

    የፎቶው ባለመብት, Iran

    የኢራን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ መሐመድ ባጋር ጋሊባፍ “ከሕዝባችን እና አገራችን መብት አናፈነግጥም” ማለታቸው ተገለጸ።

    ከፓኪስታን ጦር አዛዥ ፊልድ ማርሻል አሲም ሙኒር ጋር የተወያዩት አፈ ጉባዔው “በተለይም አታላይ ከሆነ እና ከማናምነው አካል ጋር ሆነን ከሕዝባችን እና አገራችን መብት አናፈነግጥም” ብለዋል።

    “በተኩስ አቁሙ ወቅት ጦራችን ራሱን መልሶ ገንብቷል። ትራምፕ ጦርነቱን መልሰው ከጀመሩ ቂል ናቸው። ጦርነቱ ከተጀመበት ጊዜ በበለጠ የሚጎዳቸው ይሆናል” ሲሉም አስጠንቅቀዋል።

    ፓኪስታን ሁለቱን አገራት ለማደራደር የምታደርገው ጥረት ቢቀጥልም አሜሪካ በኢራን ላይ በድጋሚ ጥቃት ለመክፈት ማሰቧን የሚጠቁሙ ዘገባዎች ወጥተዋል።

  11. የአሜሪካ ልዑክ የኃይል አቅርቦትን በተመለከተ ከሕንድ ባለሥልጣናት ጋር እንደሚወያይ ተገለጸ

    ማርኮ ሩቢዮ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ለአራት ቀናት ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ሕንድ የገቡት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ የኃይል አቅርቦትን በተመለከተ ከኒው ደልሂ ባለሥልጣናት ጋር እንደሚወያዩ ተገለጸ።

    ሩቢዮ ከጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ጋር ሲገናኙ ዋነኛ አጀንዳ ከሚሆኑ ነጥቦች መካከል የኃይል አቅርቦት አንዱ ነው።

    ሩቢዮ ከኒው ደልሂ በመቀጠል ወደ ኮልካታ፣ ጃንፑር እና አግራ ግዛቶች እንደሚጓዙም ተገልጿል።

    የሆርሙዝ ወሽመጥ መዘጋት የመላው ዓለምን የኃይል አቅርቦት አናግቷል።

    1.4 ቢሊዮን ዜጎች ያሏት ሕንድ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው የኃይል ፍላጎቷ በኢራን ጦርነት ምክንያት ፈተና ገጥሞታል።

    የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር “ለሕንድ የኃይል አቅርቦታችንን መሸጥ እንፈልጋለን። የአሜሪካ ምርት እና የውጭ ንግድ በታሪክ ታይቶ በማይታወቅ መጠን ከፍተኛ መሆኑ ይታወቃል” ብለዋል።

    ሕንድ ለኃይል አቅርቦት አሜሪካን አጋር የማድረግ ፍላጎት እንዳላት ይታመናል።

    ሆኖም ግን አሜሪካን ዋነኛ የኃይል አቅርቦት አጋር ማድረግ ከርቀት እና ከክፍያ አንጻር እምብዛም እንደማያዋጣ ተንታኞች ይገልጻሉ።

  12. የፓኪስታን የጦር አዛዥ ከኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር ተወያዩ

    የፓኪስታን ጦር አዛዥ ፊልድ ማርሻል አሲም ሙኒር ከኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ ጋር

    የፎቶው ባለመብት, tasnim

    የፓኪስታን ጦር አዛዥ ፊልድ ማርሻል አሲም ሙኒር ከኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ ጋር ተወያዩ።

    ቴህራን የሚገኙት የፓኪስታን ጦር አዛዥ ጦርነቱን መግታት ስለሚቻልባቸው መንገዶች ከአራግቺ ጋር “እስከ ትናንት ምሽት ድረስ” መወያየታቸው ተገልጿል።

    የጦር አዛዡ ወደ ቴህራን ሲጓዙ የአሁኑ ለሁለተኛ ጊዜ ነው። ባለፈው ሳምንት የፓኪስታን የአገር ውስጥ ሚኒስትርም ወደ ቴህራን አቅንተዋል።

    ፓኪስታን አሜሪካ እና ኢራንን የማሸማገል ጥረቷን እንደቀጠለች ነው።

  13. አሜሪካ በድጋሚ ኢራን ላይ ጥቃት ለማድረስ እየተዘጋጀች መሆኑ ተዘገበ

    ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ኢራን እና አሜሪካን ለማሸማገል ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ቢቀጥሉም ዋሽንግተን ቴህራን ላይ በድጋሚ ጥቃት ለመፈጸም እየተዘጋጀች መሆኑ ተዘገበ።

    የቢቢሲ የአሜሪካ አጋር ሲቢኤስ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮቹን ጠቅሶ እንደዘገበው፤ የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር አዲስ ጥቃት ለመሰንዘር ዝግጅት እያደረገ ይገኛል። ሆኖም ግን ጥቃት ለመፈጸም የመጨረሻው ውሳኔ እንዳልተላለፈ የሲቢኤስ ዘገባ ይጠቁማል።

    ትራምፕ “የመንግሥት ጉዳዮች” ስላሉባቸው የልጃቸውን ሠርግ መታደም እንደማይችሉ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው አስታውቀዋል።

    የዛሬውን ዕለት ኒው ጀርሲ በሚገኘው ቅንጡ መኖሪያቸው እንደሚያሳልፉ ቢጠበቅም ወደ ዋይት ሀውስ ማቅናታቸው ተገልጿል።

    የአሜሪካ መከላከያ እና ደኅንነት አመራሮችም እረፍት ለመውጣት ይዘውት የነበረውን ዕቅድ እንደሰረዙ የተለያዩ ምንጮች ጠቁመዋል። ይህም ኢራን ላይ በድጋሚ ጥቃት ለመክፈት በሚደረገው ዝግጅት ምክንያት እንደሆነ ተመልክቷል።

    የአሜሪካ ሠራዊት እና ደኅንነት ባለሥልጣናት በተጠባበቅ ላይ በነበሩ ወታደሮች ዝርዝር ላይ ለውጥ ማድረጋቸውን ምንጮቹ ጠቁመዋል።

    በተለያዩ የመካከለኛው ምሥራቅ ወታደራዊ ሰፈሮች የሚገኙ የአሜሪካ ወታደሮች ኢራን በምትወስደው የመልሶ ማጥቃት እርምጃ ዒላማ እንዳይሆኑ ከካምፖቹ እንዲወጡ እንደሚደረግ ተገልጿል።

    ኢራን እና አሜሪካ ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ከደረሱበት ጊዜ አንስቶ አንዳቸው በሌላቸው ላይ ቀጥተኛ ጥቃት ከመፈጸም ተቆጥበዋል። የድርድር ጥረቶችም እንደቀጠሉ ነው።

  14. የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢራን ሆርሙዝን የማትከፍት ከሆነ “አንድ ሰው የሆነ ነገር ማድረግ አለበት” አሉ

    የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ፤ ከኢራን ጋር ስምምነት ተደርሶ የሆርሙዝ ወሽመጥ የማይከፈት ከሆነ “አንድ ሰው የሆነ ነገር ማድረግ ይኖርበታል” ሲሉ ተናገሩ።

    ሩቢዮ እና የኔቶ አባል አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ወሳኙ የባሕር መተላለፊያን መልሶ ስለመክፈት እየተወያዩ መሆናቸውን አሶሺዬትድ ፕሬስ (ኤፒ) ዘግቧል።

    የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በዋሽንግተን እና ቴህራን መካከል ስምምነት የማይደረስ ከሆነ ወሽመጡን በተመለከተ “ሁለተኛ እቅድ” እንደሚያስፈልግ በአጽንኦት እንዳነሱ ዘገባው ያመለክታል።

    “በዚያ ሁኔታ ውስጥ፤ በራሳቸው ፈቃድ ወሽመጡን አይከፍቱትም” ያሉት ሩቢዮ ስምምነት ካልተደረሰ አንዳች እርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባ አሳስበዋል።

    እንደ ኤፒ ዘገባ፤ ሩቢዮ ይህንን ጉዳይ ለበርካታ አውሮፓውያን አጋሮቻቸው አቅርበው “ይሁንታ” ማግኘታቸውን ገልጸዋል።

    “ኢራን [ሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ] የክፍያ ሥርዓት ለመዘረጋት እየሞከረች ነው። ይሄ ተቀባይነት የለውም። ሊሆን አይችልም” ብለዋል።

    “ይህ የሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ የሚፈጠር ከሆነ በዓለም ዙሪያ ሌሎች አምስት ቦታዎችም ላይም ይሆናል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

    አክለውም ግን ከኢራን ጋር በሚደረገው ድርድር ላይ መሻሻል እየታየ መሆኑን በመጥቀስ የኢራን ባለሥልጣናት የተናገሩትን ደግመዋል።

    እየተካሄደ ባለው ድርድር ላይ የታየውን ውጤት “አላጋንነውም፤ ደግሞም አላድበሰብሰውም” ያሉት ሩቢዮ፤ “መከናወን ያለበት ተጨማሪ ሥራ አለ” በማለት ተናግረዋል።

  15. የኦክስፎርድ ተመራማሪዎች በወራት ውስጥ ዝግጁ የሚሆን አዲስ የኢቦላ ክትባት እየሰሩ መሆኑን ተናገሩ

    ተመራማሪ ቤተ ሙከራ ውስጥ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች አሁን የተከሰተውን የኢቦላ ወረርሽኝ ለማስቆም ጥቅም ላይ ሊውል እንዲሁም በወራት ጊዜ ውስጥ ዝግጁ ሊሆን የሚችል አዲስ ክትባት መስራታቸውን ገለጹ።

    ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ውስጥ በተከሰተው የኢቦላ ወረርሽኝ 177 ሰዎች የሞቱ ሲሆን በበሽታው የተጠረጠሩ ሰዎች ቁጥር ደግሞ 750 ደርሷል።

    ቡንዲቡግዮ በተሰኘው እና እምብዛም ባልተለመደ በዚህ የቫይረስ ዝርያ ከሚያዙ ሰዎች ውስጥ አንድ ሦስተኛው ሕይወታቸው ያልፋል። እስካሁን ድረስም የተረጋገጠ ክትባት አልተገኘለትም።

    የኦክስፎርድ ተመራማሪዎች ወረርሽኙ የሚስፋፋበት እንዲሁም በሙከራ ላይ ያለው ክትባታቸው የሚፈለግበት ሁኔታ ይፈጠር ከሆነ በሚል ሥራቸውን በፍጥነት እያከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።

    የኦክስፎርዱ ክትባት ውጤታማ ስለመሆኑ እስካሁን ማረጋገጫ የለም። መጀመሪያ በእንስሳት ላይ ተሞክሮ ምርምር መደረግ ያለበት ሲሆን እርግጠኛ ለመሆን ደግሞ በሰዎች ላይ ይሞከራል።

    ተመራማሪዎቹ ክትባቱን ለመስራት እየተጠቀሙት ያለው ቴክኖሎጂ በኮቪድ ወረርሽኝ ጊዜ ስራ ላይ ሲያውሉት የነበረ ነው።

    በኮቪድ ጊዜ የቫይረሱን ጄኔቲክ ኮድ በመውሰድ ቴክኖሎጂውን ተጠቅመዋል። አሁን ደግሞ ቡንዲቡግዮ የተባለውን የኢቦላ ዝርያ ጄኔቲክ ኮድ ይወስዳሉ ተብሏል።

    ክትባቱ ኦክስፎርድ ውስጥ በእንስሳት ላይ እየተሞከረ መሆኑን ቢቢሲ ተረድቷል።

  16. የካናዳዋ አልበርታ ግዛት የአገሪቱ አካል ሆና በመቀጠሏ ጉዳይ ላይ ሕዝበ ውሳኔ ልታካሂድ ነው

    የአልበርታ ጠቅላይ ሚኒስትር ዳኒኤል ስሚዝ ሐሙስ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የካናዳዋ አልበርታ ግዛት የአገሪቱ አካል ሆና ትቀጥል ወይስ የመገንጠል ጉዳይ ላይ ለሁለተኛ ጊዜ አስገዳጅ ድምፅ ይሰጥ የሚለው የሚወሰንበት ሕዝበ ውሳኔ ሊካሄድ ነው።

    ይህ ሕዝበ ውሳኔ ከአስርት ዓመታት በኋላ የካናዳን አንድነት ፈተና ውስጥ የሚከት እርምጃ ሆኗል።

    የግዛቷ ጠቅላይ ሚኒስትር ዳኒኤል ስሚዝ ሐሙስ ዕለት ሕዝበ ውሳኔው እንደሚካሄድ ያስታወቁት የአልበርታን መገንጠል የሚደግፉ ነዋሪዎች በተያዘው የአውሮፓውያን 2026 መጀመሪያ ከ300 ሺህ በላይ ሰዎችን ፊርማ ካሰባሰቡ በኋላ ነው።

    አልበርታ የካናዳ ግዛት ሆና መቀጠሏን የሚደግፍ ሌላ የፊርማ ማሰባሰቢያ ላይ ደግሞ ከ400 ሺህ በላይ ፈርመዋል።

    በነዳጅ ሐብት በበለጸገችው ግዛት ውስጥ ነጻነትን የሚያቀነቅን እንቅስቃሴ እያደገ መጥቷል። ይህ እንቅስቃሴ የተነሳው ለዓመታት ከቆየው የአገሪቱ ሕግ አውጪዎች አልበርታን ችላ ይሏታል የሚል ቅሬታ ነው።

    የሕዝብ አስተያየት ዳሰሳዎችን እንደሚያሳዩት ግን አሁንም ቢሆን አብዛኞቹ የአልበርታ ነዋሪዎች መገንጠልን ደግፈው ድምጽ አይሰጡም።

    የግዛቷ ጠቅላይ ሚኒስትር በቴሌቪዥን በተላለፈ ንግግራቸው ላይ እንደገለጹት ሕዝበ ውሳኔው የሚካሄደው ጥቅምት ላይ ነው።

    በሕዝበ ውሳኔው ድምጽ የሚሰጠው አልበርታ በካናዳ ውስጥ ግዛት ሆና መቀጠል አለባት ወይስ መገንጠልን በተመለከተ አስገዳጅ የግዛት ሕዝበ ውሳኔ ለማካሄድ ሕጋዊው ሂደት መጀመር አለበት” የሚለውን ለመወሰን እንደሆነ አብራርተዋል።

    ጠቅላይ ሚኒስትሯ ድምጻቸውን የሚሰጡት አልበርታ የካናዳ ግዛት ሆና መቀጠል አለባት የሚለውን በመደገፍ እንደሆነ ተናግረዋል።

  17. አውሮፓ በሂደት አሜሪካ ላይ ያላትን ጥገኝት እንደምትቀንስ የኔቶ ዋና ፀሐፊ ተናገሩ

    የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ዋና ጸሐፊ ማርክ ሩቴ እና ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ዋና ፀሐፊ ማርክ ሩተ፤ ጥምረቱ ራሱን የሚያጠናክርባቸው መንገዶች እየተከተለ መሆኑን እና በሂደት አሜሪካ ላይ ያለውን ጥገኝነት እንደሚቀንስ ገለጹ።

    ዋና ፀሐፊ ስዊዲን ውስጥ እየተካሄደ ባለው የኔቶ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት ይህ አካሄድ ለአሜሪካም ሆነ ለአውሮፓ አገራት ጠቃሚ ነው።

    እርምጃው አሜሪካ ሌሎች ቅድሚያ በምትሰጣቸው ጉዳዮች ላይ እንድታተኩር፤ የኔቶ አባላት የሆኑ የአውሮፓ አገራት ደግሞ የመከላከያ በጀታቸውን እንዲያሳድጉ እንደሚያስችል አስረድተዋል።

    አሜሪካ ኔቶ ውስጥ የሚታወጣውን የገንዘብ መጠን ለማመጣጠን “አስፈላጊ” እምርጃ መሆኑንም አክለዋል።

    ዋና ፀሐፊው ሩተ ይህንን ያሉት፤ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከእስራኤል ጋር በመሆን ኢራን ላይ ለከፈቱት ጦርነት የጦር ሠፈራቸውን ለማስጠቀም ፈቃደኛ ያልሆኑ የኔቶ አባል አገራት ላይ ወቀሳ ካሰሙ በኋላ ነው።

    ዋና ፀሐፊው፤ አውሮፓውያን አጋሮች ጦር ሠፈሮችን ክፍት ማድረግ በተመለከተ በሁለትዮሽ ስምምነት ማዕቀፍ መሠረት የአሜሪካን ፍላጎት እያሟሉ ነው ብለዋል።

    የአውሮፓ አጋሮች የሆርሙዝ ወሽመጥን በተመለከተ እያደረጉት ያለውን ጥረት ያነሱት ሩተ፤ "እንደ አውሮፓውያን አጋሮች፤ ለአሜሪካ ሊደረግ የሚችለውን ከፍተኛ ድጋፍ ማቅረብ እንችላለን” ብለዋል።

  18. ስፔናዊው የማንችስተር ሲቲ አሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ ከኃላፊነታቸው እንደሚለቁ ክለቡ አስታወቀ

    ፔፕ ጋርዲዮላ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ለ10 ዓመት የዘለቀው የፔፕ ጋርዲዮላ የማንችስተር ሲቲ የአሰልጣኝነት ዘመን መጠናቀቁን ክለቡ ይፋ አደረገ።

    ጋርዲዮላ ከአሰልጣኝነት ኃላፊነታቸው ቢለቁም ዓለም አቀፍ የሲቲ ግሩፕ አምባሳደር ሆነው እንደሚቀጥሉ ክለቡ አስታውቋል።

    ፔፕ ጋርዲዮላ በማንችስተር ሲቲ የ10 ዓመት ቆይታቸው ሻምፕዮንስ ሊግን ጨምሮ 20 ዋንጫዎችን ለክለቡ ማንችስተር ሲቲ አስገኝተዋል።

    በዚህ ዓመትም የኤፍኤ ዋንጫ እና ካራባኦ ዋንጫ አሸንፈዋል።

    ፔፕ ከቀናት በፊት የውድድሩ ዓመት መጨረሻ ላይ እንደሚለቁ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ሲነገር የነበረ ሲሆን ዛሬ ክለቡ ይህንኑ አረጋግጧል።

    በመሆኑም ፔፕ የመጨረሻ ጨዋታቸውን እሁድ በማንችስተር ሲቲ ሜዳ ከአስቶን ቪላ ጋር አድርገው ያጠናቅቃሉ። በምትካቸው የቀድሞው ምክትላቸው እና የቼልሲ አሰልጣኝ የነበሩት ኤንዞ ማሬስካ እንደተሾሙ ተነግሯል።

  19. በሕንድ ሊደረግ የነበረው የአፍሪካ ጉባኤ በኢቦላ ስጋት ምክንያት ተራዘመ

    እጇን የምትታጠብ ሴት

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    በሚቀጥለው ሳምንት ሊካሄድ የነበረው የሕንድ-አፍሪካ ጉባኤ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና ኡጋንዳ በተቀሰቀሰው የኢቦላ ቫይረስ ቀውስ ምክንያት መራዘሙ ተገለፀ።

    አራተኛው የሆነው ጉባኤው በአፍሪካ አገራት እና በሕንድ መካከል ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን ለማሳደግ ያለመ ነው።

    የዘንድሮው ጉባዔ ከአስር ዓመታት ቆይታ በኋላ ከግንቦት 20 እስከ ግንቦት 23 2018 ዓ.ም. ድረስ በዴሊ ሊካሄድ ቀን ተቆርጦለት የነበረ ነው።

    ሕንድ እና የአፍሪካ ኅብረት ሐሙስ ዕለት በጋራ ባወጡት መግለጫ ጉባዔው በአህጉሩ በተቀሰቀሰው የኅብረተሰብ ጤና ስጋት ምክንያት መራዘሙን እና ጉባኤው ሊሰናዳበት የሚችል አዲስ ቀን ይፋ እንደሚሆን ገልፀዋል።

    እርምጃው የዓለም የጤና ድርጅት ቫይረሱን “የዓለም የኅብረተሰብ ጤና አደጋ” ብሎ ካወጀ በኋላ የመጣ ነው።

    እንደ ድርጅቱ መረጃ በቫይረሱ ተይዘዋል ተብለው የተጠረጠሩ ሰዎች 600 ሲሆኑ፤ እስካሁን 139 ሰዎች በቫይረሱ ሕይወታቸው ማለፉ ታውቋል።

    የቫይረሱ ምልክቶች እስኪታዩ ድረስ ከሁለት እስከ 21 ቀናት ይወስዳል።

  20. የፓኪስታን ልዑክ ከኢራን ባለሥልጣናት ጋር ለመወያየት ዳግም ቴህራን ገቡ

    የፓኪስታን የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሳይድ ሞሺን ናቅቪ ከኢራኑ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር

    የፎቶው ባለመብት, @s_a_araghchi

    የምስሉ መግለጫ, የፓኪስታን የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሳይድ ሞሺን ናቅቪ ከኢራኑ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር

    የኢራኑ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከፓኪስታን ልዑክ ጋር ዛሬ አርብ በቴህራን ተገናኝተው ከአሜሪካ ጋር የተጀመረውን ጦርነት ለማስቆም ባቀረቡት የሰላም ዕቅድ ላይ መወያየታቸውን የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘገቡ።

    ቴህራን እና ዋሺንግተን በሆርሙዝ ወሽመጥ እና በከፍተኛ ደረጃ ተብላልቶ በተከማቸው ዩራኒየም ላይ መግባባት ላይ መድረስ አልቻሉም።

    ታስኒም የዜና ወኪል ፓኪስታን የአሜሪካን መልዕክት ለኢራን ካቀረበች ከሁለት ቀናት በኋላ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሳይድ ሞሺን ናቅቪ በቴህራን ለተጨማሪ ውይይት መገኘታቸውን ዘግቧል።

    የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ እየተደረጉ ባሉ ንግግሮች ላይ“ጥሩ ምልክቶች አሉ” በማለት ቴህራን በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ ቀረጥ የምትጥል ከሆነ ግን ፋይዳ አይኖረውም ብለዋል።

    በንግግሩ ላይ የተወሰኑ ለውጦች ስለመኖራቸው “ጥሩ ምልክቶች አሉ” ያሉት ሩቢዮ “በጣም ተስፈኛ መሆን አልፈልግም. . . በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት ምን አንደሚሆን እናያለን” ብለዋል።

    አንድ ከፍተኛ የኢራን ባለሥልጣን ለሮይተርስ የዜና ወኪል ሐሙስ ዕለት እስካሁን ምንም ዓይነት ስምምነት ላይ ባይደርስም ልዩነቶች እየጠበቡ መምጣታቸውን ተናግረዋል።