ቀጥታ, ትራምፕ ከኢራን ጋር የሚደረገው ድርድር የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ መድረሱን ተናግረው ካልተሳካ ጥቃት ለመፈጸም ዛቱ

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዛሬ ረቡዕ ከኢራን ጋር የሚደረገው ድርድር የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ መድረሱን አስታውቀው ከስምምነት ላይ መድረስ ካልተቻለ ግን ጥቃት እንደሚፈጽሙ አስጠነቀቁ። ትራምፕ ‘ኦፕሬሽን ኤፒክ ፊዩሪ’ ብለው የሰየሙትን ዘመቻ በተኩስ አቁም ጋብ ካደረጉት ስድስት ሳምንታት ቢያልፉም በሁለቱ አገራት መካከል የሚካሄደውን ጦርነት ለማስቆም የሚደረገው ንግግር ግን እምብዛም ለውጥ እያሳየ አይደለም።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. ፕሬዝዳንት ሙሴቬኒ በልጃቸው የሚመራ የፀረ ሙስና ዘመቻ በባለሥልጣናት ላይ ጀመሩ

    ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ እና ልጃቸው ሙሁዚ ካይኔሩጋባ

    የፎቶው ባለመብት, X

    የምስሉ መግለጫ, ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ እና የጦሩ አዛዥ ልጃቸው ሙሁዚ ካይኔሩጋባ

    ፕሬዝዳንት ሙሴቬኒ የኡጋንዳ ጦር ሠራዊት አዛዥ በሆነው በልጃቸው የሚመራ በአገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ላይ የፀረ ሙስና ዘመቻ መጀመራቸው ተዘገበ።

    በዚህም የተነሳ ካምፓላ የሚገኘው የተሰናባቿ የአገሪቱ ፓርላማ አፈ ጉባዔ መኖሪያ ቤት በኡጋንዳ የደኅንነት ኃይሎች ተፈትሾ ሮልስ ሮይስ እና ሬንጅ ሮቨርን ጨምሮ ቅንጡ መኪኖች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተነግሯል።

    የአገሪቱ ጦር አዛዥ እና የፕሬዝዳንቱ ልጅ የሆኑት ሙሁዚ ካይኔሩጋባ አባታቸው ኡጋንዳ ውስጥ የሚገኝ ማንኛውንም ሰው በቁጥጥር ስር የማዋል ሥልጣን እንደሰጧቸው ተናግረዋል።

    የፀረ ሙስና ዘመቻው ለአራት አስርት ዓመታት ኡጋንዳን እየመሩ ባሉት በፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ ትዕዛዝ የሚካሄድ ሳይሆን እንደማይቀር ይታመናል።

    ቤታቸው የተፈተሸው አፈ ጉባዔዋ የፕሬዝዳንቱ የቅርብ ሰው ተደርገው ይታዩ የነበረ ሲሆን ለረዥም ጊዜ ስማቸው ከሙስና ጋር ሲነሳ ቆይቷል። በዚህም በብሪታኒያ እና በአሜሪካ ማዕቀቦች ተጥሎባቸዋል።

    አሁን ከባለሥልጣኗ ቤት የተያዙት ውድ ንብረቶች በጨረታ ተሽጠው ገንዘቡ ለሕዝብ እንደሚመለስ የጦሩ አዛዥ ተናግረዋል።

    በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በሚያጋሯቸው መልዕክቶች አነጋጋሪ የሆኑት የፕሬዝዳንቱ ልጅ ከሰሞኑ ባሠራጩት ጽሁፍ በዋና ከተማዋ ባሉ መንገዶች ላይ ጉድለት ከተገኘ የግንባታውን ኮንትራት የወሰዱትን ሰዎች አንገታቸውን እንደሚቀሉ አስጠንቅቀዋል።

  2. ትራምፕ ከኢራን ጋር የሚደረገው ድርድር ከመጨረሻው ምዕራፍ መድረሱን እና ካልተሳካ ግን ጥቃት እንደሚጀምሩ አስጠነቀቁ

    ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዛሬ ረቡዕ ከኢራን ጋር የሚደረገው ድርድር የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ መድረሱን አስታውቀው ከስምምነት ላይ መድረስ ካልተቻለ ግን ጥቃት እንደሚፈጽሙ አስጠነቀቁ።

    ትራምፕ ‘ኦፕሬሽን ኤፒክ ፊዩሪ’ ብለው የሰየሙትን ዘመቻ በተኩስ አቁም ጋብ ካደረጉት ስድስት ሳምንታት ቢያልፉም በሁለቱ አገራት መካከል የሚካሄደውን ጦርነት ለማስቆም የሚደረገው ንግግር ግን እምብዛም ለውጥ እያሳየ አይደለም።

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ በዚህ ሳምንት በኢራን ላይ ተጨማሪ ጥቃት እንዲፈጸም ለማዘዝ ተቃርበው እንደነበር ተናግረው ለድርድር ተጨማሪ ጊዜ ለመስጠት በሚል መሰረዛቸውን ተናግረዋል።

    ትራምፕ ዛሬ ለጋዜጠኞች “ከኢራን ጋር የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ደርሰናል። ምን እንደሚሆን እናያለን። ከስምምነት ላይ እንደርሳለን ወይንም ትንሽ አስቀያሚ የሆነ ነገር እናደርጋለን። ነገር ግን ያ አይሆንም ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ” ማለታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።

    “ተጨማሪ ዕድል መስጠት እፈልጋለሁ፤ ምንም የሚያስቸኩለኝ ነገር የለም” ብለዋል።

    አክለውም "በሀሳብ ደረጃ ከብዙ ሰዎች ይልቅ ጥቂቶች ቢሞቱ እመርጣለሁ። በማንኛውም መንገድ ልናደርገው እንችላለን።"

    ቴህራን በበኩሏ ትራምፕ ጦርነት ለመጀመር እያሴሩ ነው ስትል በመወንጀል ማንኛውም ጥቃት ቢፈጸምባት ከመካከለኛው ምሥራቅ ባሻገር አጸፋ ለመስጠት ዝታለች።

    የአገሪቱ አብዮታዊ ዘቡ ባወጣው መግለጫ “በኢራን ላይ ዳግም ጥቃት ከተፈጸመ በአካባቢው የሚታሰበው ጦርነት አሁን ከቀጣናው ያልፋል” ብሏል።

    የኢራን ፓርላማ አፈጉባዔ እና ዋነኛ ተደራዳሪ የሆኑት ባጋር ጋሊባፍ በበኩላቸው በድምጽ ባስተላለፉት መልዕከት “ጠላት በይፋም ሆነ በስውር የሚያደርገው እንቅስቃሴ” አሜሪካኖች አዲስ ጥቃት ለመክፈት እየተዘጋጀ መሆኑን ያሳያል ብለዋል።

    የፓኪስታን የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር በዛሬው ዕለት ቴህራን መሆናቸው ተሰምቷል። ኢራን አዲስ የሰላም ዕቅዷን በፓኪስታን በኩል ለአሜሪካ የሰጠችው በዚህ ሳምንት ነው።

    ነገር ግን የሰላም ዕቅዱ ከዚህ በፊት ካቀረበችው የሚለይ ነገር እንደሌለው ተንታኞች ተናግረዋል።

  3. የኢራን ዋነኛ ተደራዳሪ አሜሪካ “አዲስ ጦርነት ለመጀመር” ትፈልጋለች አሉ

    የኢራን ፓርላማ አፈ ጉባዔ ሞሐመድ ባጋር ጋሊባፍ

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    የኢራን ፓርላማ አፈ ጉባዔ ሞሐመድ ባጋር ጋሊባፍ አሜሪካ አዲስ ጦርነት ለመጀመር ትፈልጋለች ሲሉ ተናገሩ። አፈጉባዔው አክለውም አሜሪካ እስላማዊ ሪፐብሊክ ኢራን እጅ እንደምትሰጥ ተስፋ ታደርጋለች ብለዋል።

    ጋሊባፍ በኢራን መገናኛ ብዙኃን ላይ በሰጡት የድምጽ አስተያየት “ጠላት በግልጽም ሆነ በስውር የሚያደርገው እንቅስቃሴ ከፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጫና ባሻገር ወታደራዊ ዓላማዎቹን ፈጽሞ እንዳልተዋቸው እና አዲስ ጦርነት ለመጀመር እንደሚፈልግ ያሳያል” ብለዋል።

    አፈ ጉባዔው አክለውም “ሁኔታውን በቅርበት ስንከታተለው ዩናይትድ ስቴትስ ኢራናውያን እጃቸውን ይሰጣሉ ብላ ተስፋ ታደርጋለች” ብለዋል።

    ታስኒም የዜና ወኪል ላይ በድምጽ በተላለፈ መልዕክታቸው የአገሪቱ መከላከያ በተኩስ አቁሙ ወቅት “ጥንካሬውን ዳግም መገንባቱን” ተናግረዋል።

    ጋሊባፍ “ጠላት ኢራንን ዳግም ቢያጠቃ እንዲጸጸት እናደርገዋለን” ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን ላይ ዳግመኛ ጦርነት ለመክፈት ጥቂት ሰዓት ሲቀራቸው ሃሳባቸውን መለወጣቸውን ተናግረው ነበር።

    ፕሬዚዳንቱ የኢራን ባለሥልጣናት ከአሜሪካ ጋር ስምምነት ላይ ለመድረስ “እየለመኑ” እንደነበረም ገልጸዋል።

    ትራምፕ በድጋሚ ኢራን ላይ ጥቃት መሰንዘር ሊያስፈልግ ይችላል ማለታቸውም ተዘግቧል።

    ከኢራን ጋር በቀጣይ ቀናት ስምምነት ላይ ካልተደረሰ ጥቃት መፈጸም እንደሚቀጥሉ አስጠንቅቀዋል።

  4. 6 ሚሊዮን በርሜል ነዳጅ የጫኑ መርከቦች የሆርሙዝ ወሽመጥን አቋረጡ

    በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ የምትቀዝፍ መርከብ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ለሁለት ወራት በባሕረ ሰላጤው አገራት ቆመው የነበሩ ሦስት ግዙፍ ነዳጅ ጫኝ መርከቦች ረቡዕ ዕለት የሆርሙዝ ወሽመጥን ማቋረጣቸው ተገለጸ።

    ከመካከለኛው ምሥራቅ ወደ ቻይና እና ደቡብ ኮሪያ የሚጓጓዝ 6 ሚሊዮን በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ የጫኑ ናቸው የተባሉት እነዚህ መርከቦች ወደ እስያ ጉዞ መጀመራቸውን ኤልኤስኢጂ እና ኬፕለር የተባሉ የመርከብ እንቅስቃሴን የሚከታተሉ ተቋማት አስታውቀዋል።

    እነዚህ ግዙፍ ነዳጅ ጫኝ መርከቦች በዚህ ወር ኢራን እንዲያልፉ ከፈቀደችላቸው እና ባሕረ ሰላጤውን ለቅቀው ከወጡ በጣት የሚቆጠሩ መርከቦች መካከል መሆናቸው ተገልጿል።

    የካቲት 21 2018 ዓ.ም. እስራኤል እና አሜሪካ በቴህራን ላይ ጦርነት ከከፈቱ በኋላ የዓለም አንድ አምስተኛ ነዳጅ የሚተላለፍበት ሆርሙዝ በመዘጋቱ ከፍተኛ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ተከስቷል።

    የደቡብ ኮሪያን ባንዲራ የሚያውለበልበው እና 2 ሚሊዮን በርሜል የኩዌት ድፍድፍ ነዳጅን የጫነው ግዙፍ መርከብ ሁለት የቻይና መርከቦችን ተከትሎ ወሽመጡን ረቡዕ ዕለት አቋርጧል።

    የኬፕለር መረጃ እንደሚያሳየው መርከቡ ጭነቱን ለማራገፍ የአገሪቱ የነዳጅ ማጣሪያ ወደሚገኝበት ኡስላን እያመራ ነው።

    የደቡብ ኮሪያ ኤነርጂ ኩባንያ ኤስኬ ኢነርጂ በጉዳዩ ላይ መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል።

  5. የዓለም ጤና ድርጅት በኢቦላ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ከዚህ በላይ እንደሚጨምር አስታወቀ

    የዲሞክራቲክ ኮንጎ ባለሥልጣናት 51 ሰዎች በኢቦላ መያዛቸው በምርመራ መረጋገጡን አስታውቀዋል

    የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, የዲሞክራቲክ ኮንጎ ባለሥልጣናት 51 ሰዎች በኢቦላ መያዛቸው በምርመራ መረጋገጡን አስታውቀዋል

    የዓለም ጤና ድርጅት በኢቦላ መያዛቸው የተጠረጠረ ሰዎች 600 መድረሳቸውን እና በቫይረሱ ምክንያቱ እንደሞቱ የሚገመቱ ሰዎች ቁጥር ደግሞ 139 መድረሱን አስታወቀ።

    ድርጅቱ አክሎም ቫይረሱን ለመመርመር ረዘም ያለ ጊዜ በመውሰዱ የሟቾች ቁጥር ሊያሻቅብ እንደሚችል ተናግሯል።

    በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ብቻ 51 ሰዎች በኢቦላ መያዛቸው ሲረጋገጥ በጎረቤት ኡጋንዳ ደግሞ አንድ ግለሰብ በቫይረሱ መያዙ በምርመራ ተደርሶበታል ሲሉ የዓለም ጤና ድርጅት ኃላፊ የሆኑት ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ረቡዕ ዕለት ተናግረዋል።

    በጄኔቫ ለጋዜጠኞች መግለጫ የሰጡት ኃላፊው በአሁን ሰዓት የተከሰተው የኢቦላ ቫይረስ ቡንዲቡግዮ የተባለው ዝርያ ሲሆን “ከሁለት ወራት በፊት” መሰራጨት እንደጀመረ ይገመታል ብለዋል።

    እሁድ ዕለት የዓለም ጤና ድርጀት ባይረሱ ወረርሽኝ የሚባል ደረጃ ላይ አለመድረሱን በመግለጽ የዓለም አቀፍ ስጋት የሆነ የኅብረተሰብ ጤና አደጋ ነው ሲል አውጇል።

    ዶ/ር ቴድሮስ የድርጅቱ ጤና ባለሙያዎች ማክሰኞ ዕለት ተሰብስበው “የወረርሽኝ አደጋ” አለመሆኑ ላይ መስማማታቸውን ተናግረዋል።

    "ድርጅቱ የጤና ስጋቱን በብሔራዊ እና ቀጣናው ደረጃ ከፍተኛ መሆኑን በዓለም አቀፍ ደረጃ ግን አነስተኛ መሆኑን ገምግሟል” ብለዋል።

    በኢቦላ መያዛቸው በምርመራ የተረጋገጠው የዲሞክራቲክ ኮንጎ ዜጎች የሚኖሩት ቫይረሱ በጀመረበትት ኢቱሪ ነው። በኡጋንዳ በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሁለት ሕሙማን ደግሞ ከኮንጎ መትተው ካምፓላ ያረፉ መሆናቸው ተገልጿል።

    የድርጅቱ ኃላፊ “በኮንጎ ያለው ስርጭት ሰፊ መሆኑን እናውቃለን” ሲሉ አክለዋል።

    በኮንጎ በቫይረሱ መያዝዋ የተረጋገጠው የመጀመርያዋ ሴት ነርስ ናት።

    ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ከዚህ ቀደም 17 ጊዜ የኢቦላ ወረርሽኝ አጋጥሟት የሚያውቅ ቢሆንም ቡዲቡግዮ የተባለው ዝርያ ግን ላለፉት አስርት ዓመታት ተከስቶ አያውቅም።

  6. ቻይና ከዶናልድ ትራምፕ ጉብኝት በኋላ 200 ቦይንግ አውሮፕላኖችን እንደምትገዛ አረጋገጠች

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና ዢ ጂንፒንግ

    የፎቶው ባለመብት, AFP

    ቻይና የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና ዢ ጂንፒንግ ባለፈው ሳምንት በቤይጂንግ ከተገናኙ በኋላ 200 የቦይንግ አውሮፕላኖችን ለመግዛት መስማማቷን አረጋገጠች።

    በስምምነቱ መሠረት አሜሪካ ለአውሮፕላን ሞተር ክፍሎች እና መለዋወጫዎች የሚያገለግሉ ቁሳቁሶችን ለቻይና እንደምትሰጥ የቤይጂንግ የንግድ ሚኒስቴር ረቡዕ ዕለት አስታውቋል።

    ሁለቱ ወገኖች በጥቅምት ወር የተስማሙበትን የታሪፍ ቅነሳ ለማራዘም እና እያንዳንዳቸው 30 ቢሊዮን ዶላር ወይም ከዚያ በላይ በሚያወጡ እቃዎች ላይ የታሪፍ ቅነሳ ለማድረግ እንደሚሰሩ ሚኒስቴሩ ጠቅሷል።

    ቻይና ይህንን ይፋ ያደረገችው ትራምፕ ቤይጂንግን ከጎበኙ ከጥቂት ቀናት በኋላ እና የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ወደ አገሪቱ መጥተው ከፕሬዚዳንቱ ጋር ውይይት እያደረጉ ባለበት ወቅት ነው።

    ትራምፕ በቻይና በነበራቸው ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ወቅት በሁለቱ አገራት መካከል በርካታ የንግድ ስምምነቶች ተደርሷል። ከእነዚህም መካከል የአሜሪካ ገበሬዎች ወደ ቻይና ገበያ በቀላሉ እንዲገቡ ማድረግ የሚለው ይገኝበታል።

    ትራምፕ አርብ ዕለት የቻይና ጉብኝታቸውን አጠናቅቀው ወደ አገራቸው ሲመለሱ ለጋዜጠኞች "ከቦይንግ ከ200 በላይ አውሮፕላኖችን መግዛትን ጨምሮ ብዙ ጥሩ የሚባሉ የንግድ ስምምነቶችን አድርገናል፤ 750 አውሮፕላኖችን ለመግዛት ፍላጎት አሳይተዋል። ይህም እስካሁን ድረስ ከነበረው ትልቁ ትዕዛዝ ይሆናል" ብለዋል።

    ከትራምፕ ጋር ወደ ቻይና ከተጓዙት የንግድ ልዑካን መካከል የቦይንግ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኬሊ ኦርትበርግ እንዲሁም የቴስላ ኃላፊ ኤለን መስክ እና የግዙፉ ናቪዲያ የአይአይ ቺፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ጄንሰን ሁዋንግም ይገኙበታል።

    ቦይንግ ከጉብኝቱ በኋላ ባወጣው መግለጫ "ወደ ቻይና በጣም የተሳካ ጉዞ አድርገናል እናም የቻይና ገበያን ለቦይንግ አውሮፕላኖች እንደገና የማስከፈት ዋና ግባችንን አሳክተናል" ብሏል።

    "ይህም መጀመሪያ 200 አውሮፕላኖችን ለመግዛት የተደረሰ ስምምነትን ያካትታል፤ ከዚህ የመጀመሪያ ስምምነት በኋላም ተጨማሪ ትዕዛዞች እንደሚመጡ እንጠብቃለን" ሲል አክሏል።

    የቻይና እና የአሜሪካ ባለሥልጣናት እአአ በጥቅምት 2025 በደቡብ ኮሪያ ባካሄዱት ስብሰባ ላይ እስከ ኅዳር ወር ድረስ የታሪፉን ገደብ ለማራዘም ስምምነት ላይ ደርሰዋል።

    ይህ ስምምነት የአሜሪካን የቻይና እቃዎች ላይ የሚጣሉትን ታሪፍ መቀነስ እና ቤይጂንግ ብርቅዬ ማዕድናት እና ማግኔቶችን ወደ ውጭ መላክ ላይ የጣለችውን ገደብ ማንሳትን ያካትታል።

  7. ሩሲያ እና ቻይና የአሜሪካን “ወታደራዊ ጀብዱዎች” አወገዙ

    የቻይና ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ እና የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ሩሲያ እና ቻይና በጋራ ባወጡት መግለጫ አሜሪካ የምትፈጽማቸውን “ወታደራዊ ጀብዱዎች” አወገዙ።

    አሜሪካ “በመላው ዓለም የምታካሂዳቸውን ወታደራዊ ጀብዱዎች” እንደሚያወግዙ የሁለቱ አገራት ፕሬዝዳንቶች ገልጸዋል።

    የቻይና ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ እና የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በቤጂንግ ከተወያዩ በኋላ ባወጡት የጋራ መግለጫ “በሌሎች አገራት የሚፈጸሙ ድንገተኛ ወታደራዊ ጥቃቶችን” ተችተዋል።

    የሁለቱ አገራት መግለጫ ኢራን እና ቬንዝዌላን እንደሚመለከት ይታመናል።

    በመግለጫቸው “ድርድርን በመጠቀም ጥቃት መፈጸምን፣ የሉዓላዊ አገራት መሪዎችን መግደልን፣ በአገራት የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባትን፣ በአደባባይ መሪዎችን ይዞ ለፍርድ ማቅረብን እና የመንግሥት ለውጥ ለማድረግ መሞከርን” አውግዘዋል።

    አሜሪካ የምትወስዳቸው እርምጃዎች የመንግሥታቱ ድርጅትን ስምምነቶች እና ዓለም አቀፍ ሕግጋት “ክፉኛ” እንደሚጥሱም ገልጸዋል።

  8. ኢራን በድጋሚ ጥቃት ከተከፈተባት ግጭቱ “ቀጣናውን እንደሚሻገር” አስጠነቀቀች

    የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ወታደሮች

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ በድጋሚ ጥቃት ከሰነዘሩ ግጭቱ “ከቀጠናውም ያለፈ እንደሚሆን” የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ አስጠነቀቀ።

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና እስራኤል በድጋሚ ኢራን ላይ ጥቃት ለመጀመር እየዛቱ ይገኛሉ።

    የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ባወጣው መግለጫ “ኢራን ላይ በድጋሚ ወረራ ከተፈጸመ፤ ቀጣናውን ያዳርሳል የተባለው ጦርነት ከቀጣናውም ይሻገራል” ብሏል።

    “የምንወስደው ደምሳሽ እርምጃ አስባችሁ የማታውቁት ቦታ ሳይቀር ይደርሳል” ሲልም አብዮታዊ ዘቡ አስጠንቅቋል።

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ አሜሪካ በድጋሚ ጥቃት መሰንዘር ከጀመረች “ብዙ አዳዲስ ነገር ይጠብቃታል” በማለት ለትራምፕ ዛቻ ምላሽ ሰጥተዋል።

  9. አሜሪካ እና እስራኤል ማህሙድ አህመዲነጃድን ወደ ኢራን መሪነት ለማምጣት ዕቅድ እንደነበራቸው ተዘገበ

    የኢራን የቀድሞ ፕሬዝዳንት ማህሙድ አህመዲነጃድ

    የፎቶው ባለመብት, EPA-EFE/REX/Shutterstock

    የምስሉ መግለጫ, የኢራን የቀድሞ ፕሬዝዳንት ማህሙድ አህመዲነጃድ

    አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ በፈጸሙት የመጀመሪያ ጥቃት ወቅት በቁም እስር ላይ ናቸው የተባሉትን የኢራን የቀድሞ ፕሬዝዳንት ማህሙድ አህመዲነጃድን ለማስለቀቅ እና የመንግሥት ለውጥ ለማምጣት የተቃደ ዓላማ እንደነበረው የአሜሪካው ጋዜጣ ኒው ዮርክ ታይምስ ዘገበ።

    ጋዜጣው እንዳለው የእስራኤልን የመጀመሪያ ዙር ጥቃት ተከትሎ የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ከተገደሉ በኋላ ፕሬዝዳንት ትራምፕ በይፋ ሁኔታው የአገሪቱን አመራር ለመረከብ “አገር ውስጥ ላለ አንድ ሰው የተሻለ ነው” ሲሉ ተናግረው ነበር ሲል አስታውሷል።

    “ይህም አሜሪካ እና እስራኤል ወደ ጦርነቱ የገቡት ግልጽ የሆነ እና ያልተጠበቀ ዓላማን ይዘው እንደሆነ አሁን ግልጽ ሆኗል” በማለት “በፀረ እስራኤል እና አሜሪካ ጠንካራ አቋማቸው የሚታወቁት የቀድሞው የኢራን ፕሬዝዳንት መሐሙድ አህመዲነጃድ” ምርጫቸው እንደነበሩ ዘግቧል።

    ኒው ዮርክ ታይምስ “ስለ ዕቅዱ ገለጻ የተደረገላቸው የአሜሪካ ባለሥልጣናት ይህ ያልተጠበቀ ሐሳብ የተዘጋጀው በእስራኤል መሆኑን እና አህመዲነጃድም እንደሚያውቁት ተደርጎ የነበረ ቢሆንም በፍጥነት ከታሰበው ውጪ ሆኗል” በማለት ገልጿል።

    የቀድሞውን ፕሬዝዳንት ከቁም እስር ለማስለቀቅ በመኖሪያ ቤታቸው ላይ ጥቃት የተፈጸመ ሲሆን ዜናውም በተነገረበት ጊዜ አህመዲነጃድ በጥቃቱ መገደላቸው ቢዘገብም በአጭር ጊዜ ውስጥ በሕይወት እንዳሉ የማስተባበያ ዜናዎች ወጥተዋል።

    ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ ባለፉት ሦስት ወራት ማህሙድ አህመዲነጃድ በጥቃቱ ስለደረሰባቸው ጥቃትም ሆነ ስላሉበት ሁኔታ ምንም የተነገረ ነገር ካለመኖሩም በተጨማሪ በይፋ ታይተው አይታወቁም።

  10. በእስራኤል ጥቃት ቢያንስ 19 ሰዎች መገደላቸው ተገለጸ

    በደቡብ ሊባኖስ የደረሰው ጥቃት

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    እስራኤል በደቡብ ሊባኖስ ባደረሰችው የአየር ጥቃት ቢያንስ 19 ሰዎች መገደላቸውን የአገሪቱ ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

    ከተገደሉት መካከል ሦስት ሕጻናት እና ሦስት ሴቶች እንደሚገኙበት ተገልጿል።

    አሥር የሚደርሱት ሰዎች በዲር ቆኖን ከተማ አንድ ቤት ላይ በተፈጸመ ጥቃት መገደላቸው የጤና ሚኒስቴር ይፋ አድርጓል።

    አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ ጦርነት መክፈታቸውን ተከትሎ የሊባኖስ ታጣቂ ቡድን ሄዝቦላህ የውጊያው አካል ሆኗል።

    እስራኤል እና ሊባኖስ የተኩስ አቁም ስምምነታቸውን በ45 ቀናት ማራዘማቸውን የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው ሳምንት ቢናገሩም፤ ጥቃቶች መቀጠላቸው ተገልጿል።

    አብዛኛው ጥቃት እየደረሰ ያለው በደቡብ ሊባኖስ ነው። እስራኤል ሄዝቦላህን ዒላማ ማድረጓን ብትገልጽም ሕጻናትን ጨምሮ ንጹኃን ዜጎችም መገደላቸውን ሊባኖስ አስታውቃለች።

  11. የቻይናው ፕሬዝዳንት የመካከለኛው ምሥራቅ ሁኔታ “ቁልፍ የሆነ ነጥብ ላይ” ደርሷል አሉ

    የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ

    የፎቶው ባለመብት, GETTY IMAGES

    የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ የመካከለኛው ምሥራቅ ሁኔታ “ቁልፍ የሆነ ነጥብ ላይ” ደርሷል ማለታቸው ተገለጸ።

    የቻይና ብሔራዊ ጣቢያ እንደዘገበው አሁን ያለው ሁኔታ ከጦርነት ወደ ሰላም የሚደረግ ሽሽግር ላይ የሚገኝ ነው ብለዋል።

    የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንን እያስተናገዱ የሚገኙት ጂንፒንግ “ግጭቱን በድጋሚ መጀመር ተቀባይነት የለውም” ሲሉም ተናግረዋል።

    በመካከለኛው ምሥራቅ ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍን ባለ አራት ነጥብ ምክረ ሐሳብ ማቅረባቸውን የተናገሩት ፕሬዝዳንቱ “ዓላማዬ ዓለም አቀፍ ስምምነት መፍጠር እና ውጥረትን ማርገብ” ብለዋል።

    ባለፈው ወር ከአቡ ዳቢ ልዑል አልጋ ወራሽ ሼኽ ካሊድ ቢን መሐመድ ዛይን አል ናህያ ጋር በተገናኙበት ወቅት ባለ አራት ነጥብ ምክረ ሐሳብ አቅርበዋል።

    ምክረ ሐሳቡ ሰላም፣ ብሔራዊ ልዕልና፣ ዓለም አቀፍ ሕግ ማክበር እንዲሁም ለልማት እና ደኅንነት መተባበር ላይ የተመረኮዘ ነው ተብሏል።

  12. አሜሪካ በድጋሚ ጥቃት ከከፈተች “ብዙ አዳዲስ ነገር ይጠብቃታል” ስትል ኢራን አስጠነቀቀች

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ

    የፎቶው ባለመብት, EPA/Shutterstock

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ አሜሪካ በድጋሚ ጥቃት መሰንዘር ጀመረች “ብዙ አዳዲስ ነገር ይጠብቃታል” በማለት ለፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዛቻ ምላሽ ሰጡ።

    ትራምፕ ቴህራን ላይ በድጋሚ ጥቃት ለመክፈት መዛታቸውን ተከትሎ “ወደ ውጊያ አውድማ ከተመለሱ ብዙ አዳዲስ ነገር እንደሚጠብቃቸወ ላረጋግጥ እወዳለሁ” ሲሉ አራግቺ አስጠንቅቀዋል።

    አራግቺ በኤክስ ገጻቸው “የኢራን ጦርነት ከተጀመረ ከወራት በኋላ በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር የጦር አውሮፕላን መውደሙን የአሜሪካ ምክር ቤት አምኗል” ብለዋል።

    “ኃያል የሆነው ጦራችን ኤፍ-35 ተዋጊ ጀትን መትቶ በመጣል የመጀመሪያው መሆኑ ተረጋግጧል” ሲሉም አክለዋል።

    ትራምፕ በበኩላቸው ኢራን ላይ ዳግመኛ ጦርነት ለመክፈት ሊወስኑ “አንድ ሰዓት ሲቀራቸው” ሐሳባቸውን መለወጣቸውን ገልጸዋል።

    የኢራን ባለሥልጣናት ከአሜሪካ ጋር ስምምነት ላይ ለመድረስ “እየለመኑ” እንደነበረ ተናግረዋል። ትራምፕ በድጋሚ ኢራን ላይ ጥቃት መሰንዘር ሊያስፈልግ ይችላል ማለታቸውም ተዘግቧል።

    የኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ለትራምፕ ዛቻ በሰጡት ምላሽ “ወደ ውጊያ አውድማው ከተመለሱ፤ ባገኘነውን ትምህርት እና ተሞክሮ አማካኝነት ብዙ አዳዲስ ነገሮች እናሳያቸዋለን” ብለዋል።

    ትራምፕ ኢራን ላይ ጥቃት ሊከፍቱ ይዘውት የነበረውን ዕቅድ በባሕረ ሰላጤው አገራት ጥያቄ መሠረት መሰረዛቸውን አስታውቀዋል።

    ሳዑዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና ኳታር ለድርድር ዕድል እንዲሰጥ እንደጠየቁ ተገልጿል።

  13. ትራምፕ ኢራንን ዳግም ለማጥቃት ሊወስኑ “አንድ ሰዓት ሲቀራቸው” ሐሳባቸውን እንደለወጡ ተናገሩ

    ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Bloomberg via Getty Images

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን ላይ ዳግመኛ ጦርነት ለመክፈት ሊወስኑ “አንድ ሰዓት ሲቀራቸው” ሐሳባቸውን መለወጣቸውን ተናገሩ።

    የኢራን ባለሥልጣናት ከአሜሪካ ጋር ስምምነት ላይ ለመድረስ “እየለመኑ” እንደነበረም ገልጸዋል።

    ትራምፕ በድጋሚ ኢራን ላይ ጥቃት መሰንዘር ሊያስፈልግ ይችላል ማለታቸውም ተዘግቧል።

    ከኢራን ጋር በቀጣይ ቀናት ስምምነት ላይ ካልተደረሰ ጥቃት መፈጸም እንደሚቀጥሉ አስጠንቅቀዋል።

    “ሁለት ወይም ሦስት ቀን ያለው። አርብ፣ ቅዳሜ፣ እሑድ ወይም ቀጣይ ሳምንት። ውስን ዕድል አለ። የኒውክሌር መሣሪያ እንዲታጠቁ መፍቀድ የለብንም” ብለዋል።

    ትራምፕ ዛሬ ማክሰኞ ኢራን ላይ ጥቃት ሊከፍቱ ይዘውት የነበረውን ዕቅድ በባሕረ ሰላጤው አገራት ጥያቄ መሠረት መሰረዛቸውን አስታውቀዋል።

    ሳዑዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና ኳታር ለድርድር ዕድል እንዲሰጥ እንደጠየቁ ተገልጿል።

    ኢራን እና አሜሪካ “በጣም ተቀባይነት ያለው” ስምምነት ላይ እንደሚደርሱ ሦስቱ አገራት እንደገለጹላቸው ትራምፕ ጠቅሰዋል።

  14. በኬንያ በነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ምክንያት የተጠራው አድማ ከመንግሥት ጋር ለመደራደር ተቋረጠ

    አድመኞች

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የኬንያ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች በነዳጅ ዋጋ መጨመር ምክንያት በመላው አገሪቱ ለሁለት ቀናት ያካሄዱት የሥራ ማቆም አድማ ከመንግሥት ጋር ድርድር ካደረጉ በኋላ ለጊዜው እንዲቋረጥ አደረጉ።

    እስከሚቀጥለው ማክሰኞ ድረስ አድማው የቆመው የትራንስፖርት ማኅበራቱ ከመንግሥት ጋር ለሚያደርጉት ድርድር አመቺ ሁኔታን ለመፍጠር ነው ብለዋል።

    ሰኞ እና ማክሰኞ የተካሄደው የትራንስፖርት ማቆም አድማ ለጊዜው የተቋረጠው ዋና ከተማዋን እና ሌሎች የአገሪቱን ከተሞች እንቅስቃሴ ቀጥ እንዲል ካደረገ በኋላ ነው።

    የኬንያ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ኪፕቹምባ ሙርኮሜን እንዳሉት አድማውን ያስቆመው ስምምነት የተደረሰው ከሕዝብ ትራንስፖርት ሰጪ ተወካዮች ጋር ምክክር ከተደረገ በኋላ “በከፍተኛ ደረጃ” ንግግሩን ለመቀጠል በመግባባቸታው ነው።

    ሰኞ ዕለት ከመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ውይይት ከተደረገ በኋላ የአገሪቱ ኤነርጂ ሚኒስትር ከፍተኛ ጭማሪ ተደርጎበት በነበረው የናፍጣ ዋጋ ቅናሽ መደረጉን ቢገልጹም ተጨማሪ ቅናሽ በመጠየቅ አድማው ቀጥሎ ነበር።

    ከአድማው ጋር ተያይዞ በተከሰተ ጉዳት ቢያንስ አራት ሰዎች ሲገደሉ 30 ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን እንዲሁም ከ700 በላይ ሰዎች መታሰራቸውን ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።

  15. ኢቦላ መጀመሪያ ከተገመተው በላይ በፍጥነት እየተሰራጨ ሊሆን እንደሚችል የዓለም የጤና ድርጅት ሐኪሞች አስጠነቀቁ

    ሕፃን አዝላ እጇን የምትታጠብ ሴት

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ተቀስቅሶ የተገኘው ኢቦላ በጎረቤት ኡጋንዳም ተገኝቷል

    በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ዳግም የተቀሰቀሰው ኢቦላ 131 ሰዎችን ሲገድል፤ የዓለም የጤና ድርጅት ተወካዮች ከታሰበው በላይ በፍጥነት ሊሰራጭ እንደሚችል ማስጠንቀቂያ ሰጡ።

    ዶ/ር አን አኒሲያ ለቢቢሲ ድርጅቱ ምርመራውን ባጠናከረ ቁጥር በሽታው በሌሎች አካባቢዎች መዛመቱ ግልፅ ሆኗል ብለዋል።

    እስከ ማክሰኞ ድረስ 513 ሕሙማን መኖራቸው በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የተመዘገበ ሲሆን በኡጋንዳ የአንድ ሰው ሕይወት አልፏል።

    ይሁን እንጂ መቀመጫውን ለንደን ያደረገ የተላላፊ በሽታዎች ማዕከል ሠኞ ዕለት ይፋ ባደረገው ትንታኔ አሁንም በኢቦላ መያዛቸው ያልታወቀ ሕሙማን መኖራቸውን እና ከአንድ ሺህ በላይ ሰዎች በቫይረሱ ተይዘው ሳይገኙ እንዳልቀረ ጠቁሟል።

    ባለፈው ሳምንት በሽታውን ዓለም አቀፍ ድንገተኛ አደጋ ሲሉ ያወጁት የዓለም የጤና ድርጅት ኃላፊ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም “መጠኑ እና የበሽታው ፍጥነት በጣም እንዳሳሰባቸው” ተናግረዋል።

    በሽታው በሚያዚያ መጨረሻ ከመገኘቱ በፊት ለሣምንታት ቆይቷል የሚል ስጋት አለ።

    አሁን የተቀሰቀሰው የኢቦላ ቫይረስ ዝርያ ክትባት የሌለው ሲሆን፤ የዓለም የጤና ድርጅት ሌሎች መድኃኒቶች መከላከያ ሊሆኑ የሚችሉ ከሆነ በሚል ምርመራ እያረገ ነው።

  16. ኢራን በጦርነቱ ለደረሰባት ውድመት ካሳ እንዲሁም የአሜሪካ ወታደሮች እንዲወጡ የሚጠይቅ ሃሳብ አቀረበች

    ኢራናውያን ባንዲራ ይዘው

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ኢራን በሁሉም ግንባሮች የተከፈቱ ጦርነቶች እንዲቆሙ እና ለደረሰባት ጉዳት ካሳ እንዲከፈላት የሚጠይቅ የስምምነት ሃሳብ አቀረበች።

    አዲሱ የሰላም ዕቅድ በሊባኖስ ውስጥ የሚካሄደውን ጨምሮ በሁሉም ግንባሮች የሚደረጉ ጦርነቶች እንዲቆሙ፣ በኢራን አቅራቢያ የሰፈሩ የአሜሪካ ወታደሮች እንዲወጡ እና በጦርነቱ ለደረሰባት ውድመት ካሳን እንዲከፈላት የሚጠይቅ መሆኑን የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

    ቴህራን የሰላም ዕቅዱን በሚመለከት በሰጠችው የመጀመሪያ አስተያየት ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ካዘም ጋሪባባዲ ማዕቀቦች እንዲነሱ፣ እንዳይንቀሳቀሱ የታገዱ ንብረቶቿ እንዲለቀቁ አንዲሁም የአሜሪካ ባሕር ኃይል የጣለውን እገዳ እንዲያነሳ መጠየቃቸውን ኢርና የዜና ወኪል ዘግቧል።

    የኢራን መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት ከሆነ የቴህራን አዲሱ ዕቅድ ከዚህ በፊት ካቀረበችው እና የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ “ቆሻሻ” ሲሉ ውደቅ ካደረጉት ብዙም የተለየ አይደለም።

    ትራምፕ ሰኞ ዕለት አቅደውት የነበረውን ጥቃት ያቆሙት ቴህራን ለዋሺንግተን አዲስ ሰላም ዕቅድ መላኳን ተከትሎ መሆኑን ተናግረው፤ የኢራንን የኒውክሌር ፕሮግራም ለመገደብ እና ከስምምነት ላይ ለመድረስ “በጣም ጥሩ ዕድል አለ” ብለዋል።

    ትራምፕ በማኅበራዊ ሚዲያ ልጥፋቸው ላይ ኳታር፣ ሳዑዲ አረቢያ እና ዩናይትድ አረብ ኤሜሬትስ “አሜሪካ እንዲሁም የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ሊቀበሉት የሚችሉት ስምምነት ላይ ሊደረስ ይችላል” በማለት ጥቃቱ እንዲዘገይ መጠየቃቸውን ተናግረዋል።

    ዶናልድ ትራምፕ ሰኞ ዕለት ቴህራን የኒውክሌር የጦር መሣሪያ እንዳታገኝ የሚያደርግ ስምምነት ላይ መድረስ ከተቻለ ደስተኛ እንደሚሆኑ ተናግረዋል።

  17. ጋና ዜጎቿን ከደቡብ አፍሪካ የፊታችን ሐሙስ ልታስወጣ ነው

    በበርካታ የደቡብ አፍሪካ ከተሞች ጸረ ስደተኛ ሠልፎች ተካሄደዋል

    የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, በበርካታ የደቡብ አፍሪካ ከተሞች ጸረ ስደተኛ ሠልፎች ተካሄደዋል

    የጋና ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሐሙስ ዕለት ዜጎቹን ከደቡብ አፍሪካ ሊያስወጣ መሆኑን አስታወቀ።

    የጋና መንግሥት ከዚህ በፊት 300 ዜጎቹን ከደቡብ አፍሪካ ለማስወጣት ምዝገባ ማከናወኑን ገልጾ የነበረ ሲሆን የመጓጓዣ ሙሉ ወጪያቸውንም እንደሚሸፍን ተናግሯል።

    የጋና ፕሬዚዳንት ጆን ማሃማ በደቡብ አፍሪካውያን የጸረ ስደተኞች ሰልፍ መካሄዱን ተከትሎ ዜጎቻቸውን በአስቸኳይ ለማስወጣት ትዕዛዝ ማስተላለፋቸው ተነግሯል።

    የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሳሙኤል ኦኩድዜቶ አብላክዋ በኤክስ ገጻቸው ላይ የጋናውያን ደህንነት ያለምንም ድርድር ቅድሚያ የሚሰጠው መሆኑን ጽፈዋል።

    የመጀመርያው ዙር መንገደኞች ሐሙስ ዕለት 5 ሰዓት ላይ ከኦ አር ታምቦ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ እንደሚነሱ ተገልጿል።

    አንድ ጋናዊ በተቃዋሚዎች ተከብቦ ሲወዋከብ የሚያሳይ ቪዲዮ በስፋት ከተዘዋወረ በኋላ በጋና እና በደቡብ አፍሪካ መካከል ዲፕሎማሲየዊ ውጥረቱ ተባብሷል።

    ሁለቱ አገራት ውጥረቱን ለማርገብ በተደጋጋሚ ንግግሮች ቢያደርጉም የጋና መንግሥት ለዜጎቹ ደህንነት ቅድሚያ እንደሚሰጥ በመግለጽ እርምጃዎቹን መውሰዱን ቀጥሏል።

    ናይጄሪያም ፈቃደኛ የሆኑ ዜጎቿን ከደቡብ አፍሪካ ለማስወጣት ዝግጁ መሆኗን አስታውቃለች።

    በደቡብ አፍሪካ በተደጋጋሚ ጸረ ስደተኛ ሰልፎች የተካሄዱ ሲሆን አፍሪካውያን ስደተኞች ዒላማ ተደርገው ጥቃት ደርሶባቸዋል።

    ባለፈው ሳምንት የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ በስደተኞች ላይ ጥቃት የሚፈጽሙ ተቃዋሚ ሠልፈኞችን ኮንነው የአገሪቱን የስደተኛ ፖሊስ ለማሻሻል ቃል ገብተዋል።

    እንዲህ ዓይነት ተግባር ደቡብ አፍሪካንም ሆነ ፖሊሲዎቿን አይወክልም ያሉት ፕሬዚዳንቱ ሁሉም የአገሪቱን ሕግ እዲያከብር ጠይቀዋል።

  18. ዶናልድ ትራምፕ ኢራን ላይ ለመፈጸም ያሰቡትን ጥቃት ካዘገዩ በኋላ ከሥምምነት ላይ ለመድረስ “ጥሩ ዕድል” መኖሩን ተናገሩ

    ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሰኞ ዕለት ኢራን የጦር መሣሪያ እንዳይኖራት ለማድረግ የሚያስችል ስምምነት ላይ ለመድረስ “በጣም ጥሩ ዕድል” መኖሩን ተናገሩ።

    ትራምፕ ይህንን የተናገሩት በኢራን ላይ ጥቃት ለመፈጸም ይዘውት የነበረውን ዕቅድ ካዘገዩ ከሰዓታት በኋላ ነው።

    ፕሬዚዳንቱ ቁልፍ የመካከለኛው ምሥራቅ አጋሮቻቸው ማክሰኞ ዕለት ለመፈጸም አቅደውት የነበረውን ዕቅድ ከቴህራን ጋር የሚደረገው ድርድር እንዲቀጥል በሚል እንዲያዘገዩት መጠየቃቸውን ተናግረዋል።

    ትራምፕ ሰኞ ዕለት ለጋዜጠኞች "አንድን ነገር ላይ ለመድረስ የሚያስችል በጣም ጥሩ ዕድል ያለ ይመስላል። በቦምብ ሳንደበድባቸው ያንን ማድረግ ከቻልን በጣም ደስተኛ እሆናለሁ" ብለዋል።

    የዩናይትድ ስቴትስ ጦር ስምምነት ላይ ካልተደረሰ ጥቃት ለመፈጸም ዝግጁ መሆኑን ፕሬዚዳንቱ ጨምረው አስታውቀዋል።

  19. በአሜሪካ መስኪድ ላይ በተከፈተ ተኩስ ሦስት ሰዎች መሞታቸው እና ተጠርጣሪዎቹ ራሳቸውን ማጥፋታቸው ተገለጸ

    በሳንዲያጎ ታዳጊዎች ባደረሱት ጥቃት የሞቱ ሰዎች ማንነት ገና ይፋ አልሆነም

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    ሁለት ታዳጊዎች ራሳቸውን ከማጥፋታቸው በፊት በአሜሪካ ሳንዲያጎ በሚገኝ መስኪድ ላይ ጥቃት ከፍተው ሦስት ሰዎች መግደላቸውን ፖሊስ አስታወቀ።

    ጥቃቱ የተፈጸመው ሰኞ ማለዳ ሲሆን ፖሊስ ተጨማሪ ምርመራ እያደረገ መሆኑን አስታውቋል።

    ፖሊስ በሳንዲያጎ በሚገኘው የሙስሊሞች ማዕከል ተኩስ መከፈቱን የሚገልጽ ጥቆማ አንደደረሰው ወደ ስፍራው ሲደርስ ሦስት ሰዎች በጥይት ተመትተው ማግኘቱን ገልጿል።

    ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ በአቅራቢው ከሚገኝ መኪና ውስጥ ተኩስ መሰማቱን የሚገልጽ መረጃ ደርሶት ወደ ሥፍራው ሲያመራ የ17 እና የ18 ዓመት ታዳጊዎች ራሳቸውን አጥፍተው ማግኘቱን አስታውቋል።

    የከተማዋ ባለሥልጣናት ጥቃት ከደረሰባቸው እና ከሞቱት መካከል አንዱ በጥቃቱ የባሰ ጉዳት እንዳይደርስ “ወሳኝ ሚና የተጫወተ” የማዕከሉ ዘብ መሆኑን ተናግረዋል።

    የሳንዲያጎ ፖሊስ አዛዥ ስኮት ዋህል በጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት “የጀግና ተግባር ነው የፈጸመው ማለት እንችላለን” ሲሉ አድንቀው “ያለምንም ጥርጥር ዛሬ ሕይወት አድኗል” ብለዋል።

    የከተማዋ ባለሥልጣናት የሟቾቹን ስም ይፋ አላደረጉም። ነገር ግን የማዕከሉ ዘብ የስምንት ልጆች አባት መሆኑን በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር የሆነው ሲቢኤስ ዘግቧል።

    መርማሪዎች ጥቃቱ የተፈጸመበት ምክንያት እንዳልተወቀ ተናግረዋል።

    ነገር ግን በሳንዲያጎ ግዙፍ በሆነው መስኪድ ላይ ጥላቻ ያላቸው ሊሆኑ አንደሚችሉ ተጠርጣሪው ከጻፈው በመነሳት ያላቸውን ጥርጣሬ ተናግረዋል።

  20. እስራኤል በሊባኖስ በፈጸመችው ድብደባ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ3,000 ማለፉን የአገሪቱ ባለሥልጣናት ተናገሩ

    በእስረኤል ጥቃት የሞቱ ቤተሰቦቻቸውን የሚቀብሩ ሴቶች

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, በእስራኤል እና በሊባኖስ መካከል የተኩስ አቁም ቢደረስም ከሄዝቦላህ ጋር የሚደረገው ውግያ እንደቀጠለ ነው

    የሊባኖስ ጤና ሚኒስቴር በእስራኤል ጥቃት የተገደሉ ሰዎች ቁጥር 3,000 ማለፉን አስታወቀ።

    እስራኤል እና ሄዝቦላህ ዳግም ወደ ግጭት የገቡት የኢራን ጦርነት በተጀመረ በሦስተኛው ቀን ነው።

    በሁለቱ አገራት መካከል በተደጋጋሚ የተኩስ አቁም ቢደረሰም አሁንም ውጊያዎች እየተካሄዱ ሲሆን ይህም ሰኞ ዕለት የሟቾችን ቁጥር 3,020 አድርሶታል።

    ሊባኖስ ዳግም ወደ ጦርነት ተጎትታ የገባችው በኢራን የሚደገፈው ሄዝቦላህ የቴህራኑ ጠቅላይ መሪ መገደላቸውን በመቃወም ወደ እስራኤል ሮኬቶችን በማስወንጨፉ ነው።

    አርብ ዕለት እስራኤል እና ሊባኖስ የተኩስ አቁማቸውን በ45 ቀናት ቢያራዝሙም የሟቾች ቁጥር እየጨመረ ነው።

    ሁለቱ አገራት ዳግም ድርድራቸውን በሰኔ ወር መጀመርያ ላይ ለመቀጠል ተስማምተዋል።

    የሊባኖስ ጤና ሚኒስቴር ከ400 በላይ ሰዎች የተገደሉት የተኩስ አቁም ስምምነቱ ሚያዚያ 9 2018 ዓ.ም. ከተደረሰ በኋላ ነው ሲል አስታውቋል።

    አሜሪካ ያደራደረችው ይህ የተኩስ አቁም ስምምነት እስራኤል የሄዝቦላህን ወታደራዊ እንቅስቃሴ ለመመከት ጥቃት እንድትፈጽም ይፈቅዳል።

    ሊባኖስ ጥቃቶቹን አውግዛ አገሪቱ ዳግም ታጣቂዎች የያዙትን መሣሪያ ለመቆጣጠር የምታደርገውን ጥረት ዝቅ የሚያደርግ ነው ብላለች።

    አርብ ዕለት ዳግመኛ የተኩስ አቁሙ ከተራዘመ በኋላ እስራኤል በደቡባዊ ሊባኖስ የሚገኙ መንደሮችን በማጥቃት በርካቶችን ገድላለች።

    ቅዳሜ ዕለት በበርካታ መንደሮች ላይ ጥቃት ብትፈጽምም አካበቢውን ለቅቀው እንዲወጡ ቅድመ ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው ግን ዘጠኙ ብቻ ናቸው።

    የዚያኑ ዕለት ሄዝቦላህ በርካታ የድሮን ጥቃቶችን በእስራኤል ላይ መፈጸሙን አስታውቋል።

    የእስራኤል ጦር ቅዳሜ ዕለት አንድ ወታደሩ መገደሉን የገለጸ ሲሆን ይህም በዚህ ጦርነት የተገደሉ የእስራኤል ወታደሮችን ብዛት 20 አድርሶታል።