ሊባኖስ እና እስራኤል የደረሱት የ10 ቀን የተኩስ አቁም ስምምነት ከመጀመሩ አስቀድሞ ከቢቢሲ ጋር ቃለ መጠይቅ ያደረጉት የሄዝቦላህ ከፍተኛ አመራር ዋፊቅ ሳፋ ቡድን
“መቼም፣ ጭራሽ” ትጥቅ እንደማይፈታ ገለጹ።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ
ሄዝቦላህን ትጥቅ ማስፈታት በቀጣይ ከሊባኖስ መንግሥት ጋር ለሚደረግ ድርድር የተቀመጠ መሠረታዊ ጥያቄ መሆኑን ተናግረዋል።
ስለ ትጥቅ መፍታት የተጠየቁት ሳፋ ግን “ተገቢ
ተኩስ አቁም፣ ትክክለኛ የሆነ እስከሚደረስ አይደረግም" ብለዋል።
"እስራኤል ለቅቃ እስካልወጣች ድረስ አይሆንም። እስረኞች ከመመለሳቸው፣ የተፈናቀሉ
ሰዎች ወደ ቀያቸው ከመመለሳቸው እና መልሶ ግንባታ ከመጀመሩ በፊት ትጥቅ መፍታት አይኖርም። እስከዚያው ድረስ ስለ ሄዝቦላህ
የጦር መሳሪያ ማውራት አይቻልም” ሲሉ ቅድመ ሁኔታዎቻቸውን ዘርዝረዋል።
ቤይሩት ውስጥ በሚገኝ የመኖሪያ ሕንጻ ላይ የተደረገው
ይህ ቃለ መጠይቅ በሄዝቦላህ እና በቀጣናዊ አጋሩ ኢራን መካከል ያለውን ቅንጅት ያሳያል። “ሄዝቦላህ እና ኢራን በአንድ ሰውነት ውስጥ ያሉ ሁለት ነፍሶች ናቸው” ብለዋል።
“ያለ ኢራን ሄዝቦላህ ሊኖር አይችልም። ያለ
ሄዝቦላህም አራን አትኖርም” ሲሉ በሁለቱ አካላት መካከል ስላለው “ሃይማኖታዊ፣ ሕጋዊ እና ርዕዮተ ዓለማዊ” ግንኙነት ገልጸዋል።
የሺዓ እስልምና ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ ቡድን
የሆነው ሄዝቦላህ እንደ አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ እስራኤል እና በርካታ የዓለም አገራት በሽብርተኛ ድርጅትነት ተፈርጇል።
ቡድኑ የአሁኑን የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት
የተቀላቀለው የካቲት ላይ ወደ እስራኤል ሮኬቶችን ከተኮሰ በኋላ ነበር።
ሄዝቦላህ ይህንን ጥቃት የፈጸመው በኢራን ጠቅላይ
መሪ ላይ ለተፈጸመው ግድያ እንዲሁም ከህዳር 2016 ዓ.ም. አንስቶ እስራኤል በየቀኑ በሚባል ደረጃ ሊባኖስ ላይ ስትፈጽም ለነበረው
ጥቃት በአጸፋ ምላሽነት መሆኑን ገልጿል።
እስራኤልም ከፍተኛ የአየር ጥቃቶችን በመፈጸም
እና ደቡባዊ ሊባኖስን በእግረኛ ወታደሮች በመውረር ምላሽ ሰጥታለች። ሄዝቦላህ ትጥቅ እስከሚፈታ ድረስም ይህንን ዘመቻ እንደምትቀጥል
ተናግራለች።
ሄዝቦላህ ቅድሚያ የሚሰጠው ለሊባኖስ ጥቅም ወይስ
ለኢራን የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው ሳፋ፤ “ያለ ምንም ጥርጥር ሄዝቦላህ የሚመለከተው የሊባኖስን ጥቅም ነው” ብለዋል።
ኢራን ተኩስ አቁም ላይ እንዲደረስ ያሳደረችውን ግፊት
ጨምሮ የምታደርጋቸው ድጋፎች ሊባኖስን ማገዛቸውን ጠቅሰዋል። ቢቢሲ ያነጋገራቸውን ጨምሮ በርካታ ሊባኖሳውያን ግን ቡድኑ ትጥቅ እንዲፈታ
ይፈልጋሉ። አገሪቱን ግጭት ውስጥ ከትቷል ሲሉም ይወቅሳሉ።
ሄዝቦላህ ትጥቅ ለመፍታት ፈቃደኛ ባለመሆኑ እና
ሰፋ ያሉ ቅድመ ሁኔታዎችን በማስቀመጡ እንዲሁም እስራኤል የደኅንነት ጥያቄዎቿን አጥብቃ በመያዟ የተነሳ በሊባኖስ ተግባራዊ የሚሆን ማንኛውም ተኩስ አቁም ለረጅም ጊዜ የሚቆየውን ግጭት ለጊዜው ከመግታት ያለፈ ጥቅም ላይኖረው ይችላል።