ትራምፕ ልዑካቸው ለድርድር ወደ ፓኪስታን መጓዙን ገልጸው ንግግሩ ካልተሳካ የኢራንን ኃይል ማመንጫዎች እንደሚያወድሙ ዛቱ
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ ልዑክ ከኢራን ጋር ለሚደረገው ሁለተኛ ዙር ድርድር ወደ ፓኪስታን ማቅናቱን ገለጹ። በአሁኑ ድርድር አሜሪካ የምታቀርበውን ስምምነት ኢራን የማትቀበል ከሆነ በአገሪቱ የሚገኙ “የኃይል ማመንጫዎች እና ድልድዮችን እንደሚመቱ” ዝተዋል።
ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል ማኀበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ፤ “የእኔ ተወካዮች ወደ ኢስላማባድ፣ ፓኪስታን እየሄዱ ነው። ነገ ማታ ለድርድር እዚያ ይሆናሉ” ብለዋል።
አሜሪካ እና ኢራን በፓኪስታን አሸማጋይነት ባለፈው ሳምንት ድርድር አድርገው የነበረ ቢሆንም ያለ ውጤት መጠናቀቁ ይታወሳል። በመጀመሪያው ዙር ድርድር የአሜሪካ ልዑክ የተመራው በምክትል ፕሬዝዳንቱ ጄዲ ቫንስ ሲሆን የኢራን ተደራዳሪ ቡድን ደግሞ በአፈ ጉባኤው ሞሐማድ ባገር ጋሊባፍ ተመርቷል።
ትራምፕ በዛሬው ጽሑፋቸው፤ “እጅግ ፍትሐዊ እና ምክንያታዊ ስምምነት አቅርበናል፤ እንደሚቀበሉት ተስፋ አደርጋለሁ” ብለዋል።
አክለውም ግን “የማይቀበሉት ከሆነ አሜሪካ ኢራን ውስጥ ያሉትን እያንዳንዱን የኃይል ማመንጫ እና ድልድይ ትመታለች” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
ንግግሮቹ የማይሳኩ ከሆነ “ከእንግዲህ ጥሩ ሰው አልሆንም” ያሉት ትራምፕ፤ የአገሪቱ ድልድዮች እና የኃይል ማመንጫዎች “በፍጥነት ይወድቃሉ፣ በቀላሉ ይወድማሉ” ሲሉም ጽፈዋል።
ሁለተኛ ዙር ድርድር ሊደረግ ስለመሆኑ እስካሁን ከኢራን በኩል አልተሰማም። የኢራን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ግን ለቀጣይ ዙር ድርድር የተቆረጠ ቀን አለመቀመጡን መናገራቸውን ሮይተርስ ዛሬ ዘግቦ ነበር።
ሌላኛው የዜና ወኪል ኤፒ ያወጣው ዘገባ ደግሞ ድርድሩ ይካሄዳል ተብሎ በሚጠበቅበት ኢስላማባድ ከተማ የደኅንነት እና ሌሎች ዝግጅቶች እየተደረገ መሆኑን ያመለክታል።