
የፎቶው ባለመብት, Reuters
ሳዑዲ አረቢያ፣ ቱርክ እና ፓኪስታን በአንዳቸው
ላይ የሚፈጸም ጥቃት በሦስቱም ላይ የተከፈተ ሆኖ እንደሚቆጠር የሚገልጽ ወታደራዊ ስምምነት ተፈራረሙ።
ስምምነቱ ይፋ የሆነው የሳዑዲ ዓረቢያው አልጋ
ወራሽ መሐመድ ቢን ሰልማን፣ የቱርኩ ፕሬዚዳንት ረሲፕ ታይፕ ኤርዶዋን እና የፓኪስታኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ሼህባዝ ሸሪፍ በሳዑዲ ዓረቢያዋ
መካ ከተማ በተካሄዱት ስብሰባ ላይ ነው።
ሦስቱ አገራት ወታደራዊ አጋርነታቸውን ያጠናከሩት
አሜሪካ እና ኢራን የሚያደርጉት ጦርነት ሳዑዲ ዓረቢያ ጎትቶ ባስገባት በዚህ ወቅት ነው።
ወሳኝ የነዳጅ መጓጓዣ በሆነው ሆርሙዝ
ወሽመጥ እንዲሁም በቀይ ባሕር በኩል የሚደረጉ የመርከቦች ጉዞዎችም መስተጓጎል ውስጥ ናቸው።
ሳዑዲ ዓረቢያ እና ፓኪስታን ባለፈው ዓመትም
ተመሳሳይ የጋራ የመከላከያ ስምምነት መፈጸማቸው አስታውቀው ነበር።
አሁን የተፈረመው የመካ የጋራ የመከላከያ ስምምነት
"ማንኛውንም የጥቃት እርምጃ ለመከላከል የሚያችል የጋራ የመከላከል አቅምን የማጠናከር” ዓላማ አለው።
ያወጡት መግለጫ “ከሦስቱ አገራት በአንዱ ላይ የሚፈጸም ማንኛውም
የትጥቅ ጥቃት በሁሉም ላይ እንደተፈጸመ ጥቃት ይቆጠራል" ይላል።
በተጨማሪም ስምምነቱ "በሦስቱ አገራት
መካከል የሚኖሩ የመከላከያ ትብብር ዘርፎችን በሙሉ ያሳድጋል” ብለዋል።
ስምምነቱ በሦስቱ የሱኒ እስልምና ተከታይ አገራት አንዳቸው
ለሌላቸው እገዛ እንደሚያቀርቡ ቢገልጽም፤ የእያንዳንዱ አገር የሚኖርበትን ግዴታ አልዘረዘረም።
ሮይተርስ በዘገባው የጠቀሳቸው አንድ
የቱርክ ባለሥልጣን፣ ስምምነቱ "በባህሪው የመከላከል ብቻ” እንደሆነ ገልጸዋል።
ሳዑዲ አረቢያ ያላትን ከፍተኛ ፋይናንስ አቅም
ለዚህ የመከላከያ ትብብር ታቀርባለች። በተጨማሪም ሳዑዲ በከፍተኛ መጠን መሣሪያ ከሚገዙ አገራት አንዷ ነች።
በኔቶ ጥምረት ውስጥ ከፍተኛ ወታደራዊ ኃይል
በመያዝ ሁለተኛ የሆነችው ቱርክ ደግሞ ዘመናዊ የመከላከያ መሣሪያዎችን የማምረት አቅም አላት። ሦስተኛዋ ተፈራራሚ አገር ፓኪስታን
በአንጻሩ የኒውክሌር መሣሪያን ታጥቃለች።
ሦስቱ አገራት፣ የኢራን ጦርነት የመቋጨት ምልክት
እያሳየ ባለመሆኑ እንዲሁም አሜሪካ ጦርነቱ ያስከተለውን የቀጣናዊ ተፅዕኖውን መቆጣጠር አለመቻሏን በመጥቀስ ስጋታቸውን ገልጸዋል።
የአሸማጋይነት ሚናን የያዘችው ፓኪስታን፤ አሜሪካ
እና ኢራን ያደረጓቸውን የተኩስ አቁም ድርድሮች አስተናግዳለች።
ሳዑዲ ራሷን ከግጭቱ ውጪ አድርጋ ብትቆይም፣
ሦስት አቅጣጫ ከደረሰባት ምት በኋላ ባለፈው ወር ላይ ከአሜሪካ ጋር በመሆን ኢራቅ ውስጥ የሚገኙ የኢራን ተቀጽላ ታጣቂዎች ላይ
ጥቃት ፈጽማለች።
በተጨማሪም ባለፈው ወር የየመኖቹ ሁቲዎች ሳዑዲ
ላይ “የባሕር ጉዞ ማዕቀብ” መጣላቸውን ያሳወቁ ሲሆን፣ በአገሪቱ አየር ማረፊያዎች፣ የነዳጅ መሠረተ ልማቶች እና በቀይ ባሕር ሲጓዝ
የነበረ ነዳጅ ጫኝ መርከብ ላይ ጥቃት ፈጽመዋል።
ሳዑዲ አረቢያም በሁቲ ይዞታዎች ላይ ጥቃት በማድረስ
አጸፋውን መልሳለች።