ዩክሬን በጥቁር ባሕር ወደብ ላይ በፈጸመችው ጥቃት የሩሲያን ዋነኛ ኤክስፖርት ጣቢያ መታች

የፎቶው ባለመብት, Volodymyr Zelensky/Telegram
ዩክሬን በሩሲያ ኖቮሮሲይስክ ወደብ በፈጸመቻቸው “ግዙፍ” የድሮን እና ሚሳዔል ጥቃቶች ሁለት ዋነኛ የጥራጥሬ መላኪያ ጣቢያዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው እና የመጨረሻው ትልቁ የሩሲያ የባሕር ኃይል ሰፈር መመታቱ ተገለጸ።
ዩክሬን ሌሊቱን በፈጸመቻቸው ጥቃቶች የስምንት ዓመት ልጅን ጨምሮ ሦስት ሰዎች ሲገደሉ፣ 24 ሰዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው የአካባቢው ባለሥልጣናት ተናግረዋል።
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቭሎድሚር ዜሌንስኪ አገሪቱ ጦር የሩሲያን ጦር ሰፈር ለማጥቃት በካሄደው “ልዩ ኦፕሬሽን” ሮኬቶች፣ ጄት እና የባሕር ድሮኖችን ማስወንጨፉን ተናግረዋል። የእህል ጣቢያዎች ስለመመታታቸው ግን አልጠቀሱም።
የዩክሬን ጦር ኋላ ላይ ባወጣው መረጃ፣ አራት የሩሲያ የጦር መርከቦች መመታታቸውን ገልጿል። ሩሲያ ስለዚህ ጥቃት አስተያየት አልሰጠችም።
ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ፣ “የሩሲያ ጥቃት እስከቀጠለ ድረስ ወራሪ መርከቦች እና እነርሱን የሚደግፉ መሠረተ ልማቶች በሙሉ ደኅንነታቸው የተጠበቀ አይሆንም” ብለዋል።
አብዛኛው የሩሲያ የጥቁር ባሕር መርከቦች የሚገኙት ከአገሪቱ ትልቅ ወደቦች አንዱ በሆነው ኖቮሮሲይስክ ነው። በዚህ ወደብ የሰፈሩት መርከቦቹ ከዚህ ቀደም በሩሲያ ወረራ በተያዘው ክሪሚያ የነበሩ ሲሆን በዚያ የሚገኘው ወደብ ለዩክሬን ጥቃቶች በእጅጉ የተጋለጠ ነው።
ረቡዕ ምሽት ጥቃት በተፈጸመበት ስፍራ የሚገኘው ዋነኛ የጥራጥሬ ንግድ ኩባንያ፣ የእህል መላኪያ ጣቢያው እንደተመታ ‘ታስ’ ለተባለው የሩሲያ ዜና ወኪል አረጋግጧል። ሌላ ኩባንያም ተመሳሳይ ጉዳት ማጋጠሙን ለሮይተርስ ተናግሯል።
የኤክስፖርት ጭነቶችን ጉዞ ባልቲክ እና ካስፒያን ባሕሮች ላይ ወደሚገኙ ወደቦች እንዲሁም ወደ የምድር የጉዞ መስመሮች ለማዘዋር እየተሰራ መሆኑን የሩሲያ የግብርና ሚኒስቴር አስታውቋል።
በዩክሬን ጥቃት መፈጸሙን ያልጠቀሰው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ፣ ለውጡን የሚያደርገው ቢሆንም “ወቅታዊ የሎጂስቲክስ ገደቦችን ግምት ውስጥ በማስገባት” መሆኑን ገልጿል።




















