ቀጥታ, የአሜሪካ የደህንነት ኃላፊ ኢራን በተለያዩ አገራት የሚገኙ አሜሪካውያንን ዒላማ ለማድረግ እያሴረች ነው ሲሉ አስጠነቀቁ

የአሜሪካ ብሔራዊ ደህንነት ዳይሬክተር ጄይ ክላይተን አርብ ዕለት ኢራን በውጭ አገራት የሚኖሩ “አሜሪካውያንን ዒላማ ለማድረግ የምታደርገውን ጥረት በከፍተኛ ሁኔታ ጨምራለች” በማለት አስጠንቀቁ። ቴህራን በመካከለኛው ምሥራቅ እና በሌሎች አገራት የሚገኙ አሜሪካውያንን ለመግደል የምታደርገው ሴራ “ከፍ ያለ ደረጃ ላይ” መድረሱን ዳይሬክተሩ ጨምረው ገልጸዋል። ማስጠንቀቂያው ሚስጥራዊ ያልሆነ ሰነድን የያዘ ሲሆን ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ የተላከ ነው።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. ኪም ጆንግ ኡን ለ12 ዓመታት ሥራ ላይ ሳይውል በቆየው ድልድይ በኩል ወደ ቻይና ገቡ

    የሰሜን ኮሪያ መሪ ኪም ጆንግ ኡን
    የምስሉ መግለጫ, የሰሜን ኮሪያ መሪ ኪም ጆንግ ኡን

    የሰሜን ኮሪያ መሪ ኪም ጆንግ ኡን በቅርቡ በተከፈተው አዲስ ድልድይ አማካኝነት ቻይና መድረሳቸውን የደቡብ ኮሪያው ዮንሃፕ የዜና ወኪል ዘገበ።

    የዜና ወኪሉ ስማቸውን ያልገለጻቸው የደቡብ ኮሪያ ምንጭ “ኪም ጆንግ ኡን በአዲሱ የያሉ ወንዝ ድልድይ አማካኝነት ወደ ቻይናዋ ዳንዶንግ ከተማ ገብተዋል” ማለታቸውን ጠቅሷል።

    አራት መኪኖችን ማሳለፍ የሚችለው ይህ ድልድይ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2014 ቢጠናቀቅም፣ በሰሜን ኮሪያ በኩል የመንገድና የጉምሩክ ተቋማት ባለመሟላታቸው ለ12 ዓመታት ሥራ ላይ ሳይውል ቆይቷል።

    ድልድዩ ከሳምንት ገደማ በፊት በይፋ የተከፈተ ሲሆን፣ ይህም በጎረቤት አገራቱ መካከል ያለውን የኢኮኖሚ ግንኙነት ለማጠናከር የተወሰደ ጉልህ እርምጃ ተብሎ ተቆጥሯል።

    ቻይና የሰሜን ኮሪያ ትልቋ የንግድ አጋር ስትሆን፣ ለተገለለችውና የኒውክሌር መሣሪያ ላላት አገር ዋነኛ የዲፕሎማሲ፣ የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ድጋፍ ምንጭ ነች።

    ቤጂንግም ሆነ ፒዮንግያንግ የኪም ጉብኝትን በይፋ አላረጋገጡም።

    ኪም የቻይናውን ጠቅላይ ሚኒስትር ያገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።

    የደቡብ ኮሪያው ዮንሃፕ የዜና ወኪል እንደዘገበው፣ ኪም ጆንግ ኡን ከቅዳሜው ጉብኝት በኋላ ወደ ሰሜን ኮሪያ ይመለሳሉ።

    ጉዳዩን የሚያውቁ አንድ የደቡብ ኮሪያ ባለሥልጣን ለሮይተርስ እንደገለጹት፣ ከሰኞ ጀምሮ በሚካሄደው ከፍተኛ የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ስብሰባ በፊት ኪም ወደ ቤይጂንግ የማምራታቸው ዕድል ዝቅተኛ ነው።

    የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ ስለ ጉዳዩ ለቀረበለት ጥያቄ ወዲያውኑ ምላሽ አልሰጠም።

    ቻይናና ሰሜን ኮሪያ በዚህ ወር መጀመሪያ 3 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለውን አዲሱን የያሉ ወንዝ ድልድይ በይፋ ከፍተዋል።

  2. ትራምፕ በኢራን ላይ ተጨማሪ ወታደራዊ እርምጃ ሊወሰድ እንደሚችል ተናገሩ

    የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ

    የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዓርብ ዕለት አሜሪካ በኢራን ላይ ሌላ ወታደራዊ ዘመቻ ልታካሂድ እንደምትችል ተናገሩ።

    ፕሬዚዳንቱ ይህንን ያሉት የኢራን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን ለመያዝ በተቃረበበት እና የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ በአሜሪካ የአጋማሽ ዘመን ምርጫ ላይ ተጽእኖ እያሳደረ ባለበት ወቅት ነው።

    ትራምፕ በፍሎሪዳ በነበራቸው የምርጫ ቅስቀሳ ላይ “ሌላ ትንሽ ‘ኢፒክ ፊውሪ’ ልናካሂድ እንችላለን” ሲሉ ተናግረዋል።

    “ኢፒክ ፊውሪ” የአሜሪካ ጦር በኢራን ጦርነት ለሚያካሄደው ዘመቻ የተሰጠው ስም ነው። ሆኖም ፕሬዚዳንቱ ስለ ዘመቻው ተጨማሪ መረጃ አልሰጡም።

    ትራምፕ ቀደም ሲል ጦርነቱን በፍጥነት ማስቆም እንደሚቻል ቢናገሩም፣ ዋሽንግተን ፈጣን መቋጫ መፈለግ ወይስ ግጭቱ ቀስ በቀስ እንዲቆም መፍቀድ የሚል ጥያቄ አንስተዋል።

    ስለ ጦርነቱ ዓላማና የጊዜ ሰሌዳ የተለያዩ አቋሞችን ሲያቀርቡ የቆዩት ትራምፕ፣ በቅርቡ ባደረጉት ንግግር “ጦርነቱ በአንድ መንገድ ወይም በሌላው በቅርቡ ያበቃል” ብለዋል።

    በዚህ ወር መጀመሪያ ትራምፕ አሜሪካ ከአንድ ሳምንት በኋላ በምታካሄደው የአጋማሽ ዘመን ምርጫ በፊት በኢራን ላይ ጥቃት እንደማትፈጽም ተናግረው ነበር።

    አሜሪካና እስራኤል የካቲት 21/2018 ዓ.ም. በጋራ በመሆን ኢራንን ሲያጠቁ ቴህራን በምላሹ በእስራኤልና የአሜሪካ ጦር ሠፈሮች በሚገኙባቸው የባህረ ሰላጤ አገራት ላይ ጥቃት ፈጽማለች።

    የኢራን ባለሥልጣናት ጦርነቱ እንደገና የሚቀሰቀስ ከሆነ ቴህራን ይበልጥ ሰፊ ምላሽ ለመስጠት መዘጋጀቷን ተናግረዋል።

    ሁለት ከፍተኛ የኢራን የደህንነት ባለሥልጣናት እንዳሉት፣ አሜሪካና እስራኤል እንደገና ጥቃት ከፈጸሙ ቴህራን በባህረ ሰላጤው ውቅያኖስ ስር የሚገኙ የኢንተርኔት ኬብሎችን ለማጥቃት ዝርዝር ዕቅድ አዘጋጅታለች።

  3. ሳዑዲ አረቢያ የሚሳዔል እና የድሮን ጥቃቶችን መቅረጽ እና ማጋራት እንደማይቻል አስጠነቀቀች

    ሳዑዲ አረቢያ

    የሳዑዲ አረቢያ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር የሚሳዔሎች እና ድሮኖች ጥቃቶችን ማክሸፍን የሚመለከቱ መረጃዎችን መቅረጽ፣ ማጋራት ወይም ማሰራጨት ሕጋዊ ተጠያቂነትን ሊያስከትል እንደሚችል በመግለጽ አስጠነቀቀች።

    በተጨማሪም፣ የከሸፉ ሚሳዔሎች፣ ድሮኖች ወይም የእነዚህ መሣሪያዎች ስብርባሪዎች ያረፉባቸውን ቦታዎች መቅረጽ ወይም ስለእነዚህ ቦታዎች መረጃ ማሰራጨትም በዚህ ማስጠንቀቂያ ውስጥ እንደሚካተት ሚኒስቴሩ ገልጿል።

    በኢራን የሚደገፉት የሁቲ አማፂያን በሳዑዲ አረቢያ አውሮፕላን ማረፊያዎች፣ የነዳጅ እና ወታደራዊ ተቋማት ላይ ጥቃታቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል።

    በዚህም ግዙፉ የሳዑዲ አረቢያ የነዳጅ ኩባንያ የአራምኮ ዋና መስሪያ ቤትን ጨምሮ በሪያድ የሚገኝ የዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ዒላማ ሆኗል።

    በቅርቡ ባገረሸው የየመን ግጭት የሁቲ አማጽያን በቀይ ባህር ዳርቻ እና በባብ ኤል-ማንደብ አቅራቢያ የሚገኙ ስልታዊ ቦታዎችን የተቆጣጠሩ ሲሆን፣ በሳዑዲ የሚመራው ጥምር ኃይል ቦታዎቹን ለማስለቀቅ ከፍተኛ ወታደራዊ ዘመቻ ጀምሯል።

    “ሚሳዔሎችን እና ድሮኖችን ስለመመከት እንዲሁም ስለሚመቱባቸው ቦታዎች መረጃን መቅረጽ፣ መለጠፍ ወይም ማጋራት ለሕግ ተጠያቂነት ይዳርጋል” ሲል የሳዑዲ አገር ውስጥ ሚኒስቴሩ በሰጠው ማስጠንቀቂያ ላይ ገልጿል።

    መግለጫው በአየር ላይ የሚሰነዘሩ ጥቃቶችን ለመመከት ከሚደረጉ እንቅስቃሴዎች እንዲሁም በእነዚህ እንቅስቃሴዎች ከተጎዱ አካባቢዎች ጋር የተያያዙ ምስሎችን፣ ቪዲዮዎችን ወይም ሌሎች መረጃዎችን ማሰራጨት ላይ ያሉ ገደቦችን አጽንኦት ሰጥቶታል።

    ይህንን ማስጠንቀቂያ ተላልፈው የሚገኙ ሰዎች ላይ ስለሚጣለው ቅጣት ሚኒስቴሩ ምንም አላለም።

    ማስጠንቀቂያው የሚሳዔል እና ድሮን ጥቃትን እንዲሁም የማክሸፍ ጥረትን ባለመቅረጽ እና ባለማሰራጨት ላይ የተጣለውን ገደብ ማኅበረሰቡ እንዲያከብር ጥሪ አቅርቧል።

  4. ፈረንሳይ ዛሬ ለመካሄድ በታቀደው ሠልፍ ላይ ሁከትን ለመከላከል 70,000 ፖሊሶችን ልታሰማራ ነው

    ባለፈው ሳምነት ቅዳሜ፣ በፓሪስ በተማሪዎችና በሠራተኛ ማኅበራት ተደራጅቶ የነበሩትና በአብዛኛው ሰላማዊ የነበሩ ሠልፎች ወደ ሁከትና ዘረፋ ተለውጠዋል
    የምስሉ መግለጫ, ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ፣ በፓሪስ በተማሪዎችና በሠራተኛ ማኅበራት ተደራጅቶ የነበሩትና በአብዛኛው ሰላማዊ የነበሩ ሠልፎች ወደ ሁከትና ዘረፋ ተለውጠዋል

    ፈረንሳይ ቅዳሜ ዕለት በመላ አገሪቱ ለመካሄድ የታቀደው የተቃውሞ ሠልፍ ላይ ሁከትን ለማስወገድ ወደ 70,000 የሚጠጉ ፖሊሶችን ልታሰማራ መሆኑን አስታወቀች።

    ይህ እርምጃ የተወሰደው፣ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ እየጨመረ የመጣውን የኑሮ ውድነት በመቃወም በተደረጉ ሠልፎች ወቅት፣ ከበርካታ ዓመታት ወዲህ ታይቶ የማይታወቅ የከፋ የጎዳና ላይ ሁከት ከተከሰተ በኋላ ነው።

    የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ላውረንት ኑኔዝ አርብ ዕለት እንደተናገሩት አሸባሪዎችን ለመከላከል ከመደበኛ የጸጥታ ኃይሎች በተጨማሪ ልዩ ኮማንዶዎች ይሰማራሉ።

    በተጨማሪም “ግራ ዘመም” ቡድኖች በማኅበራዊ ሚዲያ አማካኝነት ለጥቃት ጥሪ ማቅረባቸውን ገልጸዋል።

    ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በመሩት እና የተለያዩ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ሚኒስትሮች በተሳተፉበት ስብሰባ ማብቂያ ላይ ኑኔዝ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት “በሰላማዊ መንገድ ስለሚካሄድ የተቃውሞ ሠልፍ አይደለም እያወራን ያለነው” በማለት “ነገ [ቅዳሜ] እጅግ ጥብቅ እርምጃ ለመውሰድ ተዘጋጅተናል፤ ማንኛውንም ዓይነት ጥቃትም አንታገስም” ብለዋል።

    ባለፈው ሳምንት በነበረ የተቃውሞ ሠልፍ ወቅት ጥቁር ልብስ የለበሱና ፊታቸውን በጭምብል የሸፈኑ አንዳንድ በሁከት የተሳተፉ ቡድኖች፣ በፓሪስ፣ ማርሴይ እና በሌሎች ከተሞች መኪኖችንና ሕንፃዎችን ሲያቃጥሉ እንዲሁም የንግድ ተቋማትን ሲዘርፉ ታይተዋል።

    በፈረንሳይ የሚገኙ አንዳንድ ሕንጻዎች እና የንግድ ተቋማት፣ ቅዳሜ ከሚካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ አስቀድመው መስኮቶቻቸውን በቺፑድ ሸፍነዋል
    የምስሉ መግለጫ, በፈረንሳይ የሚገኙ አንዳንድ ሕንጻዎች እና የንግድ ተቋማት፣ ቅዳሜ ከሚካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ አስቀድመው መስኮቶቻቸውን በቺፑድ ሸፍነዋል

    በማዕከላዊዋ የፈረንሳይ ከተማ ሊሞዥ፣ ቅዳሜ ዕለት ሁከት ፈጣሪዎች ባስነሱት እሳት በ19ኛው ክፍለ ዘመን የተገነባውና ባማሩ ጌጣጌጦች የተዋበው የከተማዋ ማዘጋጃ ቤት በእሳት ወድሟል። እሳቱ እየተስፋፋ ሄዶ የሕንፃው የሰዓት ማማና ጣሪያ ፈርሰው እንዲወድቁ አድርጓል።

    ሉቭርን፣ኦርሴ ሙዚየምን፣ ፒካሶ ሙዚየምን እና ግራንድ ፓሌን ጨምሮ ዋና ዋና ሙዚየሞች ቅዳሜ ዕለት ዝግ ይሆናሉ።

    ከዓለም ቀዳሚ የዘመናዊ ጥበብ ትርኢቶች አንዱ የሆነው “አርት ባዝል” (Art Basel) አርብ ዕለት ለሕዝብ ክፍት ሆኖ የነበረ ቢሆንም፣ አለመረጋጋት ሊፈጠር ይችላል ከሚል ስጋት የተነሳ ቅዳሜና እሁድ ዝግ ሆኖ ይቆያል።

    በፓሪስ የሚገኙ ነጋዴዎች ሱቆቻቸውን ለመከላከል ሲሉ ሳምንቱን ሙሉ መከላከያዎችን ሲገነቡ ቆይተዋል። ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ ሁከት ከተከሰተባቸው አካባቢዎች አንዱ በሆነው ‘ፕላስ ደ ላ ሪፑብሊክ’ አቅራቢያ፣ አንድ ባንክ እና ሌሎች የንግድ ተቋማት ዘረፋን ለመከላከል ሲሉ መስኮቶቻቸውን በእንጨት ሰሌዳዎች ሸፍነዋል።

    ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን እና መንግሥታቸው የፕሬዚዳንት ምርጫ ለመካሄድ ስድስት ወራት ብቻ ሲቀሩት በድንገት የተከሰተውን ይህንን ቀውስ ለመቆጣጠር እየታገሉ ይገኛሉ።

    ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ዕለት የነበረውን ሁከት ተከትሎ መንግሥት “ሁኔታውን መቆጣጠር አቅቶት እንደነበር” አምኗል።

    የፈረንሳይ ፖሊስበዋና ዋና አደባባዮች ተሰማርቷል
  5. በኮንጎ ለተከሰተው የኢቦላ ወረርሽኝ የመጀመርያው የክትባት ሙከራ ተጀመረ

    ኤርቬቦ

    የዓለም ጤና ድርጅት በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ለተከሰተው የኢቦላ ወረርሽኝ የተዘጋጀ ክትባት ሙከራ መጀመሩን አስታወቀ።

    የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም አርብ ዕለት እንደገለጹት፣ በሰሜን ምሥራቅ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በሚገኘው የኢቱሪ ግዛት ዋና ከተማ በሆነችው ቡኒያ፣ የመጀመሪያዎቹ ተሳታፊዎች 'ኤርቬቦ' (Ervebo) የተሰኘውን የኢቦላ ክትባት ወስደዋል። ይህ ግዛት የወረርሽኙ ማዕከል ነው።

    ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፈቃደኛ በሆኑ ሰዎች ላይ የኢቦላ ክትባት ሙከራ መጀመሩን አስታውቃለች። የመጀመሪያው በጎ ፈቃደኛ አርብ ዕለት በአገሪቱ ምሥራቃዊ ክፍል በምትገኘው ቡኒያ ከተማ ክትባቱን ወስዷል።

    በስዋሂሊኛ ቱማይኒ” (ተስፋ) በሚል የተሰየመው ይህ ሙከራ፣ የተለያዩ ክትባቶች ሰዎችን ከኢቦላ ቡንዲቡግዮ ቫይረስ መከላከል ይችሉ እንደሆነ ይፈትሻል። በአሁኑ ወቅት ለዚህ የቫይረስ ዝርያ የተፈቀደ ክትባት የለም።

    በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እስካሁን ከተመዘገቡት ሁሉ ትልቁ የቡንዲቡግዮ ቫይረስ ወረርሽኝ በተከሰተበት ወቅት ነው ይህ የሙከራ ክትባት የተጀመረው።

    የሕክምና ባለሙያዎች ከ4000 በላይ ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈውን ይህንን ወረርሽኝ በአገሪቱ ታሪክ እጅግ ገዳይ የሆነ ብለውታል።

    ከጤና ባለሥልጣናት የተገኘው የቅርብ ጊዜ ሪፖርት እንደሚያሳየው፣ 9,704 ሰዎች በቫይረሱ ​​የተያዙ ሲሆን፣ 4,687 ሰዎች ደግሞ ሕይወታቸው አልፏል።

    ተመራማሪዎች ዛየር ለተሰኘው የኢቦላ ዝርያ የተፈቀደውን 'ኤርቬቦ' (Ervebo) የተሰኘውን ክትባት በመጀመሪያ ይፈትሻሉ ተብሏል።

    በተጨማሪም፣ በሞደርና እና በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የተዘጋጁ እና ከቡንዲቡግዮ የኢቦላ ዝርያ ለመከላከል የታሰቡ ሌሎች ክትባቶችም፣ በቀጣይነት በሙከራው ውስጥ ይካተታሉ ተብሎ ይጠበቃል።

    ጥናቱ በኢቦላ መያዛቸው ከተረጋገጠ ሰዎች ጋር ግንኙነት የነበራቸውና ለበሽታው የመጋለጥ እድላቸው ከፍተኛ የሆኑ ግለሰቦችን መከተብ ላይ ያተኮረ ስልት ይጠቀማል።

    ይህንን ሙከራ በጋራ የሚመሩት የኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ብሔራዊ የባዮሜዲካል ምርምር ተቋም እና የአንትወርፕ ዩኒቨርሲቲ ናቸው። ለዚህም የኮንጎ መንግሥት፣ የዓለም ጤና ድርጅት፣ የአፍሪካ ሲዲሲ፣ ሜዴሲን ሳንፍሮንቲየር እንዲሁም ሌሎች አጋሮች ድጋፍ ያደርጋሉ።

  6. በዮርዳኖስ በአንድ ቤተ ክርስትያን ለቀብር የተሰባሰቡ ሐዘንተኞች ላይ ታጣቂዎች በከፈቱት ተኩስ ሰባት ሰዎች ተገደሉ

    አርብ ዕለት የጸጥታ አባላት እና የኅብረተሰብ ክፍሎች ከግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ውጭ ተሰባስበው
    የምስሉ መግለጫ, አርብ ዕለት የጸጥታ አባላት እና የኅብረተሰብ ክፍሎች ከግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ውጭ ተሰባስበው

    በዮርዳኖስ በሚገኝ አንድ ቤተ ክርስትያን ቀብር ላይ በነበሩ ሰዎች ላይ በተፈጸመ ጥቃት ሰባት ሰዎች መገደላቸውን የአገሪቱ ባለሥልጣናት አስታወቁ።

    አርብ ዕለት በካራግ ግዛት ህሙድ በሚባል አካባቢ በምትገኝ ቤተክርስቲያን ላይ ታጣቂዎች ተኩስ በመክፈታቸው ቢያንስ 34 ሌሎች ሰዎች ቆስለዋል።

    ማንነታቸው ያልታወቁት ታጣቂዎች በመኪና ወደ ቤተክርስቲያኗ በመምጣት ለቀብር የተገኙ ሰዎች ላይ ተኩስ ከፍተው መሸሻቸው ታውቋል።

    ጥቃቱን በሚመለከት ማንም ኃላፊነት አልወሰደም።

    ካራክ በርካታ ሙስሊሞች በሚገኙባት ዮርዳኖስ ውስጥ የክርስትያን ማኅበረሰብ የሚኖርባት ግዛት ናት።

    የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ማዘን አል-ፋራያ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ የአገሪቱ ፖሊስ "የአክራሪዎች ቡድን" ሲሉ የገለጿቸውን ወንጀለኞች ለመያዝ እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል።

    የዮርዳኖስ ንጉሥ አብዱላህ ዳግማዊ በበኩላው "ካራክ ላይ ያነጣጠረውን የሽብር ተግባር የፈጸሙ እጅግ ከባድቅጣት ይጠብቃቸዋል" ብለዋል።

    የአገሪቱ ባለሥልጣናት ይፋ ባደረጉት መረጃ በጥቃቱ መገደላቸው የተረጋገጠው እስካሁን ሰባት ሰዎች ብቻ ናቸው። የመንግሥት ቃል አቀባይ መጀመርያ ላይ ስድስት ሰዎች መሞታቸውን ተናግረው የነበረ ቢሆንም በኋላ ላይ ግን የሟቾችን ቁጥር ወደ ሰባት ከፍ ብሏል።

    በካራክ በደረሰው ጥቃት የተጎዱ ሰዎች በሚታከሙበት ሆስፒታል ዋይታ እና ለቅሶ የሚሰማ ሲሆን ከፍተኛ የሆነ የፖሊስ ጥበቃም አለ።

    በጥቃቱ ቤተሰቦቻቸውን ያጡ እና የተጎዱባቸው ሰዎች “መንግሥት በአሸባሪዎች ላይ ጠንካራ እርምጃ መውሰድ አልቻለም” በሚል በከፍተኛ ቁጣ ውስጥ መሆናቸው ተነግሯል።

    ወደ ሆስፒታሉ የሚወስዱ መንገዶች የተዘጉ ሲሆን መኪኖችንም ማቆም የተፈቀደው ራቅ ባለ ስፍራ ነው።

    የደህንነት ሁኔታው የተጠናከረው ንጉሥ አብዱላህ ዳግማዊ የተጎዱትን ሰዎች ለመጎብኘት እንደሚመጡ ከተገለጸ በኋላ መሆኑም ተሰምቷል።

    የሊባኖስፕሬዚዳንት ጆሴፍ አውን በቤተ ክርስቲያኑ ላይ የተፈጸመው "አሰቃቂ የሽብር ጥቃት"፣ "የሞትንና ለሟች የሚያዝኑ ሰዎችን ክብር የጣሰ እንዲሁም ከማንኛውም ሃይማኖታዊና ሰብአዊ እሴቶች ጋር የሚቃረን ነው" ሲሉ መናገራቸውን የሊባኖስ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

  7. የአሜሪካ የደህንነት ኃላፊ ኢራን በተለያዩ አገራት የሚገኙ አሜሪካውያንን ዒላማ ለማድረግ እያሴረች ነው ሲሉ አስጠነቀቁ

    ማርኮ ሩቢዮ

    የአሜሪካ ብሔራዊ ደህንነት ዳይሬክተር ጄይ ክላይተን አርብ ዕለት ኢራን በውጭ አገራት የሚኖሩ “አሜሪካውያንን ዒላማ ለማድረግ የምታደርገውን ጥረት በከፍተኛ ሁኔታ ጨምራለች” በማለት አስጠንቀቁ።

    ቴህራን በመካከለኛው ምሥራቅ እና በሌሎች አገራት የሚገኙ አሜሪካውያንን ለመግደል የምታደርገው ሴራ “ከፍ ያለ ደረጃ ላይ” መድረሱን ዳይሬክተሩ ጨምረው ገልጸዋል።

    ማስጠንቀቂያው ሚስጥራዊ ያልሆነ ሰነድን የያዘ ሲሆን ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ የተላከ ነው።

    ይህ ባለ አንድ ገጽ ሰነድ ኢራን አላት ስለተባለው ዕቅድ የሚገልጽ መረጃ፤ አደጋ ላይ ሊወድቁ ለሚችሉ ነገር ግን በአሁኑ ወቅት ይህንን ሚስጥራዊ መረጃ የማግኘት ዕድል ለሌላቸውን ጨምሮ፣ ለተለያዩ የአሜሪካ መንግሥት ሠራተኞች ተደራሽ መደረግ እንዳለበት ያስጠነቅቃል።

    ማስጠንቀቂያው የተሰጠው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኙ ዲፕሎማቶችን እና የአሜሪካ ጦር በቀጣናው ያለውን የሰው ኃይል እየቀነሰ ባለበት ወቅት ነው። እነዚህ እርምጃዎች የተወሰዱት ከኢራን የሚመጡ ቀጥተኛ ስጋቶችን እንዲሁም በየመን ከሚገኘውና በኢራን ከሚደገፈው የሁቲ አማፂ እንቅስቃሴ የሚመጡ ስጋቶች በተጠናከሩበት ወቅት ነው።

    "የአሜሪካ ዜጎችን ለመግደል ኢራን የነደፈቻቸው ሴራዎች በመካከለኛው ምሥራቅ እና በሌሎች አንዳንድ አገራት ወደ ከፍተኛ ደረጃ ደርሰዋል" ሲሉ ክሌይተን ጽፈዋል።

    የትራምፕ አስተዳደር በኢራን ላይ ወታደራዊ ጥቃቶችን እንደገና ለመጀመር እያሰበ ባለበት ወቅት የወጣው ይህ ሰነድ፣ የተወሰኑ ዒላማዎችን ወይም ሴራዎቹ እየተጠነሰሱባቸው ናቸው የተባሉባቸውን አገራት በግልጽ አይጠቅስም፤ እንዲሁም ጥቃቶቹ በቅርቡ ሊፈጸሙ እንደሚችሉ የሚያሳይ ፍንጭም አይሰጥም።

    ክሌይተን እንደገለጹት፣ የአሜሪካ የደህንነት ማኅበረሰብ ከተለያዩ ምንጮች የተሰበሰቡ ሚስጥራዊ መረጃዎች ላይ የተጣለውን ገደብ ለማላላት እየሰራ ሲሆን፣ ይህም መረጃዎቹ ለውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ሠራተኞች በስፋት እንዲጋሩ ያስችላል።

    የሲአይኤ ዳይሬክተር ጆን ራትክሊፍም የዚህ ማስታወሻ ቅጂ እንዲደርሳቸው ተደርጓል።

    ይህ ማስጠንቀቂያ የተሰጠው፣ በአካባቢው በሚገኙ የአሜሪካ ዲፕሎማሲያዊ ተልዕኮዎች ላይ በርካታ የደህንነት እርምጃዎች ከተወሰዱ በኋላ ነው።

    በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ፣ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በሳዑዲ አረቢያ የሚገኙ አስፈላጊ ያልሆኑ የኤምባሲ ሠራተኞች እና ቤተሰቦቻቸው አገሪቱን ለቀው እንዲወጡ አዟል።

    በተጨማሪም በአካባቢው የሚገኙ ሌሎች በርካታ የአሜሪካ ኤምባሲዎች፣ በ”ተገደበ የአሠራር ሁኔታ” ስር ሆነው የሠራተኞቻቸውን ቁጥር ቀንሰዋል። ሲቢኤስ ኒውስ ቀደም ብሎ እንደዘገበው፣ ይህ አሠራር ሠራተኞቹ አገሪቱን ለቅቀው እንዲወጡ በይፋ ሳያዝዙ፣ የሠራተኞቹን ቁጥር ለመቀነስ ያስችላል።

  8. በዌስት ባንክ ፍልስጤማውያን እንደሆኑ የተጠረጠሩ ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት ሁለት የእስራኤል ወታደሮች ተገደሉ

    ጥቃቱን እንዳደረሱ ከሚጠረጠሩ ታጣቂዎች አንዱን የሚያሳይ፣ በኤኤፍፒ የተጋራ ፎቶ
    የምስሉ መግለጫ, ጥቃቱን እንዳደረሱ ከሚጠረጠሩ ታጣቂዎች አንዱን የሚያሳይ፣ በኤኤፍፒ የተጋራ ፎቶ

    ፍልስጤማውያን እንደሆኑ የተጠረጠሩ ሁለት ታጣቂዎች በወረራ በተያዘው ዌስት ባንክ በከፈቱት ተኩስ ጥቃት ሁለት የእስራኤል ወታደሮች መገደላቸውን የአገሪቱ ጦር አስታወቀ።

    ተጨማሪ ሦስት እስራኤላውያንን አቁስለዋል የተባሉት ታጣቂዎች እንደተገደሉ ባለሥልጣናት ተናግረዋል። ተኩስ የተከፈተው የኬብሮን ከተማ መግቢያ ላይ በሚገኝ ወታደራዊ የፍተሻ ኬላ ላይ ነው።

    ይህንን ጥቃት ተከትሎ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ፣ የአገሪቱ ጦሩ ከዛሬ አርብ ጀምሮ ሙሉ ዌስት ባንክ ላይ ሙሉ የእንቅስቃሴ እገዳ ለመጣል እንዲዘጋጅ ትዕዛዝ መስጠታቸውን ተናግረዋል።

    ጥቃቱ የተፈጸመው በአካባቢው ከፍተኛ ውጥረት በነገሰበት ወቅት ነው። “ፅንፈኛ አይሁዳውን ሰፋሪዎች” ዓመታዊውን የወይራ ምርት ስብሰባ በሚያካሂዱ ፍልስጤማውያን ላይ ጥቃቶችን ሲፈጽሙ ነበር። የእስራኤል ጠቅላላ ምርጫ ሊካሄድም አራት ቀናት ቀርተውታል።

    ቢቢሲ ትክክለኛነቱን ያረጋገጠው አንድ ቪዲዮ ላይ በእስራኤል ወታደሮች እና በታጣቂዎቹ መካከል ከፍተኛ የተኩስ ልውውጥ ሲደረግ እንደነበር አሳይቷል።

    የእስራኤል ጦር፣ በታጣቂዎቹ ተሽከርካሪ ውስጥ ከፍተኛ መጠን ያለው ጥይት ማግኘቱን አስታውቋል።

    ታጣቂዎቹ በአቅራቢያ በሚገኝ አካባቢ ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃት ለመፈጸም አስበው እንደነበር፣ ነገር ግን የፍተሻ ኬላ ሲያጋጥማቸው እዚያው ተኩስ ለመክፈት ወስነዋል ተብሎ እንደሚታመን እስራኤል ጦር ገልጿል።

    ትክክለኛነቱ ባልተረጋገጠ የደኅነነት ካሜራ ቪዲዮ ላይ ደግሞ ሁለት ታጣቂዎች ሽጉጥ እና ጠመንጃ የሚመስሉ መሣሪያዎችን ይዘው ከመኪና ሲወርዱ እንዲሁም ኬላው ላይ በነበሩ ወታደሮች ላይ ተኩስ ሲከፍቱ እና የአጸፋ ምላሽ ሲሰጣቸው ታይቷል።

    ዛሬ ከሰዓት ላይ ጥቃቱ የተፈጸመበትን ቦታ የጎበኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ፣ መንግሥታቸው በዌስት ባንክ “ከፍተኛ እርምጃ” ለመውሰድ ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል።

    ቀኝ አክራሪው የሆነው ጥምር መንግሥት አጋራቸው የሆኑት ቤዛሌል ስሞትሪች “እንደ ጋዛ ወይም ሊባኖስ አይነት” ዘመቻ ዌስት ባንክ ውስጥ እንዲጀመር ጠይቀዋል።

    የቀኝ አክራሪው የብሔራዊ ደኅንነት ሚኒስትር ኢታማር ቤን ግቪር ደግሞ እስራኤል የፍልስጤም አስተዳደርን እንድታፈርስ ጥሪ አቅርበዋል።

  9. የትግራይ ባለአደራ አስተዳደር ተፈናቃዮች “በቅርቡ” መመለስ እንደሚጀምሩ ገለጸ

    የባለአደራ አስተዳደሩ የፖለቲካ እና ሕዝብ አደረጃጀት ዋና አስፈጻሚ የሆኑት ረዳኢ ኃለፎም

    በፌደራል መንግሥት የተመሠረተው የትግራይ ባለአደራ አስተደዳር በክልሉ የሚገኙ ተፈናቃዮችን ወደ ቅያቸው የመመለስ ተግባር “በቅርቡ እንደሚጀመር” አስታወቀ።

    የባለአደራ አስተዳደሩ የፖለቲካ እና ሕዝብ አደረጃጀት ዋና አስፈጻሚ የሆኑት ረዳኢ ኃለፎም ዛሬ አርብ ጥቅምት 13/2019 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ አስተዳደሩ በይፋ ወደ ሥራ መግባቱን ገልጸዋል።

    በፌደራል መንግሥት የተሾሙት ዋና አስፈጻሚዎች የአስተዳደሩ ምክር ቤቱን ሰብሳቢነት በየ45 ቀኑ በየተራ እንደሚረከቡ የገለጹት ረዳኢ፣ “የወቅቱ ጊዜያዊ አስተባባሪ ወይም ሰብሳቢ አቶ አሰፋ አብርሃ ናቸው” ሲሉ ተናግረዋል።

    የፖለቲካ እና ሕዝብ አደረጃጀት ዋና አስፈጻሚው በዛሬ መግለጫቸው በባለአደራ አስተዳደሩ ይፈጸማሉ ካሏቸው ተግባራት አንዱ የተፈናቃዮች መመለስ ነው።

    በጌታቸው ረዳ ይመራ የነበረው ጊዜያዊ አስተዳደር 2016 ዓ.ም. ተፈናቃዮችን የመመለስ ጥረት አድርጎ እንደነበር የተናገሩት ረዳኢ፣ “እንዳይመለሱ ያደረገው አሁን ጦርነት ያወጀው አካል ነው” ሲሉ የህወሓት አመራሮችን ወቅሰዋል።

    “የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ካቤኒ እንዲመለሱ ተስማምቶ፣ ከኢፌድሪ መንግሥት ጋርም ስምምነት ላይ ተደርሶ እንዲመለሱም ተፈልጎ ነበር። ነገር ግን [ህወሓት] ‘የእኔ ካድሬ አብሮ ካልገባ የእኔም ሠራዊት አብሮ ካልገ እነሱ አይመለሱም’ ተብሎ እንደ መያዣ ነበር የተጠቀመባቸው” ሲሉ ከስሰዋል።

    የህወሓት አመራር ይህንን ያደረገው “ተፈናቃዮች ከተመለሱ አጀንዳ” ስለማይኖረው ነው በማለት ተናግረዋል።

    “አሁን [የተፈናቃዮችን ጉዳይ] እንደ መያዣ የሚይዘው አካል በመረጠው መንገድ እየጠፋ ስለሆነ ተፈናቃይ ወገኖቻችን ወደ ቅዬአቸው የሚመለሱ ይሆናል” ሲሉ ተደምጠዋል።

    ይህ ስራ “በቅርብ እንደሚጀመር” የተናገሩት ዋና አስፈጻሚው፣ የፌደራል መንግስት ተሳትፎ እንዳለበትም ጠቁመዋል።

    “ተፈናቃይ ወገኖቻችን ወደነበሩበት ቀያቸው ወደ ቦታቸው እንዲመለሱ የማድረግ ስራው በቅርብ የሚጀመር ይሆናል” ብለዋል። ተፈናቃዮቹ የሚመለሱት “አስፈላጊው ድጋፍ ተደርጎላቸው፣ ሰብአዊ ክብራቸውን በጠበቀ መንገድ” እንደሚሆንም ገልጸዋል።

    ከ2013 ዓ.ም. በተጀመረው የትግራይ ጦርነት ምክንያት የተፈናቀሉ ነዋሪዎች ላለፉት ስድስት ዓመታት በክልሉ ውስጥ በሚገኙ የተፈናቃይ መጠለያዎች እንዲሁም ወደ ወደ ሱዳን ሸሽተው ይገኛሉ።

    በጌታቸው ረዳ ይመራ የነበረው ጊዜያዊ አስተዳደር በሰኔ 2016 ዓ.ም. ወደ ፀለምት አካባቢዎች ነዋሪዎችን መመለስ ጀምሮ ነበር።

    በዚያው ተመሳሳይ ወቅትም፣ ከጦርነቱ በኋላ በአማራ ክልል ሥር ተቋቁመው የነበሩት የአካባቢው አስተዳደሮች እንዲፈርሱ ተደርጎ ነበር።

    ይሁን እንጂ ይህ ተፈናቃዮችን የመመለስ ተግባር ሳይጠናቀቅ ቆሟል። የጌታቸው አስተዳደር ለዚህ ተጠያቂ የሚያደርገው የህወሓት አመራርን ነው።

    ህወሓት በበከሉ የይገባኛል ውዝግብ ከተነሳባቸው እንደ የወልቃይት እና ፀለምት አካባቢዎች የተፈናቀሉ ነዋሪዎችን ለመመለስ የደኅንነት ስጋት መኖሩንም ሲያነሳ ቆይቷል።

  10. የማላዊ ፕሬዚዳንት ለጉብኘት በሔዱበት ደቡብ አፍሪካ ረጅም ጊዜ መቆየታቸው ጥያቄ አስነሳ

    ፕሬዝዳንት ፒተር ሙታሪካ

    የነዳጅ እጥረት፣ የኃይል መቆራረጥ እና የምጣኔ ሀብት ቀውስ ውስጥ ያለችውን ማላዊ የሚመሩት ፕሬዝዳንት ለጉብኘት በሔዱበት ደቡብ አፍሪካ ለረጅም ቀናት መቆየታቸውን በተመለከተ ማብራሪያ እንዲሰጣቸው ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጠይቀዋል።

    የ86 ዓመቱ ፕሬዝዳንት ፒተር ሙታሪካ “የግል ጉብኝት” በሚል ወደ ደቡብ አፍሪካ ከሔዱ ከሁለት ሳምንት በላይ ሆኗቸዋል።

    ፕሬዝዳንቱ በዚህ ዓመት ብቻ አምስት ጉብኝቶችን ያደረጉ ቢሆንም ስለ እያንዳንዱ ጉዟቸው ለሕዝብ ይፋ የተደረገው መረጃ በጣም ውስን መሆኑ ተገልጿል።

    የማላዊ ኮንግረስ ፓርቲ የተሰኘው የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅት “ማላዊ ወሳኝ ሁኔታ ውስጥ ናት ጠንካራ እርምጃዎች መውሰድ ያስፈልጋል” ብሏል።

    ሐሙስ ዕለት የማላዊ ኮንግረስ ፓርቲ የዘመቻ ዳይሬክተር ሞሰስ ኩንኩዩ፤ በአገሪቱ ዋና ከተማ ሊሎንግዌ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ ፕሬዝዳንቱ ለግል ጉዳያቸው የመጓዝ መብታቸው ላይ ፓርቲያቸው ጥያቄ እንደሌለው ገልጸዋል።

    ነገር ግን አገሪቱ ባጋጠማት ፈተናዎች ላይ ምክትል ፕሬዝዳንቱ ማብራሪያ ይስጠን በማለት ጠይቀዋል። ሞሰስ አክለውም የማሊ ዜጎች አገሪቱን እያስተዳደረ ያለው አካል ማን እንደሆነ የማወቅ መብት አላቸው ብለዋል።

    'ዋናው ችግር ሕዝቡ እየተሰቃየ መሆኑና አገሪቱን የሚመራ እና ኃላፊነት የሚወስድ ሰው መኖሩን ማረጋገጥ አስፈላጊ መሆኑ ነው በማለት ተናግረዋል።

    የማላዊ የማስታወቂያ ሚኒስትር ሻድሪክ ናማሎምባ በበኩላቸው የፕሬዝዳንቱ አለመኖር የአመራር ክፍተት ይፈጥራል መባሉን አጣጥለዋል።

    ባለፈው ዓመት የጥቅምት ወር ወደ ሥልጣን የመጡት ሙተሪካ በአውሮፓውያኑ 2014 እስከ 2016 ባሉት ዓመታት ማላዊን መርተዋል።

  11. የኢራኑ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሜሪካ ለእስራኤል የሚሳዔል መከላከያ 11 ቢሊዮን ዶላር አውጥታለች አሉ

    የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ

    የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ አሜሪካ ለእስራኤል የምታደርገውን ወታደራዊ ድጋፍ ተቹ።

    አራግቺ ዋሺንግተን ባለፉት ሦስት ዓመታት ለእስራኤል የሚሳዔል መከላከያ 11 ቢሊዮን ዶላር አውጥታለች ሲሉ ተናግረዋል።

    "አሜሪካ ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ፣ ከግብር ከፋዮች በተሰበሰበ ገንዘብ ለእስራኤል ሚሳዔል መከላከያ ሥርዓት 11 ቢሊዮን ዶላር አውጥታለች" በማለት በኤክስ ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።

    አክለውም "እስራኤልን ለመከላከል ሲባል አሜሪካ የተኮሰቻቸው የመከላከያ ሚሳዔሎች ቁጥር እስራኤል ራሷ ካላት ይበልጣል" ብለዋል።

    አራግቺ የአሜሪካ ውጭ ፖሊሲ ተንታኝ የሆኑት ስቴፈን ሴምለርን የፔንታጎን ሰነዶችን እና ሌሎች ምንጮችን ጠቅሰው ይፋ ያደረጉትን መረጃ ተጠቅመው፣ የአሜሪካ ጦር ኃይሎች እአአ ከጥቅምት 2023 ጀምሮ እስራኤልን ለመከላከል 609 የሚሳዔል መቃወሚያዎችን ተኩሷል ብለዋል።

    “ይህ የጋራ ተጠቃሚነት የሚታይበት ግንኙነት ሳይሆን ጥገኝነት ነው” ሲሉ በልጥፋቸው ላይ አስፍረዋል።

    አሜሪካ እና እስራኤል ባለፈው ዓመት የካቲት ወር መጨረሻ ላይ በጋራ በመሆን ቴህራን ላይ ጦርነት ከፍተዋል።

    ኢራን በበኩሏ በባሕረ ሰላጤው የሚገኙ የአሜሪካ ወዳጅ አገራት ላይ ሚሳዔል እና ድሮኖችን ተኩሳለች።

    እንዲሁም የዓለም አንድ አምስተኛው ነዳጅ ዘይት የሚተላለፍበት የሆርሙዝ ወሽመጥን ዘግታለች።

    በዚህም የተነሳ የዓለም ነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ የዋጋ ጭማሪ አሳይቷል።

  12. የኬንያ ቀይ መስቀል በሞያሌ ከግጭት የሸሹ ኢትዮጵያውያንን ለመደገፍ እርዳታ እያቀረበ መሆኑን አስታወቀ

    በሞያሌ ከተማ ከእሁድ ዕለት ጀምሮ በተቀሰቀሰ ግጭት ቤቶች ሲቃጠሉ ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ነዋሪዎች ሕይወትም አልፏል
    የምስሉ መግለጫ, በሞያሌ ከተማ ከእሁድ ዕለት ጀምሮ በተቀሰቀሰ ግጭት ወደ ኬንያ የሸሹ ኢትዮጵያውያን

    የኬንያ ቀይ መስቀል በዚህ ሳምንት በሞያሌ የተቀሰቀሰውን ግጭት በመሸሽ ወደ ኬንያ ለገቡ ኢትዮጵያውያን ሰብዓዊ እርዳታ እየላከ መሆኑን እና በመጀመሪያው ዙር ለ1,000 ቤተሰቦች እንደሚደርስ ገለፀ።

    የኬንያ ቀይ መስቀል እና የድንበር አካባቢው የመንግሥት ባለሥልጣናት እንዳሉት፣ የሞያሌው ግጭት ረቡዕ ዕለት ከተጀመረ በኋላ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን፣ በተለይም ሴቶች፣ ሕፃናት እና ወጣቶች ወደ ኬንያ ተሻግረዋል።

    ሐሙስ ዕለትም በኢትዮጵያ ሞያሌ በኩል የተኩስ ድምፆች ሲሰሙ መዋላቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል።

    በደቡብ ኢትዮጵያ ሞያሌ ከተማ የኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልል በሚዋሰኑበት አካባቢ ከእሁድ ጀምሮ "ባንዲራ ያልተገባ ቦታ መተከሉ"ን ተከትሎ በተቀሰቀሰ ግጭት የሰላማዊ ሰዎች ሕይወት መጥፋቱን ነዋሪዎች እና የአካባቢው ባለሥልጣን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

    ቢቢሲ ያነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎች በግጭቱ ከሁለቱም ወገን ከ10 ዓመት ታዳጊ ጀምሮ በርከት ያሉ ነዋሪዎች መገደላቸውን ተናግረዋል።

    ቢቢሲ የሟቾቹን ቁጥር ከገለልተኛ ወገን ማጣራት ያልቻለ ሲሆን፣ ከሶማሌ ክልል በኩል የባለሥልጣናትን አስተያየት ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

    ከኢትዮጵያዋ አጎራባች ከተማ ጋር ተመሳሳይ ስም ያላት የኬንያዋ ሞያሌ ሰላማዊ እንደሆነች ብትቀጥልም፣ ድንበር ተሻጋሪ ተባራሪ ጥይቶች በመኖራቸው የተነሳ ፖሊስ በተጠንቀቅ ላይ ነው።

    የኬንያ ቀይ መስቀል ጊዜያዊ መጠለያዎችን ማቋቋም መጀመሩን ገልፆ፣ ድንኳኖችን፣ ብርድ ልብሶችን፣ የውኃ ጀሪካኖችን፣ የወጥ ቤት ዕቃዎችን እና ዱቄትን የመሳሰሉ የምግብ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ ድጋፎችን እያከፋፈለ እንደሚገኝ ሮይተርስ ዘግቧል።

    “ብዙዎቹ ስደተኞች በጣም ጥቂት ቁሳቁስ ይዘው ነው የመጡት። እናም በአስቸኳይ መጠለያ፣ ምግብ፣ ውኃ እና የጤና አገልግሎት ያስፈልጋቸዋል” ሲል ድርጅቱ ሐሙስ አመሻሽ ላይ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

    ሮይተርስ ተመለከትኩት ያለው የፖሊስ ሪፖርት፣ በግጭቱ መሀል የተተኮሰ ተባራሪ ጥይት በኬንያ ሞያሌ ከተማ የምትኖር አንዲትን ሴት አንገት ላይ መምታቱን አመልክቷል። ሴቲቱ ወደ ግል ሆስፒታል ገብታ ጥይቱ ወጥቶላት አሁን ጤናዋ በጥሩ ሁኔታ ላይ ነው ሲል ሪፖርቱ ጨምሮ ገልጿል።

    በኬንያ በኩል ያሉ የአካባቢው መንግሥት ባለሥልጣናት ለተፈናቀሉ ቤተሰቦች የሚውል የሰብዓዊ እርዳታ ለማስተባበር ዛሬ ዓርብ ጥቅምት 13/2019 ዓ.ም ስብሰባ እንደሚያካሂዱ ዘገባው ጠቁሟል።

    በሞያሌ ከተማ ከእሁድ ዕለት ጀምሮ በተቀሰቀሰ ግጭት ቤቶች ሲቃጠሉ ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ነዋሪዎች ሕይወትም አልፏል
    የምስሉ መግለጫ, በሞያሌ ከተማ ከእሁድ ዕለት ጀምሮ በተቀሰቀሰ ግጭት ወደ ኬንያ የሸሹ ሰዎች
  13. በደቡብ አፍሪካ በተፈጸመ የደቦ ጥቃት አንድ ስደተኛ መገደሉን ፖሊስ አስታወቀ

    በደቡብ አፍሪካ የተካሄዱ የጸረ ስደተኛ የተቃውሞ ሰልፎች ሰነድ አልባ የሆኑ ስደተኞች አገሪቱን ለቅቀው እንዲወጡ ጠይቀዋል
    የምስሉ መግለጫ, በደቡብ አፍሪካ የተካሄዱ የጸረ ስደተኛ የተቃውሞ ሰልፎች ሰነድ አልባ የሆኑ ስደተኞች አገሪቱን ለቅቀው እንዲወጡ ጠይቀዋል

    በደቡብ አፍሪካ ደርባን ወደ 50 የሚጠጉ ሰዎች አንድ የውጭ ዜጋ ላይ ድብደባ ፈጽመው ሕይወቱ ማለፉን ፖሊስ አስታወቀ።

    ፓሊስ የሟች ማንነትን ያልገለጸ ሲሆን እድሜው በ30ዎቹ መጨረሻ ወይም በ40ዎቹ መጀመሪያ ላይ እንደሚገመት ተናግሯል።

    ግለሰቡ መጀመሪያ ሁለት ሰዎች ካስቆሙት በኋላ በመቀጠል በርከት ያለ ቁጥር ያላቸው ጥቃት አድረሰውበት ሕይወቱ ማለፉ ተገልጿል።

    ፖሊስ በግድያው ላይ ምርመራ መጀመሩን አስታውቋል።

    በዚህ ዓመት በደቡብ አፍሪካ በርካታ ጸረ ስደተኛ ሰልፎች ሲካሄዱ የነበረ ሲሆን በኋላ ላይ ወደ አመጽ ተቀይረዋል።

    በዚህ ወር መጀመርያ ላይ በደርባን እና ጆሃንስበርግ አቅራቢያ በምትገኘው ሶዌቶ ሱቆች እና መኪናዎች ተቃጥለዋል።

    የአካባቢው ፖሊስ ቃል አቀባይ ሮበርት ኔትሺዩንዳ ለቢቢሲ በደርባን ለተፈጸመው ግድያ መነሻ ምን እንደሆነ መገመት እንደማይችሉ ገልጸው ጉዳዩ ሲጣራ ተጨማሪ መረጃ እንደሚሰጡ ተናግረዋል።

    መንግሥት፣ስደተኞችን በሚመለከት የፖሊሲ ማሻሻያ እንደሚያስፈልግ ቢቀበልም፣ ተቃውሞ የሚያሰሙ ሰዎች በሰላማዊ መንገድ እንዲንቀሳቀሱ ጥሪ አቅርቧል።

    በተጨማሪም ባለፈው ዓመት አጋማሽ ጀምሮ ሰነድ አልባ ስደተኞች ላይ ጥብቅ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን አስታውቆ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የውጭ ዜጎች ከአገር እንዲወጡ መደረጋቸውን ገልጿል።

    ጸረ ስደተኛ ተቃውሞዎችን ከሚያደርጉ ቡድኖች መካከል አንዱ የሆነው ማርች ኤንድ ማርች መጀመርያ ላይ ሰነድ አልባ ስደተኞች እስከ ባለፈው ዓመት ሰኔ 30 ድረስ ደቡብ አፍሪካን ለቅቀው እንዲወጡ ቀነ ገደብ አስቀምጦ ነበር።

    ከቀነ ገደቡ በፊት በርካታ የተቃውሞ ሠልፎች የተካሄዱ ሲሆን አፍሪካውያን ስደተኞች ላይ ጥቃቶች ተሰንዝረዋል።

    ይህም እንደ ዚምቧብዌ፣ ናይጄሪያ እና ጋና ያሉ አገራት ተጨማሪ ጥቃት ሊኖር ይችላል በሚል ስጋት ዜጎቻቸውን አስወጥተዋል።

  14. የጀርመን ቻንስለር አገራቸው ከፍተኛ ስለላ እየተደረገባት መሆኑን ተናገሩ

    ቻንስለር ፍሪድሪክ ሜርዝ በጀርመን የሚካሄደው የሩሲያ የስለላ እንቅስቃሴ "እየጨመረ " እንደሚገኝ ተናገሩ
    የምስሉ መግለጫ, ቻንስለር ፍሪድሪክ ሜርዝ በጀርመን የሚካሄደው የሩሲያ የስለላ እንቅስቃሴ "እየጨመረ " እንደሚገኝ ተናገሩ

    ለሩሲያ ሰልሏል በሚል ጥርጣሬ አንድ የዩክሬን ዜጋ መታሰሩን ተከትሎ፣ ጀርመን ከፍተኛ ስለላ እየተደረገባት መሆኑን እና እንቅስቃሴው "እየጨመረ" መሆኑን የጀርመን ቻንስለር ፍሬድሪክ ሜርዝ ተናገሩ።

    የጀርመን ባለሥልጣናት ተጠርጣሪው ቫዲም ዋይ እንደሚባል ገልጸው የአገሪቱን ወታደራዊ ደህንነት መረጃዎቸን ሰብስቧል ብለዋል።

    ሜርዝ የተጠርጣሪውን በቁጥጥር ሥር መዋል “ውጤታማ” ካሉ በኋላ ነገር ግን "በጀርመን የሚንቀሳቀሱት የሩሲያ ሰላዮች እንቅስቃሴ አሁንም በከፍተኛ ደረጃ ላይ ስለሚገኝ ራሳችንን አናዘናጋ" በማለት አስጠንቅቀዋል።

    በዘንድሮው ዓመት በጀርመን፣ ለሩሲያ እና ለሌሎች የውጭ ኃይሎች ይሰልላሉ ተብለው የተጠረጠሩ በርካታ ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል።

    እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2022 ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወረራ ከፈጸመች ጊዜ አንስቶ፣ ጀርመን ለዩክሬን የጦር መሳሪያ ከሚያቀርቡ ዋና ዋና የአውሮፓ አገራት አንዷ ነች።

    የጀርመን ፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ መስሪያ ቤት በአገሪቱ ሕግ መሠረት ሙሉ ስሙ እንዳይገለጽ የተደረገው ቫዲም ዋይ ቢያንስ ከሐምሌ 2025 ጀምሮ በሦስተኛ ወገን በኩል ከሩሲያ የስለላ አገልግሎት ጋር ግንኙነት ሲያደርግ እንደነበር አስታውቋል።

    ዩክሬናዊው “የጦር ሠራዊቱ መኪኖች ፣ የጦር መሣሪያዎች እና ፈንጂዎች ምርቶችን” የሚመለከቱ መረጃዎች ሰብስቧል ብለዋል።

    አርብ ዕለት ፍርድ ቤት ይቀርባል ተብሎ ይጠበቃል።

    ባለፈው ዓመት ታህሳስ ወር ላይ ሌላ ተጠርጣሪ በሩሲያ ኤምባሲ ለሚገኝ የደህንነት ባልደረባ መረጃዎችን ስትሰበስብ በቁጥጥር ስር መዋሏ ተገልጾ ነበር።

    የጀርመን አቃቤ ሕግ መስሪያ ቤት በዚህ ዓመት ከተፈጸሙ ሌሎች እስሮች መካከል ከጀርመን ወደ ዩክሬን ድሮኖችን የሚያቀርብን ግለሰብ በስለላ ተከታትለዋል በሚል የተጠረጠሩ አንዲት ሮማኒያዊት ሴት እና አንድ ዩክሬናዊ ወንድ ይገኙበታል።

  15. ኢትዮጵያዊቷ የማራቶን አትሌት የተከለከለ ንጥረ ነገር በመጠቀምና የሐሰት የሕክምና ሰነድ በማቅረብ ስድስት ዓመት ታገደች

    አትሌት ሩቲ እአአ በ2017 በበርሊን ማራቶን ላእ ካሸነፈች በኋላ
    የምስሉ መግለጫ, አትሌት ሩቲ እአአ በ2017 በበርሊን ማራቶን ላእ ካሸነፈች በኋላ

    ኢትዮጵያዊት የማራቶን አትሌት ሩቲ አጋ፣ የተከለከለ ንጥረ ነገር በመጠቀምና የሐሰት የሕክምና ሰነድ በማቅረብ የስድስት ዓመት እገዳ ተጣለባት።

    የ32 ዓመቷ አትሌት እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2019 የተካሄደው የቶኪዮ ማራቶንን አሸንፋለች።

    እአአ በመጋቢት 2026 በቻይና በተካሄደ የግማሽ ማራቶን ውድድር ከተሳተፈች በኋላ በተደረገላት የዶፒንግ ምርመራ ሜቲልፕሬድኒሶሎን (Methylprednisolone) የተባለ የተከለከለ ንጥረ ነገር በሰውነቷ ውስጥ መገኘቱ ተገልጿል።

    ከአራት ዓመታት በፊት በተደረገላት ቃለ መጠይቅ ወቅት መርማሪዎችን ስታሳስት እንደነበር እና የተጠቀመችበትን ንጥረ ነገር ለማስረዳትም ሐሰተኛ የሕክምና ማዘዣ አቅርባ እንደነበር መረጋገጡ ተዘግቧል።

    በዚህም መሠረት ጉዳዩን ሲከታተል የነበረው አትሌቲክስ ኢንተግሪቲ ዩኒት (Athletics Integrity Unit) የተከለከለውን ንጥረ ነገር በመጠቀሟ የሁለት ዓመት፣ የሐሰት ሰነድ በማቅረቧ ደግሞ የአራት ዓመት እገዳ ተጣልባታል። በድምሩም የስድስት ዓመት ከባድ የውድድር እገዳ ተጥሎባታል።

    ሩቲ አጋ ከመስከረም 10 ጀምሮ ከማንኛውም ሩጫ በጊዜያዊነት ታግዳ ቆይታ ነበር።

    በተጨማሪም እገዳው ከየካቲት 2026 ጀምሮ ተፈጻሚ እንዲሆንና ከመስከረም 10 ቀን 2026 ጀምሮ ያስመዘገበቻቸው ውጤቶች እንዲሰረዙ መወሰኑ ተገልጿል።

    አትሌቷ በዋና ዋና ዓለም አቀፍ ውድድሮች ሁለት ጊዜ ሦስተኛ እንዲሁም ሦስት ጊዜ ሁለተኛ በመሆን አጠናቅቃለች።

  16. ግብፅ የየመንን ቀውስ ለመፍታት ፖለቲካዊ መፍትሄ እንዲፈለግለት ጥሪ አቀረበች

    የግብፁ ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታህ አልሲሲ ከብሔራዊ መከላከያ ምክር ቤት አባለት ጋር ተሰብስበው
    የምስሉ መግለጫ, የግብፁ ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታህ አልሲሲ ከብሔራዊ መከላከያ ምክር ቤት አባለት ጋር ተሰብስበው

    የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ አገራቸው በየመን የሚካሄደውን ግጭት በውይይት ለመፍታት የሚቻሉትን አማራጮች ሁሉ መሞከር እንደምትፈልግ ተናገሩ።

    ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት የግብፅ ጦር በኢራን ድጋፍ ከሚንቀሳቀሱት ሁቲዎች ጋር በሚደረገው ጦርነት ሳዑዲ አረቢያን ለመደገፍ ያቀረበው ምክረ ሃሳብ ላይፓርላማው በሚቀጥለው ሳምንት ድምፅ ከመሰጠቱ አስቀድሞ ነው።

    በቀጣናው ካሉት ትላልቅ ኃይሎች አንዱ የሆነው የግብፅ ጦር በቀጥታ በዚህ ግጭት ውስጥ መሳተፉ፣ በሳዑዲ አረቢያ እና በሁቲዎች መካከል ያለውን ውጥረት በእጅጉ ያባብሰዋል።

    ይህ ግጭት አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ እያካሄዱት ባለው እና እየተስፋፋ በመጣው ጦርነት ውስጥ አለመረጋጋትን ይበልጥ እያባባሰ መጥቷል።

    ፕሬዚዳንት አብደል ፋታህ አል ሲሲ ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ዕለት ለሳዑዲ አረቢያ የሚደረገውን ወታደራዊ ድጋፍ ለማጽደቅ አስቸኳይ የፓርላማ ስብሰባ እንዲጠራ ጠይቀዋል።

    እሁድ ዕለት ዝግ ስብሰባ ከተካሄደ በኋላ፣ የፓርላማ አባላቱ ለውይይት ተጨማሪ ጊዜ እንዲኖር በማሰብ ድምፅ የመስጠት ሂደቱን እስከ የሚቀጥለው ሳምንት ሰኞ ድረስ አራዝመውታል።

    የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባድር አብደላቲ እና የስለላ አገልግሎት ኃላፊው ሀሰን ራሻድ ረቡዕ ዕለት ወደ ሪያድ ተጉዘው ከፕሬዚዳንት ሲሲ የተላከ ደብዳቤ ለሳዑዲ አልጋ ወራሽ መሐመድ ቢን ሳልማን አድርሰዋል።

    ፕሬዚዳንት ሲሲ እንደገለጹት፣ ግብፅ የምታደርገው ወታደራዊ ድጋፍ የሳዑዲ አረቢያን ግዛትና ድንበሮችን መከላከል ላይ ብቻ የተገደበ መሆኑን ገልጸው የመን ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ዕቅድ እንደሌላቸው ተናግረዋል።

    ግብፅ የምትሰጠው ድጋፍ ምን እንደሆነ እስካሁን ድረስ ግልጽ አይደለም።

    አብደላቲ ሐሙስ ዕለት ግብፅ ወደ ፖለቲካዊ መፍትሔ ለመድረስ የሚቻሉትን መንገዶች በሙሉ ለመፈተሽ ትፈልጋለች ብለዋል።

    በተጨማሪም ግብፅ፣ ሁቲዎች በመስከረም ወር በባብ አል-ማንደብ ወሽመጥ አቅራቢያ ከተቆጣጠሯቸው አካባቢዎች ሙሉ በሙሉ እንዲወጡ ትፈልጋለች።

    ይህ ወሽመጥ ወደ ቀይ ባህር መግቢያ ላይ የሚገኝ ወሳኝ የመርከብ መስመር ሲሆን፣ ወደ ግብፅ የስዊዝ ካናል የሚያደርስም ቁልፍ መተላለፊያ ነው።

    አብደላቲ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ሳዑዲ አረቢያ የምታደርገውን ጥረት እየደገፈች በሌላ በኩል ደግሞ ፖለቲካዊ መፍትሄን መከተል እንደምትፈልግ ተናግረዋል።

    በየመን ዓለም አቀፍ እውቅና ያለውን መንግሥት የሚደግፈው እና በሳዑዲ አረቢያ በሚመራው ጥምረት ከሁቲ ታጣቂዎች ጋር የሚያደርገው ውጊያ ተባብሶ ቀጥሏል።

    ሁቲዎች ወደ ባብ አል-ማንደብ ወሽመጥ መጠጋታቸው በዓለም አቀፍ የነዳጅ አቅርቦት ላይ ተጨማሪ ጫና ፈጥሯል።

    ከዚያ ወዲህም ቡድኑ በሳዑዲ አረቢያ የሚገኙ አውሮፕላን ማረፊያዎችን እና የነዳጅ ተቋማትን አጥቅቷል።

    በዓለም ቀዳሚ የነዳጅ ላኪ የሆነችው ሳዑዲ አረቢያ፣ ለግብፅ ወሳኝ ስትራቴጂካዊ እና ኢኮኖሚያዊ አጋር ነች።

    በየመን ውስጥ ሰብዓዊ ቀውስ ያስከተለው ጦርነት የተጀመረው እንደ አውሮፓውያኑ በ2014 ሁቲዎች ዓለም አቀፍ እውቅና የተሰጠውን መንግሥት ከሰሜናዊው ዋና ከተማ ሲያስወጡ ነው።

    ይህም በሳዑዲ አረቢያ የሚመራ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነትን አስከትሏል።

  17. ኢልሃን ኦማር በቤቷ ላይ ብርበራ ከተደረገ በኋላ ለቅቃ ለመውጣት መገደዷን ተናገረች

    ኢልሃን ኦማር

    የአሜሪካ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆነችው ኢልሃን ኦማር ባለፈው ሳምንት የፌዴራል የደህንነት አካላት ቤቷን ከበረበሩ በኋላ ፍተሻው የመኖሪያ አድራሻዋን ለሌሎች አጋልጦ ሊሆን ይችላል በሚል ስጋት በዋሽንግተን ዲሲ በሚገኘው መኖሪያ ቤቷ ውስጥ መኖር እንደማትችል ተናገረች።

    ኢልሃን ኦማር ቤቷ በፌደራል ጸጥታ አካላት ከተበረበረ በኋላ በሰጠችው የመጀመርያ ቃለ ምልልስ “እየደረሱብኝ ያሉት የግድያ ዛቻዎች እንዳሉ ሆነው፣ እኔና ልጆቼ በዚያ ቤት ውስጥ መኖራችን ከአሁን በኋላ አስተማማኝ አይደለም” ብላለች።

    ኦማር ኤምኤስኤን ናው ለተባለ መገናኛ ብዙኃን የአገር ውስጥ ደህንነት ሠራተኞች ስልኮቿን ጨምሮ ማስታወሻ ደብተሮቿን እና በርካታ ንብረቶቿን ለምርመራ በሚል መውሰዳቸውን ተናግራለች።

    መንግሥት ኦማር በምን ወንጀል እንደተጠረጠረች ባይናገርም ነገር ግን ብርበራው የተካሄደው “ከፌደራል ወንጀል ምርመራ ጋር በተያያዘ” መሆኑን ገልጿል።

    ኦማር ቤቷ ከመመርመሩ በፊት እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2020 ካገኘችው የአሜሪካ ዜግነቷን ጨምሮ በርካታ ጥያቄዎ ቀርበውባት ነበር።

    በምርመራው ሂደት ውስጥ፣ የኦማር ቤተሰብ አባላት ላይ ከአስራ ሁለት በላይ የፍርድ ቤት መጥሪያዎች ወጥተዋል። እንደ ዘገባዎቹ ከሆነ፣ የግል ኮምፒውተሮቿ እና ፓስፖርቷ ከተያዙት ንብረቶች መካከል ይገኙበታል።

    በቤቷ ላይ ለሰዓታት ለቆየው ፍተሻ በተመለከተ ለኤምኤስ ናው አስተያየቷን የሰጠችው ኦማር፣ “ይህ በእርግጠኝነት ሁላችንንም በጣም አስደንግጦናል” ብላለች።

    ኦማር የደህንነት አባላት እርሷ እና ባለቤቷ እንቅልፍ ላይ እያሉ “በራችንን ደብድበዋል” ስትል ፍተሻው የተደረገበትን ሁኔታ አብራርታለች።

    “እየጮህን ነበር” ያለችው ኦማር፣ ጥንዶቹ ከመኝታ ክፍላቸው ወደ በሩ እየሮጡ መጥተው መክፈታቸውን ሁኔታው “እጅግ እንግዳ ነገር” እንደነበርም አስረድታለች።

    ኦማር ከ15 እስከ 25 የሚሆኑ የደህንነት አባላት ቤቷን መክበባቸውን ነገር ግን ሁሉም “በሥነ ስርዓት ሥራቸውን ማከናወናቸውን” ገልጻለች።

    የደህንነት አባላት በር ላይ እያሉ የፍርድ ቤት ማዘዣ ይዘው እንደሆነ መጠየቋን እና ማሳየታቸውን ጨምራ አብራርታለች።

    የደህንነት አባላቱ ብርበራውን ሲያከናውኑ ሶፋ ላይ ተቀምጣ መመልከቷን የገለፀችው ኢልሃን ኦማር አምስት ያህል የፈጀ ብርበራ መካሄዱን ጨምራ አስታውቃለች፥።

    የእጅ ስልኮች፣ ማስታወሻ ደብተሮች እና የባለቤቷን ካሜራ ጨምሮ 17 ነገሮች መውሰዳቸውንም ተናግራለች።

    ቢቢሲ የአሜሪካ ፍትህ ቢሮን ለማነጋገር ቢጠይቅም ወደ አገር ውስጥ ደህንነት ቢሮ ተመርቷል።

    መንግሥት ምርመራውን ያደረገበትን መንገድ የተቸችው ኦማር ለማስፈራራት ታስቦ የተደረገ እንደሆነ ገልጻለች።

    ባለፈው ሳምንት በተካሄደው ብርበራ ዙሪያ፣ ኦማር በኢንተርኔት ላይ በለቀቀችው መግለጫ ድርጊቱን “ከባድ የሥልጣንን አላግባብ መጠቀም” ያለች ሲሆን ባለስልጣናት የፌዴራል ሕግ አስከባሪ አካላትን በመጠቀም የፖለቲካ ተቃዋሚዎቻቸውን ዒላማ እያደረጉ ነው ስትል ከስሳለች።

    የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማም ብርበራውን አጥብቀው የተቹ ሲሆን፣ ድርጊቱንም “እጅግ አስቀያሚ” ሲሉ ገልጸውታል።

  18. ከአንድ ዓመት በላይ በኒጀር ታግተው የነበሩት ሁለት አውሮፓውያን ሊቢያ ውስጥ ተለቀቁ

    የ76 ዓመቷ ኢቫ ግሬትዝማቸር በኒጀር ለብዙ ዓመታት በእርዳታ ድርጅት ውስጥ ሰርታለች
    የምስሉ መግለጫ, የ76 ዓመቷ ኢቫ ግሬትዝማቸር በኒጀር ለብዙ ዓመታት በእርዳታ ድርጅት ውስጥ ሰርታለች

    አንድ የስዊዝ እና አንዲት ኦስትሪያዊ ከአንድ ዓመት በፊት በኒጀር ከታገቱ በኋላ በሊቢያ ቤንጋዚ መለቀቃቸውን ተገለጸ።

    የ76 ዓመቷ ኦስትሪያዊት ኤቫ ግሬትዝማቸር እና የ69 ዓመቷ ስዊዘርላንዳዊት ክላውዲያ አብት፣ ባለፈው ዓመት ጥር እና ሚያዚያ ወራት በሰሜናዊ ኒጀር አጋዴዝ ከተማ ታግተው ተወስደው ነበር።

    ግለሰቦቹን ያገታቸው ማን አንደሆነ እና ፍላጎታቸው ምን እንደነበር አልተገለጸም።

    ሁለቱ አውሮፓውያን በምን ስምምነት እንደተለቀቁም የተባለ ነገር የለም።

    የኦስትሪያ እና የስዊዘርላንድ መንግሥታት ግለሰቦቹ መለቀቃቸውን አረጋግጠዋል።

    የስዊዘርላንድ መንግሥት አብት ነጻ እንደወጣችና ወደ አገሯ በመመለስ ላይ እንደምትገኝ የገለጸ ሲሆን፣ የኦስትሪያ መንግሥት በበኩሉ ግሬትዝማቸር "ከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች" ከተደረጉ በኋላ መለቀቋን አስታውቋል

    "ኤቫ ከ21 ወራት በላይ በእገታ ስር ከቆየች በኋላ ነጻ በመውጣቷ ሁላችንም ከፍተኛ እፎይታ ተሰምቶናል፣ ለበርካታ ወራት ከቀጣናዊ፣ ከአውሮፓውያን እና ከዓለም አቀፍ አጋሮቻችን ጋር በቅርበት፣ በስውር እና በመተማመን መንፈስ ስንሰራ ቆይተናል። እነዚህ የጋራ ጥረቶችም ፍሬ አፍርተዋል" ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቤአቴ ሜይንል ራይዚንገር በመግለጫቸው ተናግረዋል።

    የስዊዘርላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ የአገሪቱ ባለሥልጣናት በቤንጋዚ ከአብት ጋር ተገናኝተው የነበረ ሲሆን የሕክምና ድጋፍ ተሰጥቷታል ብሏል።

    "ካሳለፈችው ሁኔታ አንጻር በጥሩ ሁኔታ ላይ ትገኛለች፤ በአሁኑ ወቅትም ወደ ስዊዘርላንድ በመመለስ ላይ ትገኛለች" ሲልም ገልጿል።

    ግሬትዝማቸር ለብዙ ዓመታት በኒጀር የእርዳታ ድርጅት ሠራተኛ የነበረች ሲሆን፣ አብት ደግሞ በአጋዴዝ ለበርካታ ዓመታት የማኅበረሰብ ሠራተኛ በመሆን አገልግላለች።

  19. ኢራን ሰባት ነዳጅ ጫኝ መርከቦች በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል ለማለፍ ሲሞክሩ መመታታቸውን አስታወቀች

    መርከቦች በሆርሙዝ ወሽመጥ

    ኢራን ሌሊቱን በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ ሰባት መርከቦች በተተኳሽ ወይንም በፈንጂ ተመትተው በእሳት መያያዛቸውን አስታወቀች።

    የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ የባህር ኃይል ሐሙስ ዕለት በሰሜናዊው የፋርስ ባሕረ ሰላጤ ሕገ ወጥ የነዳጅ ዝውውር ላይ የተሳተፉ አራት መርከቦች ክትትል ከተደረገባቸው በኋላ ተመትተው በእሳት ተያይዘዋል ብሏል።

    አክሎም ሦስት ተጨማሪ መርከቦች ከሆርሙዝ ወሽመጥ በስተ ምዕራብ በፈንጂ ተመትተው በእሳት ተያይዘዋል ብሏል።

    አብዮታዊ ዘቡ በቀጣይ ትንኮሳ የሚኖር ከሆነ በቀጣናው በሚገኙ የጦር ሠፈሮች ላይ መጠነ ሠፊ የአጸፋ እርምጃ እንደሚወስድ አስጠንቅቋል።

    ይህ የቴህራን እርምጃ በቀጣናው ዳግም ጦርነት ይቀሰቀሳል የሚል ስጋት ባየለበት ወቅት የተፈጸመ ነው።

    በእስራኤል የሚካሄደው እንዲሁም በአሜሪካ የሚካሄደው የአጋማሽ ዘመን ምርጫ ጥቂት ሳምንታት በቀሩት በዚህ ወቅት የኢራን ጥቃት የነዳጅ ዋጋ ላይ ከፍተኛ ጭማሪ ይፈጥራል ተብሎ ተፈርቷል።

    አሜሪካ እና እስራኤል ኢራን ላይ የሚፈጽሙትን ጥቃት ዳግም ይጀምራሉ የሚል ስጋት በከፍተኛ ሁኔታ ተፈጥሯል።

    “ኔታንያሁ ኢራንን ማጥቃት ይፈልጋሉ፤ ይህ አጠያያቂ ጉዳይ አይደለም” ሲሉ በእስራኤል ብሔራዊ ደህንነት ጥናት ተቋም ተመራማሪ የሆኑትና ቀደም ሲል በእስራኤል ወታደራዊ እና የስለላ ተቋማት ውስጥ የኢራን ጉዳይ ባለሙያ በመሆን ያገለገሉት ዳኒ ሲትሪኖዊች ለአሶሼትድ ፕሬስ ተናግረዋል።

    እስራኤል ስትራቴጂዋን ሳታሻሽል ከኢራን ጋር ወደ ሌላ ግጭት ለመግባት እየተጣደፈች ነው ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

    ከአምስት ቀን በኋላ ጥቅምት 27 በሚካሄደው ምርጫ ኔታንያሁ በግልጽ ካሸነፉ፣ ጥቃት የመሰንዘሩ ዕድል እጅግ ከፍተኛ ወይም እርግጠኛ ማለት ይቻላል ሲሉም አስተያየታቸውን አጠናቅቀዋል።

  20. በምሥራቅ ሳዑዲ አረቢያ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ በደረሰ ጥቃት ሁለት ሰዎች መገደላቸውን ባለሥልጣናት ገለጹ

    ዳማም በሳዑዲ አረቢያ ምሥራቃዊ ክፍል የምትገኝ ትልቋ ከተማ ናት
    የምስሉ መግለጫ, ዳማም በሳዑዲ አረቢያ ምሥራቃዊ ክፍል የምትገኝ ትልቋ ከተማ ናት

    በረቡዕ ምሽት በምሥራቅ ሳዑዲ አረቢያ ዳማም ከተማ በአውሮፕላን ማረፊያ ላይ በደረሰ ጥቃት ሁለት ሰዎች ሲገደሉ ስምንት መቁሰላቸውን የአገሪቱ የሲቪል አቪየሽን ባለሥልጣናት ተናገሩ።

    በንጉሥ ፋሃድ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የተገደሉት የሳዑዲ እና ሕንዳዊ ዜጎች መሆናቸውን ባለሥልጣናቱ ገልጸው የተጉዱት ደግሞ የሳዑዲ፣ የመን፣ ሕንድ፣ ባንግላዲሽ እና የኔፓል ዜጎች ናቸው ተብሏል።

    የሲቪል አቪየሸን ባለሥልጣናቱ ስለ ደረሰው ጥቃት ዓይነት ማብራሪያ ያልሰጡ ቢሆንም የየመን ሁቲዎች ግን በተደጋጋሚ የሳዑዲን አውሮፕላን ማረፊያዎች በድሮኖች እና ሚሳዔሎች ሲያጠቁ ነበር።

    ረቡዕ ማለዳ ወደ አገሪቱ ምሥራቃዊ ክፍል ተተኩሶ የነበረ ድሮን እንዲከሽፍ ከተደረገ በኋላ በወደቁ ስብርባሪዎች ሁለት ሰዎች መገደላቸው ተገልጿል።

    የሳዑዲ አረቢያ ኤነርጂ ሚኒስቴር ድሮኖቹ ዒላማ ያደረጉት የአገሪቱን የነዳጅ ማቀነባበሪያን እንደነበር ገልጾ አንድ መኪና በእሳት መቃጠሉን አስታውቋል።

    ሁለቱ በድሮን ስብርባሪዎች የሞቱት ሰዎች የፊሊፒንስ እና ኔፓል ዜጋ መሆናቸው ሲገለጽ፣ ረቡዕ ምሽት ተጨማሪ አራት ወደ አካባቢው የተተኮሱ ድሮኖች እንዲከሽፉ መደረጉ ይፋ ሆኗል።

    ሁቲዎች ስለጥቃቱ ወዲያውኑ ምላሽ ባይሰጡም ከዚህ በፊት ግን የሳዑዲን አውሮፕላን ማረፊያ፣ የኢነርጂ ተቋማት እና ወታደራዊ ጦር ሠፈር እንደሚያጠቁ ተናግረዋል።