ተወልደ ገብረማሪያም የተረከቡት ኤር ኢንዲያ አብራሪዎች የአደንዛዥ ዕጽ ምርመራ እንዲያደርጉ ታዘዙ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በቅርቡ ኢትዮጵያዊው ተወልደ ገብረ ማሪያምን በዋና ሥራ አስፈጻሚነት የሾመው የሕንዱ አየር መንገድ አብራሪዎቹ በሙሉ የተከለከሉ ዕጾችን መውሰድ አለመውሰዳቸውን በአስቸኳይ ሊመረምር መሆኑን አስታወቀ።

ኤር ኢንዲያ ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው ባለፈው ሳምንት ከታይላንድ ፑኬት ወደ ዴልሂ ይበር የነበረ አውሮፕላን በድንገት ከፍታውን መቀነሱን ተከትሎ ነው።

የሕንድ ሁለተኛው ትልቁ አየር መንገድ የሆነው ኤር ኢንዲያ የቀድሞውን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ተወልደ ወልደማሪያምን ዋና ሥራ አስፈጻሚው አድርጎ የሾመው በቅርቡ ነው።

ክስተቱን ተከትሎ የወጣው ቅድመ ምርመራ ሪፖርት ዋና አብራሪው የአደንዛዥ ዕጽ ምርመራ ዳግም ማድረግ አለበት ይላል።

የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን አብራሪው ማሪዋና መውሰዱን የሚያመለክት ውጤት መገኘቱን ዘግበዋል።

የኤር ኢንዲያ አካል የሆነው ኤር ኢንዲያ ኤክስፕረስ አብራሪዎችም ከሐሙስ ጀምሮ አደንዛዥ ዕጽ ምርመራ እንደሚደረግላቸው ተገልጿል።

በሕንድ ያሉ መመሪያዎች ቢያንስ 10 በመቶ አብራሪዎች በድንገት የአደንዛዥ ዕጽ ምርመራ እንዲደረግላቸው ያስገድዳል።

ኤር ባስ ሐምሌ 28/2018 ዓ.ም. ለበረራ በተነሳ በጥቂት ደቂቃ ውስጥ በድንገት ከፍታውን በ91 ሜትር በቀነሰበት ክስተት አስራ ሰባት መንገደኞች እና የበረራ አባላቱ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

የሕንድ ባለሥልጣናት ከኤርባስ እና ከፈረንሳይ የአየር ደኅንነት ኤጀንሲ ጋር በመሆን ምርመራ እያደረገ መሆኑን አስታውቋል።

ምርመራው እስኪጠናቀቅ ድረስ ሁለቱም የአውሮፕላን አብራሪዎች ከሥራቸው ታግደዋል።

ቢቢሲ የተመለከተው የውስጥ ማስታወሻ ኤር ኢንዲያ "ምርመራው መቀጠል አለበት" ብሏል።

"ከቁጥጥር መስፈርቶች በላይ የሚሄደው ይህ እርምጃ፣ ከፍተኛውን የደኅንነት እና የሙያዊ ብቃት ደረጃዎችን ለመጠበቅ እንዲሁም ለተሳፋሪዎቻችን፣ ለባለድርሻ አካላት እና ለኅብረተሰቡ በአጠቃላይ ማረጋገጫ ለመስጠት ያለንን ቁርጠኝነት የሚያንፀባርቅ ነው" ሲል ገልጿል።

ባለፈው ዓመት ሰኔ 2025 ላይ ከአህመዳባድ ወደ ለንደን ይበር የነበረ አውሮፕላን ለበረራ በተነሳበት ጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ተከስክሶ 241 ተሳፋሪዎቹ እና በምድር ላይ የነበሩ 19 ሰዎችን ለሞት ከዳረገው አደጋ ወዲህ፣ አየር መንገዱ ምመርራ እየተደረገበት ይገኛል። ከአደጋው የተረፈው አንድ ተሳፋሪ ብቻ ነው።

በአቪዬሽን ደንቦች መሠረት የተከለከሉ ዕጾችን እና መድኃኒቶችን ለመለየት የሚደረጉት እነዚህ ምርመራዎች፣ በኤር ኢንዲያ አካዳሚ የመረጃ ማዕከላት እና ቢሮዎችን ጨምሮ በሌሎችም ቦታዎች እየተከናወኑ ነው።