ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በባሕር ላይ ከ250 ቀናት በላይ የቆዩት የአሜሪካ አውሮፕላን ተሸካሚ መርከቦች ሁኔታ ስጋት ፈጠረ
በአውሮፕላን ተሸካሚ መርከቦች ላይ ከ250 ቀናት በላይ የቆዩ በሺህዎች የሚቆጠሩ የአሜሪካ ጦር አባላት የምግብ እጥረት፣ የቁሳቁሶች መሠበር እና መሠላቸት እንደገጠማቸው ተገለጸ።
የአሜሪካ የሕግ አውጪዎች በጉዳዩ ላይ ፔንታጎን ምላሽ እንዲሰጣቸው እንዲሁም የትራምፕ አስተዳደር የኢራንን ጦርነት እንዲያጠናቅቅ ጫና እያደረጉ መሆኑ ተሰምቷል።
የወታደራዊ ጉዳዮችን የሚዘግቡ አንዳንድ መገናኛ ብዙኃን በዩኤስኤስ አብራሃም ሊንከን መርከብ ላይ የሚገኙ የተወሰኑ ባህረተኞች ከመሰላቸታቸው የተነሳ ወደ ውቅያኖስ ለመዝለል መሞከራቸውን እና ቤተሰቦቻቸውም በመርከቡ ላይ የሚገኙ ሠራተኞች የአእምሮ ጤና ጉዳይ እንዳሳሰባቸው ዘግበዋል።
የመከላከያ ሚኒስትሩ ፒት ሄግሴት ሐሙስ ዕለት ዘገባዎቹ "ፍጹም ሁሉንም የማይወክሉ ናቸው" ሲሉ አጣጥለዋል።
የጦር አውሮፕላኖችን የሚጭነው መርከብ ከካሊፎርንያ ወደ ደቡባዊ ቻይና የተንቀሳቀስው በኅዳር ወር ሲሆን የኢራን ጦርነት ከመጀመሩ በፊት ወደ መካከለኛው ምሥራቅ እንዲሄድ ተደርጓል።
መጀመሪያ ላይ በግንቦት ወር ያበቃል ተብሎ የነበረው ዘመቻው በተደጋጋሚ ተራዝሟል።
የባህር ኃይል አባላቱ ወደ ቤተሰቦቻቸው የሚመለሱበት ቀን አልተገለጸም፣ ነገር ግን ሐሙስ ዕለት በርካታ የዜና አውታሮች እንደዘገቡት አሜሪካ መርከቡን በዩኤስኤስ ጆርጅ ዋሽንግተን ለመተካት እየተዘጋጀች ነው።
ሴናተር ሪቻርድ ብሉሜንታል ለሄግሴት በጻፉት ደብዳቤ በመርከቡ ላይ የሚገኙ 5,000 የሚያህሉ ሠራተኞች "የመሠረታዊ አቅርቦቶች እጥረት፣ የውሃ ብክለት፣ የቧንቧ መሰበር፣ የአእምሮ ጤና ችግር፣ የመርከቧ ደህንነት ስጋቶች እና በፖስታ ስርዓቱ ውስጥ ያሉ መስተጓጎሎች ለወራት ወደ መርከቡ የተላኩ መልዕክቶች በጉዞ ወቅት እንዲጠፉ ምክንያት ሆኗል" ሲሉ ተፈጠሩ ያሏቸውን ችግሮች ዘርዝረዋል።
በመከላከያ ኮሚቴ ውስጥ የሚያገለግሉት ዴሞክራቶች በበኩላቸው "እነዚህ ሪፖርቶች አፋጣኝ ትኩረት ያስፈልጋቸዋል" ሲሉ ጽፈዋል።
አክለውም የባሕር ኃይሉ አሁን የሚጠበቅበትን ዘመቻ በሚፈለገው ፍጥነት ማስቀጠል ይችል እንደሆነ ጠይቀዋል።
ሌላኛው የዲሞክራቱ ሴናተር ሩበን ጋሌጎ፣ ጦሩ የኮንግረስ ልዑክ መርከቧን እንዲጎበኝ እና "በዚህ አስከፊ ሁኔታ ላይ ክትትል እና ምርመራ እንዲያካሂድ" ጥሪ አቅርበዋል።
በተጨማሪም በኤክስ ገጻቸው ላይ "እንዳንጎበኝ የምንከለከልበት ምንም ምክንያት የለም" ብለዋል።
የቢቢሲ የአሜሪካ አጋር የሆነው ሲቢኤስ ኒውስ በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ አንድ መርከበኛ ከጀልባዋ ለመዝለል መሞከሩን እና ወደ ሕክምና ተቋም ተወስዶ ክትትል እንደተደረገለት፣ አሁንም ተጨማሪ እንክብካቤ እያገኘ መሆኑን ሁለት በስም ያልጠቀሳቸውን ባለሥልጣናትን ጠቅሶ ዘግቧል።
በዚህ ባህረተኛ ጤና ላይ የተከሰተውን ዝርዝር ሁኔታ ለማወቅ ምርመራ እየተደረገ መሆኑ ተገልጿል።
ሚልታሪ ታይምስ እና ስታርስ ኤንድ ስትራይፕስ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ እንደዘገቡት በርካታ የጦር ሠራዊት አባላት ከመርከብ በላይ መዝለል ማሰባቸውን ለቤተሰቦቻቸው ተናግረዋል። ለረዥም ጊዜ በባህር ላይ በመቆየታቸው እና በመርከቧ ውስጥ ያሉት ሁኔታዎች የአንዳንድ አባላትን የአእምሮ ጤና እየጎዳ እንደሆነ ጨምረው አስረድተዋል።
ባህረተኞቹ ከጠቀሷቸው የመርከቧ ሁኔታዎች መካከል አንዱ ከአንድ ሳምንት በላይ ልብስ ማጠብ አለመቻል ይገኝበታል።
በተጨማሪም ትኩስ ምግብ አለመመገብ እና በየጊዜው ወደ ወደቦች ሄዶ መናፈስ አለመቻል ሁኔታዎችን ካባባሱት መካከል መሆናቸው ተዘርዝሯል።
በመርከቡ ላይ የሚገኝ የአንድ መርከበኛ ቤተሰብ ለቢቢሲ ኒውስ እንደተናገረው የቤተሰባቸው አባል መርከቧ ላይ ከተመደበ ጊዜ ጀምሮ 29 ኪሎ ግራም ቀንሷል።
ቅጣት ሊጣልበት ይችላል በሚል ማንነታቸው እንዳይገለጽ የጠየቁት እኚህ የቤተሰብ አባል ባህረተኞቹ ከመርከቡ ለመዝለል መሞከራቸውን መስማታቸውን ገልጸዋል።
በቅርብ ጊዜ በዋትስአፕ ባደረጉት የመልዕክት ልውውጥ ወቅት " 'ደክሞኛል' ሙትት እስክል ድረስ ነው የዛልኩት" ማለቱን ጨምረው ተናግረዋል።
ባህረተኞቹ ከመርከቡ ሞተርና አውሮፕላኖች ሲነሱና ሲወርዱ በሚሰማው የማያቋርጥ ድምፅና ንዝረት መቸገራቸውንም ገልጸዋል።
"የተሰጠውን ተልዕኮ ይገነዘባል፤ ነገር ግን ይህ ተስማሚ ሁኔታ እንዳልሆነ ያውቃል" ሲሉ የቤተሰብ አባሉ ተናግረዋል።
"እረፍት አይደለም የሄደው። ምን ማድረግ እንዳለበትም ያውቃል። ግን ወደብ ሳይኖር፣ መሬት ላይ እግር ሳይረግጥ፣ ምንም ዓይነት ስሜትን ዘና የሚያደርግ ሁኔታ ሳይኖር መቀጠል ከባድ ነው። የማያቋርጥ ንዝረት ይሰማል። ጠዋት፣ እኩለ ቀን እና ማታ ስትተኛ፣ ስትበላ፣ ሻወር ስትወስድ። በአእምሮህ ውስጥ የሰላም ጊዜ የለም።"
የካሊፎርኒያ ኮንግረስማን ማይክ ሌቪን በኤክስ ገጻቸው ላይ "ሻጋታ የከበበው ገላ መታጠቢያ፣ የተሰበረ መጸዳጃ ቤት፣ ለሳምንታት የማይሰራ የልብስ ማጠቢያ፣ ያለ ሙቅ ውሃ ረጅም ጊዜ መቆየት፣ ግማሽ ኩባያ ሩዝ እና ሁለት ቶርቲላ ብቻ መመገብ፣ የሳሙና፣ ዲኦድራንት ወይም የጥርስ ሳሙና አለመኖር " ባህረተኞቹ ከሚጋፈጧቸው ችግሮች መካከል መሆናቸውን ዘርዝረዋል።
በጥር ወር 2025፣ 956 የአሜሪካ ባህር ኃይል ባህረተኞች ላይ በተደረገ ጥናት "ከባድ የሥነ ልቦና ጫና" እንዳለባቸው ታይቷል።
ጥናቱ እንደ ደካማ የመኖሪያ ሁኔታ፣ ጫጫታ እና ለእንቅልፍና ለእረፍት በቂ ጊዜ የማይሰጡ አድካሚ የሥራ ሁኔታዎች ለጭንቀት መነሻ መሆናቸውን ጠቅሷል።
በአሜሪካ የባሕር ኃይል አባላት መካከል ራስን ማጥፋት በከፍተኛ ቁጥር ተመዝግቧል።