ከእገታ እስከ ግድያ፡ ሐኪሞች ዒላማ እየሆኑበት ያለው የአማራ ክልል ግጭት

የታገቱ የጤና ባለሙያዎች

የፎቶው ባለመብት, Debark Hospital

የምስሉ መግለጫ, ከደባርቅ ሆስፒታል የታገቱት ዶ/ር አስማረ ጌታነህ (በስተግራ)፣ ታደሰ እውነቱ (መሀል) እና መሳፍንት ሰረበ (በስተቀኝ)
የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

በአማራ ክልል በመጋቢት መጨረሻ ሳምንታት በተፈፀሙ ጥቃቶች ሦስት የጤና ባለሙያዎች ሲገደሉ ሦስት ባለሙያዎች መታገታቸውን እና አንድ ሐኪም ደግሞ መታሰሩን ቢቢሲ ከተለያዩ ምንጮች ያሰባሰባቸው መረጃዎች አመለከቱ።

በአማራ ክልል ውስጥ በመንግሥት ኃይሎች እና በታጣቂዎች መካከል ግጭት ከተቀሰቀሰበት ከ2015 ዓ.ም. መጨረሻ ጀምሮ የጤና ባለሙያዎች ከባድ ዋጋ እየከፈሉ እንደሆነ ይናገራሉ።

መጋቢት 24 በሰሜን ጎጃም ዞን ሰሜን ሜጫ ወረዳ ሐሙሲት በተባለች አነስተኛ ከተማ የሚያገለግሉ ሦስት የጤና ባለሙያዎችን ጨምሮ ሰዎች መገደላቸው ታውቋል።

በአካባቢ ግጭት እንደነበር አንድ የተጎጂ ቤተሰብ ለቢቢሲ የተናገሩ ሲሆን፣ ከፋኖ ታጣቂዎች ጋር ትስስር ያላቸው የመገናኛ ብዙኃን ግጭት መካሄዱን ዘግበዋል።

ባለሙያዎቹ በውጊያ የቆሰለን የፋኖ ታጣቂ አክመው በባጃጅ እየተመለሱ ሳለ መርዓዊ ከተማ አካባቢ "ቻይና ካምፕ" የሚባል ስፍራ ሳይደርሱ ከባጃጅ ሹፌሩ ጋር እንደተገደሉ አንድ የሟች ቤተሰብ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ሁለቱ የጤና ባለሙያዎች አብዮት ፋና ጤና ጣቢያ (ሐሙሲት ጤና ጣቢያ) ባለሙያ ሲሆኑ፣ አንደኛው ባለሙያ ደግሞ በግል ክሊኒክ የሚሠራ እንደሆነ ታውቋል።

የጤና መኮንን እና የሦስት ልጆች አባት የሆነው ቤተሰባቸው ከሟቾቹ መካከል እንደሆነ የቤተሰብ አባሉ ተናግረዋል።

"ነፍሴን አለውቅም" ሲሉ የቤተሰባቸውን ሞት የተረዱበትን ቅፅበት የገለፁት ግለሰብ፤ የጤና ባለሙያው የቤተሰብ አስተዳዳሪ እና አጋዥ መሆኑን ገልጸዋል።

የቤተሰብ አባሉ የጤና ባለሙያዎች ከጤና ጣቢያው ውጭ ለሕክምና እንዴት እንደወጡ ሲናገሩ "[በፋኖ ኃይሎች] 'ኑ ተብለን በግዴታ ነው የሄድነው' ብለዋል። እንዴት ሆነው እንደሄዱ እኔ እንጃ" ብለዋል።

የዓለም የጤና ድርጅት ኃላፊ ዶ/ር ቴድሮስ አድኃኖም ረቡዕ መጋቢት 30/2018 ዓ.ም. ባወጡት መግለጫ ሦስት የጤና ባለሙያዎች በጥይት ተመተው መገደላቸውን አስታውቀው፤ ግድያውን ማን እንደፈፀመ ግን ያሉት ነገር የለም።

ይሁን እንጂ ግድያውን በክልሉ በመንግሥት ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ግጭቱ እየተስፋፋ ባለበት ወቅት የተፈፀመ ነው ብለዋል።

ዶ/ር ቴድሮስ ባለፈው የካቲት ወር ባወጡት ተመሳሳይ መግለጫም እስርን እና ድብደባን ጨምሮ የጤና ባለሙያዎች ለተለያዩ ጥቃቶች ዒላማ መሆናቸውን አስታውቀው፤ ዶ/ር ፀጋሁን ስሜ የተባለ ሐኪም በባሕር ዳር ከተማ ውስጥ በፀጥታ ኃይሎች ከተወሰደ በኋላ ሕይወቱ አልፎ መገኘቱን ጠቅሰዋል።

"የጤና ባለሙያዎች በማንኛውም ጊዜ ሊጠበቁ እና ለሚያስፈልጋቸው ሰው ሁሉ ሕይወትን የሚያድኑ ሥራዎቻቸውን ሊያከናውኑ ይገባል" ሲሉ አሳስበዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት ከክልሉ ዋና ከተማ በቅርብ ርቀት የተፈፀመውን የጤና ባለሙያዎች ግድያ "ገለልተኛ አካል" እንዲመረምረው ጠይቋል።

ቢቢሲ ከሰሜን ሜጫ ወረዳ አስተዳዳሪ በጤና ባለሙያዎቹ ላይ ስተፈጸመው ግድያ መረጃ ለማግኘት በተደጋጋሚ ያደረገው ጥረት ምላሽ አላገኘም።

ጤና ጣቢያ አገልግሎት ለማግኘት የተቀመጡ ሠዎች

የፎቶው ባለመብት, Amhara Health Bureau

የምስሉ መግለጫ, ባለፈው ማክሰኞ የደባርቅ ሆስፒታል ስፔሻሊት ሐኪምን ጨምሮ ሦስት ባለሙያዎች መታገታቸው ተነግሯል
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በአማራ ክልል የጤና ባለሙያዎች ላይ ባነጣጠረ ሌላ ክስተት ደግሞ ሦስት የደባርቅ ሆስፒታል ባለሙያዎች መታገታቸው ታውቋል።

እገታው መጋቢት 29/2018 ዓ.ም. ባለሙያዎቹ መድኃኒት ጭነው ወደ ሆስፒታሉ እየመጡ ሳለ በወገራ ወረዳ አርባ አራት በተባለ ቦታ ላይ መፈፀሙን ሆስፒታሉ ገልጿል።

የእገታው ሰላባ ከሆኑት ውስጥ "ብቸኛ" የሆስፒታሉ የማህፀን እና ፅንስ ስፔሻሊስት ሐኪም የሆኑት ዶ/ር አስማረ ጌታነህ ይገኙበታል።

የታጋቾችን ስም ዝርዝር ያወጣው ሆስፒታሉ፤ የፋርማሲ ባለሙያ ታደሰ እውነቱ እና የአምቡላንስ ሹፌር የሆነው መሳፍንት ሰረበ እንደሆኑ አስታውቋል።

አንድ የሆስፒታሉ ሐኪም ስለፋርማሲ ባለሙያው ምስክርነታቸውን ሲሰጡ "በጣም ጎበዝ፤ ታታሪ ሠራተኛ" ብለዋቸዋል።

"ይህ እንደሚሆን ይታወቅ ነበር" ያሉት ሐኪሙ በአካባቢው የጤና ባለሙያዎች በተለይም የአምቡላንስ ሹፌሮች ተደጋጋሚ እገታ እና ዝርፊያ እንደሚፈፀምባቸው ተናግረዋል።

"አማራጭ የለም በቃ። ምክንያቱም ምንም ነገር በሌለበት፤ ሕይወት ከአቅም በላይ ሲሆን ነው ወደ ሆስፒታል ሪፈር የምናደርገው። በዚህ ሰዓት ደግሞ የመጨረሻው ሐኪሙ፤ ምኑም አይደለም፤ እነርሱ [የአምቡላንስ ሹፌሮች] ናቸው።

"ሦስት የአምቡላንስ ሹፌሮች አሉ። ሦስቱም ተዘርፈዋል። ሦስቱም እጃቸው ላይ ስማርት ስልክ አይታይም፤ ትንሿን ስልክ ነው የሚይዙት። ምክንያቱም እንደሚዘረፉ ስለሚያውቁ። በፓንት ብቻ አስቀርተዋቸው ሌላ ሆስፒታል አድረው ያውቃሉ" የሚሉት ሐኪሙ እገታ ድረስ ይሄዳሉ ተብሎ አልተቀም ሲሉ የክስተቱን ክብደት ገልፀዋል።

የደባርቅ ሆስፒታል "ብቸኛ" የተባሉት የማህፀን እና ፅንስ ስፔሻሊስት ሐኪም ከ11 ወራት ቆይታ በኋላ መመደባቸውንም ጠቁመው፤ በቀን በአማካነዕ እስከ ሦስት ሕፃናት በቀዶ ሕክምና (በኦፕሬሽን) እንደሚወለዱ ተናግረዋል።

የባለሙያዎቹ እገታ ለአራት ሚሊዮን ሕዝብ አገልግሎት ለሚሰጠው የደባርቅ ሆስፒታል እና ማኅበረሰቡ ላይ የሚኖረውን ጫና ገልፀዋል።

"ለሚቀጥሉት ስድስት እና ሰባት ወራት አንድ ስፔሻሊስት [ሐኪም] አይታይም" በማለት በደኅንነት ስጋት ምክንያት የባለሙያዎች እጥረት እንደሚኖር በእርግጠኝነት ተናግረዋል።

ደባርቅ ሆስፒታል እገታው በማን እና ለምን እንደተፈፀመ ሳይጠቅስ ባወጣቸው ጠንከር ያሉ መግለጫዎች "ባለሙያዎች ብቻ ሳይሆኑ የታገቱት ማኅበረሰቡም ነው" ብሏል።

ስሜ አይጠቀስ ያሉት የሆስፒታሉ ቀዶ ሕክምና ባለሙያ እገታው ከገንዘብ ጋር የተያያዘ ነው የሚል እምነት እንዳለቸው፤ በአካባቢው የማስለቀቂያ ገንዘብ በመጠየቅ የሚፈጸሙ እገታዎች የተለመዱ መሆናቸውን በመግለፅ "የሥርዓት መላላቱን በመጠቀም ይመስለኛል" ብለዋል።

ቢቢሲ ከሆስፒታሉ የሥራ ኃላፊዎች ስለ አስገታው ተጨማሪ መረጃ እንዲሁም አጋቾች የማስለቀቂያ ገንዘብ ጠይቀው ከሆነ ለማወቅ ተደጋጋሚ ሙከራ አድርጎ አልተሳካለትም።

የአማራ ሐኪሞች ማኅበር ፕሬዝዳንት ዶ/ር ታደሰ ፈንታ በክልሉ ባለው ጦርነት የጤና ባለሙያዎች ዛቻ፣ እገታ እና ግድያን የመሰሉ ጥቃቶች እየደረሱባቸው መሆኑን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ባለሙያዎች "እከሌን አከምክ፤ እከሌን አከምክ" እየተባሉ ጥቃት እንደሚፈፀምባቸው የጠቆሙት ዶ/ር ታደሰ፤ የጤና ባለሙያው ቀጥታ ተጠቂ የሆነው በጦርነቱ የቆሰሉ ሰዎችን በማከሙ በወንተኛነት እየተፈረጀ መሆኑን ገልፀዋል።

የጤና ባለሙያዎች በተፋላሚ ኃይሎች ፍረጃ እና አግተው ገንዘብ ለመቀበል በሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ዒላማ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

"ጉዳት ከደረሰባቸው በኋላ ወደ ጤና ተቋም ነው የሚመጡት። በጤና ሥርዓቱ ደግሞ እንዲህ አድርግ፤ እንዲህ አታድርግ ሊል የሚችለው ደግሞ ኃይለኛው ማነው ነው።. . . ኃይሉን የያዘው እንዴት መሥራት እንዳለበት ማዘዝ ይፈልጋል" ሲሉ ሌላ የጤና ባለሙያ ጫናውን ገልፀዋል።

በአማራ ክልል ግጭት የጤና ባለሙያዎች ከዛቻ ጀምሮ "መጠነ ሰፊ" ጥቃቶች እንደሚፈፀምባቸው የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ሪፖርት ያመለካክታል።

ቢቢሲ የክልሉ የጤና ቢሮ ኃላፊን ለሁለት ቀናት ለማነጋገር ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

ባለፈው ዓመት በክልሉ ዋና ከተማ ባሕር ዳር የሚገኘው የጥበበ ጊዮን ሆስፒታል ታዋቂ ሰብ ስፔሻሊስት ሐኪም ከነበሩት ዶ/ር አንዱዓለም ዳኜ ግድያ በኋላ ባለሙያው ክልሉን ለቆ እየሸሸ መሆኑን ዶ/ር ታደሰ ተናግረዋል።

"በየትኛውም አቅጣጫ፤ በየትኛውም ወገን ቢሆን የጤና ባለሙያ ውለታ ያልዋለለት ሰው ማግኘት አይቻልም" ሲሉ የጤና ባለሙያዎች እንዲከበሩ እና እንዲጠበቁ ተማፅነዋል።