በጦርነቱ ውስጥ ምሥጢር ሆነው የተከሰቱት የቀድሞው የኢራን ፕሬዝዳንት አህመዲነጃድ

የፎቶው ባለመብት, Isna
"ይህ የተጠላ መንግሥት [እስራኤል] ለመፍረስ መንገድ ላይ እንዳለ ልታውቁ ይገባል፤ እናም በፈጣሪ ፈቃድም ይፈርሳል። እናም ማንኛውም ነገር ሊያድነው አይችልም። ይህ መንግሥት የጉዞው መጨረሻ ላይ ደርሷል፤ በቅርብ ጊዜ ከዓለም ካርታ ላይ ይሰረዛል።"
ለረጅም ዓመታት ይህን ዓይነት ንግግሮች የቀድሞውን የኢራን ፕሬዝዳንት ማህሙድ አህመዲነጃድ በዓለም ላይ ከሚታወቁ ከፍተኛ የእስራኤል ተቃዋሚዎች ውስጥ አንዱ አድርጓቸዋል።
በናዚዎች እጅ የተፈጸመውን የአይሁዶችን ጭፍጨፋን በጥርጣሬ ይጠይቃሉ። እስራኤልን "የተፈበረከ አገዛዝ" ብለው ይጠራሉ። እንዲሁም ማዕቀቦች ቢጣሉባቸውም የኢራንን የኒውክሌር ፕሮግራም መቀጠል እንዳለበት ይሞግታሉ።
ይህ አቋማቸው በእስራኤል ሹማምንት ተነቅሶ በመውጣት ኢራን እውነተኛ ስጋት እንደሆነች በተደጋጋሚ ዋቢ አድርገው ይጠቅሙበታል።
እንዲህም ሆኖ የኒው ዮርክ ታይምስ እንደዘገበው አሜሪካ እና እስራኤል "በድኅረ ጦርነት ዕቅድ" አህመዲነጃድ ከኢራን የደኅንነት ተቋማት ተለይተው ወደፊት ሊመጡ የሚችሉ መሪ ሊሆኑ ይችላሉ የሚል ምልከታን ይዘው ነበር።
ነገር ግን ይህ ዕቅድ ከሽፏል። እንደ ኒው ዮርክ ታይምስ ዘገባ ከሆነ ውጥኑ የከሸፈው በጦርነቱ መጀመሪያ ቀናት አህመዲነጃድን ከቁም እስር ነጻ ለማውጣት የተፈፀመው ጥቃት ይልቁንም ራሳቸውን በማቁሰሉ ነው።
አህመዲነጃድ ወይም አጋሮቻቸው በዚህ ጉዳይ ላይ መልስ አልሰጡም። አሁን ያሉበት ቦታም አይታወቅም።
ይህ ዘገባ በበርካታ የአሜሪካ እና የእስራኤል ተንታኞች በጥርጣሬ ተወስዷል። ምክንያቱም ለረጅም ጊዜ ለእስራኤል የመረረ አቋም ሲያራምዱ የቆዩ ከመሆናቸው አንጻር ከእርሳቸው ጋር ለምን መሥራት ይፈልጋሉ? ሲሉ ይጠይቃሉ።
ይህ መጣረስ አንዳንዶች የአህመዲነጃድ ምሥል ከዚህ ቀደም እንደታየው ቀላል እንዳልነበር፤ ምንአልባትም ከሚታመነው የበለጠ ውስብስብ ሊሆን ይችላል በሚል እንዲጠራጠሩ አድርጓቸዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ለእስራኤል ጠቃሚ ባላንጣ?
ይህን ውስብስብ ጉዳይ ለመረዳት አህመዲነጃድ በኢራን ፖለቲካ ውስጥ ወዳደጉበት ዘመን ላይ መመለስ ያስፈልጋል። በአውሮፓውያኑ 2003 በፖለቲካው ሜዳ ምንም እውቅና ሳይኖራቸው የቴህራን ከንቲባ ሆነው ተመርጠዋል። በ2005 ደግሞ በጠቅላይ መሪው አሊ ኻሜኔይ ድጋፍ ፕሬዝዳንት ሆኑ።
በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት ስለ ፍትሕ፣ ስለ ቀላል ኑሮ እና ሙስናን ስለ መዋጋት መሪ ቃላቸው አድርገው ተጠቅመዋል። ወዲያው በዓለም ታዋቂ ሰው ሆኑ፤ በውስጣዊ ፖሊሲዎቻቸው ሳይሆን ግን በእስራኤል፣ በአሜሪካ እና በአይሁዶች ጭፍጨፋ ላይ ባደረጓቸው ንግግሮች ምክንያት ነበር።
በጥቅምት 2005፣ "ያለ ፂዮናዊነት የሚታይ ዓለም" በተባለ በቴህራን በተካሄደ ጉባኤ ላይ አህመዲነጃድ "ያለ አሜሪካ እና ከፂዮናዊነት ዓለም ማየት ይቻላል" ብለው ተናግረዋል።
ከአንድ ዓመት በኋላ ደግሞ ዓለም አቀፍ ቁጣ ያስነሳው "የአይሁዶች የጅምላ ፍጅት ዓለም አቀፍ ዕይታ መገምገም" የተባለ ስብሰባ በቴህራን ተካሂዷል። በዚህም ስብሰባ የአይሁዶችን ጭፍጨፋ በመካድ የሚታወቁ ሰዎች ተሳትፈዋል።
ከዓመታት በኋላ አንዳንድ የእስራኤል ባለሥልጣት እና ተንታኞች አህመዲነጃድ በከባድ ንግግሮቻቸው እና የአይሁዶችን ጭፍጨፋ በመካዳቸው በእርግጥ ለእስራኤል እንደጠቀሙ ተደርገው ታይተዋል።
በአውሮፓውያኑ 2008 የቀድሞው የእስራኤል የስለላ ድርጅት ሞሳድ ኃላፊ ኤፍሬም ሀሌቪ አህመዲነጃድን "ለእስራኤል የኢራን ትልቁ ስጦታ" ብለው ገልፀዋቸዋል። በንግግራቸው ኢራን የደቀነችውን አደጋ ዓለም እንዲያስተውል እንዳደረጉ ተናግረዋል።
ነገር ግን የአህመዲነጃድ ደጋፊዎች ይህን አስተያየት ውድቅ ያደርጋሉ። እስራኤልን እና ምዕራቡን ዓለም የሚጋፈጥ በጣም ጠንካራ እና ርዕዮተ ዓለማዊ ፖሊሲ ተከታይ ናቸው ሲሉ ይናገራሉ።
ከሥልጣን በኋላ የገፅታ ለውጥ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከፕሬዝዳንትነት በ2013 ከተነሱ በኋላ አህመዲነጃድ ከጠቅላይ መሪው አሊ ኻሜኒይ እና ከኢራን የደኅንነት አካላት፣ በተለይም ከኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ጋር የነበሯቸው ግጭት ጨምሯል። ከዚያም በኋላ በኢራን የበላይ ጠባቂ ምክር ቤት በተደጋጋሚ በፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እንዳይወዳደሩ ታግደዋል።
በኒው ዮርክ ታይምስ ዘገባ ላይ በኤክስ ገፃቸው ምላሽ የሰጡት በእስራኤል የብሔራዊ ደኅንነት ጥናት ተቋም ውስጥ የኢራን እና የ'ሺዓ አክሲስ' ፕሮግራም ኃላፊ ራዝ ዚምት፤ አህመዲነጃድ ብዙ ጊዜ የተቃርኖ እና ያልተጠበቁ አቋሞችን እንደሚያሳዩ ተናግረዋል።
"አህመዲነጃድ በፕሬዝዳንትነት ዘመናቸው የሕዝበኛነት እና አጋጣሚውን የመጠቀም የተዋሃደ ማንነት ያላቸው ነበሩ" ሲሉ አጋርተዋል።
በቅርብ ዓመታትም አህመዲነጃድ በማኅበራዊ የትስስር ገፆች ላይ ዓለም አቀፋዊ ገጽታቸውን እንደገና ለመገንባት ሞክረዋል። በእንግሊዝኛ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ይጽፋሉ እንዲሁም የአሜሪካ ዝነኛ ራፐር ቱፓክ ሻኩርን ዋቢ አድርገው ጠቅሰዋል።
ይህም ብቻ ሳይሆን ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ "በአሜሪካ ውስጥ የፖለቲካ ሙሰኝነትን በመዋጋታቸው" አሞግሰዋል።
ነገር ግን ዚምት ይህን እርምጃ አህመዲነጃድ ለምዕራቡ ዓለም ተመልካቾች ራሳቸውን የለዘብተኛ አቋም ምሥል ለመፍጠር እንደሆነ ይገልፃሉ።
አህመዲነጃድ ከ90 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት አገር ውስጥ ሥልጣን መያዝ የሚያስችል ድጋፍ እንደሌላቸውም ያክላሉ።
በአሜሪካ ተንታኞች መሀል ያደረው ጥርጣሬ
ቢቢሲ ፐርሺያን (የኢራን ቋንቋ አገለግሎት) ያነጋገቸራው ሦስት የአሜሪካ ተንታኞች አህመዲነጃድን ወደ ሥልጣን ለመመለስ የተዘጋጀ "ጠንካራ የትግበራ ዕቅድ" ስለመኖሩ ይጠራጠራሉ።
በኖርዝዌስተርን ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ፕሮፌሰር እና የፀረ ሽብር ባለሙያ የሆኑት ማክስ አብራምስ፤ ሪፖርቱ "በጣም በከፍተኛ ጥርጣሬ" መታየት እንዳለበት በመናገር፤ ከጦርነቱ ጋር የተያያዙ ከፍተኛ የሐሰት መረጃዎች መኖራቸውን ይጠቁማሉ።
እስራኤል የአይሁድን ጭፍጨፋ የካዱ እና የኢራንን የኒውክሌር መርሃ ግብር በማሳደግ ባላቸው ሚና ምክንያት የአህመዲነጃድን መመለስ ትቀበላለች ማለት ከባድ ነው ይላሉ። ለትራምፕም ቢሆን ለአገዛዝ ለውጥ ፍላጎታቸው አህመዲነጃድ የሚስማሙ አይደሉም ብለዋል።
ከአሜሪካ የውጭ ፖሊሲ ምክር ቤት ኢላን በርማን ደግሞ ታማኝ የሆነ የአሜሪካ–እስራኤል ዕቅድ መሆኑን አይቀበልም። የአህመዲነጃድ ስም መሪ ይሆናሉ ተብሎ ቢነሳ እንኳ ተመረጭ መሪ ሊሆኑ አይቻሉም ይላሉ።
የአሜሪካን ኢንተርፕራይዝ ተቋም ባልደረባ የሆኑት ማይክል ሩበን ሪፖርቱን "ከእውነት የራቀ ተረት" ብለው ይጠሩታል።፣
ኒው ዮርክ ታይምስ በስም የማይጠቅሳቸው ምንጮች ላይ ብዙ ጊዜ ይመሠረታል ሲሉ ነቅፈዋል። ነገር ግን በርካታ ምዕራባዊያን አህመዲነጃድ በኢራን ማኅበረሰብ ክፍሎች ያላቸውን ቁቡልነት በስህተት ይረዳሉ ብለው ያምናል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ኒው ዮርክ ታይምስ በኤክስ ገፁ ሪፖርቱ ላይ "ሙሉ እምነት" እንዳለው ገልጿል። ሪፖርቱ ከአሜሪካ፣ ከእስራኤል እና ከኢራን ባለሥልጣናት እና ለጉዳዩ ቅርብ ከሆኑ ከሌሎች ምንጮች ጋር በተደረጉ ቃለ ምልልሶች ላይ የተመሠረተ መሆኑን አስምሯል።

የፎቶው ባለመብት, khamenei.ir
እስራኤል ምላሽ
አንዳንድ የእስራኤል የደኅንነት ባለሙያዎች እንዲህ ያለ የቢሆን ዕይታ እስራኤል ስለ ኢራን ያላት ግንዛቤ ምን ያህል እንደሆነ አተኩረዋል።
ብሔራዊ የደኅንነት ጥናት ተቋም ባልደረባ የሆኑት ዳኒ ሲትሪኖዊች በኤክስ ገፃቸው አህመዲነጃድ ላይ "ዘውድ ለመድፋት" የሚደረግ ማንኛውም ሙከራ የኢራን የፖለቲካ ሥርዓት ላይ ከፍተኛ የተሳሳተ አረዳድ እንዳለ ፍንትው አድርጎ ያሳያል" ብለዋል።
አህመዲነጃድ እውነተኛ የሥልጣን መሠረት የሌላቸው እና በኢራን አብዮታዊ ዘብ ድጋፍ እንደማይኖራቸው ገልፀዋል። ስለዚህም እርሳቸው ሥልጣን መያዝ የሚችሉት በአሁኑ ጊዜ በኢራን ያለው ሙሉ የኃይል ሥርዓት ሙሉ በሙሉ ሲፈርስ ብቻ ነበር ብለዋል። ነገር ግን ይህን የአሜሪካ እና የእስራኤል ጥቃቶች ማሳካት አልቻሉም።
ታዋቂ የእስራኤል የደኅንነት ተንታኝ የሆኑት ዮሲ መልማን በተመሳሳይ "ይህ ዘገባ በብዙ ደረጃዎች አስገራሚ ነው" ብለዋል።
በአናሳ ቡድኖች የአመፅ እንቅስቃሴ እና በአየር ጥቃቶች አገዛዙ ይወድቃል የሚል ማንኛውም ሀሳብ በእስራኤል እና በአሜሪካ ያሉ ዕቅድ አዘጋጆች "በምናባዊ ዓለም ውስጥ እየኖሩ እንደነበር" ያሳያል ብለዋል።
የአህመዲነጃድ ሥም ከጅምሩ እንዴት ተነሳ?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
እነዚህ ሁሉ ጥርጣሬዎች ቢኖሩም፤ ለምን አህመዲነጃድ? የሚለው ጥያቄ ግን አልተመለሰም።
መልሱ ከሦስት የተለዩ ባህሪያቸው ጥምረት ውስጥ ሊገኝ ይችላል። እነዚህም ታዋቂነታቸው፣ የውስጥ ልምዳቸው እና ከጠቅላይ መሪው የተለዩ መሆኑ ናቸው።
አህመዲነጃድ በኢራን ውስጥ በደንብ የታወቁ ሰው ናቸው፤ መንግሥትን የማስተዳደርም ልምድ አላቸው፤ የአንዳንድ ዝቅተኛ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ቋንቋ ይረዳሉ፤ እናም በእስላማዊ ሪፐብሊክ ውስጥ የኃይል መዋቅሮችን ያውቃሉ። በተመሳሳይ ጊዜ ግን ከኻሜኔይ ጋር ያላቸው ግጭቶች እንደ ተራ የመንግሥት የውስጥ ሰው ተደርገው እንዳይታዩ ያደርጋቸዋል።
ከአንዳንድ የውጭ ፖሊሲ ባለሙያዎች ዕይታ እነዚህ ባህሪያት እርሳቸውን በቀውስ ጊዜ ሊጠቀሙባቸው የሚችሉ ሰው እንደሆኑ ሊያመለክት ይችላል። ይህም ማለት እንደ አጋር ሳይሆን፤ በአገሪቱ የኃይል መዋቅር ውስጥ ክፍል ለመፍጠር ጊዜያዊ መሪ ተርገው ታይተው ሊሆን ይችላል።
አህመዲነጃድ ማን ናቸው?
አንዳንድ የኢራን ተቃዋሚዎች እና አስተያየት ሰጪዎች አህመዲነጃድ ባለፉት ዓመታት ከፕሬዝዳንትነታቸው እና ከአወዛጋቢ የውጭ ጉብኝቶቻቸው፤ በቅርቡ በተነሳው ጦርነት ወቅት እስከመረጡት ዝምታ ድረስ ያላቸው ባህሪ ፖለቲካዊ አቋማቸው ላይ አዲስ ጥያቄዎችን እንዲያነሱ አስገድዷቸዋል።
በፖሊሲዎቻቸው ኢራን ከዓለም እንድትነጠል፣ የኒውክሌር ቀውሱ እንዲባባስ እና በመጨረሻም እስራኤል በቴህራን ላይ ለምታቀርበው ፖለቲካዊ መልዕክት መሣሪያዎች እንድታገኝ አግዘዋል ይላሉ። አሁንም የኒ ውዮርክ ታይምስ ዘገባም እነዚህን ክርክሮች እንደገና አስነስቷል።
ይህንም ሲያደርግ የመጀመሪያው አይደለም።
በፕሬዝዳንትነት ዘመናቸው ሥልጣናቸውን ለማፅናት ታዋቂ ተራማጅ አመራሮችን እና የቀድሞ ከፍተኛ ባለሥልጣናትን በአመፃ ከስሰዋል። ከሥልጣን ከለቀቁ በኋላ የኢራን መገናኛ ብዙኃን ከእነዚህ ተመሪዎች ጋር ለመታረቅ መሞከራቸነን ዘግበዋል።
ይህ የአቋም ለውጥ ወይም እንደገና አጋርነት መፈለግ ጠንካራ ርዕዮተ ዓለማዊ መመሪያ ከመከተል ይልቅ በውስጥ የኃይል ሽኩቻ ውስጥ ለመንቀሳቀስ የሚያደርጉት ሙከራ ብቻ ሊሆን ይችላል። ይህም ከውጭ ኃይሎች ጋር የተደበቀ ግንኙነት እንዳላቸው የሚያመለክት አይደለም። በእርግጥም አህመዲነጃድን ከእስራኤል ወይም ከአሜሪካ ጋር የሚያገናኝ ማስረጃ አልተገኘም።
ነገር ግን ዋነኛው ተቃርኖ በከፍተኛ ፀረ እስራኤላዊ ንግግራቸው የታወቁ ፖለቲከኛ አሁን የኢራን የወደፊት አማራጭ ሆነው መታየታቸው ነው። ይህም አህመዲነጃድ በኢራን ፖለቲካ ውስጥ ባላቸው ስፍራ ለዘመናት የቆየ ጥያቄን እንደገና አስነስቷል።















