ኢድ አል-አደሃ: በተለያዩ ሃይማኖቶች እንስሳት ለምን በመስዋዕትነት ይቀርባሉ?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ የእርድ በዓል ተብሎ የሚታወቀው የኢድ አል-አደሃ በዓል ነብዩ ኢብራሂም ወንድ ልጃቸውን መስዋዕት ለማድረግ ፍቃደኛ መሆናቸውን ለማሰብ ይከበራል።
ነብዩ ኢብራሂም በአላህ ትዕዛዝ ልጃቸው እስማኤልን መስዋዕት ለማድረግ ተዘጋጅተው ነበር። ነብዩ ኢብራሂም ልጃቸውን ለመስዋዕትነት ሲያዘጋጁ አላህ አስቁሟቸው በልጃቸው ፈንታ በግ መስዕዋት እንዳደረጉ ይታመናል።
ባለንበት ዘመንም በመላው ዓለም የሚገኙ የእስልምና ዕምነት ተከታዮች የተለያዩ እንስሳትን መስዋዕት እያደረጉ በዓሉን ያከብራል።
እንስሳትን መስዋዕት በማድረግ ዙሪያ በሌሎች ሃይማኖቶችን እንዴት ይታያል? በክርስትና፣ በሂንዱ እና በአይሁድ እምነቶች እንስሳትን መስዋዕት ማድረግን በተመለከተ እንዴት ይታያል?
አይሁዶች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
እንስሳትን መስዋዕት ከማድረግ ጋር በተያያዘ የአይሁድ እና የክርስት እና ሃይማኖቶች ከእስልምና ታሪክ ጋር ተመሳሳይነት አላቸው።
የአይሁድ የሃይማኖት መሪ የሆኑት ጌሪ ሶመርስ በአይሁድ የእምነት ጽሑፎች ውስጥ በተለያዩ ጊዜያት እና ቦታዎች የተለያዩ የእንስሳት መስዋዕትነቶች ተጠቅሰው ይገኛሉ ይላሉ።
ይሁን እንጂ አሁን ላይ መስዋዕትነት ይፈጸምባቸው የነበሩ ስፍራዎች ባለመኖራቸው የእምነቱ ተከታዮች መሰል ተግባራትን አያከናውኑም። "አሁን እነዚያን መስዋዕትነትን በጸሎት ብቻ ነው የምናስባቸው" ይላሉ።
በአሜሪካን ጂዊሽ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ራባይ ብራድሊ ሻቪት (ዶ/ር) የእስሳት መስዕዋትነት የሚፈጸምባቸው የሃይማኖት ስፍራዎችን ሮማውያን በማውደማቸው አሁን ላይ የእንስሳትን መሰዋት አይፈቀድም ይላሉ።
"ሮማውያን ሁለተኛውን የሃይማኖት ሰፍራ በማውደማቸው የእንስሳት መስዋዕትነት በአይሁድ እምነት አይፈቀደም። ብዙዎች ሙሉ በሙሉ እንደተከለከለ አድርገው ያስባሉ ሌሎች ደግሞ መሲህ ከመጣ በኋላ ሥርዓቱ ዳግም ይጀመራል ብለው ያምናሉ" ይላሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ብራድሊ የወደመው የአይሁድ የሃይማኖት ስፍራ ብለው የሚገልጹት በአሁኑ ወቅት በኢየሩሳሌም ከተማ የአል-አቅሳ መስጂድ በሚገኝበት ስፍራ ላይ የነበረን ቦታ ነው።
አይሁዳውያን ይህ የሃይማኖት ቦታ ተመልሶ ተገንብቶ እንስሳትን መስዋዕት የማድረግ ተግባራቸውን መልሰው መቀጠልን ይመኛሉ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ምንም እንኳ አብዛኛው አይሁድ እንስሳትን መስዋዕት በማድረግ ተግባር ባይሳተፍም በኢየሩሳሌም ያሉ እና ሳማሪታንስ የተባሉ አይሁዶች አሁንም ድረስ ሃይማኖታዊ ተግባሩን አስቀጥለዋል።
ለመስዋዕትነት የሚቀርቡት እንስሳት እንደ በግ፣ ላም፣ ፍየል ወይም ጎሽ ያሉት በእምነቱ ተቀባይነት ያላቸው "ኮሸር" የሆኑ እንስሳት መሆን አለባቸው።
ክርስቲያኖች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
እንስሳትን በመስዋዕትነት በማቅረብ ረገድ ክርስትና ስር መሠረቱ ከአይሁድ እምነት ጋር ይያያዛል። የአይሁዶች ሃይማኖታዊ ጽሑፍ እንዲሁ ከብሉይ ኪዳን ጋር ተመሳሳይነት አለው።
በኢንዶኔዢያ ዳካ ከተማ የሚገኘው የካቶሊክ ቤተ-ክርስቲያን አገልጋይ የሆኑት ፕኦሻንቶ ቲ ሬቤኢሮ (ዶ/ር) በብሉይ ኪዳን ዘሌዋውያን 17 ላይ እንስሳት እንዴት መስዋዕት መሆን እንዳለባቸው በዝርዝር ይገልጻል ይላሉ።
አንዳንድ ጊዜ እንስሳት ለመስዋዕትነት የሚቀርቡት ከፈጣሪ ይቅርታን ለማግኘት በማሰብ ነው ይላሉ እኚህ አገልጋይ።
ይሁን እንጂ የኢየሱስ ክርስቶስ ሞት እንደ የመጨረሻው መስዋዕትነት ተደርጎ ስለሚታሰብ ይህ ልማድ በሃይማኖቱ አይተገበርም።
እየሱስ በክርስትና እንደ ‘የእግዚአብሔር በግ’ ይቆጠራል።
ሂንዱዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ምንም እንኳን በሂንዱ እምነት ውስጥ በእንስሳት መስዋዕትነት ዙሪያ የተለያዩ አለመግባባቶች ቢኖሩም፤ በተወሰኑ ሂንዱዎች ዘንድ ተግባራዊ ይደረጋል።
ለምሳሌ፣ በብዙ የሕንድ ወይም የባንግላዴሽ አካባቢዎች በሃይማኖታዊ ሥርዓቶች እንስሳትን መስዋዕት የማድረግ ተግባር በሰፊው ይከናወናል።
እንስሳትን መስዋዕት ማድረግ ከክርስቶስ ልደት በፊት በ1500 እና 500 መካከል የተለመደ ተግባር እንደሆነ ይታመናል። እንስሳው ለፈጣሪ ተብሎ መስዋዕት ከሆነ በኋላ ሥጋው ለሃይማኖቱ ተከታዮች በግብዣ መልክ ይቀርብ ነበር።
ይሁን እንጂ በዘመናዊት ሕንድ የእንስሳትን መስዋዕትነትን በተመለከተ የተለያዩ አስተያየቶች አሉ።
የሃይማኖቱ መሪዎች እንደሚሉት ሰዎች በሃይማኖት ሰበብ እንስሳትን መስዋዕት ማድረጋቸውን የቀጠሉት ለግላዊ ፍላጎት እንጂ ሃይማኖታዊ ፍይዳ ኖሮት አይደለም ይላሉ።
እንደ ስሪ ላንካ እና ኔፓል ያሉ አገራት በሂንዱ እምነት እንስሳትን መስዋዕት ማድረግን ከልክለዋል። ይሁን እንጂ ይህ ትዕዛዝ ሁሌም የሚከበር አይደለም።















