በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ የወርቅ ማውጫ ስፍራ ተደርምሶ ከ100 በላይ ሰዎች ሕይወት አለፈ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በምዕራብ ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ከካሜሩን ድንበር አቅራቢያ በሚኝ 'ዛምቦይ' የተባለ የወርቅ ማውጫ ስፍራ ላይ በተከሰተ የመሬት መንሸራተት ከ100 በላይ ሰዎች መሞታቸውን የካሜሩን ባለሥልጣን ለቢቢሲ ተናገሩ።

በማኅበራዊ ሚዲያ በተሰራጩ ቪዲዮዎች ላይ፣ ተዳፋት በሆነ ስፍራ የተሰበሰቡ ሰዎች ላይ መሬት ሲናድ እና ሌሎች ራሳቸውን ለማዳን ሲሮጡ ታይቷል።

አደጋው የተከሰተው ማክሰኞ ከሰዓት እንደሆነ የካሜሩን ድንበር ከተማ ጋሩዋ ቡላይ ከንቲባ አዳሙ አብዶን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የነፍስ አድን ስራዎች እየተከናወኑ ቢሆንም የሟቾች ቁጥር ከዚህ ሊበልጥ ይችላል የሚስ ስጋት ተፈጥሯል።

ወርቅ ማውጫ ስፍራው ላይ የመሬት መንሸራትት እንዲከሰት ምክንያት የሆነው ጉዳይ እስካሁን ግልፅ አይደለም።

እስካሁንም "107 አስከሬኖች ከናዳው ውስጥ መውጣታቸውን" ከንቲባው አብዶን ተናግረዋል።

ሴድሪክ ምባንጎ የተባለ በስፍራው የነበረ ማዕድን አውጪ "መሬቱ ሙሉ በሙሉ ተንዶ ሰዎችን ቀብሯል" ሲል ለፈረንሳዩ ዜና ወኪል ኤኤፍፒ በሰጠው ቃል ሁኔታውን ገልጿል።

"ይህንን እየተናገርኩ ባለሁበት ሰዓት፣ ሌሎችም ሰዎች እንደተቀበሩ ነው" ብሏል።

ከሟቾቹ መካከል ቢያንስ ሦስቱ ካሜሩናውያን እንደሆኑ የካሜሮን ምሥራቅ ግዛት አስተዳዳሪ ለአገሪቱ መንግሥት መገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል።

የሟቾቹ አስከሬን ለቀብር ወደ አገራቸው እየተመለሰ መሆኑን የተናገሩት አስተዳዳሪው፣ ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች ህክምና ለመስጠት እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆኑን ገልጸዋል።

ከአደጋው የተረፉት ሰዎች ከማዕድን ማውጫው 50 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ባቡዋ ከተማ ወደሚገኝ ሆስፒታል እየተወሰዱ መሆኑን ኤኤፍፒ ዘግቧል።

የማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ መገናኛ ብዙኃን እንደገዘቡት፣ የአገሪቱ ባለሥልጣናት መሬት መንሸራተቱ የተከሰተበትን ምክንያት ለማወቅ ምርመራ ጀምረዋል።

የባቡዋ ዓቃቤ ሕግ ባወጣው መግለጫ፣ "ማዕድን አውጪዎች የሚቆፍሩባቸው በርካታ የመሬት ስር ዋሻዎች መናዳቸው" አደጋውን አስከትሏል ተብሎ እንደሚታመን መግለጹን የኤኤፍፒ ዘገባ ያመለክታል።

ከፍተኛ የጉልበት ሥራ የሚጠይቀው ባህላዊ ማዕድን ቁፋሮ፣ በግዛቱ ለሚገኙ ነዋሪዎች ዋነኛ የገቢ ምንጭ ነው።

ይሁን እንጂ በአካባቢው ባለው ደካማ የሥራ ሁኔታ ምክንያት፣ አብዛኛውን ጊዜ ማዕድን ቆፋሪዎች ለጤና እና ለተፈጥሮ አደጋዎች ተጋላጭ ናቸው።

ብዙውን ጊዜ ጉድጓዶች በማይደፈኑበት እና ከባድ ዝናብ አፈሩን በሚሸረሽርበት በዚህ የማዕድን ማውጫ አካባቢ፣ የመሬት መንሸራተት አዲስ ክስተት አይደለም።