ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኢትዮጵያውያንን የሚመለከቱ አራት የፕሬዝዳንት ትራምፕ የኢሚግሬሽን ውሳኔዎች
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ ያደርጉ በነበረበት ወቅት ዋነኛ አጀንዳቸው ካደረጓቸው ጉዳዮች መካከል ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ይገኙበታል።
ሁለት ዓመት ሊሞላው ወራት በቀረው የሥልጣን ዘመናቸውም፣ ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎችን ዒላማ ያደረጉ ትዕዛዞችን አሳልፈዋል።
ትራምፕ ያስተላለፏቸው ውሳኔዎች፣ ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች የሚስተናገዱበትን አሠራር ከማጥበቅ አንስቶ ከአሜሪካ ግዛት እስከማባረር እንዲሁም የአገሪቱ የስደተኞች እና ጉምሩክን አቅም ማጠናከር ይደርሳሉ።
የኢሚግሬሽን ሕግ አስከባሪ መሥሪያ ቤት ባልደረቦች ስደተኞች ላይ የወሰዷቸው የኃይል እርምጃዎች ከሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ተቃውሞ ማስነሳታቸው ይታወሳል።
የትራምፕ አስተዳደር "ወንጀለኞች ናቸው" የሚላቸውን ስደተኞች ወደ አፍሪካ እና ሌሎችም አካባቢዎች የማባረር እርምጃውም ይጠቀሳል።
በአሜሪካ ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ የሚሰጣቸው ሰዎች በመንግሥት ላይ የሚኖራቸው ጥገኝነት እና ሌሎችም ቅድመ ሁኔታዎችን ከግምት ውስጥ በማስገባት ጥያቄያቸው ውድቅ ሊደረግ የሚችልበት አዲስ አሠራርም ይገኝበታል።
የትራምፕ አስተዳደር ውሳኔዎች ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ላይ ብቻ ያነጣጠሩ አይደሉም። ተማሪዎች፣ ጎብኚዎች፣ ቪዛ ጠያቂዎች እንዲሁም በአሜሪካ የሚወለዱ ሰዎችንም የሚመለከቱ ጥብቅ መመሪያዎች ወጥተዋል።
በተለያየ መንገድ ኢትዮጵያውያን ላይ ጫና ሊያሳድሩ የሚችሉ የትራምፕ አስተዳደር አራት ውሳኔዎችን እንመልከት።
1. ጥብቅ የቪዛ ቅድመ ሁኔታዎች
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ወደ አገሪቱ ለመግባት የንግድ እና የቱሪስት ቪዛ የሚያመለክቱ ሰዎች እስከ 20 ሺህ ዶላር የሚደርስ ገንዘብ በማስያዣነት ሊጠየቁ እንደሚችሉ አስታውቋል።
ከአንድ ዓመት በፊት በሙከራ ደረጃ ይፋ የተደረገው አሠራር በቋሚነት እንደሚተገበር የተገለጸው በቅርቡ ነው።
የትራምፕ አስተዳደር ውሳኔው ከቪዛ ጊዜያቸው በላይ የሚቆዩ ጎብኚዎችን "ለመከላከል" ያለመ መሆኑን አስታውቋል።
አሠራሩ የሚተገበረው ለረዥም ጊዜ የሚቆዩ ዜጎች ባሏቸው አገራት እና የአገር ውስጥ ሰነዶች ላይ የላላ ቁጥጥር በሚያደርጉ አገራት ላይ እንደሆነ ተገልጿል።
የቢ-1/ቢ2 ቪዛ ጠያቂዎች 5,000, 10,000, 15,000 ወይም 20,000 ዶላር በማስያዣነት እንዲያቀርቡ ሊጠየቁ ይችላሉ። ተጓዦች በተሰጣቸው የቪዛ መቆያ ጊዜ መሠረት ወደ አገራቸው የሚመለሱ ከሆነ ያስያዙት ገንዘብ እንደሚመለስላቸውም ተገልጿል።
በትራምፕ የመጀመሪያው የሥልጣን ዘመን ማብቂያ ላይ ተመሳሳይ አሠራር ተግባራዊ ሆኖ ነበር። ነገር ግን ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ የዓለም አቀፍ ተጓዦች ቁጥር በመቀነሱ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ አልሆነም።
በሌላ በኩል በኢትዮጵያ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ያለፈው ዓመት ሐምሌ ላይ ለኢትዮጵያውያን የሚሰጠው ቪዛ የቆይታ ጊዜ ወደ ሦስት ወር ማጠሩን ማስታወቁ ይታወሳል።
ስደተኛ ባልሆኑ የቪዛ አመልካቾች ላይ በተደረገው የፖሊሲ ለውጥ ምክንያት፤ ለንግድ እና ለጉብኝት ወደ አሜሪካ የሚጓዙ ኢትዮጵያውያን የሚያገኙት ቪዛ ለአንድ ጊዜ ብቻ የሚያገለግል እና የሦስት ወር ቆይታ ያለው እንደሆነ ይፋ ተደርጓል።
ቀድሞ በነበረው አሠራር፤ በዚህ ምድብ ውስጥ የሚገኙ ተጓዦች የሚያገኙት ቪዛ ለሁለት ዓመት የሚቆይ ነበር። በተጨማሪም የቪዛው የቆይታ ጊዜ እስከሚጠናቀቅ ድረስ በተደጋጋሚ ወደ አሜሪካ መግባት ይቻል ነበር።
የትራምፕ አስተዳር "የደኅንነት ስጋት ናቸው" ባላቸው አገራት ዜጎች ላይ የጉዞ ክልከላ መጣሉም አይዘነጋም።
ከእነዚህ አገራት መካከል ኤርትራ፣ ቻድ፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ሊቢያ፣ ሶማሊያ እና ሱዳን ይገኙበታል።
2. የጊዜያዊ ከለላ መነሳት
የአሜሪካ የፌደራል ፍርድ ቤት ከ5000 በላይ ለሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ተሰጥቶ የነበረውን በአገሪቱ የመኖር እና የመሥራት መብት ወይም ሕጋዊ ከለላ የትራምፕ አስተዳደር እንዲያቆም ፈቅዷል።
ጊዜያዊ ጥበቃ የሚሰጥበት አሠራር (ቲፒኤስ) በተፈጥሮ አደጋዎች፣ በጦርነቶች ወይም በሌሎች ከባድ ክስተቶች ለተጎዱ አገራት ዜጎች የሚቀርብ ከለላ ነው።
ለኢትዮጵያውያን ተሰጥቶ የነበረው ጊዜያዊ ከለላ መቋረጡን የስደተኞች መብት ተሟጋቾች ተቃውመዋል።
ያለፈው ሰኔ ላይ የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሺህዎች የሚቆጠሩ የሄይቲ እና የሶሪያ ስደተኞች ሕጋዊ ከለላ እንዲያቋርጥ መፍቀዱም ይታወሳል።
ሕጋዊ ከለላው ለመጀመሪያ ጊዜ ለኢትዮጵያውያን የተሰጠው በቀድሞው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር ነበር።
አፍሪካን ኮሚኒቲስ ቱጌዘር የተሰኘው የመብት ተሟጋች ቡድን የፖሊሲ እና የጥብቅና ጉዳዮች ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዲያና ኮናቴ "በኢትዮጵያ ያለው ቀውስ አሁንም የቀጠለ ሲሆን፤ ይህ ውሳኔ በአሜሪካ የሚኖሩ በሺህዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን ሕይወት ከፍተኛ አደጋ ላይ ይጥላል" በማለት የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ኮንነዋል።
ባለፈው ሰኔ ላይ የአሜሪካ የአገር ውስጥ ደኅንነት ኃላፊ ማርክዌይን ሙሊን፤ በአሜሪካ ጊዜያዊ የጥገኝነት ከለላ አግኝተው የሚገኙ የተለያዩ አገራት ዜጎች ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ ለማግኘት ጥያቄ ማቅረብ ወይም አገሪቱን ለቅቀው መውጣት እንዳለባቸው ማሳሰባቸው ይታወሳል።
ከጦርነት፣ ሰብአዊ ቀውስ እና የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች በመሸሽ በአሜሪካ ጊዜያዊ ከለላ አግኝተው የሚኖሩ ሰዎች ከ350 ሺህ በላይ ናቸው።
የአሜሪካ የአገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤት የኢትዮጵያውያን ሕጋዊ ከለላ እንዲቋረጥ ባለፈው ታኅሣሥ ላይ ውሳኔ አሳልፎ ነበር። በውሳኔው መሠረት በ60 ቀናት ውስጥ አገሪቱን ለቅቀው እንዲወጡም አዝዞ ነበር።
ይሁን እንጂ በቦተስን የፌደራል ፍርድ አቤቱታ በመቅረቡ እርምጃው ታግዶ ቆይቷል።
አሁን ላይ የቦስተን ዲስትሪክት ፍርድ ቤት ዳኛ ብራያን ሕጋዊ ከለላው እንዳያቋርጥ ይከለክል የነበረውን የመጨረሻ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ቀልብሰዋል።
3. በመወለድ የሚገኝ ዜግነት መገደብ
የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ትራምፕ በመወለድ የሚገኝ ዜግነትን ለማስቀረት ያደረጉትን ሙከራ ውድቅ ቢያደርግም፤ ፕሬዝዳንቱ ሁለት አዳዲስ ትዕዛዞች አስተላልፈዋል።
ያለፈው ሰኔ ላይ የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሰጠው ውሳኔ፣ የአሜሪካ ዜግነት ከሌላቸው ሰነድ አልባ ስደተኞች በአሜሪካ የሚወለዱ ልጆች የአገሪቱ ዜግነትን የማግኘት መብታቸውን ለመቀልበስ የተደረገውን ጥረት አግዷል።
ከዘጠኙ የጠቅላይ ፍርድ ቤት የዕድሜ ዘመን ዳኞች አብላጫውን ቁጥር የያዙት በመወለድ የሚገኝ የዜግነት መብት እንዲቀልበስ አልፈቀዱም።
ትራምፕ ከሳምንታት በፊት ካስተላለፉት ትዕዛዝ አንዱ፤ የአሜሪካ ዜጋ ያልሆኑ ሰዎች ልጆቻቸው ዜግነት እንዲያገኙ የሚያደርገውን አሠራር ትርጓሜ ያሰፋል።
ሁለተኛው ትዕዛዝ ነፍሰ ጡር ሴቶች ወደ አሜሪካ ለጉብኝት ሄደው እዚያው በመውለድ ልጆቻቸው ዜግነት የሚያገኙበትን አሠራር ይመለከታል።
150 ዓመታት ባስቆጠረ ሕግ መሠረት፤ በአሜሪካ የሚወለዱ ሰዎች ዜግነት የማግኘት መብት አላቸው። የትራምፕ አስተዳደር ይሄንን ለመቀልበስ በተደጋጋሚ ጥረቶች አድርጓል።
ገለልተኛ የጥናት ተቋም የሆነው ዘ ማይግሬሽን ፖሊሲ ኢንስቲትዩት ባወጣው አሐዝ፤ በየዓመቱ ወደ አሜሪካ ለቱሪዝም ሄደው ከሚወልዱ ነፍሰ ጡሮች የሚወለዱ ልጆች ከ22,000 እስከ 26,000 ይደርሳሉ።
ትራምፕ ከአውሮፓውያኑ 2015 ጀምሮ በመወለድ የሚገኝ ዜግነትን ለማስቀረት መሞከራቸውን ቀጥለዋል።
4. የተማሪዎች የቪዛ ደንቦች መጥበቅ
የትራምፕ አስተዳደር ለውጭ አገራት ተማሪዎች ጥብቅ የቪዛ ደንቦችን ለመተግበር የመጨረሻ ውሳኔ ላይ መድረሱን ያስታወቀው ያለፈው ሐምሌ ላይ ነው።
ፖሊሲው የሚተገበረው ከቀጣዩ መስከረም አንስቶ እንደሆነ ተገልጿል።
ውሳኔው፤ ተማሪዎች ያለ ፌደራል መንግሥት ፈቃድ ከአራት ዓመት በላይ በአሜሪካ እንዳይቆዩ ማገድ እና ሌሎችም ጥብቅ እርምጃዎችን ያካትታል።
ዩኒቨርሲቲ መለወጥ ወይም የትምህርት ክፍል መቀየር ላይም ገደብ እንደሚጣል ተገልጿል። እስካሁን ድረስ በነበረው አሠራር ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ቪዛ እንዲራዘም የማድረግ ሥልጣን ነበራቸው።
በተጨማሪም ኤፍ-1 እና ጄ-1 የውጭ አገራት ተማሪዎች ቪዛ ያላቸው ሰዎች ትምህርት እስከሚያጠናቅቁ ድረስ በአሜሪካ መቆየት ይፈቀድላቸው የነበረ ሲሆን፤ ከዚህ በኋላ ግን የተማሪዎች የቆይታ ጊዜ ላይ ገደብ የሚጣል ይሆናል።
አዲሱ ፖሊሲ ተማሪዎች ከተመረቁ በኋላ በ30 ቀናት ውስጥ ከአሜሪካ መውጣት አለባቸው። ሌላው አማራጭ የቪዛ ዓይነት መቀየር ሲሆን፤ ይህም 60 ተጨማሪ ቀናት ለማግኘት ይረዳል።
የዓለም አቀፍ የመምህራን ማኅበር ውሳኔውን "የተዛባ እና አላስፈላጊ" ሲል ኮንኖታል።