ሕንዳውያን ለአንድ ዓመት ወርቅ እንዳይገዙ የተጠየቁት ለምንድን ነው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኢራን ጦርነት ወደ ሦስተኛ ወሩ ቀስ እያለ ሲያዘግም የሕንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ሕንዳውያን ቀበቷቸውን እንዲያጠብቁ እየጠየቁ ይገኛሉ።
ከቻላችሁ ከቤታችሁ ሥሩ፤ አላስፈላጊ የሆነ የውጭ ጉዞ አስወግዱ፤ አነስተኛ ወርቅ ግዙ፤ የነዳጅ ፍጆታችሁንም ቢሆን ቀንሱ የሚሉት የጠቅላይ ሚኒስትሩ መልዕክቶች ናቸው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት እሁድ ዕለት በሃይደርባድ በተዘጋጀ አንድ ሥነስርዓት ላይ ነው። ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ምልዕክት በኮቪድ ወረርሽኝ ወቅት ከተሰማው ክልከላ እና እገዳ ጋር ተመሳሳይነት አለው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአሁኑ ንግግራቸው ዶላር መቆጠብ እና ኢኮኖሚውን መታደግ የሚል ተልዕኮን ያነገበ ነው። ይህ መልዕክት ግን በመላው ሕንድ በሚገኙ የፋይናንስ ገበያዎች ድንጋጤን ፈጥሯል። ለረዥም ጊዜ በሕንድ ባንክ ውስጥ ያገለገለው ኡዳይ ኮታክ "የእኔ አስተያየት የከፋ ነገር ከመምጣቱ በፊት መዘጋጀት አለብን የሚል ነው" ሲሉ ተናግረዋል።
በዙሪያው ለተሰበሰቡ የኢንዱስትሪው አመራሮች "የከፋ ነገር ይመጣል ብለን መዘጋጀት አለብን" ሲሉ አክለዋል።
ኮታክ "የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት ምጣኔ ሃብታዊ ተጽዕኖን ባለፉት ሁለት ወራት አላየንም። . . . አሁን ግን እየመጣ ነው፤ እና ደግሞ ግዙፍ ሆኖ እየመጣ ነው። ደንበኞች ጫናው ፈጽሞ ገና አልተሰማቸውም" ብለዋል።
ሕንድ የኢራን ጦርነት ተጽዕኖ ቀጥተኛ ተጋላጭ ናት።
አገሪቱ በግምት 90 በመቶ ድፍድፍ ነዳጅ ዘይት እንዲሁም ግማሽ ያህል ያጋዝ ፍጆታዋን የምታስገባው ከውጭ ነው። በኢራን ጦርነት የተነሳ የሆርሙዝ ወሽመጥ ላላፉት ሁለት ወራት ዝግ ሆኖ በመቆየቱ የሕንድ የገቢ ወጪ በቢሊዮን ዶላሮች አሻቅቧል።
የአውሮፕላን ትኬት ዋጋ ንሯል። የሽርሽር ወጪዎች ተወድደዋል። የወርቅ ግዢ የውጭ ምንዛሬውን ክምችቱን እያመናመነው ነው። በዚህም የተነሳ መንግሥት ወርቅ እና ብር ከውጭ ለሚያስገቡ ነጋዴዎች 15 በመቶ የታክስ ጭማሪ አድርጓል።
በኢንድራ ጋንዲ ኢኒስቲትዩት ኦፍ ዴቬሎፕመንት ሪሰርች ውስጥ የኢኮኖሚ ተመራማሪ የሆኑት ራጄስዋሪ ሴንጉፕታ "መጀመርያ ላይ ጊዜያዊ ጭማሪ መስሎ ይታይ የነበረው አሁን እየተራዘመ መጥቷል። ይህ የሚቀጥል ከሆነ የሕንድ ምጣኔ ኃብት በጦርነቱ ምክንያት ክፉኛ ከተጎዱት መካከል ይሆናል" ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከሞዲ ያልተለመደ ቀጥተኛ ተማጽኖ ጀርባ በኒው ደልሂ የበለጠ ጭንቀት ሰፍኗል። ሕንድ በአውሮፓውያኑ 1991 እንደገጠማት የምጣኔ ኃብት ቀውስ ወቅት ዶላር ባታጣም የአገሪቱ የዶላር ፍላጎት አልጣጣም ብሏል።
በወቅቱ ሕንድ ለሦስት ሳምንታት ብቻ የገቢ ንግዷን ለመሸፈን የሚበቃ የዶላር ክምችት ነበራት።
ዛሬ ግን ሕንድ ለ11 ወራት የምታስመጣቸውን እቃዎች ለመደገፍ የሚበቃ፣ በዓለም ላይ ካሉት ግዙፍ ከሆኑ የመጠባበቂያ ክምችቶች አንዱ የሆነ ወደ 690 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ክምችት አላት።
ዕዳዋን ለመክፈል የሚያስችል ዶላር ከገበያው ላይ ይጠፋል የሚል ስጋት የለም፤ ነገር ግን ምጣኔ ሃብታዊ ጫናው ግን ቀላል አይደለም።
የውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰት እየተዳከመ፣ የወጪ ንግድ እየቀነሰ እና የቀጣናዊ አለመረጋጋት ገበያዎችን እያናጋ ባለበት በአሁኑ ወቅት ነዳጅ፣ ጋዝ፣ ማዳበሪያ እና ወርቅን የመሳሰሉ ከውጭ የሚገቡ ምርቶች የዶላር ክምችቱን እየበዘበዙት ነው። የሕንድ የውጭ ምንዛሪ ክምችት የኢራን ጦርነት ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በ38 ቢሊዮን ዶላር ቀንሷል።
የነዳጅ ሚኒስትሩ ሃርዲፕ ሲንግ ፑሪ የነዳጅ እጥረት እንደሌለ በመግለጽ የተበሳጩትን አሽከርካሪዎችን ለማረጋጋት ሞክረዋል። ነገር ግን በበርሜል 100 ዶላር የሚገዛው ነዳጅ የመንግሥትን የፋይናንስ አቅም እየፈተነ ነው።
"የሞዲ አስተያየቶች በመንግሥት የፊስካል ፋይናንስ ላይ ያለው ጫና ጫፍ እየደረሰ መሆኑን ያሳያል፤ ሩፒ የበለጠ ዋጋው እንዳይቀንስ እና አንዳንድ የዋጋ ማስተካከያዎች ወደ ሸማቾች ለማስተላለፍ ፍላጎት መኖሩን ያመለክታሉ" ሲሉ አውሮዲፕ ናንዲ እና ሶናል ቨርማ ተናግረዋል።
እንደ ኖሙራ ገለጻ፣ የሕንድ የፊስካል ጉድለት፤ በመንግሥት ወጪ እና በገቢ መካከል ያለው ልዩነት፣ እአአ እስከ መጋቢት 2027 ድረስ ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት (ጂዲፒ) ወደ 4.6% እንደሚጨምር ይገመታል። ወደ አገር ውስጥ የሚገባው እና ወደ ውጭ የሚወጣው የገንዘብ ፍሰት መካከል ያለው ክፍተት ከ70 ቢሊዮን ዶላር በላይ ሆኗል።

የፎቶው ባለመብት, LightRocket via Getty Images
የሕንድን የውጭ ሚዛን በመቆጣጠር ተጨማሪ የሩፒ የመግዛት አቅም መቀነስን መከላከል በዚህ ዓመት "ዋናው የማክሮ ኢኮኖሚ ፈተና" እንደሚሆን የሕንድ የኢኮኖሚ አማካሪ ቪ አናንታ ናጌስዋራን በቅርቡ ተናግረዋል።
ነገር ግን የኢኮኖሚ ባለሙያዎች የሩፒ ችግሮች ከጦርነቱ በፊት የነበሩ እና በቁጠባ ብቻ ሊፈቱ እንደማይችሉ ይከራከራሉ።
የውጭ ባለሀብቶች በቅርቡ ከሕንድ አክሲዮኖች 22 ቢሊዮን ዶላር የሚያህሉ ገንዘባቸውን አውጥተዋል። ይህም የሆነው በዓለም አቀፍ ደረጃ የንግድ እንቅስቃሴ መቀዛቀዝ፣ የአሜሪካ የታሪፍ ስጋቶች እና ሕንድ እንደ የሰው ሠራሽ አስተውሎት፣ ባትሪዎች እና የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ባሉ አዳዲስ ኢንዱስትሪዎች መስክ ሊኖራት በሚቸል የመወዳደር አቅም ላይ ስጋት ስላላቸው ነው።
"ሕንድ በሰው ሠራሽ አስተውሎት ወይም በታዳሽ ኃይል ወይም በዘመናዊ ኤሌክትሮኒክስ ዘርፎች ብዙ ስላላከናወነች፣ ባለሀብቶች አሁን በሌሎች የእስያ አገራት የሚያሳዩትን ዓይነት ተጨማሪ ገንዘብ የማውጣት ወይም በረጅም ጊዜ ትርፍ የሚያስገኙ ብዙ ኢንዱስትሪዎች ላይ መሳተፍ አይፈልጉም " ይላሉ ሴንግፑታ።
"ኢኮኖሚው ከ6 - 6.5 በመቶ ቢያድግም፣ ሰፊው የኢንቨስትመንት ታሪክ ብዙም አሳማኝ አይመስልም።"
የተጣራ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ቀንሷል። ይህም ሩፒን በዚህ ዓመት በእስያ ካሉት ደካማ ምንዛሬዎች አንዱ እንዲሆን አድርጎታል፣ እስካሁን ከ6 - 7 በመቶ ቀንሷል።
"ባለኝ የ30 ዓመታት ልምድ ውስጥ እንደ አሁኑ [ባለሀብቶች] ለሕንድ ገበያ ግድየለሽ ሲሆኑ አይቼ አላውቅም" ሲሉ ዓለም አቀፍ ባለሀብት እና ደራሲ ሩቺር ሻርማ በቅርቡ በሕንድ ኤክስፕረስ ጋዜጣ በተዘጋጀ ውይይት ላይ ተናግረዋል።
ብዙ የኢኮኖሚክስ ሊቃውንት ይህ ሕንድን ምጣኔ ሃብታዊ ቀውስን ከመቀበል በስተቀር ብዙም አማራጭ እንደሌላት ያሳያል ይላሉ። እንደ የነዳጅ ዋጋ መጨመር ያሉ ውጫዊ ጫናዎች ደግሞ ወጪዎችን ከፍ ማድረጋቸው፣ ምንዛሬዎችን ማዳከማቸው እና የሸማቾችን ፍላጎት መቀነሳቸው የማይቀር ነው።
ነዳጅ ውድ ከሆነ ሰዎች መኪኖቻቸውን ለማቆም ይገደዳሉ። የተፈጠሮ ጋዝ ዋጋ ሲጨምር ቤተሰቦች ፍጆታቸው ይቀንሳል። ደካማ የሩፒ የመግዛት አቅም መቀነስ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ዋጋ ከፍ ያደርገዋል እና ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን የበለጠ ተወዳዳሪ ያደርጋል፣ ይህም በጊዜ ሂደት የአሁኑን የሂሳብ ጉድለት ለማጥበብ ይረዳል።

የፎቶው ባለመብት, LightRocket via Getty Images)
በመንግሥት የሚተዳደሩ የነዳጅ ኩባንያዎች እየጨመረ የመጣውን ኪሳራ የመሸከም አቅማቸው እየተሟጠጠ ነው።
አሁን ሕንድ ውስጥ ያለው ክርክር ዋጋ መጨመር አለበት የለበትም የሚለው ሳይሆን ጫናውን ማን ሊሸከም ይገባል የሚል ነው።
መንግሥት እስካሁን ድረስ የተፈጠረውን የዋጋ ንረት እየደጎመ ቆይቷል።
ነገር ግን እንደ ምጣኔ ሃብት ባለሙያው ሴንጉፕታ ያሉ በድጎማ የተነሳ ርካሽ የሆነ ነዳጅ እያቀረቡ መቆየት ዘላቂነት የለውም በማለት ይከራከራሉ።
በምትኩ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ቤተሰቦች በተለይም ለማብሰያ ጋዝ የሚውል ድጎማ ማድረግ አዋጭ መሆኑን ይከራከራሉ። ነገር ግን ለሌሎች ሸማቾች ላይ ዋጋ መጨመር የግድ መሆኑን ይናገራሉ።
የሕንድ የዋጋ ግሽበት ከዚህ ቀደምም ቢሆን ከፍ ያለ ነው። ኤችኤስቢሲ የቅርብ ጊዜውን የዋጋ ግሽበት "ከመጨመሩ በፊት የተረጋጋ" ነበር ሲል ገልጾታል። አሁን ዋጋዎች የተረጋጉ ቢመስሉም በአየር ጠባይ እና በኢነርጂ ዋጋ መናር የተነሳ መጨመራቸው እንደማይቀር እና ማዕከላዊ ባንክም ከፍተኛ የወለድ ጭማሪ እንደሚያደርግ ይናገራል።
ለዓመታት የሕንድ የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች የአገሪቱን ኢኮኖሚ ለማረጋጋት ብዙ ጥረዋል። አሁን ግን የነዳጅ ዋጋ ርህራሄ የለውም። የነዳጅ ዋጋን በድጎማ ባለበት ማቆየት ቢቻልም የከፋው ምጣኔ ሃብታዊ ጫናው ግን ቢዘገይም አይቀሬ ነው።














