የኩባ የነዳጅ እጥረት በተባባሰበት ወቅት የሲአይኤ ኃላፊ አገሪቱን ጎበኙ

በኩባ የኤነርጂ ቀውስ በማባሱን ተከትሎ በእንጨት ምግብ የሚያበስል ሰው

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በኩባ የኤነርጂ ቀውስ በማባባሱ የተነሳ በእንጨት ምግብ የሚያበስል ሰው
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

አሜሪካ በኩባ ላይ የጣለችውን የነዳጅ እገዳ ተጽዕኖን ለማቃለል የ100 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ለማድረግ እንደምትፈልግ ከገለጸች በኋላ የሲአይኤ ዳይሬክተር ጆን ራትክሊፍ በሃቫና በሚገኘው የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ከኩባ አቻቸው ጋር ተገናኙ።

ከኩባ በኩል የተሰጠው መግለጫ እንዳመለከተው የባለሥልጣናቱ ውይይት ያተኮረው ሃቫና ለአሜሪካ ደህንነት ስጋት አለመሆኗን በመግለጽ እና ቀጣይ የሚደረጉ ንግግሮችን ማሻሻል ላይ ነው።

አንድ የሲአይኤ ባለሥልጣን ለቢቢሲ የአሜሪካ አጋር ለሲቢኤስ ኒውስ እንደተናገሩት አሜሪካ "ኩባ መሠረታዊ ለውጦችን ካደረገች ብቻ በኢኮኖሚ እና በደህንነት ጉዳዮች ላይ ለመሳተፍ ዝግጁ ነች" ብለዋል።

አሜሪካ በአገሪቱ ላይ የጣለችውን የነዳጅ ዘይት እገዳ በአገሪቱ ላይ ከፍተኛ የነዳጅ እጥረት የፈጠረ ሲሆን በዚህም የተነሳ ሆስፒታሎች መደበኛ ሥራቸውን እንዳይሰሩ እና ትምህርት ቤቶችና የመንግሥት ቢሮዎች እንዲዘጉ አስገድዷል።

በተናጠል የኩባ ፕሬዝዳንት ሚጌል ዲያዝ-ካኔል እርዳታ ከመስጠት ይልቅ አሜሪካ የጣለችውን እገዳ ካነሳች ሁኔታዎች በፍጥነት ሊሻሻሉ ይችላሉ ብለዋል።

በስብሰባው ላይ የተገኙት የቀድሞ ፕሬዝዳንት ራውል ካስትሮ የልጅ ልጅ ራውል ሮድሪጌዝ ካስትሮ፣ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ላዛሮ አልቫሬዝ ካሳስ እና የኩባ የስለላ ኃላፊ መሆናቸውን የሲአይኤ ባለስልጣን ለሲቢኤስ ተናግረዋል።

የልዑካን ቡድኑ "የፕሬዝዳንት ትራምፕን መልእክት በግል ለማድረስ" ወደ ሃቫና ማቅናቱን የሲአይኤ ባለሥልጣን ተናግረዋል።

"በስብሰባው ወቅት ዳይሬክተር ራትክሊፍ እና የኩባ ባለሥልጣናት የስለላ ትብብርን፣ የኢኮኖሚ መረጋጋትን እና የደህንነት ጉዳዮችን ተወያይተዋል፣ ሁሉም ኩባ በምዕራባዊው ንፍቀ ክበብ ውስጥ ለተቃዋሚዎች አስተማማኝ መሸሸጊያ መሆን እንደማትችል ተግባብተዋል" ሲሉ ባለሥልጣናቱ አክለዋል።

ኩባ በበኩሏ ከባለሥልጣናቱ ንግግር በኋላ ባወጣችው መግለጫ "ሁለቱም ወገኖች በሕግ አስከባሪ አካላት መካከል የሁለቱንም አገራት ደህንነት እንዲሁም የቀጣናዊ እና የዓለም አቀፍ ደህንነትን ለማስጠበቅ የሁለትዮሽ ትብብርን ለማሳደግ ያላቸውን ፍላጎት ገልጸዋል።"

ኩባ እና አሜሪካ በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ድርድር መጀመራቸውን ገልጸው የነበረ ቢሆንም ነገር ግን የነዳጅ እገዳው እየገፋ ሲሄድ ድርድሩ ተቋርጧል።

የሲአይኤ ዳይሬክተር ጆን ራትክሊፍ (በስተግራ) በኩባ ሃቫና በስብሰባ ላይ ሆነው

የፎቶው ባለመብት, CIA

የምስሉ መግለጫ, የሲአይኤ ዳይሬክተር ጆን ራትክሊፍ (በስተግራ) በኩባ ሃቫና በስብሰባ ላይ ሆነው

ከዚህ ቀደም ኩባ ነዳጅ የምታገኘው ከቬንዙዌላ እና ሜክሲኮ ነበር። ሆኖም የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ኩባ ነዳጅ የሚልኩ አገሮች ላይ ታሪፍ ለመጣል ከዛቱ በኋላ ሁለቱ አገራት አቅርቦታቸውን አቋርጠዋል።

ሐሙስ ዕለት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ብሩኖ ሮድሪጌዝ ኩባ "የአሜሪካን የእርዳታ ዕቅድ ዝርዝር እና እንዴት ተግባራዊ እንደሚሆን ለመስማት ዝግጁ ናት" ብለው ነበር።

ረቡዕ ዕለት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር "ለኩባ ሕዝብ እርዳታ ለመስጠት" ዳግም ቃል ኪዳኑን ማደሱን አስታውቋል።

ባለፈው ሳምንት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ሃቫና ቀደም ሲል 100 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ የሰብዓዊ እርዳታ ድጋፍ ውድቅ ማድረጓን ተናግረው ነበር፤ ኩባ ግን ይህንን አስተባብላለች።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ የኩባን መንግሥትን ገለል በማድረግ ድጋፉ "ከካቶሊክ ቤተክርስቲያን እና ከሌሎች አስተማማኝ ነጻ የሰብአዊ ድርጅቶች ጋር በመተባበር" መከፋፈል እንዳለበት ግልጽ አድርጓል።

አጭር ቁምጣ የለበሰች ሴት ውሻዋን ይዛ ጎዳናውን ስታቋርጥ

የፎቶው ባለመብት, EPA/Shutterstock

የምስሉ መግለጫ, በሃቫና ጎዳናዎች ላይ የሞሉ የቆሻሻ ማጠራቀሚያዎች ይታያሉ

አክሎም "የእኛን የእርዳታ አቅርቦት መቀበል ወይም ወሳኝ የሕይወት አድን እርዳታን መከልከል እና በመጨረሻም ለኩባ ሕዝብ ወሳኝ እርዳታን በመከልከል ተጠያቂ መሆን" ውሳኔው የኩባ መንግሥት መሆኑን ገልጿል።

የኩባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሮድሪጌዝ በሰጡት ምላሽ የአሜሪካ እርዳታ በጥሬ ገንዘብ ወይም በዓይነት የሚደረግ ስለመሆኑ ግልጽ አይደለም ብለዋል።

አክለውም "የኩባ መንግሥት በመሠረታዊነት፣ በቅን ልቦና እና በእውነተኛ ትብብር ዓላማ የሚደረግን የሁለትዮሽም ሆነ ባለ ብዙ ዘርፍ የውጭ እርዳታን አልቀበልም አይልም" ብለዋል።

አሜሪካ ኩባን ለመርዳት የምትችልበት ከሁሉ የተሻለው መንገድ "ባለፉት ወራት ውስጥ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ሁኔታ የተጠናከሩትን የኢነርጂ፣ የኢኮኖሚ፣ የንግድ እና የፋይናንስ እገዳ እርምጃዎች መቀነስ" እንደሆነ አክለዋል።

የቢቢሲ የአሜሪካ አጋር የሆነው ሲቢኤስ ኒውስ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ወገኖችን ጠቅሶ ከ30 ዓመታት በፊት በተከሰከሰ አውሮፕላን ምክንያት አሜሪካ የቀድሞውን ፕሬዝዳንት ራውል ካስትሮ እና ወንድማቸውን ፊደልን ለመክሰስ እየተዘጋጀች መሆኑን ዘግቧል።

ክሱ የሚሆነው ኩባ እአአ በ1996 በዓለም አቀፍ ውሃ አካል ላይ በሰብዓዊነት ላይ የተሰማሩ ወንድማማቾች ንብረት የሆነች አውሮፕላን መትታ በመጣሏ እና በውስጡ የነበሩ ሰዎች በመሞታቸው የተነሳ ነው።

ይህ በኩባ ላይ ጫና ለመፍጠር የተወሰደ ሌላ እርምጃ እንደሆነ ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ይናገራሉ።