ፓኪስታን፤ አፍጋኒስታን በፈፀመችው ጥቃት 28 ሰዎች መገደላቸውን የመንግሥታቱ ድርጅት አስታወቀ

በጥቃት የፈራረሰ ሕንፃ እና በአካባቢው የተሰበሰቡ ሰዎች

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, አብዛኞቹ የጠዕቃቱ ሰለባዎች ማንዶኪላ መንደር የሚገኙ ነዋሪዎች እንደሆኑ ባለሥልጣናት ተናግረዋል
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ፓኪስታን እሑድ ዕለት በድንበር በሚገኙ የአፍጋኒስታን ግዛቶች ላይ በፈፀመችው የአየር እና የምድር ጥቃት ቢያንስ 28 ሰዎች መገደላቸውን የመንግሥታቱ ድርጅት የአፍጋን ተልዕኮ አስታወቀ።

በጥቃቱ ተጨማሪ 49 ሰዎች እንደቆሰሉ እና ከተጎጂዎች መካከል ሴቶች እና ሕፃናት እንደሚገኙበት ተልዕኮው ገልጿል።

በታሊባን የሚመራው የአፍጋኒስታን መንግሥት የሰላማዊ ሰዎች ቤቶች መደብደባቸውን ገልፆ፤ ጥቃቱን "አፀያፊ ተግባር" እና "ጭካኔ" ብሎታል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ፓኪስታን በአፍጋንስታን ፓክቲያ፣ ፓክቲካ እና ኩናር ግዛቶች የታጣቂ ምሽግችን ዒላማ ማድረጓን አስታውቃለች።

ጎረቤት አገራቱ ለሳምንታት የዘለቀ ከባድ ግጭት ከተቀሰቀሰ በኋላ ባለፈው ጥቅምት የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ቢደርሱም፤ ስምምነቱ ከዚህ ወዲያ ፈርሷል።

የጥቃቱ አብዛኛው ተጎጂዎች በፓክቲያ ግዛት በምትገኝ ማንዶኪላ መንደር የሚገኙ ነዋሪዎች መሆናቸውን የፓኪስታን መንግሥት አስታውቋል።

የ63 ዓመቱ አደም ካህን "ሆስፒታል ያየኋቸውን ሕፃናትን ሁኔታ ወይም የወላጆቻቸውን እና የእህት ወንድሞቻቸውን ጩኸት በቃላት መግለፅ አልችልም" ሲሉ ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል ተናግረዋል።

ከጥቃቶቹ መካከል በአንደኛው ጥቃት የተገደሉት "ቤታቸው ውስጥ ተኝተው የነበሩ ሕፃናት፣ አረጋዊያን እና ሴቶች" እንደሆኑም አክለዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የአፍርጋኒስታኑ የታሊባን መንግሥት የንፁሃን ሟቾቹ ቁጥር 36 እንደሆነ እና የቆሰሉ ሰዎች ደግሞ 160 መሆናቸውን ገልጿል።

የፓኪስታን የኢንፎርሜሽን ሚኒስትር አቱላህ ታራር "በንፁኃን ሰዎች ላይ በቅርቡ ለደረሰ የሽብር ጥቃት" አገራቸው በሰጠችው ምላሽ 29 ታጣቂዎች መገደላቸውን አስታውቀዋል።

ቢቢሲ በሁለቱም ወገኖች የተጠቀሱ አሃዞችን በገለልተኛነት ማረጋገጥ አልቻለም።

ጥቃቱ የተፈፀመው የፓኪስታን ጦር 'ሲንዲ ሬንጀርስ' ተብለው የሚታወቁት ኃይሎች ዋና ቢሮ ውስጥ ሦስት አባላቱ እንደተገደሉ ካስታወቀ ከአንድ ቀን በኋላ ነው። በራስን ማጥፋት ጥቃቱ ሦስት ታጣቂዎች ሲገደሉ፤ አፍጋኒስታዊ የሆነው አራተኛው ታጣቂ በቁጥጥር ስር መዋሉን የፓኪስታን ባለሥልጣናት ገልፀዋል።

ፓኪስታን ላይ ለደረሰው ጥቃት 'ተሪክ ታሊባን ፓኪስታን' ከተባለው ታጣቂ ቡድን ተነጥሎ የወጣው 'ጃማት ኡል አህራር' ኃላፊነት ወስዷል።

የፓኪስታን ታሊባን ተብሎ የሚጠራው 'ተሪክ ታሊባን ፓኪስታን' እና 'ጃማት ኡል አህራር' ከዚህ ቀደም በተፈፀሙ ጥቃቶች ባላቸው ተሳትፎ ምክንያት በፓኪስታን እና በመንግሥታቱ ድርጅት የታገዱ ቡድኖች ናቸው።

ፓኪስታን፤ አፍጋኒስታን ድንበር ተሻጋሪ ጥቃቶችን የሚፈፅሙ ቡድኖችን ታስጠልላለች የሚል ክስ ለረጅም ጊዜ ስታሰማ ቆይታለች። የታሊባን መንግሥት ክሱን ውድቅ ያደርጋል።

ካቡል በአንፃሩ ኢስላማባድን ንፁሃንን የሚገድሉ ምክንያት አልባ ጥቃቶችን እንደፈጸመች በመግለጽ ትከስሳለች። ፓኪስታን ደግሞ ታጣቂዎችን ብቻ ዒላማ እንደምታደርግ ትገልፃለች።

ባለፉት ሳምንታት በሁለቱ አገራት ድንበሮች አካባቢ በሚፈፀሙ ጥቃቶች በርካታ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን ከአገራቱ የሚወጡ መረጃዎች ያመላክታሉ።

ባለፈው የካቲት በሁለቱ አገራት መካከል በተቀሰቀሰ ግጭት በርካታ ሰዎች ተገድለዋል። በመጋቢት ወር ደግሞ ፓኪስታን በካቡል በሚገኝ የአደገኛ ዕፅ ማገገሚያ ማዕከል ላይ በፈፀመችው ጥቃት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል።

በሰኔ መጀመሪያ ላይ ፓኪስታን በፈፀመችው ከበድ የአየር ጥቃት 26 ታጣቂዎች መገደላቸው ተዘግቧል። የአፍጋኒስታን የታሊባን መንግሥት በጥቃቶቹ በአብዛኛው ሕፃናት የሆኑ 13 ሰዎች ተገድለዋል ብሏል።