ኢቶሪካ: ቴዲ አፍሮ በየዘመኑ ለምን መነጋገሪያ ሆነ? ሥራዎቹንስ ምን ልዩ ያደርጋቸዋል?

ቴዎድሮስ ካሳሁን

የፎቶው ባለመብት, TeddyAfro FB

የንባብ ጊዜ: 8 ደቂቃ

ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ስድስተኛ አልበሙን ሐሙስ ዕለት ሚያዚያ 8/2018 ዓ.ም. ከቀኑ ስምንት ሰዓት ላይ በራሱ የዩቲዩብ ገጽ ላይ ለአድማጮቹ አድርሷል።

18 ሙዚቃዎችን የያዘው ይህ አልበም በአድናቂዎቹ እጅግ የተወደዱ እና በሚሊዮኖች አድማጭ ያገኙ ሥራዎች ተካተውበታል።

ቴዎድሮስ ካሳሁን ከዚህ ቀደም አቡጊዳ፣ ቴዲ፣ ያስተሠርያል፣ ጥቁር ሰው፣ ኢትዮጵያ የተሰኙ አልበሞችን ለአድማጮቹ አድርሶ ተወደውለታል።

አሁንም የሙዚቃ ሥራው በዩቲዮብ ገፁ ላይ ከተጫነ በኋላ በነበሩት 24 ሰዓታት ውስጥ ብቻ "ዳስ ጣል" የሚለው ሙዚቃው ከስድስት ሚሊዮን በላይ አድማጭ አግኝቷል።

በ2013 ዓ.ም. የክብር ዶክተሬቱን ከጎንደር ዩኒቨርስቲ የተቀበለው ቴዎድሮስ ካሳሁን 'ኢቶሪካ' ሲል የሰየመውን ስድስተኛ አልበሙን ለአድማጮች እንደሚያደርስ ይፋ ካደረገበት ጊዜ አንስቶ መነጋገሪያ ሆኗል።

በዓመቱ ስምንተኛ ወር በወሩ ስምንተኛ ቀን እና በቀኑ ስምነተኛ ሰዓት ላይ ለሕዝብ እንደሚቀርብ የተነገረለት የቴዲ ሙዚቃን በተመለከተ ሊሰጥ የነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ እና የቀጥታ ሥርጭቱ መሰረዙ ተነግሯል።

ከዚህም ባሻገር በቅድሚያ ሙዚቃው ይለቀቃል ተብሎ የነበረበት ሰዋሰው መልቲሚዲያ እና ቴዲ አፍሮ የነበራቸውን የሥርጭት ውል የማፍረሳቸው ወሬ ሌላው የውዝግብ አካል ሆኖ ነበር።

በኋላ ሰዋሰው መልቲሚዲያ በሰጠው መግለጫ ከቴዲ አፍሮ ጋር የገቡትን ውል ያቋረጡት በአሳታሚው እና በድምጻዊው መካከል ባለው ውል ውስጥ በተካተቱ አዳዲስ ጉዳዮች መንስኤ መሆናቸውን አብራርቷል።

አራት ዓመት ሊሞላው ሁለት ወር ቀርቶት የነበረው የቴዲ እና የሰዋሰው ውልን ለማደስ በተደረጉ ተደጋጋሚ ውይይቶች የቀረቡ አዳዲስ ሀሳቦች ሁለቱንም ወገኖች ሳያግባቡ ቀርተዋል ተብሏል።

ቴዎድሮስ ካሳሁን ኢትዮጵያ የሰኘ አልበሙ ላይ ፊርማውን እያኖረ

የፎቶው ባለመብት, Teddy Afro FB

ከሕዝብ ጋር ከተዋወቀ 25ኛ ዓመቱን የያዘው ቴዲ አፍሮ

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ድምጻዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን ከአድማጮቹ ጋር ከተዋወቀ 25 ዓመታት ተቆጥረዋል።

የመጀመሪያው የቴዲ አፍሮ አልበም "አቡጊዳ" ወደ አድማጮች የደረሰው በ1993 ዓ.ም. ነበር።

ቴዎድሮስ ካሳሁን በእነዚህ 25 ዓመታት ውስጥ ስድስት የሙዚቃ አልበሞችን ወደ ለአድማጮቹ እና ለአድናቂዎቹ አቅርቧል።

ቴዲ በእነዚህ ዓመታት ሁሉ ልባቸው እንደ ሰም የሚቀልጥባቸው አድናቂዎች፣ ፊታቸው በመከፋት የሚጠይምባቸው ተቺዎችን አፍርቷል።

ኢትዮጵያዊነት እንዴት ይገፋ ለሚልላቸው የነጻነት እና የመብት ፊታውራሪ እንዲሁም የዘመኑ ድምጽ ሲሆን ልባቸው ለሚጎሽባቸው ደግሞ ድምጻዊ ብቻ ነው።

ቢሆንም ግን ቀኙም ግራውም፣ ዳር ተመልካቹም ሆነ መሃል ላይ ተውረግራጊው እኩል የሚያዳምጠው፣ የሚተነፍሰው በሺህዎች የሚመነዘርበት፣ የሚያዜመው የበርካቶችን ልብ በብርቱ መልዕክቱ የሚያንኳኳ ነው።

በ25 ዓመታት የሙዚቃ ሕይወቱ ውስጥ የቴዎድሮስ ሥራዎች ብቻ ሳይሆኑ፣ እርሱም እንደተወደደ ለመቀጠሉ ምክንያት ምንድን ነው? ምንስ ለየት ያደርገዋል? ስንል በቅርበት የሚያውቀውን እና የፊልም ባለሙያውን እና የግጥም ደራሲውን ያሬድ ሹመቴ (ጎላ ጎሕ)ጠይቀናል።

ያሬድ፣ ቴዎድሮስ ካሳሁንን ልዩ የሚያደርገው "የመጣበት መንገድ ልዩ መሆኑ ይመስለኛል" ይላል።

ቴዲ አፍሮ ሲመጣ "ማንንም መስሎ አለመምጣቱ፤ የግጥም፣ የዜማ፣ የሙዚቃ፣ የአዘፋፈን ስልቱ በሙሉ በራሱ መንገድ አዲስ ነገሮችን ይዞ የመጣ በመሆኑ" መለየቱን ያብራራል።

ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የሙዚቃ ባለሙያ ደግሞ "ድምጻዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ባለጥልቅ ተሰጥዖ የግጥም እና የዜማ ደራሲ ነው" ይላሉ።

በግጥም ዙሪያ የሚዳስሳቸው ርዕሶችም "ታሪክን የሚመረምሩ፣ ፍቅርን እና አብሮነትን የሚሰብኩ፣ ይቅር መባባልን የሚያጎሉ፣ የአገር ባለውለታዎችን የሚዘክሩ፣ የሕዝብ ውግንና ያላቸው እና ጊዜውን የሚዋጁ" መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

"የቴዲ ልዩነት ገና ከአመጣጡ ነው የሚጀምረው" የሚለው ያሬድ ሹመቴ፣ ጠንካራ መልዕክት ያላቸው ግጥሞች፣ ለአድማጭ የሚስማሙ ዜማዎች፣ በአግባቡ ተመርጠው በአንድነት የተሰደሩ ሥራዎችን ይዞ መምጣቱን በመጥቀስ ". . . ገና ሲመጣ ጀምሮ ክስተት የሆነ" ሲል ይገልጸዋል።

በድምጻዊነት፣ በግጥም እና ዜማ ደራሲነት እንዲሁም በሙዚቃው ርዕሰ ጉዳይ መረጣ ጭምር ቴዎድሮስ ካሳሁን አዲስ ነገር ይዞ መምጣቱን ያሬድ ያብራራል።

ቴዎድሮስ ካሳሁን ወደሙዚቃው ዓለም ከመቀላቀሉ በፊት በኢትዮጵያ ሙዚቃ ውስጥ "የትውልድ ክፍተት" ተፈጥሮ እንደነበር የሚያስረዳው ያሬድ፣ "ቴዲ ወደ ሙዚቃው በይፋ ከመምጣቱ በፊት የቀደሙ ሥራዎችን ደግሞ መሥራት፣ የውጭ ሙዚቃዎችን ዜማ እና ግጥም ብቻ ቀይሮ መዝፈን የተለመዱበት" እንደነበር ያስታውሳል።

ይህ ተጽዕኖ በቴዎድሮስ አልበም ላይ መታየቱን በመጥቀስ "የማያቁት አገር አይናፍቅም" የሚለውን ዘፈን አሳታሚዎች ለማስገባት ተገድደው እንደነበር ይጠቅሳል።

ቢኒያም አቡራ በቴዎድሮስ ካሳሁን የሙዚቃ ሥራዎች ላይ ያተኮረ "ወደ ፍቅር ጉዞ" የተሰኘ መጽሐፍ አሳትሟል።

በዚህ መጽሐፉ የቴዎድሮስ ካሳሁን የዘፈን ግጥሞች ተንትኗል፤ ዳስሷል።

ለዘፈን ግጥም መሠረታዊው ነገር ውስብስቡን ነገር ቀለል ባለ ቋንቋ ማቅረብ ነው የሚለው ቢኒያም፣ ቴዎድሮስ ካሳሁን ግን ከዚያም ከፍ ያሉ ነገሮችን በማቅረቡ ለየት እንደሚል ያነሳል።

ቴዎድሮስ ካሳሁን "ዝሆኖች ተጣልተው ሰበሩት ድንበሩን" ሲልም ሆነ "ዘመን ያገነነው ጅብ ቆሟል ከበሬ" ብሎ ሲያቀነቅን "አሊጎሪካዊ" በሆኑ መንገዶች ተጠቅሞ ጥልቅ መልዕክቶቹን በቀላል ቋንቋ ለአድማጩ እንደሚያደርስ ይናገራል።

ከዚህም ባሻገር በግጥሞቹ ውስጥ ትዕምርታዊ የሆኑ የአገጣጠም ብልሃቶችን መጠቀሙ አድማጩ ጎራ ለይቶ ለውይይት እንዲሰናዳ እንደሚያደርገው ቢኒያም ያስረዳል።

ቴዎድሮስ ብዙ ድምጻውያን በቀጥታ የማያነሷቸውን፣ የማይደፍሯቸውን ርዕሰ ጉዳዮች "ታሪክን በቀጥታ የመንካት እና ፖለቲካን በቀጥታ የመጋፈጥ ባህሪያት ስላሉት" እነዚያን ደግሞ በውብ ዜማ እና ቋንቋ ስለሚያስቀምጣቸው ለተወዳጅነቱም ሆነ መነጋገሪያ ለመሆኑ ሰበብ መሆናቸውን ያስረዳል።

ቴዎድሮስ ካሳሁን

የፎቶው ባለመብት, Teddy Afro FB

የቴዲ ልዩ ነገር

ለያሬድ ሹመቴ የቴዲ ልዩ ነገሩ በቅድሚያ እርጋታው ነው። "በጣም አይቸኩልም። የሆነች ቃል መጣችልኝ የሆነች ሃሳብ ተከሰተችልኝ ብሎ የሚሮጥ ሰው አይደለም" ሲል ይገልጸዋል።

ቴዲ በጣም ወደ ስሜት የቀረቡ ነገሮችን የመሥራት አቅሙ በጣም ከፍተኛ ነው የሚለው ያሬድ፣ "ቴዲ የተለየ ስሜት የማግኘት አቅም እና ያቺ የተገኘች ስሜትን የማጋባት አቅም" ያለው መሆኑ መለያው እንደሆነ ይገልጻል።

"የቴዲ ትልቁ መገለጫው ስሜት የማግኘት እና ስሜት የማጋባት አቅሙ ይመስለኛል።"

የሙዚቃ ባለሙያው በበኩላቸው ድምጻዊው ለግዙፍ ግጥሞቹ ተስማሚ አድሮጎ የሚሠራቸው ዜማዎች፣ ለጉሮሮው ምቹ ከመሆን ባለፈ የግጥሙን ሃሳብ እና መንፈስ መሸከም እንዲችሉ ተደርገው መዋቀራቸው ለየት እንደሚያደርገው ያነሳሉ።

ይህም በተለይ ከሕዝብ በሚገናኝበት የመድረክ ክዋኔ እያንዳንዱን የሙዚቃ ድርሰቶቹን በጥልቅ ስሜት እና ብቃት የሚከውን በመሆኑ ለየት ያደርገዋል።

"በተጨማሪም በተለያዩ አጋጣሚዎች ከድምጻዊው ጋር የሠሩ የሙዚቃ ቀማሪያን ሲመሰክሩ እንደሰማነው ቴዲ ከግጥም እና ዜማ ድርሰት ባለፈ ለሙዚቃው ቅንብር ይዟቸው የሚመጣው ተጨማሪ ሃሳቦች በሙዚቃ ቅንብር ላይ ያለውን ከፍተኛ መረዳት እና መሰጠት የሚያመለክቱ ልዩ ችሎታዎቹ ናቸው።"

የቴዎድሮስ ካሳሁን 'ጣል ዳስ' የተሰኘ የሙዚቃ ስራ ምስል

የፎቶው ባለመብት, Teddy Afro FB

የምስሉ መግለጫ, የድምጻዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ስድስተኛ የሙዚቃ አልበም በዩቲዩብ ገጹ ላይ በተጫነ በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ሚሊዮኖች አዳምጠውታል። 'ጣል ዳስ' የተሰኘው ስራው ብቻ በ24 ሰዓታት ውስጥ 6 ሚሊዮን ሰዎች አድምጠውታል።

'የአድናቂዎቹ እና የነቃፊዎቹ መነጋገሪያ'

ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁት ባለሙያ "ሙዚቃ ቅን ልቦና፣ እውነተኛ ስሜት እና ድርጊት ትፈልጋለች" ይላሉ።

ድምጻዊ ቴዎድሮስ ከመነሻው ይህንን ያዳበረ እና "ለሕዝብ ከገባው ቃል ለአንዴ እንኳን ፈቀቅ ያላለ፤ የእርጋታ እና የማስተዋል ፀጋ የተቀባ" በመሆኑ በሙዚቃ ሥራው ነግሶ እንዲቆይ አስችሎታል ሲሉም ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።

አክለውም ሙዚቃ በጥቂት ደቂቃ ውስጥ "መጽሐፍን መተረክ፤ ግዙፍ ሃሳብ እና አርዕስት መሸከም፤ እንዲሁም ከተደራሲ ወይም ከአድማጭ ሲደርስ በቀላሉ ስሜትን መግዛት የሚችል" ረቂቅ ጥበብ መሆኑን ያነሳሉ።

በዚህም የተነሳ ፖለቲከኛ እና ገዥዎች "ከጦር በላይ የነፃነት አቀንቃኞችን ይፈሯቸዋል" በማለት "እነዚህ የሙዚቃ ጠበብቶች የአገር ፍቅርን የመቀስቀስ፣ የማንቃት እና የሕዝብን ስሜት በጨቋኝ ገዥዎች ወይም ኢ ፍትሃዊ ፖሊሲዎች ላይ የማሰባሰብ ኃይል ስላላቸው" መሆኑን ያነሳሉ።

እነዚህ አቀንቃኞች በዘፈኖቻቸው ብዙውን ጊዜ የተቃውሞ፣ የአንድነት እና የማኅበራዊ ለውጥ መልዕክቶችን ያስተላልፋሉ፣ ካሉ በኋላ "ይህም የገዥዎች ሁኔታ የሚፈታተን እና በሥልጣን ላይ ያሉትን ሁሉ የሚያሸብር ነው።"

ያሬድ ሹመቴ፣ ድምጻዊ ቴዎድሮስ ሁሌም መነጋገሪያ መሆን የሚገርመው ነገር መሆኑን አልሸሸገም።

"ቴዲን በቅርበት እንደሚያውቀው ሰው አንድም ቀን መነጋገሪያ ለመሆን ሲያቅድ አላውቅም፤ ይህንን እኔ መመስከር እችላለሁ።"

ነገር ግን ቴዎድሮስ ካሳሁንን የአድናቂ እና ነቃፊ አጀንዳ እንዲሆን የሚያደርጉት እራሳቸው ተቺዎቹ መሆናቸውን ያሬድ ማስተዋሉን ይናገራል።

"አንድም ቀን ይህ ሊያነጋግርልኝ ይችላል፤ ይህንን እንደዚህ ላንጫጫው የሚል ዓይነት ነገር የለውም።"

የሙዚቃ ባለሙያው በበኩላቸው የነጻነት አቀንቃኞች "አድማጮች በትኩረት እንዲያስቡ" እና "ለመብታቸው እንዲቆሙ በማነሳሳት" በሕዝብ አስተያየት ላይ ተጽእኖ ሊያሳድሩ፣ አልፎ ተርፎም እንቅስቃሴን ሊያበረታቱ የሚችሉ "ተፅዕኖ ፈጣሪ ድምጾች" በመሆናቸው ሁሌም በዐይነ ቁራኛ እንደሚታዩ ያነሳሉ።

"ድምጻዊ ቴዎድሮስ በአገራችን ካሉ ሙዚቀኞች ሁሉ የነፃነት እና የመብት ፊታውራሪ አቀንቃኝ በመሆኑ አዲስ ሥራ ይዞ ሊቀርብ በተበሰረ ዕለት ሁሉ" አነጋጋሪ የመሆን ዕድሉ ሰፊ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ያሬድ፣ ቴዎድሮስ ካሳሁንን በቅርበት እንደሚያውቀው ገልጾ፣ "ለልቡ ታማኝ የሆነ ሰው ነው" ይለዋል።

ይህንንም ሲያብራራ "ከአንደበቱ የሚወጣው እርሱ የሚያምንበት ብቻ ነው፤. . .እንጂ የሚያመጣውን ተጽእኖ አስልቶ ሲያደርግ እኔ አይቼው አላውቅም። . . . እርሱ የተሰማውን ነው የሚያወጣው።"

ለእርሱ አነጋጋሪ መሆን ኃላፊነት መውሰድ የሚችሉት "ሙዚቃው ከመውጣቱ በፊት የሚሰሙት የተቃርኖ ድምጾች ናቸው ባይነኝ. . . ለእርሱ ተወዳጅነት፣ ተሰሚነት፣ አነጋጋሪ መሆን የአንበሳውን ድርሻ የሚወስዱት በተቃርኖ የቆሙ ሌሎች አካላት ናቸው።"

ቴዎድሮስ ካሳሁን "ሙዚቃን ከመዝናኛነት ወደ ትግል ሜዳ የቀየረ ሙዚቀኛ ነው" የሚለው ቢኒያም፣ ቀላል በሚመስሉ የፍቅር ታሪኮች ውስጥ ውስብስቡን የኢትዮጵያን ፖለቲካ "የመዘየብ ባህሪዎች" አሉት ይላል።

ሌላው ቴዲን በተመለከተ የሚነሳው "በታላቁ ትርክት [ኢትዮጵያዊነት] ላይ የተንጠለጠለ መሆኑ ነው።"

እንደ አጋጣሚ ሆኖ ቴዲ አፍሮ ወደ ሙዚቃው ኢንዱስትሪ የተቀላቀለበት ወቅት ይህ ኢትዮጵያዊነት የምንለው ታላቁ ትርክት 'ዲኮንስትራክት' የተደረገበት ወቅት መሆኑን ቢኒያም ለቢቢሲ ተናግሯል።

ይህ ታላቁ ትርክት 'ዲኮንስትራክት' ተደርጎ አዲስ ትርክት እየተፈጠረ በነበረበት ወቅት መገኘቱ የእርሱን አነጋጋሪነት እንዲጨምር ማድረጉን ቢኒያም ያስረዳል።

"ምክንያቱም ቴዲ በየአቅጣጫቸው ጎጣዊ ትረክቶች እንደ ልብ በሚናፈሱበት ወቅት፣ እርሱ ታላቁ ትርክት ላይ ተጣብቆ መቅረቱ በዋናነት በእርሱ ላይ እንዲነጋገሩ፣ ስለእርሱ እንዲያስቡ እና እንዲከራከሩ አድርጓቸዋል" ባይ ነው።

ይህም ተጽእኖ ፈጣሪነቱን እንዲጨምሩ ካደረጉ ነገሮች መካከል መሆኑን ቢኒያም ያስረዳል።

የቴዲ የመጀመሪያ አልበም ሽፋን

የፎቶው ባለመብት, SM

የምስሉ መግለጫ, ይህ አልበም ድምጻዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን "ቴዲ አፍሮ" የሚል መጠሪያውን ሳያገኝ በፊት ከኤክስፕረስ ባንድ ጋር የሠራው ነው

የሚያነሳቸው ርዕሰ ጉዳዮች . . .

ቴዲ አፍሮ ሁልጊዜ ውስጡ የሚያመውን፣ የሚያስጨንቀውን፣ የሚረብሸውን ሃሳብ በሙዚቃ አምጦ እንደሚወልዳቸው ያሬድ ሹመቴ ያስረዳል።

". . . ብዙ ጊዜ ከቴዲ ጋር ስንገናኝ የማስተውለው ነገር፣ ጭንቀቱ፣ ህመሙ ሁሉ የአንድነት፣ የአገር ጉዳይ፣ የኢትዮጵያዊነት ጉዳይ በጣም ያሳስበዋል። አብሮ መብላት አለመቻል። እንደልብ መንቀሳቀስ አለመቻል። ለልጆቻችን የምትተርፍ አገር እንድትሆን የማሰብ በጣም ጭንቀቶች አሉት።"

እነዚህ የሁልጊዜ ጭንቀቶቹ ወደ ድርሰቱ ሲመጡ የሰማናቸውን ሥራዎቹን መውለዳቸውን ያሬድ ይናገራል።

ቴዎድሮስ "ራሱ ሕዝብ ነው" የሚለው ያሬድ፣ ማንም ሰው የሚሰማው ስሜት እርሱንም ይሰማዋል በማለት "የሚያምንበትን ጉዳይ ብቻ" እንደሚሰራ ይጠቅሳል።

"ቴዲ ሕዝብ ይህንን ነው የሚፈልገው፤ ይህ ነው ፍላጎቱ ብሎ የሚያስብም አይመስለኝም። እኔ እንዳየሁትም አንድም ቀን ይህንን ሕዝብ እንድልለት ይፈልጋል የሚል ኃላፊነት ለራሱ አሸክሞ አያውቅም።"

የቴዲ የሙዚቃ ሥራዎች ፖለቲካዊ ሃሳቦች ይዘዋል የሚሉ "የፖለቲካ ሰዎች ናቸው" በማለት እርሱ ሲሠራ የሚሰማውን እውነተኛ ስሜት ስለሚያወጣ ያ "እውነተኛ ስሜት ደግሞ ወደ አድማጮቹ ይጋባል" ይላል።

"ሌላ ሰው ሊለው ያልቻለውን ነገር ሁሉ እኮ ይገኛል። ሁሉም ሰው ሊሰማው ይችላል በየቦታው። ግን የተሰማውን ስሜት የሚገልጽበት ቃል ሊያጣ፣ ስም ሊያጣለት ይችላል። ያ ደግሞ በተልዕኮ የሚሰጠው የጥበብ ሰው ሊኖር ይቸላል ማለት ነው።"

በየዘመኑ ሕዝቡ የተሰማውን ስሜት ለመግለጽ ቃላት አጥቶ የተቸገረበትን ነገር እንዲያወጡ "ጥበብ እንደ መለኮት ሹክ የምትላቸው ሰዎች አሉ" የሚለው ያሬድ "የዚህ ዘመን ሹክታዎች፣ እነዚያ የሕዝብ ስሜቶች ሁሉ የሚመጡበት ሰው ቴዲ ነው ብዬ አስባለሁ።"

ግን ያ ማለት ፖለቲካ ውስጥ ገብቷል ማለት አይደለም በማለት ቴዎድሮስ ካሳሁን "እውነትን ከመግለጽ ውጪ" ሌላ ሃሳብ እንደማይታይበት ይናገራል።

የጎንደር ዩኒቨርስቲ ለቴዎድሮስ ካሳሁን የክብር ዶክተሬት ዲግሪ በሰጠበት ጊዜ

የፎቶው ባለመብት, AMC

የምስሉ መግለጫ, ሐምሌ 24/2013 ዓ.ም. የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ለድምጻዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን በሰብዓዊ፣ በማኅበራዊ እና በኪነ ጥበብ ዘርፉ እያበረከተ ላለው አስተዋጽኦ የክብር ዶክተሬት ዲግሪ አበርክቶለታል

የቴዎድሮስ ካሳሁን "አፄዎች"

ቴዎድሮስ በሥራዎቹ መካከል ከሚጠቅሳቸው የቀድሞ ነገሥታት ከፊት ተርታ የተቀመጡት አፄ ኃይለ ሥላሴ ናቸው።

በ1993 ዓ.ም. በታተመው እና በኤሊያስ መልካ በተቀናበረው ሥራው ውስጥ ከተካተቱ ሥራዎች መካከል ሁለቱ የአገር ዋርካ የሆኑ ሰዎችን ያነሳሳል።

"ግርማዊነትዎ" አፄ ኃይለ ሥላሴን፣ "ኃይሌ" ደግሞ በሩጫው መድረክ የአገርን ባንዲራ ከፍ አድርጎ ያሰቀለው ኃይሌ ገብረሥላሴ ተወድሶበታል።

ይህ ግን ቀጥሎ በመጡት ሁለት የሙዚቃ ሰንዱቆቹ ውስጥም የታየ ነው።

'ቴዎድሮስ' እና 'ጥቁር ሰው' ነገሥታቱን ያወደሰበት፣ የኢትዮጵያን አንድነት የሰበከባቸው ሥራዎቹ ናቸው።

ያሬድ፣ ቴዎድሮስ ካሳሁን 'ከልጅነቴ ጀምሮ ስለቀደሙ መሪዎች ክፉ ሲነገር ሰማሁ አሁን ይበቃኛል። ደግሞ ያልተነገረውን መልካም ነገር ብናገር ይሻለኛል' እንደሚል ይናገራል።

በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በተለያየ የታሪክ አጋጣሚ መጥተው አገሪቱን ስለመሩ ነገሥታት በርከታ አሉታዊ ነገሮች ይነገራሉ።

"ስለዚህ ከቀደሙ ነገሮች የተሻለ የሚያደርጉ፣ የሚያራምዱ ጉዳዮችን ብንወስድ የሚል መነሻ አለው።"

ስለ አፄ ኃይለ ሥላሴ የአፍሪካ ኅብረትን በማቋቋም የነበራቸውን ሚና አጉልቶ አሳይቶ አስተዋጿቸውን ዘክሯል።

"እንግዲህ ጀግና ለመፍጠር ከዚህ ቀደም የነበሩ ጀግኖችን ማውሳት አዲስ ጀግና ይፈጥራል። ጀግናን ማንቆለጳጰስ ነው አዲስ ጀግና እንዲቀና መንፈሳዊ ተነሳሽነት እንዲኖረው ያደርጋል።"

በጥቁር ሰው ውስጥ ስለ ኢትዮጵያ አንድነት፣ በአንድ ስለመቆም፣ ከመላው ኢትዮጵያ ተሰባስቦ አድዋ ላይ ከትሞ ድል ስላመጣው ሰው የአንድነት ጉዳይ ነው የሚያወራው የሚለው ያሬድ "እኔ የሚመስለኝ የጥቁር ሰውን ሙዚቃ የኢትዮጵያን አንድነት የማይወድ ሰው ላይወደው ይችላል" ይላል።

ስለ አፄ ቴዎድሮስ በሠራው ሙዚቃ ላይም 'ጎንደር ጎንደር የአንዲት ኢትዮጵያ ዋልታና ማገር' በማለት ስለ አንድነት አቀንቅኗል።

"ስለዚህ እኔ የሚታየኝ የቀደሙ ነገሥታት ለአንድነት የነበራቸውን ዋጋ አጉልቶ ለማሳየት የፈለገበት ስለሆነ አንድነት ከሚለው ሃሳብ በተቃራኒው የቆሙ ሰዎች ቢጠሉት ምንም አይመስለኝም።"

ቴዎድሮስ ካሳሁን እአአ በ2018 በሲያትል መድረክ ላይ የሙዚቃ ሥራውን ሲያቀርብ

የፎቶው ባለመብት, TeddyAfro FB

የምስሉ መግለጫ, ቴዎድሮስ ካሳሁን እአአ በ2018 በሲያትል መድረክ ላይ የሙዚቃ ሥራውን ሲያቀርብ

ቴዲ አፍሮ በዓለም አቀፍ መድረክ እንዲገኝ

ብዙ የአፍሪካ አገራት ታላላቅ፣ ዓለም አቀፍ ዝና እና ማማ ላይ የደረሱ ሙዚቀኞችን አበርክተዋል።

ማሊ ሳሊፍ ኪዬታን፣ ደቡብ አፍሪካ ማሪያም ማኬባን፣ ኢትዮጵያ ሙላቱ አስታጥቄን፣ ናይጄሪያ ፌላ ኩቲን አበርክተዋል።

ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁት የሙዚቃ ባለሙያ ቴዲ አፍሮ ካለው ግዙፍ ብቃት፣ አቅም እና ሰፊ የሕዝብ ቅቡልነት አንፃር ሥራዎቹ ከተወሰነው የአገራችን የሙዚቃ ድንበር ተሻግረው በዓለም የሙዚቃ መድረክ ላይ ተፅእኖ መፍጠር የሚችሉበት ሰዓት እና ጊዜ "አሁን በመሆኑ" ጉዳዩን ቢመረምረው ይላሉ።

በመሆኑም ድምጻዊ ቴዎድሮስ ካሳሁንን ከእነዚህ ተርታ እንድናየው ያሉትን መንገዶች መፈተሽ እና መጥረግ የእርሱ ብቻ ሳይሆን "ለአገራችን ብሎም ለመጪው የሙዚቃ ተረካቢዎች ዕድልን መክፈት ነው" ይላሉ።

በመሆኑም ከቀድሞ ሥራዎቹ የበለጠ የሙዚቃ ቅርፅ ( Musical structure)፣ የሙዚቃ ቀመር (Music arrangement)፣ የሙዚቃ ቅጂ (Music recording)፣ በሳል ዜማ እንዲጠቀም ይመክራሉ።

በመሆኑም በሙዚቃ ቀረፃ ሥራው ላይ በየዘርፉ የላቁ ሰዎችን (recording engineer's, mixing and mastering engineer's)፣ በአገር አሊያም በውጪ ደረጃቸውን በጠበቁ ትላላቅ የቀረፃ ስቱዲዮ ቢያከናውን ሲሉ መክረዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሙዚቃ የሚያሠራጩ ኩባንያዎች ጋርም ቢመካከር በጎ ጎን እንዳለው አንስተዋል።