ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በዋግ ኽምራ ዞን ታጣቂዎች ሁለት ወረዳዎችን በመቆጣጠራቸው በርካታ ነዋሪዎች መፈናቀላቸው ተነገረ
በአማራ ክልል ዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን 'የአገው ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ' (አዴን) ታጣቂዎች አበርገሌ እና ፃግብጂ ወረዳዎችን "ሙሉ ለሙሉ" መቆጣጠራቸውን እና ማኅበረሰቡ በስጋት ሸሽቶ መፈናቀሉን የአካባቢው አስተዳደር እና ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናገሩ።
ከሁለት ዓመት በፊት ከመንግሥት ጋር የሰላም ስምምነት ፈርመው የነበሩት የአገው ታጣቂዎች ካለፈው ሚያዝያ ወር ጀምረው ሁለት ወረዳዎችን እንደተቆጣጠሩ አምስት የአካባቢው ነዋሪዎች እና የዞኑ ፀጥታ መምሪያ ተናግረዋል።
የአዴን ኃላፊዎች ወረዳዎቹን እንደተቆጣጠሩ ለቢበሲ አረጋግጠው፤ ነዋሪዎች ግን አልተፈናቀሉም በማለት አስተባብለዋል።
በአበርገሌ ወረዳ ሚያዚያ 12/2018 ዓ.ም. በአካባቢው ሚሊሻዎች እና በታጣቂዎች መካከል "በከባድ መሣሪያ" የታገዘ ግጭት ከተቀሰቀሰ በኋላ የአዴን ኃይሎች በከፊል ተቆጣጥረውት የነበረውን ወረዳ ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠራቸው ተነግሯል።
ቀኑን ሙሉ ውሏል በተባለው ውጊያ የአዴን ኃይሎች ከ"ህውሓት ታጣቂዎች" ጋር "ተቀናጅተው" እንደተሳተፉ ነዋሪዎች እና የዞኑ አስተዳደር ለቢቢሲ አመልክተዋል።
የአዴን የሚዲያ እና ኮምዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ሙሉጌታ ካሴ ከህውሓት ኃይሎች ጋር ተጣምረው መዋጋታቸውን አስተባብለው፤ "አመራሮቻችንን አፍነው ለመውሰድ ሲሞክሩ" ግጭቱ ተቀስቅሷል በማለት "ተገፍተን ነው [ወደ ግጭት] የገባነው" ብለዋል።
የዋግ ኽምራ ዞን የፀጥታ መምሪያ ኃላፊ ሃምሳ አለቃ አዘዘው አዳነ "ይህ ከእውነት የራቀ ነው" በማለት አስተባብለው፤ የአዴን ታጣቂዎች "ቀድመው በመዘጋጀት ጥቃት" በመፈፀማቸው ግጭቱ እንደተቀሰቀሰ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በወረዳው ግጭቱ የተቀሰቀሰው በታጣቂዎች እንቅስቃሴ ጉዳይ አለመግባባት በመፈጠሩ እንደሆነ ነዋሪዎች ተናግረዋል።
"በመኪናው ላይ እያሉ ነው ውጊያው የጀመረው" ያሉ አንድ ነዋሪ፤ "ሎጂስቲክስ ሊያሳልፉ ከመጡ የአዴን ታጣቂዎች ጋር ተኩስ ተጀመረ። 20 እና 30 ደቂቃ ጠብቆ በሦስት ግንባር፤ ከተማዋን ከበቧት" ሲሉ ግጭቱ ሲፈነዳ የተመለከቱትን ተናግረዋል።
በዚህ ግጭት ንፁሃን ሰዎች እንዳልተጎዱ አመልክተው፤ ከሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች በኩል ግን በርካታ ተዋጊዎች መገደላቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የአዴን ታጣቂዎች "ከህወሓት ኃይሎች" ጋር ፃግብጂ ወረዳን እንዲሁ ከሁለት ሳምንት በፊት እንደተቆጣጠሩም የወረዳው ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ግንቦት 18/2018 ዓ.ም. ከቀኑ ሰባት ሰዓት አካባቢ "አዴን እና የትግራይ ኃይሎች በቅንጅት ነው የገቡት" ያሉ አንድ የወረዳው ነዋሪ "አዝሪያ" በሚባል ስፍራ "በቡድን መሳሪያ" የታገዘ የተኩስ ልውውጡ እንደተጀመረ ተናግረዋል።
የተኩስ ልውውጡ እስከ 10፡00 ሰዓት ከቆየ በኋላ የመንግሥት ኃይሎች ወረዳውን ለቀው ወደ ሰቆጣ መውጣታቸውን ጠቁመዋል።
የአዴን የሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ኃላፊ አቶ ሙሉጌታ ካሴ፤ "የሀራ መሬቶችን [የትግራይ ታጣቂ ኃይል] በቅንጅት አምጥቶ ውጊያ ማስከፈት ስምምነቱን አፍራሽ ነው" በማለት ለግጭቱ ምክንያት ሰጥተዋል።
ለትግራይ ክልል አዋሳኝ በሆኑ የዋግ ኽምራ አካባቢዎች ራሳቸውን "የትግራይ ሰላም ኃይል" ብለው የሚጠሩ እና በተለምዶ "የሀራ መሬት ታጣቂዎች" እንደሚንቀሳቀሱ ይነገራል።
የዞኑ ፀጥታ መምሪያ ኃላፊ ሃምሳ አለቃ አዘዘው "ተጨባጭ መረጃ የለኝም" በማለት የሀራ መሬት ታጣቂዎችን እንቅስቃሴ እንደማያውቁ ተናግረዋል።
ሁለቱም ወረዳዎች በታጣቂዎች እጅ ከገቡ በኋላ በ"ሺዎች" የሚቆጠሩ ስጋት ያደረባቸው ነዋሪዎች ቤት ንብረታቸውን ጥለው በተለይም ወደ ዞኑ ዋና ከተማ ሰቆጣ መሸሸታቸውን ለቢቢሲ ገልፀዋል።
ከእነዚህም መካከል የአበርገሌ ወረዳ ነዋሪ እና አርሶ አደር የሆኑት አቶ ህሉፍ [ለደኅንነታቸው ስንል የመጀመሪያ ስማቸውን ብቻ ተጠቅመናል] ሰባት ቤተሰባቸውን ይዘው ወደ ሰቆጣ መፈናቀላቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በስጋት የሸሹ አንድ የመንግሥት ሠራተኛ ደግሞ "እኔ ከፖለቲካ ነፃ ነኝ ብዬ ነበር። ግን ስልክ ሲቀሙ፤ በየቤቱ እየዞሩ ሲፈትሹ ነገሩ አልጣመኝም. . .እየዞሩ ትራንስፈር አድርግ ወደሚለው ነገር ሲደርስ እየተደበቀ ነው [ነዋሪው] የወጣው" በማለት ከሁለት ቀን በኋላ አካባቢውን ለቀው መውጣታቸውን ለቢቢሲ ጠቁመዋል።
በዚህ ዓይነት ታጣቂዎቹ ከነዋሪዎቹ ላይ ንብረት እና ገንዘብ እየወሰዱ መሆናቸው እንዲሁም ቀጣይ ግጭት በመፍራት በርካታ ሰው ከመኖሪያው መፈናቀሉን የገለጹት ነዋሪው ". . . አሁን በአብዛኛው የቀሩት የሃይማኖት አባቶች እና ሽማግሌዎች ናቸው" ብለዋል።
አቶ ህሉፍ ታጣቂዎች የግዴታ ምለመላ፣ የገንዘብ ድጋፍ መዋጮ እና ቀለብ እንድናወጣ ስለሚያስገድዱን ጥለን ወጣን ያሉ ሲሆን፤ በችግር ላይ ችግር ስለተደራረበባቸው መፈናቅል ብቸኛ አማራጭ እንዳደረጉ ተናግረዋል።
ከሦስት ዓመት እስከ 15 ዓመት የዕድሜ ክልል የሚገኙ ስድስት ልጆቻቸውን እና ባለቤታቸውን ይዘው "በረንዳ" ላይ እንደተጠለሉ እና ምግብ በልመና እንደሚያገኙ ገልጸዋል።
"ቤተ ክርስቲያንም ለመሳለም በጣም አሳፋሪ ሆኗል። በግራ እና በቀኝ የተቀመጠውን ብታይ? በየምግብ ቤቱ እየዞረ የሚለምነውን ስታይ ባንፈጠር? [ያስብላል]።. . . ምግብ የሚበላውን ሁሉ አያስበላም። ደስ አይልም። ወጣት እንኳ ሸቅሎ [ሰርቶ] ይብላ ቢባል በአሁኑ ሰዓት አይቻልም። በጣም አስቸጋሪ ነው" ሲሉ ተፈናቅሎ የመጣው ሰው ያለበትን ችግር ተናግረዋል።
"እየዞርን እንለምናለን። ልጆች ይዘን በጣም ከባድ ነው፤ የሰው ፊት ደስ አይልም። ለምነን ለራስም አይሆንም እንኳን ለቤተሰብ። ከነቤተሰብ ከፍቶት፤ ልብስ ቅያሪ የሌለው ስታይ በጣም አስቸጋሪ ነው። ቀኑ ካለፈ እናያለን" ሲሉ በተስፋ መቁረጥ ስሜት ውስጥ ሆነው እራሳቸው እና ቤተሰባቸው ያሉበትን ሁኔታ አስረድተዋል።
ከአበርገሌ ወረዳ ብቻ "አስር ሺህ" የሚሆኑ ሰዎች መፈናቀላቸውን የጠቆሙ እና ለደኅንነታቸው በመስጋት ስማቸውን እንዳንጠቅስ የጠየቁ የቀበሌ ሊቀ መንበር፤ የአካባቢው ማኅበረሰብ ባለፉት ስድስት ዓመታት በጦርነት እና በድርቅ ከባድ ችግር ውስጥ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ግጭቱን ተከትሎ እርሳቸው ከሚያስተዳድሩት ቀበሌ ብቻ "ከሦስት ሺህ በላይ" ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን አስተውቀዋል። ይህም ሰባት ሺህ ከሆነው የቀበሌው ነዋሪ ግማሽ የሚጠጋው "ልጆቹን፤ ቤተሰቡን ይዞ ተፈናቅሎ ነው ያለው" ብለዋል።
"የሚበላው የሚቀምሰው የለም። መጠለያም የለም፤ ዝም ብለው በረንዳ ላይ ነው የሚያድሩት።. . .የወታደር ካምፕ ነበር፤ እዚያ ላይ ተጠግተው ነበር። ከዚያም ውጡ ተብሎ ልጆቹን ይዞ በረንዳ ላይ ነው የሚያድረው" በማለት ያሉበትን ሁኔታ "በጣም አሳሳቢ" ሲሉ ገልፀውታል።
"ለዛሬው ብቻ ሳይሆን እኛ ለቀጣዩም ነው እየሞትን ያለነው። በቀደም አዝመራ ሳንዘራ ቀረን፤ አሁን ደግሞ ሰኔ እና ሐምሌ ካልዘራን በጣም ከባድ ነው። ሁላችንም ከነቤተሰባችን ሞትን ማለት ነው። ለቀጣይ ዓመትም እኮ ነው የሞትነው" ሲሉ ስጋታቸውን ተናግረዋል።
የታጣቂ ቡድኑ አባል አቶ ሙሉጌታ ካሴ ግን ከመንግሥት ሠራተኞች፣ የሚሊሻ ቤተሰቦች እና ለንግድ ሥራ ብለው ወጥተው ከቀሩ ነዋሪዎች ውጪ ቡድናቸው ወረዳዎቹን በመቆጣጠሩ "የተፈናቀለ ሕዝብ የለም" ብለዋል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው አንድ የሰቆጣ ከተማ ነዋሪ "በጣም በርካታ ሕዝብ [ወደ ከተማዋ] መጥቷል" በማለት ተፈናቃዮች በጎዳናዎች እና በተጀመሩ ሕንፃዎች እንደተጠለሉ ተናግረዋል።
የፀጥታ መምሪያ ኃላፊው በበኩላቸው"ሲቪሉ ማኅበረሰብ ብዙ እናቶች፤ ብዙ አዛውንቶች፤ ብዙ ወጣቶች ተፈናቅለው ሰቆጣ ከተማ አስተዳደር ላይ በስፋት አሉ።. . .አብዛኛው ማኅበረሰብ ተፈናቅሎ እዚሁ ከተማ አስተዳደር ነው የሚገኘው" ብለዋል።
"ከመጣን ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ የተሰጠን [እርዳታ] የለም።ምንም እርዳታ አላገኘንም" ያሉት አቶ ህሉፍ "ከምዝገባ ያለፈ ነገር" እንደሌለ ተናግረዋል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው የቀበሌው ሊቀ መንበር "ለተወሰኑ ሰዎች" ወርልድ ቪዢን የጥሬ ገንዘብ ድጋፍ ሲያደርግ፤ ሌላ የረድኤት ድርጅት ደግሞ ለመንግሥት ሠራተኞች የቤት ቁሳቁስ መስጠቱን ጠቁመዋል።
"ከዚህ ውጪ ምዝገባ ብቻ ነው" በማለትም እርዳታ እየተደረገ እንዳልሆነ ተናግረዋል።
ቢቢሲ በተለይም የተፈናቃዮችን ሁኔታ እና የሰብዓዊ ድጋፍ በሚመለከት የዞኑን ምክትል አስተዳዳሪ ሹመት ጥላሁን እና የአበርገሌ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ነይኑ በላይን ለቀናት ለማነጋገር ያደረገው ጥረት አልተሳካም።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች እና አንድ የቀድሞ የአዴን ኃይሎች አመራር ታጣቂዎች እና የአማራ ክልል መንግሥት የሰላም ስምምነት ከደረሰ በኋላ ከአንዳንድ ትንኮሳውች ውጪ አካባቢው ተረጋግቶ እንደነበር ተናግረዋል።
ስምምነቱ በ2016 ዓ.ም. ከተፈረመ ወዲህ በግልጽ ግጭት ውስጥ ሲገባ የአበርገሌው የመጀመሪያው እንደሆነም አመልክተዋል።
አዴን ሁለት ዓመታትን በዘለቀው ደም አፋሳሹ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ወቅት የህውሓት ኃይሎችን ወግኖ በመዋጋት ስሙ ይነሳል።
በ2016 ቡድኑ ትጥቅ ለመፍታት እና "በሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ ትግል" ለመሳተፍ ከመንግሥት ጋር ስምምነት ደርሶ ነበር።
ለዚህ ስምምነት መፍረስ ሁለቱም ወገኖች እርስ በርስ እየተካሰሱ ሲሆን፣ ቢቢሲ በአካባቢው ከሚገኙ ገለግተኛ ወገኖች ስለሁኔታው ለማወቅ የሚያስችል መረጃ አላገኘም።