በሊባኖስ የኢየሱስን ሐውልት ያፈረሱ የእስራኤል ወታደሮች ተቀጡ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በሊባኖስ የኢየሱስን ሐውልት በመዶሻ ያፈረሰው እና ድርጊቱን በምስል ያስቀረው የእስራኤል ወታደር ለ30 ቀናት በወታደራዊ እስር ቤት እንደሚታሰሩ የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት አስታወቀ።
የእስራኤል ጦር ስማቸው ያልተጠቀሰው ሁለቱ ወታደሮች ምርመራ ከተደረገ በኋላ "ከዘመቻ ግዴታቸው እንደሚሰናበቱ" ተናግሯል።
በቦታው የነበሩ እና ጥፋቱን ማስቆም ወይም ጉዳዩን ለበላይ አካላት ያላሳወቁ ሌሎች ስድስት ወታደሮች ጉዳያቸው በተናጠል እንደሚታይ አስታውቋል።
በደቡባዊ ሊባኖስ በምትገኘው ዴቤል መንደር የነበረው ይህ የኢየሱስ ሐውልት ሲፈርስ እና ሲወድም የሚያሳይ ምስል በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በስፋት ከተዘዋወረ በኋላ ሰፊ ውግዘት አስከትሏል። የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በተፈጠረው ነገር "እጅግ እንደደነገጡ እና እንዳዘኑ" ተናግረዋል።
የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት ማክሰኞ ዕለት ባወጠው መግለጫ፣ ስለ ክስተቱ የተደረገ ምርመራ "የወታደሮቹ ባህሪ ከሠራዊቱ ትዕዛዝ እና እሴቶች ሙሉ በሙሉ የራቀ መሆኑን አረጋግጧል" እና "በክስተቱ ጥልቅ ሀዘን" እንደተሰማው ገልጿል።
በተጨማሪም የመከላከያ ሠራዊት አባላት ከጥቂት ጊዜ በፊት "ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር ሙሉ በሙሉ በመተባበር" የተጎዳውን ሐውልት መተካት እንደጀመሩ ተናግሯል።
በሊባኖስ የሚፈጽመው ጥቃት በኢራን በሚደገፈው ሄዝቦላህ እና በሌሎች የሽብር ቡድኖች ላይ ብቻ ያተኮረ እንጂ በሊባኖስ ሰላማዊ ዜጎች ላይ አይደለም ሲል በመግለጫው ላይ አስታውቋል።
የአካባቢው ነዋሪዎች እንደተናገሩት ሐውልቱ በዴቤል ዳርቻ በሚገኝ የአንድ ቤተሰብ መኖሪያ ቤት ውጭ የቆመ ነበር።
እስራኤል ከሄዝቦላህ ጋር እያደረገች ባለው ጦርነት ወቅት ነዋሪዎች በአካባቢያቸው ውስጥ ከቆዩባቸው ጥቂት መንደሮች አንዱ ነው።
የዴቤል ምዕመናን ኃላፊ አባ ፋዲ ፍላይፌል ክስተቱን ተከትሎ ለቢቢሲ "የመስቀሉን፣ የተቀደሰ ምልክታችንን እና ሁሉንም የሃይማኖት ምልክቶች ማዋረድን ሙሉ በሙሉ እንቃወማለን። ከሰብዓዊ መብቶች አዋጅ ጋር የሚቃረን ነው፣ እናም ጨዋነትን አያንፀባርቅም" ብለዋል።
ከዚህ በፊትም ተመሳሳይ ክስተቶች መፈጠራቸውን ጨምረው አስረድተዋል።
ድርጊቱን ካወገዙት መካከል አንዱ የሆኑት በእስራኤል የአሜሪካ አምባሳደር ማይክ ሁካቢ ሰኞ ዕለት "አስጸያፊውን ድርጊት" ተከትሎ "ፈጣን፣ ከባድ እና ለሕዝብ የሚገለጽ እርምጃ" እንዲወሰድ ጥሪ አቅርበዋል።
ኔታንያሁ "በሊባኖስ እና በዓለም ዙሪያ ባሉ ክርስትያኖች ላይ ላደረሰው ጉዳት" ማዘናቸውን ገልጸዋል።

የፎቶው ባለመብት, Israel Defense Forces
በእስራኤል እና በሊባኖስ መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት ተግባራዊ ከተደረገ በኋላ በሺዎች የሚቆጠሩ የእስራኤል ወታደሮች በደቡባዊ ሊባኖስ ሰፊ ቦታ መቆጣጠራቸውን ቀጥለዋል።
የተኩስ አቁም ስምምነቱ በእስራኤል ጦር እና በሺአ ሙስሊም ታጣቂ ቡድን ሄዝቦላህ መካከል ለስድስት ሳምንታት የዘለቀውን ጦርነት እንዲቆም አድርጓል።
ነገር ግን ሁለቱም ወገኖች እርስ በእርሳቸው የተኩስ አቁሙን በመጣስ ተካስሰዋል።
ሄዝቦላህ ኢራንን ለመደገፍ በእስራኤል ላይ ሮኬቶችን መተኮስ የጀመረው የካቲት 21 2018 ዓ.ም. እስራኤል እና አሜሪካ በቴህራን ላይ ጦርነት ከከፈቱ በኋላ ነው።
እስራኤል እአአ መጋቢት 2 በሊባኖስ ወታደራዊ ዘመቻ የጀመረች ሲሆን ይህም ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎችን አፈናቅሏል።
በእስራኤል መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ዘመቻ ከ2,290 በላይ ሰዎች መገደላቸውን ከእነዚህም ውስጥ 177 ሕፃናት እና 100 የጤና ባለሙያዎች መሆናቸው ተገልጿል።
የእስራኤል ባለሥልጣናት እንዳሉት በተመሳሳይ ጊዜ በሄዝቦላህ በተፈፀሙ ጥቃቶች 13 የእስራኤል ወታደሮች እና ሁለት ሰላማዊ ዜጎች ተገድለዋል።















