አሜሪካ አይኤስን ለመዋጋት በናይጄሪያ አሰማርታቸው የነበሩ ወታደሮቿን አስወጣች

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

አሜሪካ በናይጄሪያ ከእስላማዊ ታጣቂ ቡድኖች ጋር የሚደረገውን ትግል ለማገዝ በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ አሰማርታቸው የነበሩትን አብዛኞቹን ወታደሮቿን አስወጣች።

የአሜሪካ እና የናይጄሪያ ኃይሎች ታኅሣሥ ወር ላይ በቻድ ሐይቅ ተፋሰስ አካባቢ የጋራ ዘመቻ ከፍተው የነበረ ሲሆን በገና ዕለትም በታጣቂዎች ላይ ጥቃት ፈፅመዋል።

ከሁለት ወራት በኋላ ደግሞ በአካባቢው ወደ 200 ወታደሮችን አሰማርተዋል።

ለወራት በቆየው በዚህ ተልዕኮም የእስላማዊ ታጣቂ ቡድኑ ከፍተኛ መሪ አቡ ቢላል አል ሚኑኪ ተገድለዋል።

አሜሪካ ሐሙስ ዕለት አብዛኞቹን ወታደሮቿን ማስወጣቷን በገለፀችበት መግለጫ "ዘመቻው ውጤታማ" እንደነበር ገልጻለች።

የናይጄሪያ ጦር ቃል አቀባይ በበኩላቸው የአሜሪካ ወታደሮች መውጣት "በምንም መልኩ የእኛ እርምጃ ላይ ተፅዕኖ አያሳድርም" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ዘመቻዎች ቢካሄዱም ጂሃዳዊ ቡድኖች በተለይ በሰሜን ምሥራቅ ናይጄሪያ ጥቃት መፈፀማቸውን ቀጥለዋል።

ቃል አቀባዩ ሜጀር ጀኔራል ማይክል ኦኖጃ በሁለቱ አገራት መካከል ያለው የደኅንነት ጉዳዮች ልውውጥ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

የአሜሪካ ጦርም በመግለጫው ግንኙነታቸው እንደሚቀጥል አረጋግጧል።

በናይጄሪያ እና በአሜሪካ መካከል ያለው ወታደራዊ ትብብር የጨመረው ዋሽንግተን ተጋላጭ የሆኑ ቡድኖችን ከእስላማዊ ታጣቂዎች ለመጠበቅ በቂ እርምጃ እየወሰደች አይደለም ስትል የናይጄሪያ ባለሥልጣናትን ከከሰሰች እና በአገሪቷ "የክርስቲያኖች የዘር ማጥፋት ዘመቻ" እንዳለ ከገለፀች በኋላ ነው።

ናይጄሪያ ግን የሚፈፀመው ጥቃት ውስብስብ መሆኑን እና ሁሉንም የማኅበረሰብ ክፍሎች የጎዳ ነው ስትል ክሱን አስተባብላለች።

በናይጄሪያ ያለውን ፖለቲካዊ ጥቃት የሚከታተሉ ድርጅቶች በበኩላቸው በጂሃዳዊ ቡድኖች ጥቃት ሰለባ የሆኑ ሰዎች በአብዛኞቹ ሙስሊሞች እንደሆኑ ገልጸዋል።

ድርጅቶቹ ምክንያታቸውን ሲያስቀምጡም ታጣቂ ቡድኖች በአብዛኛው የሚንቀሳቀሱት አብዛኞቹ ነዋሪዎች የእስልምና እምነት ተከታዮች በሆኑበት ሰሜናዊ የአገሪቱ ክፍል ነው ብለዋል።

አሜሪካ፤ ናይጄሪያ የሽምቅ ውጊያ የሚያካሂዱ ታጣቂዎችን ለመዋጋት የምታደረገውን ጥረት ለማገዝ 200 ወታደሮችን እንደምታሰማራ የገለፀችው በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ነበር።

ሆኖም ወታደሮቿ በምድር ውጊያ ላይ እንደማይሳተፉ አፅንኦት ሰጥታለች።

አሁን ላይ ከእነዚህ ወታደሮቿ መካከል አብዛኞቹ መውጣታቸውን በአፍሪካ የአሜሪካ አየር ኃይል አዛዥ ጄነራል ዳግቪን አንደርሰን ሐሙስ ዕለት ተናግረዋል።

ጄነራል አንደርሰን ዘመቻው ውጤታ እንደነበር ገልጸው፣ በናይጄሪያ ያለው እስላማዊ ታጣቂ ቡድን (አይኤስ) አስተዳደር በከፍተኛ ሁኔታ ተንኮታኩቷል ብለዋል።

አንደርሰን እንዳሉት የቡድኑ የአካባቢው ዕዝ ሰንሰለት እና ሰፊው ዓለም አቀፍ ግንኙነቱ በጥምር በተካሄደው ዘመቻ የተሰናከለ ሲሆን ዘመቻው የግንኙነት አቅሙንም ውስን አድርጎታል።

አሜሪካ ወታደሮቿን ብታስወጣም ከቻድ ሐይቅ ተፋሰስ ዘመቻ አስቀድሞ የነበረው የአሜሪካ ጦር ኃይል በአገሪቷ እንደሚቆይ የጦር ኃይሎች ቃል አቀባይ ሜጀር ጀነራል ሳሜይላ ኡባ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አይኤስ ትኩረቱ ላይ ለውጥ ማድረጉን እና 90 በመቶ የሚሆነውን ጥቃት የሚፈፅመው ከሰሃራ በረሃ በታች ባሉ አገራት እንደሆነ ተንታኞች ይናገራሉ።

በናይጄሪያ ያለው ቅርንጫፉም ንቁው ነው።

ናይጄሪያ በበርካታ የፀጥታ ችግሮች እየተፈተነች ሲሆን ከእስላማዊ ታጣቂዎች በተጨማሪ የወንበዴዎች እና የወንጀል ቡድኖች ከሰሜን ወደ ማዕከላዊ እና ደቡባዊ ክፍሎቿ መስፋፋት አስጨንቋታል።