ሩሲያ ለዩክሬን ድሮኖችን አቅርባለች ያለቻትን ዩናይትድ ኪንግደምን አስጠነቀቀች

የፎቶው ባለመብት, EPA
ሩሲያ በዩክሬን ያለው ቀውስ እንዲባባስ "ሆነ ብላ እየሰራች ነው" ስትል ዩናይትድ ኪንግደምን ከሰሰች። አገሪቷ ይህን ያለችው የሩሲያን ዒላማዎችን ለመምታት ብሪታኒያ ሰራሽ ድሮኖች ጥቅም ላይ መዋላቸው ከተረጋገጠ በኋላ ነው።
በዩኬ ያለው የሩሲያ ኤምባሲ ባወጣው መግለጫ " ዩናይትድ ኪንግደም በደም አፋሳሽ ወንጀል እና የሽብር ጥቃት አጋር እና ተባባሪ እየሆነች ነው" ብሏል።
"ምላሽ የሚያስፈልገው የለንደን ድርጊት መዘዝ ማስከተሉ አይቀሬ ነው" ያለው መግለጫው፣ ዩኬ በግጭቱ ያላት ተሳትፎ እየጨመረ በመጣ ቁጥር የምትከፍለውን ዋጋ እንደሚያከፋው አስጠንቅቋል።
ሩሲያ ያቀረበችውን ክስ ተከትሎ የዩኬ የመከላከያ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ በሰጡት ምላሽ ብሪታኒያ "ከዩክሬን ጎን ትቆማለች" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"መንግሥት ሩሲያ በዩክሬን፣ በዩኬ እና በአጋሮቻችን ላይ እየፈፀመች ባለችው እብሪት በተቃራኒ መቆሙን ሩሲያ መጠራጠር የለባትም" ሲሉም በመግለጫቸው ላይ አቋማቸውን ገልጸዋል።
ጨምረውም "ዩኬ ዩክሬን [ ከሩሲያው ፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲን] ሕገ ወጥ ወረራ ራሷን ለመከላከል የሚያስችላትን መሣሪያ ለማቅረብ ቁርጠኛ ናት" ብለዋል።
መከላከያ ሚኒስቴሩ ሚያዚያ ወር ላይ ረዥም ርቀት ጥቃት መፈፀም የሚችሉ መሣሪያዎችን ጨምሮ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ድሮኖችን እንደሚያቀርብ አስታውቆ ነበር።
በብሪታንያ ሁለት የተለያዩ ኩባንያዎች የተሰሩት ድሮኖች በሩሲያ ውስጥ በተፈፀመው መጠነ ሰፊ እና ስኬታማ የሆኑ ወታደራዊ እንዲሁም የነዳጅ ማጣሪያዎችን፣ መጋዘኖችን እና የኦንላየን ጅምላ አከፋፋይ የሆነውን ዋይልድቤሪስን ጨምሮ የኢንደስትሪ ዒላማዎችን ለመምታት ጥቅም ላይ ውለዋል።
ዩክሬን የሩሲያው አማዞን የሚባለውን የኦንላየን ገበያ ድርጅት በተደጋጋሚ ዒላማ ያደረገች ሲሆን በአገሪቷ ካሉ አስር ትላልቅ የድርጅቱ የሎጂስቲክስ ማዕከላት ሰባቱ ሙሉ በሙሉ መውደማቸውን ገልጻለች።
በእነዚህ 35 ቢሊዮን ዶላር የኢኮኖሚ ጉዳት አድርሰዋል በተባሉ ጥቃቶች የዩኬ ድሮኖች ጥቅም ላይ መዋላቸውን ወታደራዊ ምንጮች ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
ሩሲያ በዩክሬን ላይ ሙሉ ወረራ የከፈተችው ከአራት ዓመታት በፊት ሲሆን አሁን ላይ አንድ አምስተኛውን የዩክሬን ክፍል ተቆጣጥራ ትገኛለች።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሯ ቃል አቀባይ ማሪያ ዛክሃሮቫ፣ በሮስቶቭ ክልል የሚገኘውን የነዳጅ ማከማቻ ጨምሮ የሩሲያን ግዛት ለማጥቃት የዩኬ ሰራሽ ድሮኖች ጥቅም ላይ ውለዋል ብለዋል።
ሞስኮ ለዩኬ ማስጠንቀቂያ የሰጠችውም ዩክሬን በሩሲያ ላይ ተከታታይ ጥቃት ከፈፀመች በኋላ ነው። ሰኞ ዕለት በተፈፀመው ጥቃት ብቻ ዘጠኝ ሰዎች ሲገደሉ አንድ ሕፃንን ጨምሮ 23 ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል።
ቅዳሜ ዕለትም ዩክሬን 822 ድሮኖችን ወደ ሩሲያ የተኮሰች ሲሆን 600 የሚሆኑት ዋና መዲናዋን ሞስኮን ለመምታት ያለሙ እንደሆኑ የአካባቢው አስተዳዳር የገለፀ ሲሆን፣ መዲናዋ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ከፈፀሙ መጠነ ሰፊ ጥቃቶች አንዱን አስተናግዳለች ብሏል። በዚህ ጥቃት ሰባት ሰዎች ሞተዋል።
በዚያው ምሽት ሩሲያ በዩክሬን ላይ በፈፀመችው ጥቃት ሰባት ሰዎች ሲገደሉ ከ39 ሰዎች በላይ ጉዳት ደርሶባቸዋል።















