አንዲት ኢራናዊት ወደ ሱዳን የጦር መሣሪያ አዘዋውራለች በሚል አሜሪካ ውስጥ በቁጥጥር ስር ዋለች

ክላሺንኮቭ የያዘ የሱዳን ወታደር

የፎቶው ባለመብት, Avaaz via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የጦር መሣሪያዎቹ ለሱዳን ጦር ተሽጠዋል ተብሏል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የአሜሪካ አቃቤ ሕግ በአገሯ ስም የጦር መሣሪያ ወደ ሱዳን በማዘዋወር ወንጀል የተከሰሰች ኢራናዊት በቁጥጥር ስር መዋሏን አስታወቀ።

የአሜሪካ የመኖሪያ ፈቃድ ያላት የ44 ዓመቷ ሻሚም ማፊ ቅዳሜ ዕለት በሎስ አንጀለስ አውሮፕላን ማረፊያ ተይዛ "በኢራን የተመረቱ እና ለሱዳን የተሸጡ ድሮኖችን፣ ቦምቦችን፣ የቦምብ ማቀጣጠያ ፊውዞችን እና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ጥይቶችን በመደለል" ወንጀል ተከስሳለች ሲል የአሜሪካ አቃቤ ሕግ ቢል ኢሴሊ በኤክስ ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።

የፍርድ ቤት ሰነዶች እንደሚያሳዩት የጦር መሣሪያዎቹ የተሸጡት ለሱዳን የመከላከያ ሚኒስቴር ሲሆን ከዚሁ ጋር 70 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ የድሮን ሽያጭ እንደሚገኝበት ተገልጿል።

ግለሰቧ የተከሰሰችው አሜሪካውያን ያለ ፈቃድ የኢራንን እቃዎች ወይም አገልግሎቶች እንዳይገበያዩ ወይም እንዳያሻሸጡ የሚከለክለውን አገሪቱ የጣለችውን ማዕቀብ በመጣሷ ነው።

ማፊ እስካሁን ድረስ በቀረበባት ክስ ላይ አስተያየት ያልሰጠች ሲሆን ጥፋተኛ ከተባለች እስከ 20 ዓመት በሚደርስ እስራት ልትቀጣ ትችላለች።

በፍርድ ቤት የቀረበውን የኤፍቢአይ የወንጀል ክስ ቢቢሲ የተመለከተው ሲሆን ማፊ "የሱዳን ልዑካን ቡድን ወደ ኢራን ያደረገውን ጉዞ አስተባብራለች፤ ከ6 ሚሊዮን ዩሮ በላይ ክፍያ ተቀብላለች፣ እንዲሁም የክፍያ ደረሰኞችን ሰጥታለች" ሲል ዘርዝሯል።

ለሱዳን የመከላከያ ሚኒስቴር 55,000 የቦምብ ማቀጣጠያ ፊውዞችን ለመሸጥ የሚገልጽ "የፍላጎት ደብዳቤ" ለኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ማስገባቷም በክሱ ላይ ተጠቅሷል።

እንደ ኤሴሊ ገለጻ፣ ማፊ "በ2016 የዩናይትድ ስቴትስ የመኖሪያ ፈቃድ ያገኘች ኢራናዊት" ነች።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የፍርድ ቤት ሰነዶች በጦር መሳሪያ ስምምነቶች ውስጥ "በብዙ ግብይቶች ላይ መደበኛ ያልሆኑ የንግድ አካላትን ደጋግማ መጠቀሟን" እንዲሁም "የአሜሪካን ማዕቀቦች ለማምለጥ ሆን ተብሎ የተደረገ ጥረት" መታየታቸው ተጠቅሷል።

በተያዘችበት ወቅት ከካሊፎርኒያ ወደ ቱርክ ለመብረር በዝግጅት ላይ ነበረች።

አቃቤ ሕጉ በማኅበራዊ ድረ ገጽ ላይ ባጋሩት ልጥፍ ማፊ እንደሆነች የተገለጸች ሴት በአውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ በደህንነት ሰዎች ተከብባ፣ በአስፋልት ላይ ድሮን እንዲሁም ጥቅል ገንዘብ ይታያል።

ሱዳን ባለፉት ሦስት ዓመታት በአገሪቱ ጦር ኃይል እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች መካከል በተቀሰቀሰ አውዳሚ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ትገኛለች።

እንደ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ገለጻ፣ ጦርነቱ በዓለም ላይ እጅግ አስከፊ የሆነውን የሰብዓዊ ቀውስ አስከትሏል።

በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሲሞቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ደግሞ ተፈናቅለዋል።

የውጭ ኃይሎች ሁለቱንም ወገኖች በመደገፍና ጥይት በማቅረብ ግጭቱን የበለጠ በማባባስ ተከሰዋል።

የመብት ተሟጋች ድርጅት አምነስቲ ኢንተርናሽናል ቀደም ሲል በሰርቢያ፣ ሩሲያ፣ ቻይና፣ ቱርክ እና የመን የተመረቱ የጦር መሳሪያዎች በሱዳን ጥቅም ላይ እየዋሉ መሆናቸውን የሚያሳይ ማስረጃ እንዳገኘ ተናግሯል።

የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ለፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ወታደራዊ ድጋፍ እንደምትሰጥ የሚያሳውን ማስረጃ ውድቅ አድርጋለች።

ኢራን ቀደም ሲል የሱዳንን ጦር በጦር መሣሪያ ትደግፋለች በሚል ተከስሳለች፤ ሱዳን ግን ይህንን ውድቅ አድርጋዋለች።

የሱዳን ጦር እንደ አውሮፓውያኑ በ2024 በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ላይ በተፈፀመው ጥቃት የኢራን የጦር መሣሪያዎች ወሳኝ ሚና እንደተጫወቱ ቢታመንም፣ የተራቀቁ የቱርክ ድሮኖችንም ተጠቅሟል።